ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “አክቲቪስት” የሚባሉ አካላት የፖለቲካው ዋነኛ ተዋናይ እየሆኑ ነው። “አክቲቪስትነት” በሀገር ጉዳይ ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር አቅም ያለው ተግባር እየሆነም ነው። “አክቲቪስትስ” ማነው? ጠቀመን ወይስ ጎዳን?
አክቲቪስትና የፖለቲካ ተንታኝ ስዩም ተሾመ “አክቲቪስትነት ለሰው ልጆች እኩልነትና ፍትህ መታገል ነው፤ አክቲቪስት ማለት የእኩልነትና ፍትህ አቀንቃኝ መሆን ነው” ይላሉ። ዓላማና ግቡም በአንድ አገር ውስጥ ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ሥርዓት እንዲገነባና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሰፍን ለማድረግ ነው ብለው ይህም የሰው ልጆች መሠረታዊ ጥያቄ ነው ሲሉ ፍቺ አስቀምጠዋል።
“አክቲቪስትነት መጠየቅ ነው” ሲሉ የአቶ ስዩምን ሃሳብ የሚጋሩት ጋዜጠኛና ደራሲ አቶ ጌታቸው ሽፈራው ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለፃ አክቲቪስት የሚባለው በገንዘብ፣ በሥልጣን፣ በሌላም መንገድ ባገኙት አቅም ሌሎችን የሚበድሉ አካላትን የሚጠይቅ ነው። ዋነኛ ዓላማውም ለሕዝብና ሀገር ጥቅም ዘብ መቆም ነው።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህርና የግጭት አፈታት ጥናት ተመራማሪ አቶ ዳንኤል መኮንን በበኩላቸው፤ አክቲቪስትነት በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝብን ማስተማር፣ መቀስቀስና ማስተማር ነው። ይህም “ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጠንካራ የፖሊሲ ወይም የተግባር ዘመቻ” ከሚለው የኦክስፎርድ
መዝገበ ቃላት ትርጉም ጋር የሚሄድ ነው ሲሉ ይበይኑታል። በአንድ የተወሰነ ማህበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ ሕዝብን የሚቀሰቅስና የሚያነቃ ሰው አክቲቪስት እንለዋለን ብለዋል።
“አክቲቪስት” የሚለውን ስም ማግኘት ያለበት ምን ዓይነት ሰው ነው? የሚለው የራሱ የሆነ አካሄድ አለው” የሚሉት የፖለቲካል ሳይንስ መምህሩ፤ በተለይም አሁን በኢትዮጵያ የሚስተዋለው “የአክቲቪስትና የአክቲቪስትነት ጉዳይ” ትክክለኛውን አካሄድ ያልተከተለና ችግር ያለበት ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለፃ አክቲቪስትነት ለሕዝብ ጥቅም ሲባል መጠየቅና ኢ-ፍትሐዊ አሠራሮችንም ማጋለጥ እንጂ የመንግሥት አካል ስለሆነ ብቻ ጥፋት እየሰራም መደገፍ ስላልሆነ ድጋፍን ብቻ የሚቀሰቅሱ የመንግሥት ፕሮፓጋንዳ ሠራተኞችም አክቲቪስት ሊባሉ አይችሉም ሲሉ ይሞግታሉ።
“ጠያቂነት ትልቅ ኃላፊነት የሚያስፈልገው
ሥራ ነው፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች መጠየቅም ከሁሉም የላቀ ተግባር በመሆኑ አክቲቪስት ከማንም በላይ ትልቅ ኃላፊነት አለበት” የሚሉት ጋዜጠኛው፤ ይህንን ኃላፊነቱን የማይወጣና ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሰራ ማንኛውም አካል አክቲቪስት ሊባልም ሊሆንም የማይችል መሆኑን ያመለ ክታሉ፡፡
ይሁን እንጂ በሕዝብ ላይ የሚያሴሩና ራሳቸው አድሏዊ አሠራርን እየተከተሉ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ ፖለቲከኞችንና የመንግሥት ባለሥልጣናትን የሚያጋልጡ ትክክለኛ አክቲቪስቶችን “ሕዝብን ከሕዝብ ልታጋጩ ነው” ማለትም የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ሕግንና ሥርዓትን ጠብቀው በኃላፊነት የሚሰሩ አክቲቪስቶች መኖራቸው ከምንም በላይ ለሀገርና ለሕዝብ ለራሱ ለመንግሥትም አስፈላጊ መሆኑን ጋዜጠኛ ጌታቸውም ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ጋር ይስማማል፡፡
እንደ አክቲቪስት ስዩም ገለጻ አንዳንድ ራሳቸውን አክቲቪስት ብለው የሚጠሩ አካላት የሚጽፏቸው ጽሑፎች ሕዝብን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚመሩ በመሆናቸው በእኛ ሀገር አክቲቪስትነት ከጥቅሙ ይልቅ አፍራሽነቱ እያመዘነ ነው የሚለውን ሃሳብ የማይስማሙበት መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡
ምክንያቱም ከመነሻው አንድ ሰው ጥላቻን በመስበክና ሕዝብና ሕዝብን በማጋጨት አገርን ለማፍረስ የሚሰራ ከሆነ “ወንጀለኛ” መባል ሲገባው እንዴት አክቲቪስት ሊባል ይችላል? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አንድ አክቲቪስት ብሔሬ ወይም ሃይማኖቴ ተገቢውን ጥቅም አላገኘም ብሎ ካሰበ መብቱንና ጥቅሙን ለማስከበር ቢታገል ችግር ላይኖረው ይችላል ሲሉም አቶ ስዩም ይከራከራሉ፡፡
“ሆኖም የእኔ ብሔር መብት በሌሎች መብት ላይ፡- የእኔ የበላይነት ይከበር ማለት አግላይነትና ዘረኝነት ነው”፡፡ የሚሉት አክቲቪስቱ፤ ስለሆነም “አክቲቪስትነትን” እና “ዘረኝነትን” ለይቶ ማየት ተገቢ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡ የሌሎችን መብትና እኩልነት ሳያከብሩ ለራስ መብት መከበር ብቻ መታገል የአክቲቪስትነትን መሠረታዊ ዓለም አቀፍ መርሆ የሚጻረር ነው ብለዋል፡፡
የአንድ አክቲቪስት ሃሳብ ለበርካታ ሰዎች የሚዳረስና በአዎንታዊም ይሁን በአሉታዊ ጎኑ በብዙኃኑ ላይ ተፅዕኖን የመፍጠር ባህርይ ያለው ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ከእያንዳንዱ ተግባራቸው ጀርባ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሆኖም አሁን በኢትዮጵያ ያለው አክቲቪስትነት ከማህበራዊ ኃላፊነት ተነጥሏል ሲሉ ይተቻሉ፡፡
አገር ሁሉ ሊያፈርስ የሚደርስ ጽሑፍ እየፃፉ ራሳቸውን እንደ አክቲቪስት የሚቆጥሩ አካላት አሉ ያሉት አቶ ዳንኤል፤ “በሰለጠኑ አገራት ያሉ አክቲቪስቶች ለእያንዳንዷ ነገር ይጠነቀቃሉ፤ አብዛኞቹ የእኛ አገር አክቲቪስቶች ግን የሚጽፉት ይቀስቀስልኛል ያሉትን ነገር ብቻ ነው፤ የሚያነሱት ጉዳይ በሀገርና በሕዝብ ላይ ሊያመጣው የሚችለውን ጉዳት አያስቡትም፤ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳለባቸው ረስተውታል” ሲሉ ይወቅሳሉ፡፡
የመረጃ ማሰራጫ ዘዴው በራሱ ማህበራዊ ኃላፊነት እንዳይኖር ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል፡፡ ምክንያቱም አብዛኞቹ በአክቲቪስት ስም የሚለቀቁ መረጃዎች ባለቤታቸው ማን እንደሆነ አይታወቁም፡፡ ባለቤት በሌለበት ሁኔታ ደግሞ ማህበራዊ ተጠያቂነትን ለመፍጠር አስቸጋሪ እንደሆነም አቶ ዳንኤል ያስረዳሉ፡፡
“የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሥርዓታችን ነው እንጂ አክቲቪስትነት በእኛ ሀገርም ብዙ መልካም ለውጦችን አምጥቷል” የሚሉት የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩና ተመራማሪው፤ አሁንም ቢሆን በኃላፊነት ከተሰራበት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
በአቶ ዳንኤል ሃሳብ የሚስማሙት አቶ ስዩም በበኩላቸው ለአክቲቪስትና ለአክቲቪስትነት ጥላቻ እንዲኖረውና ሥራው በበጎ እንዳይታይ እያደረጉ የሚገኙት በአብዛኛው ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ሸሽተው በውጭ አገራት በሃሰት ስም ሲጠቀሙ የነበሩ አካላት መኖራቸውን ይገልጻሉ፡፡ ከለውጡ በኋላ ደግሞ በሀገሪቱ የመጣውን ነፃነት ተጠቅመው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ በሕዝብ ስም በማን አለብኝነትና ጀብደኝነት ሕዝብን ለጥፋት እየቀሰቀሱ ያሉትንም ሳያነሱ አላለፉም፡፡
በመሆኑም አገርና ሕዝብን እያባሉ ራሳቸውን አክቲቪስት ነን ብለው የሚጠሩ አካላትን እነርሱ ቢሉ እንኳን ሕዝቡ አክቲቪስት ብሎ ሊጠራቸው አይገባም፡፡ እንዲያውም በወንጀል ሊጠየቁ ይገባል የሚሉት አቶ ስዩም፤ በዚህ መንገድ ዘረኝነትንና ወንጀለኝነትን ከአክቲቪስትነት መነጠል ሲቻል አክቲቪስትነትን ለትክክለኛ ዓላማው፤ እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መጠቀም የሚቻልበት ዕድል ይፈጠራል ብለዋል፡፡
‹‹የአክቲቪስትነት ሥራ መናገርና መጻፍ ከተፈቀደ በኋላም ሌላ ችግር ገጥሞታል፡፡ ለራሳቸው ጥቅምና ለግል ፖለቲካዊ ፍላጎቶቻቸው የሚሰሩ አካላት በአክቲቪስት ስም ለሕዝብ ጥቅምና ፍላጎት ያሰቡ በማስመሰል ሕዝብና ሕዝብን የሚያጋጩና በአገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ ሃሰተኛ መረጃዎች በብዛት እንዲያሰራጩ ዕድል በመፍጠሩ ሥራውን ከፍተኛ የተዓማኒነት ችግር ውስጥ አስገብቶታል፡፡ ይህም ለሕዝብ ጥቅም ከቆመው ትክክለኛው የአክቲቪስትነት ዓላማ በተቃራኒው የተሰለፈ በመሆኑ ለአክቲቪስቱና ለሥራው ትልቅ ፈተና ሆኗል›› ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡
አስተያየት ሰጪዎቹ ሲያጠቃልሉ፤በሁለቱም ወገን በመገናኛ ዘዴውም በአክቲቪስቱም በኩል የሚስተዋሉ ችግሮችን አስተካክሎ ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም ዘብ የቆመውን ሙያ ለአዎንታዊ ለውጥ ማዋልና ለመልካም ነገር ብቻ መጠቀም ይቻላል በማለት ነው፡፡
በስምና በአድራሻ ተለይተው የሚታወቁ አክቲቪስቶች የእነርሱ ሃሳብ በሕዝብና በአገር ላይ ሊያስከትለው የሚችለውን አውቀው በኃላፊነት ስሜት መስራት በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመፍታት አንደኛው መንገድ ነው፡፡ ለዚህም ሁሉም አካላት ተገናኝተው የሚመክሩበትና ለችግሩ መፍትሔ የሚፈለግባቸው ሕዝባዊ ውይይቶች ያስፈልጋሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥትም የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ሕግና ሥርዓት ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 19/2011
በይበል ካሳ