(ክፍል ፩)
በለውጡ ማግስት የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ገጥሞት ከነበር ውስብስበ ሙስናና ብልሹ አሰራር ተላቆ ከክሽፈት መዳኑ ሲረጋገጥ ግብጽ ያለ የሌለ ሀይሏን አቀናጅታና አሟጣ አገራችን ላይ የዲፕሎማ፣ የሚዲያና እንደ አሸባሪው ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ያሉ ቡችሎቿን በመጠቀም የእርስ በርስ ግጭት ለመቀስቀስና አገራችንን ለማተራመስ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም ። ከአሸባሪው ሕወሓት የሰሜን ዕዝ ጥቃትና ከቀሰቀሰው ጦርነት፤ ከአሸባሪው ሸኔና ከጀሌዎቹ የንጹሐን ጭፍጨፋ፤ ከጅግጅጋው ጭፍጨፋ፤ ከኦሮምያና ከሱማሌ ግጭት፤ ከአፋርና ከኢሳ ግጭት፤ በየዩኒቨርሲቲዎች ይቀሰቀሱ ከነበሩ ግጭቶች፤ ከድምጻዊ ሀጫሎ ግድያና እሱን ተከትሎ ከተፈጸመው ግፍና ሰቆቃ ፤ ከኢኮኖሚ አሻጥሩ፤ ከምዕራባውያን የተቀናጀና የተናበበ ጸረ ኢትዮጵያ ዘመቻ ፤ ከእነ አመነስቲና ሒውማን ራይትስ ዋች የስማ በለው ሪፖርት ፤ ከሀሰተኛ መርዘኛ መረጃዎች፤ ወዘተረፈ ጀርባ የግብጽና የተላላኪ ባንዳዎች እጅ አለበት።
በምዕራብና ቄለም ወለጋ እንዲሁም በጋምቤላ ሰሞኑን በተፈጸሙ ግፎችም እጇ አለበት። ከሳውዲ አረቢያ የዜጎቻችን ግፍ ጀርባም የግብጽ ረጅም እጅ አለበት። በዚህ አራት አመት እንደአገርና ሕዝብ የገጠመን ፈተና በታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አያውቅም ። በአንድም በሌላ በኩል ኅልቆ መሳፍርት የሌለው ሰቆቃ የሁሉንም ቤት አንኳኩቷል። ሁሉም ዋጋ ከፍሏል። ይሄን ሁሉ ዋጋ እየከፈልን ያለነው አባቶቻችን ያቆዩንን ነጻነትና ሉዓላዊነት ለማስከበርና ለማስቀጠል ነው። የተፈጥሮ ሀብታችንን አልምቶ ለመጠቀም ነው። በድህነትና በኋላቀርነት እየማቀቁ ነጻነትና ሉዓላዊነት ሙሉኡ ስለማይሆን ነው ይሄን ሁሉ መከራ የተቀበልነው። ወደፊትም የትኛውንም ፈተና ለመጋፈጥ ዝግጁ የሆነው። የሕዳሴው ግድብ እየሆንለት ያለው ነገር ሁሉ ይገባዋል(worth it) የሚለው ለዚህ ነው።
የሁለተኛው ተርባይን ፍተሻ ተጀምሯል
ለመጀመሪያ ጊዜ 375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ከጀመረ ሦስት ወራት ያለፉት የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሦስተኛ ዙር ሙሌት ከያዝነው ሐምሌ ወር አንስቶ መከናወን ይጀምራል። ሙሌቱ በተጀመረበት 2012 ዓ.ም. የግድቡ ቁመት 565 ሜትር ሆኖ 4.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ይዟል። በቀጣዩ ዓመት የግድቡ ቁመት 595 ሜትር ደርሶ 13.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ተያዘ። ግድቡ የያዘው የውኃ መጠን 18.4 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ደረሰ። በሦስተኛው ዓመት ላይ የግድቡን ቁመት 608 ሜትር ከፍታ ላይ በማድረስ 10.5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመሙላት፣ አጠቃላዩን የውኃ መጠን 28.9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የማድረስ ግብ ተጥሏል።
