አዲስ አበባ፡ -ባለፉት አራት ዓመታት የኤች አይቪን ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔን ስድስት በመቶ ያህል ዝቅ ማድረግ መቻሉን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ 36ኛውን የዓለም የኤች አይቪ ኤድስ ቀን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፤ የኤች አይቪ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔን እየቀነሰ መጥቷል፡፡ ኤች አይቪ ከእናት ወደ ልጅ የመተላለፍ ምጣኔ ከአራት ዓመታት በፊት ከነበረበት 14 ነጥብ 96 በመቶ በአሁኑ ጊዜ ወደ 8 ነጥብ 64 በመቶ ማድረስ ተችሏል።
ይህ ውጤት የተገኘው እናቶች በእርግዝና ወቅት ተገቢውን የህክምና ክትትል እንዲያገኙ፣ እንዲሁም በጤና ተቋማት እንዲወልዱ መሥራት መቻሉ መሆኑን ገልጸው፤ ለውጤቱ መገኘት የጤና ተቋማት ውጤታማ ሥራ አስተዋጽኦ ማድረጉ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ኤች አይቪ በደማቸው ከሚገኙ እናቶች የሚወለዱ ህጻናትም በወቅቱ የምርመራና ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ቫይረሱን የመከላከል ሥራ መሠራቱን ገልጸዋል።
ዶ/ር ደረጀ በዓለም ደረጃ በ2030 ኤች አይቪ ከእናት ወደ ልጅ እንዳይተላለፍ የመግታትና የመተላለፍ ምጣኔው ከአምስት በመቶ በታች ለማድረስ የተቀመጠ ግብ መኖሩንና ኢትዮጵያም ይህንን እየተገበረች ስለመሆኑ የተገኘው ውጤት ማሳያ መሆኑን አመልክተዋል።
በሀገር ደረጃ የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት መጠንን ዜሮ ነጥብ 87 በመቶ ማድረስ መቻሉን ጠቁመው፤ በሀገሪቱ የኤችይቪ ስርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም በአሁኑ ትኩረት የሚሻ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ደረጀ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባካሄደው ጥናታዊ ትንበያ መሠረትም በሀገሪቱ 606 ሺህ 238 ሰዎች ኤች አይቪ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በየዓመቱም ከሰባት ሺህ በላይ ሰዎች በኤች አይቪ ኤድስ እንደሚያዙ ገልጸው፤ ከእነዚህ ውስጥም 70 በመቶ የሚሆኑት ከ15 እስከ 29 እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የበሽታው የስርጭት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም በአዲስ አበባ፣ በሀረርና በድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም ጋምቤላ ፣ ትግራይና አማራ ክልሎች ያለው የስርጭት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በ2030 ኤች አይቪ /ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደ የማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ እቅድ መያዟን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ይህንን ራዕይ ለማሳካት የተለያዩ ግቦችን አስቀምጣ በመተግበር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት እንደ ሀገር የኤች አይቪ ስርጭት ምጣኔ በ2010 ዓ.ም ከነበረበት አንድ ነጥብ 26 በመቶ አሁን ወዳለበት ዜሮ ነጥብ 87 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል፡፡
90 በመቶ የሚሆኑ ህሙማን ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን እንዲያውቁ ፣ 94 በመቶ ያህሉን ደግሞ የጸረ- ኤች አይቪ መድሃኒት እንዲጠቀሙና መድኃኒት ከሚወስዱት ውስጥ 96 በመቶ ያህሉ የቫይረሱ ልኬት መጠን በሚፈለገው መጠን እንዲወርድ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ደረጀ በ2030 ኤች አይቪ /ኤድስ የማህበረሰቡ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በተያዘው እቅድ አተገባበር ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ገልጸው፤ በተለይ በየደረጃው የሚገኙ የኤድስ ምክር ቤት በሚፈለገው መልኩ አለመቋቋምና ሥራ ላይ አለመሆን፣ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የኤች አይቪ/ ኤድስ ፕሮግራሞችን በባለቤትነት አለመተግበር በአስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የበሽታው ስርጭት አሁንም በማህበረሰቡ ላይ የጤና፣ የልማት፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን ጠቁመው፤ ከበሽታው አሳሳቢነት አንፃር አሁንም ኤች.አይ.ቪ/ኤድስን ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
36ኛው የአለም የኤች አይቪ ኤድስ ቀን ህዳር 22 በሀገር አቀፍ ደረጃ ‹‹ሠብዓዊ መብትን ያከበረ የኤችአይቪ አገልግሎት ለሁሉም” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ጤና ሚኒስቴር ትናንትና በሰጠው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም