ዓለማችንን ከጫፍ እስከ ጫፍ በማገናኘት በአንድ ማዕድ እያቋደሰ የሚገኘው የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዕድገቱ እጅግ ፈጣን ነው። ለአብነትም በፈረንጆቹ 2019 የወጣ መረጃ መሰረት በዛው ዓመት ከዓለም ሕዝብ ግማሽ ያህሉ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ መሆኑን ማመልከቱን መጥቀስ ይቻላል።
በየሰኮንዱ ብቻ በአማካይ ከ74 እስከ 500ሺ ጂቢ በላይ መረጃዎች ሊላክበት በቅቷል። የማህበራዊ ሚዲያ (ፌስ ቡክ)፤ ቴሌግራም ቲውተርና ሌላውም አጠቃቀሙ ቀላል መሆኑም ተመራጭ ስላደረገው አብዝቶም ግላዊ፣ ማህበራዊ፤ ፖለቲካዊ ፤ የንግድ እና ሌሎች ግንኙነቶች የሚደረግበት ሆኗል። ፍጥነቱና ጠቀሜታውም እየጎላ መጥቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያየ መገናኛ ብዙሃንና ንግድ ዘርፍ የሚሰሩ ሴቶች እንደሚናገሩት ተግባርን ከማቅለልና ጊዜን ከመቆጠብ ባሻገር ራስን ለማስተዋወቅ፤ ለማንቃትና ለተለያዩ ጉዳዮች ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ተገኝቷል። የጥቅሙን ያህልም ቴክኖሎጂውን መሰረት አድርገው በሴቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ጥቃቶች እየተበራከቱ መጥተዋል።
እኤአ በ2020 ወርልድ ዋይድ ዌብ ባጠናው ጥናት ላይ ተሳታፊ የነበሩ 52 በመቶ ወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች በይነመረብን በሚጠቀሙበት ወቅት ለወሲባዊ ትንኮሳዎች ለሚያስፈራሩ መልዕክቶች፤ እንዲሁም ግላዊ ፎቶግራፎቻቸው በሌሎች ሰዎች እጅ እንዲገቡ የመደረግ ተገቢ ላልሆኑ የጥቃት ዓይነቶች ተዳርገዋል። 64 በመቶው የዚሁ ጥናት ተሳታፊዎች ደግሞ በድረ ገጽ አማካኝነት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሌሎች ሴቶችን እንደሚያውቁ የተናገሩበት አግባብ አለ። ከአሥር ሴቶች አንዷ ከ15 ዓመቷ ጀምሮ አንድ የሆነ ዓይነት የሳይበር ጥቃት ይደርስባታል። እንደዚሁም UN Women በፈረንጆቹ 2015 ባደረገው ጥናት ሴቶች ከወንዶች 27 በመቶ በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) በተደገፉና ስምና ዝናን ለሚያጎድፉ ጥቃቶች እንደሚጋለጡ ያሳያል።
ሆኖም ‹‹ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም›› እንዲሉ ሴቶች ጥቃቱን ፈርተው ከቴክኖሎጂ ራሳቸውን ማግለል አይገባቸውም ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሴቶች አበክረው ሲናገሩ ይደመጣል።
ወጣት ሶሎሜ ይግረም በንግድ ሥራ የተሰማራች ሴት ነጋዴ ስትሆን በሙያዋ ስለ ንግድ ሥራ ሌሎች ነጋዴዎችን በማማከረም ትሰራለች። ሶሎሜ እንደምትለው ዛሬ ሁሉም ነገር በበይነ መረብ (ኢንተርኔት) በቀጥታ ነው የሚከናወነው። ለአብነት በኢትዮጵያ ከሚመደበው አጠቃላይ በጀት 64 በመቶ የሚሆነውን ግዙፍ ድርሻ የሚወስደውን የመንግስት ግዢን ጨምሮ የተለያየ ጨረታ መረጃዎች የሚሞላበትን ሂደት መጥቀስ ይቻላል። በመሆኑም ቴክኖሎጂው እንደ እሷ በንግድ ላይ ለተሰማራች ሴት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ትናገራለች። በዓለም ላይ የሴትና የወንዶቹ ቁጥር የተመጣጠነ ቢሆንም ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ የሆኑት ሴቶች ቁጥር እዚህ ግባ እንደማይባል የምታወሳው ወጣቷ ነጋዴ ቴክኖሎጂው በዓለም ዙሪያ በተለይም በአገራችን በንግዱ ዘርፍ የሚሰማሩ ሴቶች ቁጥርንም ሆነ በመስኩ ያላቸውን ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብላ ታምናለች። ግን ደግሞ ሴቶች ሲጠቀሙ ለተለያዩ ጥቃቶች እንዳይጋለጡ እጅግ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው ትመክራለች። ይሄን የቀጥታ (ኦን ላይን) ጨረታ አዘወትረው ወንዶችም በክፍያ ይሞሉላቸዋል የምትለው ሶሎሜ ራሳቸውን ችለው መሙላት እንዳለባቸውና ከዚሁ ጋር በተያያዘ በኦን ላይ ከወንዶች ሊገጥማቸው የሚችለውን የጥቅም ግጭት ጫናን ተቋቁሞ በአሸናፊነት ለመውጣት እና አጠቃቀምን ጥንቃቄ የተሞላበትና ውጤታማ ለማድረግ ከቴክኖሎጂው አንዳንዶቹ ላይ ምን አልባት በዙሪያው ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ስልጠና መውሰድ ሊያስፈልግ ሁሉ እንደሚችልም ትጠቁማለች።
የትኞቹም ዓይነትና በየትኛው ደረጃ ያሉ ሴቶች በመስኩ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ራስን የበለጠ ከማሳደግና ተጠቃሚ ከማድረግ ጋር የምታያይዘው ጋዜጠኛ ቅድስት ክፍለዮሐንስም እንደምትለው በማህበራዊ ሚዲያ (ፌስ ቡክም) ሆነ በሌሎች መገናኛ ዘዴዎች የአንዲት ሴትን ራቁት ገላ እንዲሁም በወሲብ ድርጊት እየተሳተፈች እንደሆነች የሚያሳይ ምስል በመልቀቅ ሴቶች ላይ ጥቃት ይደርሳል። የሚገርመውና እጅግ የሚያሳዝነው ጥቃት ፈፃሚዎቹ በቀል በሚመስል ሁኔታ ተጠቂዋ የት እንደምትኖር የግል መረጃዎቿ ጭምር ከምስሉ ጋር የሚሰራጭበት ሁኔታ መኖሩን በተደጋጋሚ መታዘቧን ትናገራለች። ይሄ ዓይነቱ ጥቃት በተጠቂዋ፤ ብሎም በወንድም ሆነ ሴት ጓደኞቿ፤ እንዲሁም በልጆቿና በቤተሰቧ ስነ ልቦና ላይ የሚያሳድረው ጫና ቀላል አይደለም የምትለው ጋዜጠኛ ቅድስት ብዙ ጊዜ በዚሁ ጥቃት ፍራቻ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ንቁ የቴክኖሎጂው ተሳታፊ ሴቶች ራሳቸውን ከቴክኖሎጂው ተጠቃሚነት ሲያገሉ ማየቷን ታወሳለች።
ስም ማጥፋትና የሐሰት አርትኦት በቴክኖሎጂው አማካኝነት በሴቶች ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች የሚደመር መሆኑንም ትጠቅሳለች። በቅርቡ ቴክኖሎጂን መሰረት አድርገው እየደረሱ ያሉ ጥቃቶችን ለሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ለማሳወቅና ለመከላከል በተዘጋጀና በተካፈለችበት ስልጠና በሀሰት ማንነት አርትዖት በእውነተኛ የምስሉ ባለቤት ሴት ላይ የተለያየ ተፅዕኖ መፍጠሩን ያየችበትም አጋጣሚ ትናገራለች። የዚችን ሴት እውነተኛ ፊቷን ብቻ በመውሰድና ከሌላ የወሲብ ፊልም ጋር በማቀናጀት ራቁቷን እንደሆነች ወደሚያሳይ ቪዲዮ መለወጡን ተረድታለች። ይሄ ደግሞ አሁን ላይ በቴክኖሎጂው በስፋት እየተሳተፉ ያሉትን ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለመሳተፍ የሚያስቡትን በመገደብ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ ከወዲሁ መገመት እንደሚቻልም ታነሳለች።
በአብዛኛው እንዲህ ዓይነት ጾታዊ ጥቃቶች የሚሰነዘሩት በቴክኖሎጂው ንቁ ተሳታፊ በሆኑ ሴቶች ላይ ነው። እነዚህ ሴቶች በታዋቂ መገናኛ ብዙሃን ወይም በሌላ ተቋም የሚሰሩና ታዋቂዎችም ሊሆኑ ይችላሉ ስትል አስተያየቷን የሰጠችን የቃና ቲቪ ወጣት ጋዜጠኛ ምስራቅ ታረቀኝ ነች ። የዚህ ጥቃት መነሻ ምክንያት በቀልም ሆነ ምንም ዓላማው ሴቶች በስፋት በቴክኖሎጂው እንዳይሳተፉ መገደብ እንደሆነም ታነሳለች ።
እንዳለችው በተለይ በቴሌቪዥን መስኮት ሆነ በሌላ ምስላቸው እየታየ ሥራቸውን የሚሰሩ ሴቶች ይበልጥ ለጥቃቱ ተጋላጭ የሚሆኑበት አጋጣሚ የጎላ ነውም ትላለች። ማናቸውም ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እንደማናቸውም ዓይነት ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች የሴቶችን መሰረታዊ መብቶችና ነጻነቶች እንዲሁም ክብራቸውንና እኩልነታቸውን ይጥሳሉ። እኩል ተጠቃሚነታቸውን በማስተጓጎልም እያንሰራራ ያለ ዕድገታቸውን ወደ ኋላ ይጎትታሉ። በሁሉም ደረጃ በሕይወታቸው ላይ ከፍተኛም ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው አያጠያይቅም። በስነ ልቦና ላይ የሚያሳድሩት ጫናም ቢሆን ቀላል አይሆንም። በኬኒያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ሜክሲኮ ፤ ቦስኒያን ጨምሮ በሰባት አገራት የተካሄደን አንድ ጥናት ዋቢ አድርጋ ጋዜጠኛዋ እንደተናገረችው በነዚህ አገራት ከሚኖሩ ሴቶች መካከል በቴክኖሎጂ በመደገፍ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ሰለባ የሆኑ አሉ። በጥቃቶቹ በማያቋርጥ ጭንቀት፤ ድብርት፤ የአእምሮና የስሜት ውጥረት ተከታታይ ችግር ውስጥ የገቡበት ሁኔታ መኖሩን ጥናቱ እንደሚያመላክት ወጣቷ ጋዜጠኛ ምስራቅ ታወሳለች። በሴቶች ላይ የሚደርሱ ትንኮሳዎች ከማህበራዊ (ፌስ ቡክ) ገጽ ውጭ በኢሜል በሀሰተኛ ኢሜል መለያ አማካኝነት ተለጥፈው ብዙ ችግሮች ያደርሳሉም ትላለች። ጭራሽ አንዳንድ ሴቶች በወሲባዊ ድርጊት ወቅት በቪዲዮ እየተቀረፁ እንደሆነ በማያውቁበት ሁኔታ ተቀርፀው በበየነ መረብ የሚሰራጭበት አስከፊ ጥቃት የሚደርስባቸው ሁኔታም እንዳለ ትናገራለች።
ምስራቅ ጥቃቱ የሚደርስባቸውን ሴቶች ዓይነት አስመልክታም የአመነስቲ ኢንተርናሽናል ተመራማሪዎችን ዋቢ ያደረገ ሀሳቧን በማካፈል ነው አስተያየቷን የቋጨችው። እንደምትለው ታዲያ ተመራማሪዎቹ እንዳረጋገጡት በአሜሪካና በእንግሊዝ ያሉ ሴት ጋዜጠኞች እና ፖለቲከኞች በበየነ መረብ ላይ የጥቃት ሰለባ የመሆን ዕድላቸው ከነጭ አቻዎቻቸው ጋር ሲነፃፀር 84 በመቶ ከፍ ያለ ነው። ጥቁሮችና ከአናሳ ጎሳ የሆኑ ሴቶች 34 በመቶ የበለጠ በተሳዳቢዎች ወይም ችግር በሚፈጥሩ ትዊቶች ውስጥ የመጠቀስ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
አካል ጉዳተኞች ከጉዳት አልባው የሕብረተሰብ ክፍል በበለጠ በቴክኖሎጂው አማካኝነት የሚደርስ ጥቃት ተጋላጭ ናቸው ያለችን ደግሞ ጤና እና ስነ ተዋልዶ ላይ ትኩረት በማድረግ በግል ሥራ የምትተዳደረው ጋዜጠኛ ማርታ ደጀኔ ነች።
እንደ ማርታ ዲጂታል ሚዲያው ለአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚና ተሳታፊ የሚሆኑበት ሰፊ ዕድል ይዞ መምጣቱን የምታስታውሰው ማርታ በተለይ ሴት አካል ጉዳተኞች አሁንም በዕድሉ የበለጠ በመጠቀምና ተሳትፏቸውን በማጠናከር የራሳቸውን ችግር ከመፍታት ጀምሮ በሕብረተሰቡ ውስጥ የሚጠበቅባቸውን የድርሻቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። የአካል ጉዳት የሌለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በፊናቸው አካል ጉዳተኛውን የማገዝ፤ የማስተዋወቅ፤ የማዝናናት፤ የማስተማር ሥራ በማከናወን በአመለካከት ላይ ፈር ቀዳጅ መሆን ይገባቸዋል።
ጋዜጠኛ ኪያ አሊን በጉዳዩ ዙሪያ በተዘጋጀ አንድ መድረክ ላይ ለሙያ አጋሮቿ ጥናቶችን መሰረት ያደረገ ግንዛቤ ስታስጨብጥ ነው ያገኘናት። ጋዜጠኛዋ እንደምትለው ቴክኖሎጂው አዎንታዊም አሉታዊም ጎኖች አሉት። ራስን ለማስተዋወቅና ለማንቃት ብሎም ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው የዓለም ጫፍ መረጃን በቀላሉና በፍጥነት ለመለዋወጥም ሆነ ለማስተላለፍ ማገዙ፤ ሴቶችም በስፋት የዚሁ ዕድል ተቋዳሽ መሆናቸው አያጠያይቅም።
ሆኖም ቴክኖሎጂውን መሰረት አድርገው በሴቶች ላይ እየደረሱ ያሉ ጾታዊ ጥቃቶች እንዳሉ የተለያዩ ሴቶች ሲናገሩ ይደመጣሉ። ከነዚህም መካከል የማስፈራራትና የመበደል፤ ለአንዲት ሴት ተገቢ ያልሆነ እና ያልተፈለገ ትኩረት በመስጠት መከታተልና ማስጨነቅ እንዲሁም ከወሲብ ጋር የተያያዘ ባህርይን የሚያሳዩ ወሲባዊ ትንኮሳዎች ይጠቀሳሉ።
በተለይ የብልግና ስዕሎችን በሚያሳዩ መጽሔቶችና ድህረ ገጾች ጣቢያዎች በአጠቃላይ በኢንተርኔት ዌብ ወሲባዊ ትንኮሳዎች የተለመዱና ሴቶች በመስኩ ለሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ ስጋት መሆናቸውን ኪያ ትናገራለች።
በኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር የሥራ አስፈፃሚ አባል ጋዜጠኛ የሸዋ ማስረሻ እንደምትለው በመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ የተሰማሩትም ሆኑ ሌሎቹ ሴቶች ላይ በቴክኖሎጂው አማካኝነት ከሚደርሱ ጥቃቶች ድብቅ በሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ (ፌስ ቡክ) ና የተለያዩ አካውንቶች መተቸት ይጠቀሳል። ትችቱ ደረቅ ሳይሆን ማስፈራርያ፤ ስድብና ስም ማጉደፍና ሥራዎቻቸውን ማጠልሸት የተቀላቀለበት ነው። እነዚህ አጠልሺ ነገሮች በማያውቁበት ሁኔታ የገዛ አካውንታቸውን ሀክ በማድረግ የሚለጠፉበት ሁኔታም ይስተዋላል። አንዳንዶቹ በተደራጀ ቡድን የሚደረጉ ጥቃቶች ናቸው።
ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሴት ጋዜጠኞች ለዚህ ጥቃት በመዳረግ እየተሰቃዩ መሆናቸውም ማህበሩና አንዳንድ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚያደርጉት ጥናት ታይቷል። ጥቃቶቹ የሴቶችን የጾታ እኩልነት ለማረጋገጥም ተግዳሮት መሆናቸው ተመላክቷል። ጥቃቶቹ ድንበር የለሽ እንደመሆናቸው በቤተሰብ፤ በማሕበረሰብ፤ በሥራ ቦታዎች፣ በመዝናኛ ብዙሃን፤ በፖለቲካ፤ በስፖርት፤ በጤና አገልግሎቶች በትምህርት ሁነቶችና በሌሎች ሲደርሱ ይስተዋላሉ።
ግን ደግሞ በቴክኖሎጂው መስክ በተለይም በአገራችን እንዲህ ዓይነቱን ሴቶች ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በሕግ አግባብ ዳኝቶ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚደረግበት አግባብ እጅግ ጠባብ ነው። ሆኖም ጥቃቱን የሚመክቱ ህጎች አሉ። ያውም ደግሞ የበየነ መረብ አገልግሎት ገና ሳይጀመረ የነበሩ በርካታ ሕጎች ናቸው። ለምሳሌ፦ የተባበሩት መንግስታት አብዛኞቹ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ሲዘጋጁም ሆነ ወደ ትግበራ ሲገቡ እንዴውም የበየነ መረብ አገልግሎት አልተጀመረም።
በተለይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የህፃናት መብቶች ስምምነትም (CRC)ም ሆነ በሴቶች ላይ የሚደረግ መድልዎ የማስወገድ ስምምነት (CEDAW) ም እንዲሁ። እነዚህ ሰነዶች ለልጃገረዶችና ለወጣት ሴቶች ጥበቃና ከለላ የሚሰጡ ማዕቀፎች ሲሆኑ ሴቶች መሰረታዊ መብቶቻቸውን በመጠበቅ ረገድ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ይደነግጋሉ የምትለው የማህበሩ ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ አባል ጋዜጠኛ የሸዋ ማስረሻ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች የተዘጋጁት የበየነ መረብ አገልግሎት በዓለማችን ላይ ባልነበረበት ዘመን መሆኑንም ታስረዳለች።
አሁን ላይ ማህበሩ እነዚህን ሕጎች መሰረት አድርጎ አባላቱን በቴክኖሎጂው አማካኝነት ከሚደርስ ጥቃቶች ለመከላከል ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ ይገኛልም ብላለች።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2014