የተወደዳችሁ አንባቢዎች በዛሬው መጣጥፌ የአገር አድባርና ሲሳይ ሊሆን እየተገማሸረ ስላለው፤ ስለሚያውቀን፣ ስለማናውቀው፤ በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በግብፅ ጥርስ ስለአስገባን ፤ ቀይ ባህርን በማጣታችን ኮስምኖ የነበረውን የጂኦፖለቲክስ ሞገሳችንን ወደ ከፍታው ስለሚመልሰው ፤ የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አስኳል ስለሚሆን ፤ ጊዎን ወይም አባይ መረጃዎችን አነሳሳለሁ።
የዓባይ ተፋሰስ የአፍሪካን አህጉር አንድ አስረኛ ይሸፍናል። በአለማችን ከምንጩ እስከ ሜዲትራኒያን ባህር ድረስ 6ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ረዥሙ ወንዝ ነው። የአባይ ወንዝ ሁለት ታላላቅ ገባሮች አሉት። ከቪክቶሪያ ሀይቅ ተፋሰስ የሚነሳው ነጭ አባይና ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች የሚመነጨው ጥቁር አባይ ነው። ለናይል ወንዝ 77 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ ማለትም 86 በመቶ ከእነ ለም አፈሩ በመገበር ጥቁር አባይ እንደ ስሙ ታላቅ ወንዝ ነው።
ለራሱ ለጥቁር አባይ ደግሞ 49 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በመገበር አባይ ትልቁን ድርሻ ሲወስድ፤ ባሮ አኮቦ ወንዝ 17 ቢሊዮን እና የተከዜ ወንዝ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በአመት ይገብራሉ። የጥቁር አባይ የፍሰት መጠን ከአገሪቱ አጠቃላይ ፍሰት ግማሽ ከመሆኑ ባሻገር በጠቃሚ ማዕድናትም የበለጸገ ነው። ጥቁርና ነጭ አባይ ሱዳን ካርቱም ላይ ይገናኙና አባይ /ናይል/ ይሆናሉ። ዳሩ ግን የናይል ወንዝ የስምንት የራስጌ ተፋሰስ አገራት ሀብት ጭምር ቢሆንም እስከ ዛሬ በብቸኝነት እየተጠቀሙ ያሉት ግን የግርጌ ተፋሰስ አገራት የሆኑት ሱዳንና ግብፅ ናቸው።
የጋራ የውሃ ሀብት ቢሆንም የራስጌ ተፋሰስ አገራት እኤአ በ1929 በሱዳንና በግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመ አግላይ ስምምነት የተነሳ መጠቀም ሳይችሉ ቆይተዋል። በእንግሊዝ አይዟችሁ ባይነት በተፈረመው ኢፍትሐዊ ውል መሰረት ለሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ፤ የተቀረውን ማለትም 48 ነጥብ 5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ለግብፅ ጀባ ብሏል ። ከጥር እስከ ሐምሌ ያለውን ፍሰት ያካትታል። ይህ የቅኝ ግዛት ዘመን ውርዴ የሆነ ስምምነት ሱዳንና ግብፅ የራስጌ የተፋሰሱ አገራትን በድጋሚ በማግለል በራቸውን ዘግተው እኤአ እስከ ተፈራረሙበት 1959 ድረስ የቀጠለ ሲሆን ፤ በእብሪት የተወጠረው ይህ ስምምነት ፣ “ከግብጽ መንግስት ፈቃድ ውጭ የውሃ መጠኑን ሊቀንስ የሚችል የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ስራዎችን በአባይ ገባሮችና ሀይቆች ላይ መገንባት አይቻልም።” ይህ ግብዝነትንና እብሪትን የሚያሳይ ስምምነት ታዋቂው የግሪክ የታሪክ ሊቅ ሔሮዶተስ “ ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት።” የሚለውን ይትበሀል የዘነጋ ነው ። ግብፅ የአባይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ስጦታ ናት ብዬ ነው የማምነው ።
ጥንታዊ ስልጣኔዋም ሆነ የዛሬ ህልውናዋ ከአባይ ጋር የተቆራኘ ሆኖ ሳለ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከራስጌ የተፋሰስ አገራት ጋር ተቀራርቦና ተባብሮ መስራቱ ይቅርና የምታሳየን እብሪት ማንአህሎኝነትና ንቀት ያበግናል። ከግርጌዋ ተፋሰስ አገራት ለዛውም ከሱዳን ጋር ስለ ዳግም የውሃ ክፍፍሉ ምክክር ካደረገች ከ15 አመታት በላይ እንደሆናት መረጃዎች ያመለክታሉ። ይህ ፈርኦኖችም ሆኑ የዛሬዎቹ ገዥዎች ምን ያህል ከዘመኑ ጋር የመሄድና መሬት ላይ ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ለመቀበል ፍላጎቱ እንደሌላቸው ያስረዳል። ሆኖም ውሎ አድሮ ሱዳን የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ማንሳቷ አልቀረም። የ1929ኙ ስምምነት ላይ እንደገና መደራደር እንደምትፈልግ ግብፅን መወትወት ጀምራለች። የ1959ኙ የውሃ ክፍፍል ላይም ጥያቄ ማቅረብ ቀጥላለች።
የተፋሰሱን ራስጌ አገራት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋገጥ አዲስ ስምምነት መፈራረም ካልተቻለ፤ ሱዳንና ግብፅ በአንድ በኩል፣ ኢትዮጵያና ሰባቱ የራስጌ ተፋሰስ አገራት በሌላ በኩል ለግጭት የመዳረግ እምቅ አቅም እንዳለው ቀጣናዊ የውሃ ፖለቲካ ልሒቃን ያስጠነቅቃሉ። የጋራ የሆነውን የውሃ ሀብት በፍትሐዊነት መጠቀም ሲገባ፤ ግብፅ ግን ከማንኛውም ድርድር በፊት የግርጌም ሆነ የራስጌ አገራት የ1959ኙ ስምምነት እንዲቀበሉ ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች። ሆኖም ይህ የግብፅ ቁሞ ቀር ቅድመ ሁኔታ በተፋሰሱ አገራት ተቀባይነት አላገኘም። ምክንያቱም ስምምነቶቹ የተፋሰስ አገራትን በተለይ አገራችንን ያላሳተፉ ከመሆኑ ባሻገር ስምምነቶቹ የመንግስታቱ ድርጅት እኤአ በ1997 ይፋ ካደረገው የፍትሐዊ ተጠቃሚነት ድንጋጌ ጋር ይጣረሳሉ። ሆኖም የተፋሰሱ አገራት የጋራ የሆነውን የአባይ የውሃ ሀብት ለማልማት የግብፅ ፍቃድ አያስፈልጋቸውም።
ሱዳንና ግብፅ አባይን ለትላልቅ መስኖዎችና የኃይል ማመንጫነት ሲጠቀሙበት በአንጻሩ ሌሎች የራስጌ ተፋሰስ አገራት ወንዙን የሚጠቀሙበት ለአነስተኛ ኃይል ማመንጫነት ብቻ ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት የጋራ የሆነውን ሀብት በስፋት አልምተው የመጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው ሳይሆን ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት በግብፅ ተፅዕኖ የተነሳ ብድር የመስጠት ፍላጎት ስለሌላቸው ነው። የተፋሰሱ አገራት የሕዝብ ብዛት በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመር ላይ መሆኑን ተከትሎ የውሃ ፣ የምግብና የኃይል ፍላጎታቸው በእጅጉ እያሻቀበ ነው። የሚያሳዝነው እነዚህ ፍትሐዊ ያልሆኑ የፋይናንስ ተቋማት ለግብፅ ሲሆን እጃቸው ይፈታል።
በዚህም ጭው ባለ የሳይናይ በርሃ ግዙፍ መስኖዎችን፣ አገሪቱን ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ያደረጉ ትላልቅ የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን ገንብተዋል። በስተሰሜን የሱዳንና ግብፅ ድንበር ላይ ግብፅ በአለማችን ረጅሙን የአባይ ወንዝ በመገደብ በግዙፍነቱ ከዓለም 3ተኛ የሆነውን የአስዋን ግድብ ገንብተዋል ። የአስዋን ግድብ 10 አመት ከፈጀ ግንባታ በኋላ እአአ በ1970 ተጠናቋል። በ1954 ግብፅ ከዓለም ባንክ ብድር ፣ ከአሜሪካ ደግሞ እርዳታ ለማግኘት ጠይቃ ተስፋ ተሰጧት የነበር ቢሆንም ከእስራኤል ጋር በገባችበት ውዝግብ የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህ የተከፋችው ግብፅ ወዲያው ፊቷን ወደ ሶቪየት ሕብረት በማዞር ባገኘችው ብድር ግንባታውን ማካሄድ ችላለች።
ግድቡ 90ሺህ ሱዳናውያን ከማፈናቀሉ ባሻገር በቅርስነት ተከልለው የነበሩ ቦታዎችም በውሃ ተውጠዋል። እነዚህ ተፈናቃዮች ከቀዬአቸው 600 ኪሎ ሜትር ርቀው እንዲሰፍሩ ሲደረግ፤ በግድቡ የተነሳ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ግብፃውያን ግን 40 ኪሎ ሜትር ብቻ እርቀው እንዲሰፍሩ ተደርጓል። ግብፅ ይህን ግዙፍ ግድብ ስተገነባ ከሱዳን ውጭ ሌሎች አገራትን ማማከር አይደለም እወቁልኝ እንኳ አላለችም። ሱዳንንም ያማከረቻት አስባላት ሳይሆን በዜጎቿ ላይ የምትፈፅመውን ግፍ እንድታውቀው ይመስላል። የአስዋን ግድብ 2ሺህ 100 ሜጋ ዋት በማመንጨት ማለትም ግማሹን የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ያሟላ ሲሆን፣ ለከፍተኛ መስኖ ልማትም ውሏል። ግብፅ እምቅ የኃይል አማራጭ ቢኖራትም ከውኃ የኃይል ማመንጫዎች ውጭ የመጠቀም ፍላጎት የላትም።
አንዳንድ ምንጮች እንደሚጠቁሙት 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን በርሜል የነዳጅ ድፍድፍ ክምችት በምድሯ ቢኖርም በቀን እያመረተች ያለው ከ640ሺህ በርሜል በታች ነው። የተፈጥሮ ጋዝ ክምችቷ ወደ 2 ነጥብ 2 ትሪሊዮ የሚጠጋ ሲሆን፣ እያመረተች ያለው ግን ወደ 60 ቢሊዮን ኩብ የሚጠጋ ብቻ ነው። እንዲሁም 547ሺህ 500 በርሜል በቀን የተጣራ ነዳጅ ታመርታለች። ሰፊ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳላትም ጥናቶች ያመለክታሉ። ይህ ሁሉ አማራጭ የኃይልም ሆነ የመስኖ ሀብት እያላት መላው ስስቷና ቀልቧ አባይ ላይ ነው። እሷ የተሻለ አማራጭ ያላት መሆኑን አይኔን ግንባር ያርገው ብላ በየአደባባዩ እየማለች፣ እየተገዘተችና እየካደች ፤ ኢትዮጵያ ዝናብን ጨምሮ በርካታ አማራጭ የውሃ ሀብት እያላት ጥቁር አባይ ላይ ግድብ የምትገነባው ግብፅን ለማንበርከክና ጂኦፖለቲካዊ ሚዛኗን ለመጨመር ነው ስትል በየመድረኩ ትጮሀለች ።
ግብፅ እያነባች ወደ ምትወርደው እስክስታ ስንመለስ፤ ግብፅ የአባይን የተፈጥሮ ፍሰት በመቀየር በርሃውን ለማልማት 30ሺህ 300 ኪሎ ሜትር የመስኖ ቦዮችን ገንብታለች። ከአስዋን ግድብ 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ያህል ውሃ በመሳብ ቶሽካ የተባለውን ሰው ሰራሽ ሀይቅ በመገንባት በርሃውን እያለማች ትገኛለች። በአሁኑ ሰዓት ግብፅ 3 ነጥብ 76 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ታለማለች። ከአስዋን ግድብና ከአባይ ወንዝ ያልተገባ አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚነሱ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ሆኖ። በትነትና በስርገት የተነሳ በየአመቱ ከ12 እስከ 14 በመቶ የሚደርስ ውሃ ከግድቡና ከመስኖ ቦዮች ይባክናል። ለመስኖ ከሚያስፈልገው ውሃ በላይ በመጠቀም ማባከንና ጥራት የሌለው የፍሳሽ መውረጃ በግድቡ ላይ ከሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ይጠቀሳሉ ።
እንደጀመርን እንጨርሰዋለን !
አሜን።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 7 ቀን 2014 ዓ.ም