ነገሮች ማነፀሪያ እና ዋጋ ከሌላቸው ዓለም ከንቱ ናት። ይህን ለማወቅ ጊዜ እና ሁኔታን ማገናዘብ ተገቢ ነው። ይህን መግቢያ ሐሳብ ያጠናክርልኝ ዘንድ ይህን ተረት ልጠቀም ተገደድኩኝ።
ከዕለታት ባንዱ ቀን አንድ ታዳጊ አባቱን ‹‹የህይወት ዋጋው ስንት ነው?›› ሲል ጠየቀው። አባትም መልስ በመስጠት ፈንታ ልጁን እንዲህ ሲል አዘዘው። ‹‹እንካ ይህንን የድንጋይ ቁራጭ…ወደ ገበያ ውሰደው። ሰዎችም ዋጋውን ከጠየቁህ በጣቶችህ ሁለት ቁጥርን ብቻ አሳያቸው እንጂ ምንም አትናገር›› አለው።
ልጁም ድንጋዩን ወሰደ። ወጥቶም በገበያ መሃል ቆመ። አንዲት ሴትም መጣች። ‹‹ይህ ድንጋይ ዋጋው ስንት ነው? ብትሸጥልኝ ወስጄ ግቢዬ ውስጥ አስቀምጠዋለሁ›› አለችው። ልጁም እንደታዘዘው ምንም ሳይናገር ሁለት ጣቶቹን አሳያት። እሷም አለች ‹‹ሁለት ብር? እወስደዋለሁ›› ልጁም ወደ ቤቱ ተመለሰ።
በገበያ ያጋጠመውንም ለአባቱ ነገረው። አባትየውም አለው ‹‹አሁን ደግሞ ድንጋዩን ይዘህ ወደ ሙዚየም ሂድ። ዋጋውን ሲጠይቁህም ሁለት ጣቶችህን አሳይ››አለው። ልጁም ወደ ሙዚየም ወጣ። ገዢም መጥቶ ዋጋ በጠየቀው ጊዜ ሁለት ጣቶቹን አሳየው። ገዢውም ‹‹ሁለት መቶ ብር? እወስደዋለሁ!›› አለው። ልጁም በድንጋጤ ወደ ቤቱ ተመለሰ። ያጋጠመውንም ለአባቱ ነገረው።
አባትየውም ተናገረ፤ ‹‹አሁን ደግሞ በመጨረሻ ድንጋዩን ይዘህ ወደ የከበሩ ማዕድናት መሸጫ ሂድ ለባለቤቱም አሳየው›› አለው። ልጁም ሄደ። ለሱቁም ባለቤት አሳየው። የሱቁ ባለቤት በመገረም ‹‹ይህ እኮ አለም ላይ እጅግ ውድ ከሆኑ የከበሩ ድንጋዮች አንዱ ነው›› አለ። ‹‹ከየት አገኘኸው? ስንትስ ትሸጠዋለህ?›› ሲል ጠየቀው። ልጁም ምንም ሳይናገር ሁለት ጣቶቹን አሳየ። የሱቁም ባለቤት ‹‹ይህንን ድንጋይ 200ሺ ብር እወስደዋለሁ››አለው፤ ልጁም በመገረም እየሮጠ ወደ ቤቱ ተመልሶ ያጋጠመውን ለአባቱ ነገረው።
አባትየውም ‹‹ልጄ አሁን የህይወትህ ዋጋ ተገልጦልሃል›› አለው። አየህ የመጣህበት ቦታ፣ ዘርህ፣ ሃይማኖትህ፣ የቤተሰቦችህ ሃብት፣ የተወለድክበት ቦታ ልዩነት አይፈጥርም። ዋናው ራስህን የምታስቀምጥበት ቦታ፣ ራስህን የምታገኝበት የሰዎች ስብስብ ነው። ልዩነቱ ያለው ራስህን ለመሸከም በምትመርጥበት መንገድ ነው። ህይወትህን ሙሉ የሁለት ብር ድንጋይ ዋጋ ስትሰጠው ኖረህ ይሆናል።
ህይወትህን ሙሉ የኖርከው ዋጋህ ሁለት ብር ብቻ እንደሆነ በሚያስቡ ሰዎች ተከበህ ይሆናል። ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ውድ የሆነ የከበረ ድንጋይ በውስጡ ይዟል። ልዩነቱም ያለው ውስጣችን ያለውን የከበረ ድንጋይ አይተው ዋጋ በሚሰጡን ሰዎች መሃል መገኘትን ስንመርጥ ነው። ራሳችንን በገበያ ወይም በከበሩ ማዕድናት ሱቅ የማስቀመጥ ምርጫው አለን።
በሌሎች ሰዎች ውስጥ ያለውንም ውድ ዋጋ ለማየት ምርጫው የኛው ነው። ሌሎች ሰዎችም የከበረ ዋጋቸውን እንዲረዱ ማድረግ እንችላለን። አብረህ የምትውላቸውን ሰዎች በጥንቃቄ ምረጥ። ይህ በህይወትህ ልዩነትን ይፈጥራል ሲል ልጁን መከረው ይባላል።
ይህን አጭር መግቢያ ተረት መሰል ግን ቁምነገር አዘል አባባል ለመጠቀም ያስገደደኝ የአገራችን ሰሞንኛ ጉዳዮች ናቸው። በርካቶቻችን ለአንዳንዶች ምንሰጠው ዋጋ እና እነርሱ ለራሳቸው የሚሰጡት ዋጋ አለመጣጣሙ ብዙ ኪሳራ ወይንም ምንም ትርፍ የሌለው ሆኖ እናገኘዋለን።
ለዘመናት ሥናቀነቅን የነበረው የዘረኝነት፣ መንደሬነትና የዘውጌ ፖለቲካ ኢትዮጵያን ክፉኛ አጎሳቁሏታል፤ ከባድ ህመም ውስጥ ከቷተል። የእነዚህ ሰዎች ኢትዮጵያን ያለቦታው እንደተቀመጠ እንቁ አድርገዋታል። በተለይም አሸባሪቹ ሸኔ፣ ሕወሓት፣ ጽንፈኛው የቅማንት ቡድን እና በአንዳንድ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ኢ-መደበኛ ኃይሎች የኢትዮጵያን ልክ መረዳት አልቻሉም፤ መረዳትም አይፈልጉም።
አሸባሪው ሕወሓት በአምሳሉ የፈጠራቸውን በሙሉ በአይዞህ ባይነት ወደመጥፎ አረንቋ ነው የወሰዳቸው። ‹‹ግም ለግም ተያይዘህ አዝግም›› እንደሚባለው፤ ሁሉም ተያይዘው ገደል እየገቡ ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ እንደ ጠላት እየወጉ የምንታገለው ለአንተ ነው ብለው ሊያሞኙ ይፈልጋሉ።
ዘረኝነትና ተረኝነትን ከሚገባው በላይ ሲያጋግል የቆየውአሸባሪው ሕወሓት በመጨረሻ እራሱ ተለብልቦበታል። ለሕወሓት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በሚገባው ቋንቋ አነጋግረውት ተገቢውን አግኝቷል ።
አለውልህ የሚለውን ህዝብ በርሃብ አለንጋ እንዲገረፍ እሱ በለኮሰው ጦርነት ከፍ ያለ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል። አሁንም ከዚህ የሕወሓት የውርደት ሞት ያልተማሩ ፀረ- ሠላም ኃይሎች ኢትዮጵያን እየወጉ መጀገን ይፈልጋሉ።
እናቱን ከኋላ እየወጋ ጀብደኛ የተባለ አልሰማንም፤ አላየንም ወደፊትም አይኖርም። የሕወሓትን ዋጋ የሚያውቅ አካል በዚያው ልክ ለመለካት መሞከር በእጅጉ አሳፋሪ ለውድቀትና ውርደት መዘጋጀት ነው። ሸኔ እና መሰሎቹም ምኞት ይኸው ነበር።
ሸኔ ከኤርትራ በርሃ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስና በአገሩ እንዲንቀሳቀስ እድል፤ ክብርና ፍቅር ቢሰጠውም ‹‹ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ ሆኖ›› ኢትዮጵያን ከውስጥ ሆኖ እያደማት ነው። ሰንጋ አርደው እልል ብለው የተቀበሉትን ወገኖቹን እየገደለ፤ እየዘረፈ፤ እየደፈረና እያሳደደ ነው።
ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ በሠላማዊ መንገድ እንዲታገል ሲፈቀድለት አሻፈረኝ ብሎ የድል አጥቢያ አርበኛ ሆኖ ኢትዮጵያን እያደማት ነው። ኢ-መደበኛ ሃይሎችም መንግስትን እገዳደራለሁ ብለው ቡራ ከረዮ እያሉ ነው። ዳሩ ግን ይህ ልፋታቸውና የክፉ አመል ፖለቲካቸው ገደል እያስገባቸው ነው። እንኳንስ መንግስትን መገዳደር ቀርቶ በአንዲት ትንሽ መንደር ተቀባይነት አጥተው እንደ እብድ ውሻ እዚህም እዚያም እየተክለፈለፉ ነው።
ከእውነታው መረዳት የሚቻለው ርካሽ ሆነው በውድ የገመትናቸው እነዚህ የድል አጥቢያ ኃይሎች የሚጀምሩት እንጂ የሚፈፅሙት ትግል የለም። የሚመኙት እንጂ የሚዘልቁበት ወይንም የሚቆናጠጡት ስልጣን የለም። የሚያደሙት እንጂ የሚጠቅሙት ህዝብ የለም።
ከእነዚህ ኃይሎች ወቅታዊ ቁመና እና እሳቤያቸው አንድ ነገር መረዳት ይቻላል። ርካሽ ሆነው ሳለ እኛ እንደ ውድ ቆጥረናቸው ቆይተናል። እነዚህ አካላት ልክ ከላይ እንደተጠቀሰው ምሳሌ ናቸው። ከመጀመሪውኑ ዋጋቸውን በደንብ ሳንረዳ በጣም የካብናቸው ናቸው። እንደከበረ ማዕድን ስናያቸው የነበሩቱ አሁን ዋጋቸው ከሚዛኑ ወርዷል።
ቀድሞውኑ ያለቦታቸው ማስቀመጥና መመዘን አልነበረብንም። በወርቅ ሚዛን ስንለካቸው የነበረው ከአመድ አንሰው መገኘታቸውን ከግብራቸውና ምግባራቸው መረዳት ይቻላል። ልክ ታዳጊው የህይወትን ዋጋ ለመረዳት እንደተንከራተተው እኛም የእነዚህን አካላት ዋጋ ለማወቅ ዘግይተን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ጊዜ እውነተኛ መነጽር ነውና የእነዚህ የእናት ጡት ነካሾችን ዋጋ አሁን ለመገንዘብ በቅተናል፤ በፀረ ኢትዮጵያ አቋማቸው።
እነሱን ለማወቅ ያጠፋነው ጊዜ ሊቆጨን አይገባም፤ ከአሁን በኋላ ለሚመጣው መዘጋጀት እንጂ። በመሆኑም እነዚህ አካላት ዋጋቻውን ሰቅለን ከሆነም በልኩ ልንመዝናቸው፤ ያለቦታቸው አስቀምጠን ከሆነም ወደሚገባቸው ቦታ መመለስና የእነርሱን እውነተኛ ዋጋ እና ምስል ማሳየት አለብን።
ይህ የሚሆነው ደግሞ እንደ ጀበደኛ እና እንቁ የሰቀልናቸው ከትቢያ ያነሱ ስለመሆናቸው በሚገባ በማሳየት ነው። ይህ የሚሆነው ደግሞ ዋጋቸው ስንት ነው በሚል የተቃለለ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ከምንም የማይቆጠሩ መሆናቸውን በእውነተኛ ትግል ዋጋቸውን በማሳነስና ሀቁን በማስቀመጥ ነው።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6 ቀን 201”4 ዓ.ም