አዲስ አበባ፦ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግድ ትርፋማና ሳቢ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ የግል ዘርፉ አስመጪና ላኪ ተቋማት ገለጹ።
የላንፍሮንስ ትሬዲንግ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ደሳለኝ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ ላንፍሮንስ ትሬዲንግ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ላይ የተሰማራ ድርጅት ነው። ከቅባት እህሎች ሰሊጥን፤ ከጥራጥሬ ደግሞ ነጭ፣ጥቁርና ቀይ ቦለቄ እና መሰል ምርቶችን ለውጭ ገበያ ያቀርባል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፊት የወጪ ንግድ ብዙም ትርፋማ ያልሆነ አንዳንዴም በኪሳራ የሚሠራ የሥራ ዘርፍ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍሬው፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ የወጪ ንግድ ትርፋማ የሥራ ዘርፍ ሆኗል። በተለይ ከውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዘው የሚነሡ ችግሮች መፍትሔ አግኝተዋል ነው ያሉት።
ይህም የሀገር ውስጥ አምራቾች ከማበረታታቱም በላይ የውጭ ሀገር ኢንቨስተሮች ጭምር በዘርፉ እንዲሳተፉ እድል እየሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ አርሶ አደሩ ጥሩ ክፍያ እንዲያገኝ አድርጎታል። የንግድ ዘርፉ ተዋናዮችንም በሙሉ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያሳያል ብለዋል።
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የገቢና ወጪ ንግድ ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንዳሻው በላቸው በበኩላቸው፤ በላይነህ ክንዴ ግሩፕ ለዓመታት የቅባት እህሎችን በጥሬው ይልክ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እሴት ጨምሮ ወደ መላክ ተሸጋግሯል ብለዋል።
ግሩፑ በቀጣይም ያለውን አቅም በማጠናከር በወጭ ንግድ ዘርፍ የላቀ ሚናውን ይጫወታል ያሉት አቶ እንዳሻው፤ ግሩፑ ለተከታታይ ዓመታት የቅባት እህሎችን ወደ ወጭ በመላክ በቀዳሚት የሚጠቀስ ሲሆን ከ 700 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለሀገር ማስገኘት መቻሉን ገልጸዋል።
ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ ይገባል። የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በገቢም ይሁን በሌሎች መለኪያዎች የወጪ ንግድ ትርፋማ አድርጎታል ብለዋል።
በወጪ ንግድ ከተለመዱት የግብርና ምርቶች በተጨማሪ አዳዲስ ምርቶች ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርግ አቶ እንዳሻው ተናግረዋል።
ከሐምሌ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ደግሞ የንግድና ኢንቨስትመንት መስኮችን ተወዳዳሪና ውጤታማ ለማድረግ፤ የሀገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት አቅምን ማጠናከር፣ ጥራት ያለው አገልግሎት ለማቅረብና አጠቃላይ የሀገርን የምጣኔ ሀብት እድገት ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑን የኢኮኖሚ ምሁራን ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት የማሻሻያ ትግበራው በተለያዩ የኢኮኖሚ አመላካቾች አመርቂ ውጤቶች እየተመዘገበበት መሆኑ ታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፤ እንደ ሀገር የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉ ለኢኮኖሚ እድገት ማነቆ የነበሩ በርካታ ችግሮችን መፍታት አስችሏል ብለዋል።
በመጀመሪያው በሩብ ዓመት በወጪ ንግድ፣ በገቢና በሃዋላ ፍሰት የታዩ ውጤቶች ጥሩ ማሳያ መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸው፤ በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በማዕድንና በዲጂታል ዘርፎች የታዩ ውጤቶችም ማሻሻያው ፍሬ ማፍራት መጀመሩን ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 4 በመቶ ዕድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቅሰዋል፡፡
ሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም