ማዕከሉ የነፃ ህክምና አገልግሎትን በክልል ከተሞች ተደራሽ ሊያደርግ ነው

አዲስ አበባ፡- የነፃ ህክምና አገልግሎቱን በየክልል ከተሞች ተደራሽ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን በኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማዕከል ገለጸ፡፡

የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ኤሌዘር ሃይሌ እንዳሉት፤ የማዕከሉ ነጻ የሕክምና አገልግሎቱን ከአዲስ አበባ ባለፈ በክልል ከተሞች የማስፋፋት ሥራዎች እየሠራ ይገኛል፡፡ በየክልል ከተሞች ለባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት የልብ ህሙማኑ በአቅራቢያቸው ክትትላቸውን እንዲያደርጉ ለማስቻል እየተሠራ ነው፡፡

እስካሁን ድረስም 14 ለሚሆኑ በህፃናት ህክምና ዘርፍ ለሚሠሩ ስፔሻሊስት ሀኪሞች ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸው፤ እነዚህ የህክምና ባለሙያዎችም በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎቱን እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ማዕከሉ የተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡና አገልግሎት እንዲሰጡ የማመቻቸት ሥራ እንደሚሠራ ጠቁመው፤ ደረጃቸውን የጠበቁ የማዕከሉ ላብራቶሪዎችና ግብዓቶች እነዚህን ድርጅቶች ለመሳብ የሚያስችሉ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡

ክትትሉን ሳይጨምር በዓመት ከ500 እስከ 600 የሚሆኑ የልብ ቀዶ ጥገናዎች በማዕከሉ እንደሚሠሩ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ የውጭ ምንዛሪን ከማዳን አንፃር ማዕከሉ ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እንዳለው መገመት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

እያንዳንዱ ቀዶ ጥገና ቢያንስ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን እስከ ሁለት ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር የሚገመት ወጪ እንደሚያስፈልገውም ጠቁመዋል፡፡ እንዲሁም ውጭ ሀገር ለመሄድ የሚያጋጥሙ ሂደቶችንና ድካሞችን ያስቀረ አገልግሎት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዓለማችን ውድ ከሚባሉ ህክምናዎች ውስጥ የካንሰርና የልብ ህክምና ትልቁን ቦታ ይይዛሉ ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ማዕከሉ ለልብ ህክምና የሚሆኑ ግብዓቶችን ሙሉ በሙሉ ከውጭ እንደሚያስመጣ ገልፀዋል፡፡ ከዚህ አኳያ አሁንም ቀጣይነት ያለው እገዛና ድጋፍ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ ሶስት ዋና ዋና አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ገልፀው፤ የመጀመሪያው የክትትልና የመድሃኒት ህክምና ሲሆን ከዘጠኝ ሺህ እስከ 12ሺህ የሚደርሱ ታካሚዎችን አገልግሎቱን እንደሚያገኙ አመልክተዋል፡፡

ሁለተኛው አገልግሎት ደግሞ ቀዶ ጥገና ሳይፈልግ በደም ስር ብቻ ተገብቶ ቀዶ ጥገናን መሥራት የሚያስችል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ይህን አገልግሎት ለህፃናት ብቻ ሳይሆን ለአዋቂዎችም እንደሚሰጡ ጠቁመዋል፡፡ ማእከሉ በዋናነት ተደራሽነቱ ለህፃናት ቢሆንም ለአዋቂዎችም 25 በመቶ የሚሆነው አገልግሎት እንደሚያገኙ ተናግረዋል፡፡

ሶስተኛው የማዕከሉ አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ ደረት ተከፍቶ የሚሠራ የልብ ቀዶ ጥገና መሆኑን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የልብ ቀዶ ጥገና ህክምና በግል ዘርፉም መንገድ የከፈተ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ በተጨማሪም ማዕከሉ ባለሙያዎችን በማሠልጠን ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመ የልብ ቀዶ ጥገና ሀኪሞች ቡድን ያዋቀረ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ማዕከሉ ባለፉት 35 ዓመታት ምን አስተዋፅኦ አበርክቷል የሚል ጥናት መካሄዱን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በውጤቱም ድሮ በጤና ችግር ምክንያት ከትምህርት ቤት ይቀሩ የነበሩ ልጆች መቅረት አቁመው ትምህርት ቤት መግባት እንደቻሉ እንዲሁም በተለያየ ዘርፍ ተመርቀው በሥራ ላይ እንዳሉ ማወቅ ችለናል ብለዋል፡፡

ማዕከሉ የመላው ኢትዮጵያ ቤት ነው፡፡ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ያስፈልገዋል ሲሉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

“የገና ስጦታ ለልብ ህሙማን ህፃናት” በሚል መሪ ቃል እስከ ገና በዓል የሚቆይ የገቢ ማሰባሰቢያ ንቅናቄም በማዕከሉ ተጀምሯል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ኅዳር 21 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You