አንተነህ ቸሬ
የኢትዮጵያ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዚህም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት ሲከናውን ቆይቷል። በዚህም የግብርና ምርምር ተቋማት፣ የህብረት ስራ ማህበራት፣ እና የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር ርብርብ ያደረጉ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ያሳደጉና የሕዝቡን፣ በተለይም የአርሶ አደሩን ሕይወት ያሻሻሉ ውጤቶች ተመዝግበዋል። ከግብርና የሚገኘው ምርት በየዓመቱ ጭማሬ አሳይቷል፤ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥም ተችሏል፤ የአርሶ አደሩ ህይወት መቀየር ጀምሯል፤ በርካታ አርሶ አደሮችም ወደ ኢንቨስተርነት የገቡበት ሁኔታ ታይቷል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ተግባራት ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ካላት አቅም አንፃር ሲመዘኑ ለሀገሪቱ የምግብ ዋስትና፣ የስራ እድል ፈጠራና የምጣኔ ሀብት እድገትም ሆነ ለዘርፉ ችግሮች አስተማማኝ መፍትሄ የሰጡ አይደሉም። አሁንም ግብርናውን ኋላ ቀር የአስተራረስ ዘዴን ነው እየተከተለ ያለው፤ ከዝናብ ጥገኝነት መለቅቅ አልተቻለም፤ አርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከመጠቀም የራቀ ሆኖ ቆይቷል። በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አልተቻለም፤ ሚሊዮኖች ከድህነት ወለል በታች እየኖሩ ነው።
እንደ ሀገር ተግባራዊ ተደርገው በነበሩት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶች የሀገሪቱም ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ማሸጋገር አልተቻለም። አሁንም ኢኮኖሚውን እየመራ ያለው ግብርናው ነው። እናም የምጣኔ ሀብት መዋቅራዊ ለውጥን እውን ማድረግ አልተቻለም።
የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ ሀገሪቱ የግብርና አቅሟን በመጠቀም ከድህነት እንድትላቀቅ ለማድረግ ከሚቀርቡ ምክር ሃሳቦች መካከል አንዱ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ነው። ከአምስት ዓመታት በፊት የተቋቋመው የግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክቶሬት የግብርና ሜካናይዜሽን እንዲስፋፋና ምርታማነት እንዲጨምር በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ሜካናይዜሽን ዳይሬክተር አቶ በረከት ፎርሲዶ በኢትዮጵያ ስላለው የግብርና ሜካናይዜሽን እንቅስቃሴና ስለዘርፉ የወደፊት ተግባራት በተለይ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ
የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ፣ ሜካኒካል ወይም ኤሌክትሮ ሜካኒካል የሆኑ ቴክኖሎጂዎች የሰውና የእንስሳት ጉልበትን በመተካት ወይንም በመደገፍ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል አሰራር ነው። አሰራሩ ከተለያዩ የኃይል ምንጮች የሚገኙ ቴክኖሎጂዎች በግብርና ልማት ላይ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚተገበሩበት የቴክኖሎጂ ግብዓት ነው። የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች የመስኖ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች፣ የእንስሳትና ሰብል ልማት እንዲሁም ሌሎች የግብርና ተግባራት ከአየር ንብረትና ከተፈጥሮ ሀብት ጋር ተስማሚ ሆነው ምርታማነታቸው እንዲጨምር የሚያስችሉ ናቸው።
ከእነዚህ ቴክኖሎጂዎች መካከል አንዳንዶቹ የሰው ኃይልና የእንስሳትን ጉልበት ተክተው የሚሰሩ ሲሆኑ፤ ሌሎቹ ደግሞ ከሰው እና ከእንስሳት ጋር ተቀናጅተው የሚሰሩ ናቸው። ከእነዚህ በተጨማሪ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውና ያለሰው ኃይል ራሳቸውን በራሳቸው የሚቆጣጠሩ (Unmanned) የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችም አሉ።
የግብርና ሜካናይዜሽን በኢትዮጵያ
የግብርና ሜካናይዜሽን ትግበራን ውጤታማ የሚያደርጉና በግብርና ሜካናይዜሽን ስትራቴጂ ውስጥ የተቀመጡ መመሪያዎችን መሰረት በማድረግ የጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲጠናከር ተደርጓል። የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችሉ መዋቅሮች ተዘርግተዋል። የቴክኖሎጂው ተቀባይነትና የአፈፃፀም ደረጃ ግን በየክልሎቹ የተለያየ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ገና ታዳጊ ነው። ሀገሪቱ ውስጥ በአብዛኛው ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉት የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች መካከል ለመሬት ዝግጅት (ከመጀመሪያ እርሻ እስከ ዘር መዝራት ድረስ) የሚውለው ትራክተር አንዱ ነው። በትራክተር የፊትና የኋላ የመቆጣጠሪያ ክፍሎች ላይ በመገጠም የሚከናወኑ የእርሻ ኮንስትራክሽን ስራዎች፣ ማለትም የመስኖ ቦዮችና ጉድጓዶች ቁፋሮ እንዲሁም የመኖ ማጓጓዝ ተግባራትም በአሁኑ ወቅት እየተለመዱ መጥተዋል። በትራክተር ላይ በተገጠሙ የውሃ ፓምፖች ውሃን ከወንዝ የመሳብ ቴክኖሎጂም በዚህ ረገድ ይጠቀሳል።
መጠናቸው እንደየትራክተሮቹ የፈረስ ጉልበት የሚወሰን በትራክተር ላይ የሚገጠሙ መውቂያ ማሽኖችም አሉ። ሁለገብ የመውቂያ መሳሪያዎች በሀገር ውስጥ አምራቾችም እየተመረቱ ነው። እነዚህ ሁሉ መሳሪያዎች ከትራክተር ጋር እንዲገናኙ ተደርገውና ትራክተሩ የኃይል ምንጭ ሆኗቸው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ።
የእርሻ፣ አረም፣ አጨዳና ውቂያ ተግባራት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወኑት በሰው ኃይልና በእንስሳት ጉልበት ነው። የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ በመሆን ብዙ የሰውና የእንስሳት ጉልበት እንዲሁም ረጅም ጊዜ ይፈጅ የነበረውን ስራ በአጭር ጊዜ ማከናወን ተጀምሯል። ለምሳሌ ሁለገብ መውቂያ ማሽኖች በሰዓት እስከ 20 ኩንታል እህል መውቃት ይችላሉ፤ ለበቆሎ መፈልፈያ ከሆነ ደግሞ በሰዓት ከ40 እስከ 60 ኩንታል መውቃት ይችላሉ። እነዚህ ማሽኖች ምርቱ አፈር ሳይነካውና ሳይባክን ወደ ማጠራቀሚያ በቀጥታ እንዲከማች ማድረግ ያስችላሉ።
በሀገር አቀፍ ደረጃ የእነዚህ ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም እየጨመረ መጥቷል። በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት፣ በግብርና ሚኒስቴርና በአጋር አካላት ትብብር፣ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች በስፋት መተዋወቅና አገልግሎት ላይ መዋል ችለዋል።
ቴክኖሎጂዎቹ ከመገዛታቸው በፊት ተለይተው ለናሙና የቀረቡት ውጤታማነታቸው እንዲፈተሽ ይደረጋል። ቴክኖሎጂዎቹን ለማስተዋወቅ በተደረገው ጥረት አርሶ አደሩ የቴክኖሎጂዎቹን አስፈላጊነትና ለምርት መጨመር ያላቸውን አበርክቶ በመገንዘቡ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ባህሉ እያደገ መጥቷል።
የኢትዮጵያ የዘር ወቅቶች የተለያዩ በመሆናቸው ትራክተሮቹን በተለያዩ አካባቢዎች እያዘዋወሩ የመጠቀም ተግባር እየተስፋፋ ነው። ይህም የግብርና ሜካናይዜሽን ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቁጥር እንዲጨምር አድርጓል። የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ በመፈቀዱ በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር ጨምሯል።
በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ውስጥ ስምንት ሺ ትራክተሮች በስራ ላይ ይገኛሉ። ከሰባት ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች በተለያዩ የግብርና ሜካናይዜሽን ዘርፎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። በአስር ዓመቱ ሀገራዊ የልማት እቅድ ላይ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ቁጥሩን በመጀመሪያው አምስት አመት ማጠናቀቂያ ላይ ወደ 50 በመቶ፣ በሁለተኛው አምስት ዓመት ማጠናቀቂያ ላይ ደግሞ ወደ 70 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዟል። ይህን ለማሳካት ደግሞ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጥምረት መስራት ያስፈልጋል።
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎች ጥራት
የግብርና ትራንስፎርሜሽን ቴክኖሎጂዎቹ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ጥቅም ላይ እንዲውሉ መሟላት ያለባቸው ግብዓቶች አሉ። የሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲሁም የጥገናና የምህንድስና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች የሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ያስፈልጋሉ። በስራ ላይ ያሉት ትራክተሮች ቢያንስ በሁለት ፈረቃ እንዲሰሩ ለማድረግ 16ሺ ኦፕሬተሮች ያስፈልጋሉ፤በተጨማሪም ረዳቶችና የጥገና ስራ የሚሰሩ ባለሙያዎችም ያስፈልጋሉ። ይህም የዘርፉ የሰው ኃይል ፍላጎት ከፍተኛ እንደሆነ ያሳያል።
ፍላጎቱን ለማሟላትም የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ። ለአብነት ያህል በአላጌ የግብርና ቴክኒክ ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ የጥገናና ኦፕሬሽን ሙያ ትምህርት ክፍል ተቋቁሞ የጥገና ባለሙያዎችና ማሽን ኦፕሬተሮች እየሰለጠኑ ነው፤እስካሁን ድረስ ሦስተኛ ዙር ሰልጣኞች ተመርቀዋል። ስልጠናውን በሌሎች አካባቢዎችም ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ነው።
ከሰው ሀብት ልማቱ በተጨማሪ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ማሽኖች ጥራት ጉዳይም ትኩረት ይፈልጋል። ጥራታቸውን ያልጠበቁ ማሽኖች ገብተው አርሶ አደሩም ሆነ ሀገሪቱ እንዳይጎዱ ለማድረግ ግብርና ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ለ250 የግብርና ሚካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎች ደረጃ (Standard) አውጥቷል። እነዚህ ደረጃዎች ማሽኖቹ ከተቀመጠው የጥራት ደረጃ ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጫ ይሰጣሉ።
ይሁን እንጂ ደረጃውን በተግባር ለመፈተን የሚያስችል የመፈተሻ ቴክኖሎጂ እጥረት ስላለ ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት ጋር በመተባበር የግብርና ሜካናይዜሽን የልኅቀት ማዕከልን ለማቋቋም እየተሰራ ነው። ግንባታውም በቅርቡ ይጀመራል። በማዕከሉ ውስጥ የሚሰሩ የጥራት ፍተሻ ባለሙያዎች (Test Engineers) ስልጠና ስለሚያስፈልጋቸው ስልጠናውን ለመስጠት ከአዲስ አበባ እና ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶችን ለመፈራረም ዝግጅቶች ተጠናቀዋል። ከፌደራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋም ጋርም በትብብር ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሟል። ስለሆነም ማዕከሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ማሽኖች ጥራታቸው በባለሙያዎች እየተፈተሸ ወደ ተጠቃሚው ይደርሳሉ ማለት ነው።
የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት የሚደረገው ጥረት መሻሻሎችን እያሳየ ነው። በሞተር ኃይል የሚሰሩ የመውቂያ መሳሪያዎች፣ የበቆሎና የለውዝ መፈልፈያዎች እና የማጓጓዣ ጋሪዎች በሀገር ውስጥ ከሚመረቱት መካከል ይጠቀሳሉ። በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ተሰማርተው ያመርቱ የነበሩ አምራቾች ባገኙት ስልጠና ከውጭ ይገቡ የነበሩ ሁለገብ የመውቂያ መሳሪያዎችንና የለውዝ መፈልፈያ ማሽኖችን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አስማምተው ማምረት ችለዋል። ማሽኖቹን ለአርሶ አደሩ በማስተዋወቅና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር በማድረግም አርሶ አደሩ መሳሪያዎቹን ገዝቶ እንዲጠቀም ማድረግ ተችሏል። ይህ ስራ ጥሩ ውጤት ማስገኘቱን ተከትሎ ባለሀብቶች በዚህ ዘርፍ ተሰማርተው ማምረት ጀምረዋል።
የግብዓቶችን ጥራት ለመጠበቅ የግብርና ማሽኖች አስመጪዎችን አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገቡ መመሪያዎች እንዲወጡ ተደርጓል። መመሪያዎቹ አስመጪዎች ላስገቧቸው ማሽኖች ለተወሰኑ ዓመታት መለዋወጫዎችን እንዲያቀርቡና የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ የሚያደርጉ ናቸው።
ከደቡብ ኮሪያ መንግሥት ጋር በትብብር የሚቋቋመው የግብርና ሜካናይዜሽን የልኅቀት ማዕከል ከሚያከናውናቸው የፍተሻና የጥራት ማረጋገጫ ተግባራት በተጨማሪ ከውጭ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎች በሀገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉበትን ክህሎት ለመፍጠር እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ምሩቃንና ጥናትና ምርምር የሚያደርጉ ባለሙያዎች እንዲሁም በማምረቻ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎች በዚህ የክህሎት ማዳበር ስልጠና ተካፋይ ይሆናሉ። ከዚህ ቀደም የነበሩና በአሁኑ ወቅት ብዙም እንቅስቃሴ የሌላቸው የምርት ማሻሻያ ተቋማትም በዚህ አሰራር እንዲነቃቁ ጥረት ይደረጋል።
የግብርና ሜካናይዜሽን ያስገኛቸው ውጤቶች
በአጠቃላይ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ትግበራ የግብርና ስራው በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን፣ ምርት እንዲጨምርና የሀብት ብክነት እንዲቀንስ አድርጓል። የግብርናው ዘርፍ በሰለጠኑ ባለሙያዎች የታገዘ እንዲሆንም እድል ፈጥሯል። የዘርፉ ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ ብዙ ባለሙያዎችና ተቋማት የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በማምረት ላይ እንዲሰማሩ አስችሏል። አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ምርቱን ማሳደግን ቅንጦት ሳይሆን አስገዳጅና አስፈላጊ እንደሆነ በመረዳቱ ለግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂ ያለው ፍላጎት ጨምሯል።
እቅዶች
በቀጣይ ጊዜያት የሰብልና እንስሳት ልማትን አቀናጅቶ በመስራት ምርታማነትን የሚጨምሩ የግብርና ሜካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ለማስተዋወቅና ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል። በሜካናይዜሽን በመታገዝ የወተት፣ የስጋና የዶሮ ሀብት ልማትን ማሳደግም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው። ትልቅ የግብርና አቅም ያላቸው ቆላማ አካባቢዎችም የሜካናይዜሽን ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል።
የግብርና ሜካናይዜሽን ትግበራ መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንዳለው በመገንዘብ አርሶ አደሮችን ስለቴክኖሎጂው ማሳወቅ፤ ባለሀብቶችም በዚሁ ዘርፍ እንዲሰማሩ ማድረግ እንደሚገባና ግብርና ሚኒስቴርም ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ በረከት ፎርሲዶ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም