ማዕድናትን ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር ያስቻለው ኤክስፖ

ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ‹‹ማይንቴክ ኤክስፖ›› በቅርቡ በሚሊኒየም አዳራሽ መካሄዱ ይታወቃል። የማዕድን ድግስ በሚል ሊገለጽ በሚችለው በዚህ ኤክስፖ፣ ለማየት የሚያሳሱ፤ ታይተው የማይጠገቡ እጅግ የሚያምሩና ውብ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት፣ ወርቅ ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ለኢንዱስትሪና ለኮንስትራክሽን ግብዓትነት የሚውሉ እና ሌሎች ማዕድናት በየዓይነት በዓይነት ቀርበዋል። እነዚህ ሁሉ ማዕድናት እውን በኢትዮጵያ የሚገኙ ናቸው ብለን ራሳችን እንድንጠይቅ የሚያደርጉ ስማቸውን ሰምተንም ሆነ አይተናቸው የማናውቃቸው ብዙ ዓይነት ማዕድናት ቀርበው ተጎብኝተዋል።

ከኅዳር 13 እስከ ኅዳር 17 ድረስ ለአራት ቀናት በተካሄደው በዚህ ኤክስፖ ላይ የመንግሥት አካላት፣ በማዕድን ዘርፉ የተሰማሩ በርካታ አልሚዎች፣ እሴት ጨማሪዎች፣ ገዥዎች፣ ላኪዎችና በርካታ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጎብኝዎችም ተገኝተዋል።

ማዕድናትን ማስተዋወቅ፣ ለማዕድን ምርቶች የገበያ ትስስር መፍጠር፣ ቴክኖሎጂ ማሳየትና ማስተዋወቅም በስፋት በታየበትና በማዕድን ዘርፉ መልካም እድሎች፣ ፈተናዎችና መፍትሔዎች እንዲሁም ስኬቶች ላይ የተለያዩ መድረኮች በተካሄዱበት በዚህ ኤክስፖ መክፈቻ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገኝተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ኤክስፖውን በከፈቱበት ወቅት ኢትዮጵያ ያላትን እምቅ የማዕድን ሀብት በዘመናዊ መንገድ አልምቶ መጠቀም የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባ አስታውቀዋል። ሀገሪቱ ያሏትን የማዕድን ሀብቶች ለመለየት፣ ለማልማትና ለመጠቀም ዘመናዊ ሥርዓትን መከተል እና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ አመልክተው፤ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችም የእውቀት ሽግግር ለማድረግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት መጠቀም እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንደሚሉት፤ የማዕድን ሀብት የውጭ ምንዛሬ ገቢን ለማሳደግ፣ በአጠቃላይ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኝ ነው። የማዕድን ዘርፉን ለማልማት ከመንግሥት በተጨማሪ ባለሀብቶች እና ባለድርሻ አካላት እገዛ ሊያደርጉ ይገባል። ፕሬዚዳንቱ ኤክስፖውን ጎብኝተዋል፡፡

በኤክስፖው ከተሳተፉት መካከል በድንጋይ ከሰል ልማት የተሰማራው ‹‹ጂሚቲ የድንጋይ ከሰል አምራች ድርጅት›› አንዱ ነው። ድርጅቱ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጦላይ የሚባል አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ ከተቋቋመ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል። ድንጋይ ከሰል በማምረት ለሲሚንቶና ብረት ፋብሪካዎች ያቀርባል።

የድርጅቱ የሽያጭ ባለሙያ አቶ ዳዊት ኪቲላ እንደሚለው፤ ድርጅቱ ከውጭ ሀገራት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ ለመተካት ታስቦ የተቋቋመ ነው። በተፈጥሮ የሚገኘውን የድንጋይ ከሰል የሚያመረት ሲሆን፣ ከአራት ሺ 500 እስከ 5000 ኮሎሪ መጠን ያለው የድንጋይ ከሰል ያመርታል። በቀን ከሶስት ሺ ቶን በላይ የድንጋይ ከሰል እያመረተ በተመጣጣኝ ዋጋ ለፋብሪካዎች ያቀርባል።

ድርጅቱ ቀደም ሲል ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይገባ የነበረው የድንጋይ ከሰል በሀገር ውስጥ እያመረተ መሆኑን ጠቅሶ፤ የድንጋይ ከሰልን በሀገር ውስጥ ማምረት መቻል እንደ ሀገርም ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አመላክቷል።

በኤክስፖው ድርጅቱ የሚያመርተውን የድንጋይ ከሰል ይዞ መቅረቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሶ፣ በተለይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችለው ይገልጻል። ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ዓይነቶች ያላት ስለመሆኗ ግንዛቤው የሌላቸው ብዙ ሰዎች እንዳሉ ተናግሮ፣ ባለሀብቶች ከድርጅቱ ጋር መሥራት የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች እንዲያገኙ እንደሚረዳ አመልክቷል።

ድርጅቱ የገበያ ችግር ያለበት ቢሆንም ግን በድንጋይ ከሰሉ የጥራት ደረጃው የወረደ ነው ብለው የሚያስቡ አካላት እንዳሉ ጠቅሶ፣ እነዚህ አካላት ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውንም ይገልጻል።

በቀጣይ ድርጅቱ ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት የድንጋይ ከሰል ሥራውን አስፋፍቶ መሥራት እንደሚፈልግ አቶ ዳዊት አስታውቆ፣ የድንጋይ ከሰል ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ እንዳለውም ተናግሯል። ለዚህም መንግሥትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ሊያደርጉለት ይገባል ሲል አስታውቋል።

ሌላኛው የኤክስፖው ተሳታፊ ኤም ኤች ኤን ዋ ነው፤ ድርጅቱ 2014 ዓ.ም የተመሠረተ ሲሆን፤ የኢንዱስትሪ፣ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ ያቀርባል።

የድርጅቱ መስራች አቶ ነጋሽ ይርጋ ሊትየም፣ ኮፐር፣ ማንጋኒዝ እና የመሳሰሉትን ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት የሚውሉ ማዕድናት እንዲሁም እንደ ሩቢ፣ ኦፓል የመሳሰሉትን የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ ይገልጻሉ።

‹‹በኤክስፖው መሳተፋችንን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ተሳታፊዎችና ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ማዕድናትን ለማስተዋወቅ ያስችላል ሲሉ ጠቅሰው፣ ከእኛ ሥራዎች ጋር በተገናኘ ከሚያስፈልጉ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ጎብኚዎች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዲኖረን ይጠቅማል›› ብለዋል።

እሳቸው እንደሚሉት፤ እነዚህ ማዕድናት በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው። ሊትየም፣ ኮፐር እና ማንጋኒዝ ብዙ ጊዜ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልል ጉጂ አካባቢ ይገኛሉ። እንደ ሩቢና ኦፓል ያሉት የጌጣጌጥና የከበሩ ማዕድናት ደግሞ ከአማራ ክልል ውሎ አካባቢ የሚገኙ ሲሆን፤ ፍሎራየትን የመሳሰሉት ማዕድናት ደግሞ ከሶማሌ ክልል እንደሚገኙ አስታውቀዋል።

ድርጅቱ ማዕድናቱን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ የገበያ መዳረሻዎች እያሰፋ መሆኑን ገልጸው፤ የከበሩ ማዕድናት አውሮፓ፣ ቱርክ፣ ዱባይ፣ ጀርመንና ሲዊዲን እንደሚላክ ተናግረዋል። እንደ ሊትየም እና ኮፐር ያሉትን የኢንዱስትሪ ማዕድናት ደግሞ ወደ ቻይናና አልፎ አልፎም አሜሪካ ገበያ እንደሚላክ አስታውቀዋል።

አሁን ድርጅቱ ከጌጣጌጥ ማዕድናት ውጭ ያሉትን አብዛኛዎቹን ማዕድናት እሴት ሳይጨመርባቸው በጥሬው እንዳለ እንደሚልክ ጠቅሰው፤ የጌጣጌጥ ማዕድናትን ከአምራቾች ተረክቦ ፕሮሰስ በሚያደርጉ አካላት በማሠራት ለገበያ እንደሚያቀርብ ይገልጻሉ። ወደፊት እሴት ጨምራ ሥራውን በራሱ ለማከናወን አቅዶ እንደሚሰራም ይገልጻሉ።

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በማዕድናት ላይ እሴት ለመጨመር ቴክኖሎጂና በተለይ ማሽኑን ለማስመጣት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ይጠይቃል። ለአብነትም ሊትየምን በሀገር ውስጥ ፕሮሰስ ለማድረግ ቢፈልግ ብዙ ካፒታልና ባለሙያ ያስፈልጋል። አሁን ማዕድን ሚኒስቴር በተለይ በሀገር ውስጥ መመረት የሚችሉ ማዕድናትን ለማምረት እንዲቻል የሚያደርግ ምቹ ሁኔታ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። በተለይ ማዕድን እሴት ተጨምሮበት ወደ ውጭ ቢላክ ዋጋው አሁን ከሚሸጠው አራትና አምስት እጥፍ እንዲሆን ያደርገዋል።

ማዕድናቱን የሚገዙት ሀገራት ስለማዕድናቱ ያላቸው ግንዛቤ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ጥራት ያላቸው ማዕድናት እንዲቀርቡላቸው ይፈልጋሉ። ጥራት ያለው ማዕድን ከቀረበ ገዢዎቹ ደስ ብሎቸው ስለሚገዙ በዚያ ልክ ለአቅራቢዎቹ ገበያው ጥሩ ይሆናል።

ድርጅቱ አሁን ለአምስት ሰዎች የሥራ እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፣ ዘርፉ በስፋት ሊሰራበት የሚችል ገና ያልተነካ በመሆኑ ብዙ ሰዎች ሊሳተፉበት የሚችሉና ለብዙዎች የሥራ እድል ሊፈጥር የሚችል ነው ብለዋል።

‹‹ በማይቴክ ኤክስፖው መሳተፋችን ምርቶቻችንን እንድናስተዋወቅና የገበያ ትስስር እንድንፈጥር ረድቶናል። ብዙ ደንበኞችን እና አጋር ድርጅቶች እንድናፈራ እድል ፈጥሮልናል›› ሲሉም ገልጸዋል። ድርጅቱ በቀጣይ በማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ጠቁመው፣ አቅሙን እያጠናከረ ራሱንም ሀገሩንም ለመጥቀም እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

‹‹ሙዚየም ጂም ስቶን ትሬዲንግ›› ሌላኛው የማዕድን ኤክስፖው ተሳታፊ ነው። የድርጅቱ የሽያጭ ባለሙያ ወጣት ራህመት ታጁ አብደላ እንደምትለው፤ ድርጅቱ በርካታ ዓይነት የከበሩ ማዕድናት በማምረት ለውጭ ገበያ ያቀርባል። እነዚህን ማዕድናት ለተለያዩ ጌጣጌጥነት እንዲውሉ አድርጎ ይሰራቸዋል።

በጃስበር፣ ኦቨሲዲያን፣ አሜቴስት፣ አጌት እና የመሳሰሉት ማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ያቀርባል። እነዚህ ማዕድናት በወርቅና በብር ተደርገው ለጆሮ፣ ለአንገትና ለእጅ ጌጣጌጥነት እንዲያገለግሉ ሆነው ይሰራሉ። ለልብስና ለቤት ጌጣጌጥነት በሚውል መልኩ የሚሠሩ ናቸው። ማዕድናቱ በጌጣጌጥ መልኩ ከተሠሩ በኋላ ወደ ህንድ፣ ቻይና ሌሎች የኤሽያ ሀገራት ገበያ ይላካሉ።

በማዕድናት ላይ እሴት በመጨመር በጌጣጌጥነት መልኩ ሰርቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ከግለሰብ አልፎ ሀገር የሚጠቅምና የሚበረታታ ሥራ ነው የምትለው ወጣት ራህመት፤ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት በተለያየ መልኩ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዲወጡ የሚደረግበት ሁኔታ የውጭ ገበያውን ሳይቀር እንዲቀዘቅዝ እያደረገ መሆኑን ጠቁማለች። በተለይ ሕገ ወጥነትን መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት ግንዛቤ ማስፋት እንደሚያስፈልግ ጠቁማለች።

የከበሩ ማዕድናት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በስፋት እንደሚገኙ አስታውቆ፣ የአቅርቦት ችግር እንደማያጋጥም ገልጻለች፤ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታየው ጸጥታና አለመረጋጋት በሥራው ላይ እንቅፋት መፍጠሩን ጠቁማለች።

እነዚህን ምርቶች ለማስተዋወቅ የተለያዩ ፕላትፎርሞች እንደሚጠቀሙ ጠቅሳ፣ በኦንላይን ገበያ እንደሚሸጡ ራህመት ገልጻለች፤ ገበያ ማግኘት ዋነኛ ችግር እንደሆነ አመልክታ፣ ገበያው ሲገኝ የምርት እጥረት እንደሚያጋጥምም ነው ያስታወቀችው። ሥራው እነዚህ ላይ በደንብ መሥራት እንደሚጠይቅም ጠቁማለች።

ወጣት ራህመት እንዳለችው፤ ኤክስፖው በርካታ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገሮች ጎብኚዎች ስለሚያሳተፍ ድርጅቱ ምርቶቹን ለማስተዋወቅና ለመሸጥ እንዲሁም ገበያ ለማፈላለግ ጥሩ አጋጣሚን ይፈጥራል። ድርጅቱ በመድረኩ ሲሳተፍ ለሦስተኛ ጊዜ ነው፤ የመጀመሪያው ዓመት መድረክ በጣም የደመቀ እንደነበር አስታውሳ፣ ብዙ ራሳችንን ያስተዋወቅንበት ነበር ብላለች። ሁለተኛውና የአሁኑ ኤክስፖው ቀዝቀዝ ያሉ መሆናቸውን አስታውቃለች። ይህ ሦስተኛው ኤክስፖ ካለፉት ኤክስፖዎች አኳያ ሲታይ የጎብኚዎች ቁጥር በእጅጉ ዝቅተኛ መሆኑንም አመልክታለች።

ህብረተሰቡ በማዕድናት ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ለውጥ ያለው ቢሆንም አሁን የሚቀሩ ብዙ ሥራዎች አሉ የምትለው ራህመት፤ በተለይ ከሌሎቹ ማዕድናት አንጻር ሲታይ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ የተዳከመ መሆኑን ትገልጻለች። ለአብነት የኢንዱስትሪ ማዕድናት ብንመለከት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊነት ተሰጥቷቸው እንደሚሰራባቸው ሁሉ እነዚህ ማዕድናት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ስትል አስገንዘባለች።

ወጣት ራህመት እንደምትለው፤ በከበሩና በጌጣጌጥ ማዕድናት ላይ እሴት ተጨምሮ ወደ ውጭ ገበያ ሲላኩ በጥሬው ከሚላኩት 50 እና 60 በመቶ ያህል የዋጋ ጭማሪ ይኖራቸዋል፤ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኙ ይችላሉ። እነዚህ ማዕድናት በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ብዙ ሰዎች አያውቁም፤ በዚህ የተነሳም አይጠቀሙባቸውም።

ማዕድናት ሲባል የሚታወቁት ወርቅና ብር ብቻ ናቸው። የከበሩ ማዕድናት እንደ ድንጋይ እንጂ እንደ ማዕድን አይታዩም። በመሆኑም በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር ላይ በማስፋት መሥራት ያስፈልጋል። ‹‹ማዕድናቱን ለውጭ ገበያ ሲናቀርብ ከወርቅ በላይ ዋጋ ሊያወጡ ይችላሉ፤ ሀገር ለገበያ ሲቀርቡ ግን ከዚህ ባነሰ ዋጋ ነው የሚሸጡት። ይህንን የምናደርገው ህብረተሰቡ የራሱን ምርቶች እንዲጠቀም ለማድረግ ነው›› በማለት ታብራራለች።

ሌላኛው ተሳታፊ ‹‹ካውሰር የከበሩ ማዕድናት ኤክስፖርትና ኤምፖርት›› የተሰኘው ድርጅት ነው። ድርጅቱ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናትን እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማዕድናትን ለውጭ ገበያ ያቀርባል። እንደ ኦፓል፣ ሳፋየር እና ኤምራልድ ያሉ የከበሩና የጌጣጌጥ ማዕድናትን በኦንላየን ገበያ ይሸጣል። ፡

የድርጅቱ የሽያጭ ባለሙያ ሁዳ አብዳል ፈታ እንደምትለው፤ ድርጅቱ ከኢንዱስትሪ ማዕድናት መካከል እንደ ታንታለየም፣ የድንጋይ ከሰል የመሳሰሉትን ለተለያዩ ፋብሪካዎች ያቀርባል። እነዚህን ማዕድናት ከተለያዩ አምራቾች ተረክቦ ለፋብሪካዎች ያቀርባል።

ሌላው ለሜካፕ መሥሪያ የሚያገለግለው ማይካ፣ የተሰኘው ማዕድን ነው፤ ማዕድኑ ሜካፕ ለሚሰሩ ፋብሪዎች ይቀርባል። ለሀውልቶች ሥራ የሚያገለግለው ኮሪስታል ኦፓልንም እንዲሁ ያቀርባል። አምበር የተሰኘ ለተለያዩ ጌጣጌጥ መሥሪያ የሚያገለግለው ማዕድን አቅራቢም ነው።

ድርጅቱ በኤክስፖ ላይ መገኘቱ እነዚህን ምርቶች ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዳስቻለው ጠቅሳ፣ ኤክስፖው ምርቶችን ለመሸጥ፣ በርካታ የውጭና የሀገር ውስጥ ደንበኞች ለማፍራት አስችሎናል ስትል ትገልጻለች።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You