ጽጌረዳ ጫንያለው
አውሮፓውያን በዩኒቨርሲቲዎች የራስ ገዝ አስተዳደር ላይ ብዙ ሠርተዋል። እ.ኤ.አ. በ2009 ባወጡት መረጃም የራስ ገዝ አስተዳደርን አንድ ላይ ሰብስበው የአገራትን የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓቶች በአራት ዘርፎች ከፍለው እስከማስቀመጥም ደርሰዋል።
ዘርፎቹ በድርጅታዊ፣ በገንዘብ፣ በሰራተኞች እና በትምህርት የሚሉ ሲሆኑ፤ ከእነዚህም ውስጥ መቶ በመቶ ከመንግስት ቁጥጥር ነፃ የሆኑት አሸናፊ መሆናቸውን አትቷል። በአገሮች መካከልም ሆነ በአገር ውስጥ ሊለያዩ እንደሚችሉም አመላክቷል።
ሁኔታው ከውጭ የገንዘብ ድጋፍ ከመሳብ ችሎታ አንጻር ሲታይ ከገንዘብ ገዝ አስተዳደር ጋር ያስተሳስሩታል። ከፍተኛ የሰራተኞችን የመሳብ ችሎታን ሲያነሳ ደግሞ ደመወዝን ከማቀናበር ጋር ያይዘዋል። ለምሳሌ በዚህ ሪፖርት ካስቀመጣቸው መካከል ፈረንሣይ አንዷ ነች። የዩኒቨርሲቲ ሥርዓቷ የተማሪዎችን የመምረጥ፣ ሥርዓተ-ትምህርቶችን የማዘጋጀት እና የተማሪ ቁጥሮችን የመያዝ ችሎታን የሚያካትተው ትምህርታዊ የራስ ገዝነት አስተዳደሯ ሁኔታ ከማንኛውም አገር በጣም ዝቅተኛ ነው። ሆኖም በገንዘብ ራስ ገዝ አስተዳደር ረገድ የሚደርስባት የለም።
እንደውም እ.ኤ.አ. በ2011 የተደረገው ማሻሻያ የተወሰኑ የራሳቸውን ሕንፃዎች ሊገዙ እንደሚችሉ ሪፖርቱ ያሳያል። ከዚህ አንጻር ግሪክ በአራቱም ደረጃዎች ዝቅተኛ ስትሆን ዩናይትድ ኪንግደም በተከታታይ በከፍተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ መረጃውም አስቀምጧል። ይህንን የአውሮፓን ተሞክሮ ያነሳነው ያለምክንያት አይደለም። ራስ ገዝነት በምን መስክ ያሻግራል የሚለውን ከዩኒቨርሲቲዎች አንጻር ለመዳሰስ ስለወደድን ነው። በቅርቡ ውይይት የተደረገበት የዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝነት ደግሞ መነሻችን ነው።
የሌሎች ተሞክሮ ምን ይመስላል የሚለውን በማንሳትም የተጀመረው ነገር እኛን እንዴት ያሻግረናል የሚለውንም የሚመለከታቸው አካላትን ስላነጋገርን ብዙ መረጃ እንድንጨብጥበትም ያደርገናል። በተለይም እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምን አይነት እንደሆነና እንዴት ልንጠቀምበት እንደሚገባ ከባለሙያዎቹ ሀሳብ ብዙ እናገኛለንም።
ራስ ገዝነትን በተመለከተ ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመሩ ሥራዎች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር በ2014 ዓ.ም አዲስ ከተመደቡ የዩኒቨርሲቲ የቦርድ አባላት እና ፕሬዚዳንቶች ጋር ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ወቅት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዳሉት፤ በትምህርት ስርዓቱ ላይ የሚስተዋለውን የጥራት ችግር ለመፍታት የተጀመሩ የሪፎርም ሥራዎች አሉ። አንዱና ዋነኛው ደግሞ ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ማድረግ ነው። በአሁን ወቅት በአገራችን 47 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የትምህርት ጥራት ጉዳይ አጠያያቂ ደረጃ ላይ ነው። በመሆኑም በየደረጃው እየታዩ ራስ ገዝነታቸውን በማረጋገጥ ትምህርት ተኮር ሥራ እንዲሰሩ ይደረጋል።
የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አኳያ ከሁሉም በላይ ዩኒቨርሲቲዎችን ነጻ ሆነው መስራት አለባቸው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ጅማሮው በአንድ ዩኒቨርሲቲ ላይ ይከናወናል። ምክንያቱም ሁሉም ላይ ከተደረገ አደጋው ሊከፋ ይችላል። እናም በቅርብና ብዙ ነገሮች የተሟሉለት ዩኒቨርሲቲ ተመርጦ የተቀመረው ተሞክሮ በአገርኛ እሳቤ እንዲተገበር ይደረጋል። ለዚህ ደግሞ ተመራጩ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሆኗል። በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ላይ በመቶ ቀናት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል። ችግሮች እየታረሙም ወደ ሌሎቹ ዩኒቨርሲቲዎች ይቀጥላል ብለዋል።
ራስ ገዝ መሆናቸው በዋናነት የሚጠቅማቸው ከፖለቲካ ተጽዕኖ ተላቀው ሥራቸውን በነጻነት እንዲሰሩ፤ የትምህርት ተቋማት የእውቀት ማዕከላት ናቸውናም የፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀሚያዎች እንዳይሆኑ ነው። ልዩ ትኩረታቸው ትምህርት ብቻ እንዲሆንም ያደርጋቸዋል። በተለይም ዛሬ ላይ ላለው አገራዊ ሁኔታ ይህ የሚመጥን ሥራ እንደሚሆን አያጠያይቅም። ስለዚህም ከማንኛውም ተጽእኖ ነጻ የሆኑ ብቁ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ምሁራን መፍለቂያ እንዲሆኑ ይሰራል፤ አሁንም ብዙ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን አንስተዋል።
ራስ ገዝነት በብዙ መልኩ ሊተነተን ይችላል። በአብዛኛው ግን በአስተዳደርና በኢኮኖሚ ራስን ማስተዳደር እንዲሁም ከማንኛውም የፖለቲካዊ ተጽኖ መላቀቅ ነው ተብሎ ይታመናል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የራስ ገዝ አስተዳደር ሉዓላዊነት፣ ራስን በራስ ማስተዳደር፣ ነፃነት እና ኃይል ማሰባሰብ በሚለው ውስጥ ተካቶ የሚሰራበት ነው። ስለዚህም ራስ ገዝነት ውሳኔዎችን የማድረግ እና ከራስ ጋር በሚዛመዱ ጉዳዮች ላይ እርምጃ የመውሰድ ችሎታ ማግኘት ነው። የራሱ ደንቦችን እና የአስተዳደር አካላትን ለማቋቋም የሚቻልበትም ነውና ይህ እውን እንዲሆንም ያላሰለሰ ጥረት እንደሚደረግም ይናገራሉ።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ትምህርት ሚኒስቴር እንደ አዲስ ከተደራጀ በኋላ አዲስ የሥራ አመራር ቦርድ መድቦ እየሰራ ነው። ይህ ቦርድ ደግሞ ከሚሰራቸው ጉዳዮች አንዱ ዩኒቨርሲቲዎችን ነጻና ገለልተኛ ማድረግ ነው። ለዚህም ይበጃል ያለውን አሰራር ቀምሮ ራስገዝነትን ለመጀመር ውሳኔ ላይ ደርሷል። ብዙ እንቅስቃሴዎችም በመደረግ ላይ ናቸው። ሥራው የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጡ ባሻገር በርካታ ጠቀሜታዎችን ለአገር የሚያድልም እንደሆነ ታምኖበታል።
ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንዲሆኑ መደረጉ በርካታ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የገለጹት ዶክተር ሳሙኤል፤ የትምህርት ጥራት ላይ አተኩረው ውጤታማ እንዲሆኑ፣ የተሻለ የሠው ኃይል እንዲያፈሩ፣ ጥራት ያለው ምርምር እንዲያደርጉ እና በሀብት አጠቃቀም ውጤታማ እንዲሆኑ ከማስቻሉም በላይ ለአገሪቱ የሀብት ምንጭ እንዲሆኑም እድል ይሰጣል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን ታላቅ አገርነት በማረጋገጥ በአፍሪካ ደረጃ ብቻም ሳይሆን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርጋታል። ምክንያቱም የሚወዳደሩ ዩኒቨርሲቲዎች ይበራከታሉና ነው ብለዋል።
ተመራማሪና ተግባሪ ምሁራን እንዲፈጠሩም እድል ይሰጣል። ይህ ደግሞ አገሪቱ እድገቷን እንድታፋጥን ከሚያስችላት መካከል ግንባር ቀደሙን የሚይዝ ነው። ስለዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ ማድረጉ ላይ በስፋት ይሰራል። በእርግጥ ነጻ ሲባል ገደቦች ይኖሩታል። የመጀመሪያው ከአገር ህግና ደንብ መውጣት አለመቻል ነው። ይህንን እስከተከተሉ ድረስ ጫና ሳይበዛባቸው የእውቀት ማዕከልነታቸውን ያረጋግጣሉም ብለዋል።
እንደ ዶክተር ሳሙኤል ገለጻ፤ ይህንን ለማድረግ ሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ያስፈልጋሉ። አንደኛው ሀብት ሲሆን፤ ይህንን ሀብት በመንግሥት ብቻ ማምጣት የማይቻል በመሆኑ ሀብት እንዲያመነጩ እና ያላቸውን ሀብት በውጤታማነት እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል። ሁለተኛው የተሻለ ሠው እንዲሰባሰብ ያደርጋሉ። በዚህ ደግሞ ጥራት ላይ እስከታችኛው እርከን ድረስ መድረስ ይችላሉ። የተሻለ መምህር መቅጠር፣ የተሻለ ተማሪ ማስገባትና ሰራተኞች ቀልጣፋ ሆነው በሁሉም ሁኔታ ተመራጭ እንዲሆኑም ያስችላቸዋል። ሦስተኛው ምቹ የአመራር ሥርዓት መኖር ሲሆን፤ አሁን አገር ያለችበትን የአሰራር ግድፈት በብዙ መልኩ ያስተካክለዋል። በተለይም በአቅምና በእውቀት የሚሰራ ትውልድን ከመፍጠር አኳያ የማይተካ ሚና ይኖረዋል። ከስነምግባርና አገር ወዳድነት አኳያም እንዲሁ ትልቅ አቅም ይፈጠርላቸዋል። ራስ ገዝ መሆን ዩኒቨርሲቲዎች ከሙስናና እና ከሀብት ብክነት እንዲድኑም ያደርጋቸዋል።
ዶክተሩ እንደሚሉት፤ ምቹ የራስ አስተዳደር እና ራስ ገዝነት ካለ እንዲሁም ጥሩ የሚባል ሀብት ከተገኘ በዓለም ደረጃ ጠንካራ ተቋማትን መገንባት ይቻላል። ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ ይህንን እድል ካገኙ ብዙ ነገራቸውን እንደሚለውጡ እሙን ነው። እናም በቅርብ ክትትልና ድጋፍ ለማድረግ ምቹ የሆነው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለዚህ ተመራጭ ሆኖ ይተገበርበታል። በዚያ ላይ ዩኒቨርሲቲው የ71 ዓመታት ተሞክሮ ያለው ነውና እርሱን በመጠቀም ብዙ ነገሮቻችንን ያሻግራል።
ዩኒቨርሲቲውን ራስ ገዝ እንዲሆን የፖለቲካ ውሳኔ ከተወሰነ በኋላም ቢሆን በውስጥ ያሉ ዝግጅቶች ምንድናቸው የሚለውን ከማየት አልፎ በአሁን ወቅት የዝግጅቱ ማጠናቀቂያ ላይ ደርሰናል ያሉት ዶክተር ሳሙኤል፤ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ራስ ገዝ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በሁለት ዓመታት ውስጥም ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ እንደሆኑ ይደረጋሉ ብለዋል።
ለዩኒቨርሲቲዎች ራስገዝነት ሲሰጥ ያለምክንያት አይደለም። ምክንያቱ አንድና አንድ ነው። በትምህርት ተፈጥሮ ሕጎች ተመርተው ውጤታማ እንደሚሆኑ ማስቻል ሲሆን፤ በሕጋቸው ማዕቀፍ ውስጥ የራሳቸው ሕግጋት አውጥተው፤ ባለስልጣኖቻቸውን ሾመው፣ እቅዶቻቸውን እና ፕሮግራሞቻቸውን በትምህርት ነፃነት መርሆዎች ውስጥ ወስነው እንዲሰሩ ማድረግም ነው። በተለይም የምርምር ነጻነት እንዲኖር ከማስቻል አንጻር የማይተካ ሚና እንደሚኖራቸው ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ሳሙኤል ማብራሪያ፤ ዩኒቨርሲቲዎች ንብረታቸውን በነጻነት የማስተዳደር ስልጣን ይኖራቸዋል። ለባለስልጣናት፣ ለመምህራን፣ ለተማሪዎች እና ለአስተዳደር ሰራተኞች መብቶችንና እውቅና ይሰጣልም። ለምሳሌ፡- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ራስ ገዝ ብናደርገው የራሱን ችሎታ እና ሀብቶች በመጠቀም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን የመወሰን እና የማከናወን ችሎታውን እንዲያሳድግ እድል ይሰጠዋል። ተግባራትን እና አካባቢን በማጣጣም እና ድጋፎችን በመጠቀም ያለማንም አስተዋሽነትና አዛዥነት እንዲሰራም ያደርገዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ሌላም የሚጠቀሙበት ነገር እንዳለ የሚያነሱት ዶክተር ሳሙኤል፤ ዩኒቨርሲቲዎች የውጪው ፖለቲካ መጥቶ እንዳያተራምሳቸው ይሆናሉ። በራሳቸው ተሟግተውና የሀሳብ ፍጭትን አድርገው የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዲያስተላልፉም በር ይከፍትላቸዋል። የራሳቸው ሕግና ደንብ ያላቸው ስለሚሆኑ እንደስከዛሬው በብሔርና በሀይማኖት የሚጨፋጨፉበት ምክንያት አይኖርም። በቀላሉ ማንንም ሳያስፈቅዱ በአወጡት ሕግ መጓዝ እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። ግባቸው መወዳደር ሳይሆን ማሸነፍን ያደርጋሉም ይላሉ። ለዚህ ደግሞ መንግስት ብቻ ሳይሆን የቦርድ አባላቱ ሊያግዙት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃናም የሁለቱንም ሀሳብ ይጋራሉ። በአገራችን ይህ ተግባር እጅግ አስፈላጊ እንደሆነም ያነሳሉ። በተለይ እርሳቸው የሚያስተዳድሩት ዩኒቨርሲቲ መመረጡ ደግሞ ሥራውን በአግባቡ ከውኖ ለሌላው ማስተላለፍ የሚችልበት አጋጣሚ ስለሚፈጥርለት ደስተኛ ናቸው። እንደርሳቸው እሳቤ፤ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ መሆኑ ብዙ ጥቅም እንዲያገኝ ያስችለዋል። አንዱና ዋነኛው ደግሞ በየጊዜው በበጀት ጉዳይ እንዳይጨቃጨቅ ማድረጉና የፈለገውን እንዲሰራ እድል መስጠቱ ነው።
ከዓመት ወደ ዓመት እየፈሰሰ ያለው ሀብት እንዳይባክንም እድል ይሰጠዋል። ምክንያቱም ሀብቱ በራሱ የሚመጣ በመሆኑ በአግባቡ ይጠቀማል። በጀቱንም ከዓመት ወደ ዓመት ማሸጋገር ስለሚችልና ተጠያቂነት ስላለበት ሀብቱ ትምህርት ጥራቱ ላይ አሻራውን እንዲያሳርፍ ያደርጋል።
የሀብት ማሰባሰቡ ሥራ በራሱ በዩኒቨርሲቲው የሚሰራ በመሆኑ ድካሙ ታውቆ ወደ ተግባር ለመግባትም ያስችላል ያሉት ፕሮፌሰር ጣሰው፤ አሰራሩ መዘርጋቱ ካምፓስ ጭምር የሚያዋጣቸው ድረስ ሄደው እንዲከፍቱ እድል ይሰጣል። ውጪ ጭምር ሊሆን ይችላል። ከሁሉም በላይ ጥራት ያለው ትምህርት ለመስጠት ያስችላል። በተጨማሪም የዩኒቨርሲቲውን አቅም ታይቶ ባንክ ጭምር እንዲያበድረውና የተሻሉ አማራጮችን እያየ እንዲሰራም በር ይከፍትለታል። በተመሳሳይ ተወዳዳሪነት ስለሚሰፋ ወላጆችም ሆኑ ተማሪዎች የሚመርጡት ተቋም እንዲሆንም ያስችለዋል ብለዋል። እኛም ትግበራው እውን ሆኖ ትምህርት ጥራቱ የሚገባውን ውጤት ያግኝ በማለት ተሰናበትን። ሰላም!!
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም