አዲስ አበባ፡– ከለውጡ ወዲህ ሶስት ሺ 300 አዳዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገብ መቻሉ የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት፤ ከባለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሪፎርም እየተደረገ ነው፡፡ በሪፎርሙም ሶስት ሺ 300 አዳዲስ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜም ክልልን ጨምሮ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቁጥር ከስድስት ሺህ በላይ መድረሱን አመልክተው፤ ባለሥልጣኑ የሲቪል ድርጅቶች ቁጥር ከመጨመሩ ባለፈም ሥራቸውን ባግባቡ እንዲወጡ እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ለዚህም ማሳያው የሲቪል ድርጅቶች በሰላም ግንባታ ፣ በአፋጣኝ ሠብዓዊ ርዳታ ፣ በተለያዩ የልማት ሥራዎችና በሽግግር ፍትህ ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየሠሩ መሆኑ ገልጸዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ባደረገው ሪፎርም በሥራቸው ለማህበረሰቡ መትረፍ ያልቻሉ እንዲሁም በተደረገላቸው ተደጋጋሚ ጥሪ በሥራ ላይ ስለመኖራቸው ቀርበው ማስረዳት ያልቻሉ አንድ ሺ 500 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መታገዳቸውን ገልጸዋል፡፡
4ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት “ለዘላቂ ሰላም እና ፍትሃዊ ልማት ቃልኪዳናችንን እናድስ” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 27 እስከ ህዳር 29 2017 ዓ.ም እንደሚከበር የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት በዋናነት የዘርፉን ገጽታ ለመገንባት፣ ትስስር ለመፍጠር፣ በሰላም ግንባታ፣ አፋጣኝ ሠብዓዊ ርዳታ እና የልማት ሥራዎች ላይ ውይይት ለማድረግ ታላሚ ተደርጎ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።
በዚህ ሳምንትም ከስድስት በላይ የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄድና 80 የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሥራዎቻቸውን የሚያስተዋውቁበት ኤግዚቢሽን እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የግሉንና የመንግሥት ዘርፉን በማስተሳሰር ሚዛናዊ ለማድረግና ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን የሚቋቋሙበት ዋነኛ ዓላማ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሳምንቱም ድርጅቶች ራሳቸውን በደንብ እንዲያስተዋውቁ የሚረዳቸው መሆኑ አብራርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አህመድ ሁሴን በበኩላቸው ምክር ቤቱ በሀገሪቱ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ የመወከልና የማስተባበር ሃላፊነት በአዋጅ ያገኘ መሆኑ ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከአራት ሺህ በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምክር ቤቱ አባል መሆናቸውንና እነሱም በሽግግር ፍትህና በሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ ላይ አተኩረው እየሠሩ የሚገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ አህመድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሪፎርም ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ በመሆኑ የበለጠ እንዲጠናከር ድጋፍና ክትትል ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
መስከረም ሰይፉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም