ማጭድ ይሆነን ዘንድ ምንሽር ቀለጠ
ዳሩ ብረት እንጂ ልብ አልተለወጠ
ለሳር ያልነው ስለት እልፍ አንገት ቆረጠ።
ሰሞኑን በመገናኛ ብዙኃን የማያቸው ነገሮች ናቸው ይህን የበዕውቀቱ ሥዩም ግጥም ያስታወሱኝ። ባለፈው ሐሙስ ማታ ኢትዮጵያ ቴሌቭዥን አዲስ አበባ ውስጥ ከተለያዩ አካባቢዎች የሕዝብ አስተያየት ያሰባሰበበትን ዜና እያየሁ ነበር። የሁሉም አስተያየት ሰጪዎች መልዕክት የሚያሳየው በጦርነቱ ምን ያህል እንደተማረሩ ነው።
ልብ በሉ! አስተያየቱን የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። ጦርነቱ በነበረበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ደግሞ ምን እንደሚሉ መገመት በጣም ቀላል ነው። የቤተሰብ አባሎቻቸውን አጥተዋል፣ የእርሻ ማሳቸው የመቃብር ቦታ ሆኗል፣ የስነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል።
እነሆ ያ ጦርነት ሁሉንም የአገሪቱ ክፍል ነክቷል። ይሄ የጦርነት ባህሪ ነው፤ እንኳን በአንዲት አገር ውስጥ ለጎረቤት አገር እንኳን ተፅዕኖ ያደርጋል። ስለዚህ ያ ጦርነት ዳግም እንዳይከሰት የተቻለንን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል።
ባለፈው እሁድ አማራ ቴሌቭዥን ላይ አንድ ድራማ እያየሁ ነበር። ድራማውን የሰራው ሙሉዓለም የአማራ ባህልና ኪነ ጥበባት ማዕከል ከአሚኮ ጋር በመተባበር ሲሆን ደራሲው ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ነው።
ምንም እንኳን ድራማ የፈጠራ ሥራ መሆኑን ባውቅም፤ እውነተኛ ወካይ መሆኑን የተረዳሁት ገጠርን በሚገባ ማወቄ ነው። ከከብትና ከብት፣ ከውሻና ውሻ፣ ከልጅና ከልጅ…. የሚነሳ ፀብ አካባቢን ሁሉ ያጥለቀልቃል። ይሄ እያየሁት ያደግኩት ነው።
በድራማው ላይ ሁለት ውሾች ይጣላሉ። አንደኛው ልጅ ለውሻቸው አግዞ ሌላኛውን ውሻ ይመታዋል። ውሻው የተመታበት ልጅ ደግሞ ለምን መታህብኝ ብሎ ከልጁ ጋር ይጣላል። ልጆች ሲጣሉ እናቶች ይመጣሉ። እናቶች ሲመጡ ባሎቻቸው ይጣላሉ። ባሎቻቸው ሲጣሉ የባሎቻቸው ጓደኞች ለየጓደኞቻቸው ያግዛሉ። እንዲህ እንዲህ እያለ ወደ አካባቢና ጎሳ ያድጋል። ከዚያም ወደ ብሔር።
ከዚህ የምንረዳው ነገርየውን ከውሾችና ከልጆች ፀብ ላይ እያለ ማስቀረት ይቻል የነበረ መሆኑን ነው።ውሾች ምንም አያውቁም፤ አጥንት ያጣላቸዋል። ልጆችም እንደዚያው፤ ልጆች ናቸውና አያውቁም፤ አዋቂዎች ግን እዚያው ላይ ማስቆም ነበረባቸው።
የዕውቀቱ ሥዩምን ግጥም መነሻ በማድረግ ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ። ምንሽርን ወደ ማጭድ መቀየር የሚቻለው አስተሳሰብ ሲቀየር ነው። ከጦርነት ምኞትና ሀሳብ እንውጣ።‹‹ጦርነት ማን ይመኛል?›› ይባል ይሆናል። ዳሩ ግን ጦርነትን የሚመኙ አይተናል። ከዳር ሆነው ‹‹ግፋ በለው!›› የሚሉ ብዙ ናቸው።
ከሰሜኑ ጦርነት በፊት ስለ ሰላም ብዙ ተብሏል።ለሰላም ቅድሚያ ለመስጠት ያልተደረገ ነገር የለም።ምንሽር ይቅርና ማጭድ እንያዝ ተብሎ ነበር። ዳሩ ግን አስተሳሰብ አልተቀየረምና ምንሽሩ ወደ ማጭድ ስላልተለወጠ የብዙዎችን አንገት ቆረጠ።
ምንሽርን ወደ ማጭድ ለመቀየር በግለሰብ ደረጃ እንኳን ብዙ ተለፍቷል። በቀልድም በቁም ነገርም ‹‹እንደዋዛ ገንዘብ አያባክንም›› እየተባለ የሚነገርለት አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴ በግሉ አውሮፕላን ተከራይቶ ሽማግሌዎች ይዞ መቀሌ ሄዷል። በሕይወቱ አውሮፕላን የተከራየው ለዚያ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ በአንድ ቃለ መጠይቅ ላይ ሲናገር ሰምቻለሁ። ከአገር በላይ ምንም ስለሌለ በወቅቱ የትኛውንም ነገር አደርግ ነበር ብሏል።
ያ ሁሉ ሳይሳካ ቀርቶ ምንሽሩ ወደ ማጭድ ሳይቀየር ቀረ።እነዚያ ያየናቸውና የሰማናቸው ግድያዎችና ውድመቶች ደረሱ። መፈናቀል በዛ፤ ለኑሮ ውድነቱም አሉታዊ ጫናውን አሳረፈ።
አሁን ያለፈው አልፏል። ከዚያም ከዚህም ያለው ወገን ‹‹ግፋ በለው!›› ማለት ይብቃው። ሁሉም ጥፋትን አይቶታል። በተለይም የአገር ውስጥ ጦርነት ሲሆን ደግሞ አደጋው የከፋ ነው። በተለይም በክረምት የግብርና ሥራ ላይ የተመሰረተውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የከፋ ቀውስ ውስጥ ይከተዋል፤ ይሄ ደግሞ ጦሱ ለሁሉም ነው። ስለዚህ የጦርነት ዳፋ ለሁሉም ይተርፋል፤ እነሆ ተርፎም አይተነዋል።
ስለዚህ ይጀመራል ለተባለው ድርድር ሁላችንም አዎንታዊ አስተዋፅኦ ልናበረክት ይገባል። የሃይማኖት አባቶች፣ የተለያየ ዘርፍ ባለሙያዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆን አለባቸው።
ለሰላም አወንታዊ አስተዋፅኦ ስናበረክት ብዙ ነገሮችን ችለን መሆን አለበት። ከጦርነቱ አትራፊዎች በሚሰድቡን ስድብ ሁሉ መደንበርና መዋዠቅ የለብንም። እነርሱ የሚፈልጉት ሌላ ፖለቲካዊ ትርፍ ስላላቸው ነው።
ሰው ሆኖ ሰላምን የማይፈልግ የለም፤ ዳሩ ግን ቡድናዊ ጥቅም ብቻ የሚያስቡ ኃይሎች ደግሞ አሉ።በእነዚህ ኃይሎች ድርድሩ አይደገፍም።ሌላም ሰው እንዳይደግፈው የተለያዩ አሸማቃቂ ነገሮችን ይጠቀማሉ። ለምሳሌ፤ ‹‹በዚህ ጊዜ እንዲህ ብላችሁ ነበር፣ ያኔ እንዲህ ስትሉ ነበር….” የሚሉ ሙግቶችን ያመጣሉ። ይሄኔ የድርድሩ ደጋፊዎችን ሊያሳስብ የሚገባ መሆን የለበትም። ምክንያቱም እነዚያ ቡድናዊ ጥቅም አስጠባቂዎች የራሳቸውን ሥራ እየሰሩ ነው።
ሁላችንም ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተን ዳግም ጦርነት እንዳይኖር ካላደረግን፤ ለልጅ ልጆቻችን አሳፋሪ ታሪክ ነው የምናስተላልፈው። ይህን እያንዳንዱ ዜጋ ልብ ሊለው ይገባል። ዕድለኛ ሆኖ በአዛውንትነቱ ከልጅ ልጆቹ ጋር ስለወጣትነቱ የሚያወራበት ዕድል ቢያገኝ የሚያኮራ ታሪክ ነው ማውራት ያለበት። በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን እያንዳንዱ መረጃ ተሰንዶ ነው የሚቀመጥ። ስለዚህ በአዛውንትነት ዕድሜያችን ‹‹እናንተ ናችሁ እንዲህ ያደረጋችሁ አይደል?›› መባል የለብንም።
ያለፈው አልፏል። ከዚያ በኋላ ያለውን አሳምረን፣ ያለፈው ልክ እንደ አንድ የታሪክ አጋጣሚ ብቻ ‹‹እንዲህ ተደርጎ ነበር፤ ዳሩ ግን በድርድር ሰላም ሆነ›› መባል አለበት። ድርድር፣ ሰላምና እርቅ፣ ይቅር ባይነት… የኢትዮጵያ አኩሪ እሴቶች መሆናቸውን አስቀጥለን ማሳየት አለብን።
በአዛውንትነት ዕድሜያችን በአገሪቱ ውስጥ የሆነ ነገር እንኳን ቢከሰት፤ እንደ ምሳሌ የምናነሳው ጥሩ ተሞክሮ ማኖር አለብን። ልክ ዛሬ ‹‹አባቶቻችን እንዲህ አድርገው ነው ያቆዩልን›› እንደምንለው ሁሉ፤ እኛም ‹‹እንዲህ አድርገው፣ ይህን ሰርተው ነው ያቆዩዋት›› መባል አለብን። የአባቶቻችን ፈለግ መከተል ብቻ ሳይሆን እኛም ተከታይ ማፍራት አለብን።
መንግሥትም በቆራጥ ውሳኔ ድርድሩን መቋጨትና ሰላምን ማምጣት አለበት። አለበለዚያ በአስተዳደር ዘመኑ መጥፎ ታሪክ ይመዘገባል። እስከ አሁን የሆነውን ‹‹በለውጥ ወቅት የሚያጋጥም ነው›› ቢባልም ከዚህ በኋላ የሚሆነውን ግን በለውጥ ወቅት የሚያጋጥም ነው ብሎ ለመቀበል አያስችልም።
መገናኛ ብዙኃን የጦርነት አዋጅ ነጋሪነት ሊበቃቸው ይገባል። አገሪቱ ከውጭ በኩል ብዙ ስጋት የተጋረጠባት ናት። ስለዚህ የአገር ውስጥ አንድነት መኖር አለበት። ስለዚህ ደግሞ ሁላችንም መበሻሸቅንና መጠላለፍን መተው አለብን። እውነተኛ የአገር ስሜት ያለው ከወገኑ ጋር አይጣላም። ስለዚህ ከድርድር፣ ለእርቅና ይቅር ባይነት ሁላችንም ቅን እንሁን። የኑሮ ውድነት የሚያደርገውን እያየን ነውና ማጭድ እናንሳ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5/2014