አቤል ገ/ኪዳን
የእኛ ነገር ያስቀኛል። የሆነ ብዥ ያለብን ነገር ያለ ይመስላል። ምንም ነገራችን የማይያዝ የማይጨበጥ ነው። ዛሬ የወደድነውን ነገ እናራክሳለን ፤ ዛሬ የጠላነውን ነገ እናሞግሳን። ለማሞገስም ለማንኳሰስም አንፈጥናለን። ሁለቱንም ስናደርግ ግን በማስረጃ እና በመረጃ ሳይሆን በመሰለን ነው። ሁላችንም መስማት የምንፈልገውን የሚናገርልን ሰው ስናገኝ የኔ ጀግና፣ የኔ አንበሳ፣ የኔ ደፋር ምናምን እያልን እንሰቅለዋለን። ከዚያ በተቃራኒ ሰውየው የራሱን እውነት ሲናገር እና ያ የሱ እውነት እኛ እውነት ነው ብለን ከምናስበው ነገር ጋር አልገጥም ሲል እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ አድርግን እንዘልፈዋለን። ባንዳ፣ ካድሬ፣ ከሀዲ ተከፋይ ወዘተ.. የሚል ታርጋ እንለጥፍለታለን። የራሳችንን እውነት አጽድቀን ለዚያ ማረጋገጭ የሚሆን ነገር በመፈለግ ነው ተጠምደን የምንውለው።
በሥነ ልቡና ባለሙያዎች አጠራር እንዲህ አይነቱን ሁኔታ ኮንፈርሜሽን ባያዝ ይባላል። ከብዙ የአመለካከት መዛባቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ መዛባት ሰዎች የሚያገኙትን መረጃ በተሳሳተ መልኩ እንዲረዱ እና እንዲተነትኑ የሚያደርግ አደገኛ መዛባት ሲሆን የዚህ መዛባት ሰለባ የሆኑ ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ መረጃ ሰብስበው የሚወስኑ ሳይሆኑ ወስነው ውሳኔያቸውን የሚያጠናክር መረጃ ፍለጋ የሚሄዱ ናቸው። የኛም ሁኔታ እንደዚህ ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ አንዴ በሚጨበጥም መረጃ ይሁን በስሚ ስሚ አቋም እንይዛለን። ከዚያ በኋላ ያን አቋም መቀየር ይከብደናል። ስለዚህ እኛ ያመንበትን ነገር የሚያወሩ ሰዎችን ፍለጋ አደባባይ እንወጣለን። እነሱን ስናገኝ እናሞግሳለን። ከዚያ በተቃራኒ የሆነ ሃሳብ ስንሰማ ግን እውነት እንዳለው ብናውቅ እንኳ ለመቀበል እንቸገራለን።
ይህን እኛ ያለንበትን ሁኔታ የሚገልጽ አንድ ጥቅስ አንድ ቦታ ላይ ሰምቻለሁ። ‹‹The truth is what you choose to believe›› ይላል። እውነታው አንተ ለማመን የመረጥከው ነው ማለት ነው ትርጉሙ። ይሄ ነው የብዙዎቻችን ባህሪም። የኮንፈርሜሽን ባያዝ ተጠቂ ስለሆንን የምናምነው ሀቁን ሳይሆን ለማመን የምንፈልገውን ነው። ነገሩ ግን እንደዚያ ሊሆን አይችልም። ዳንኤል ፓትሪክ ሞህኒያን የተባሉ ምሁር በአንድ ወቅት እንደተናገሩትም ማንም ሰው የራሱ አስተያየት እንጂ የራሱ ሀቅ ሊኖረው አይችልም። እውነታቸውንም ነው። ሊኖር የሚችለው አንድ ሀቅ ነው። ጸሀይ በምስራቅ ወጥታ በምእራብ ትጠልቃለች። ይህ አንድ ሀቅ ነው። በዚህ ሀቅ ዙሪያ የተለየ አስተያየት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን ሀቁን ሊቀይር የሚችል ነገር የለም። ሁለተኛ ሀቅ ሊኖርም አይችልም። በብዙ ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ላይም ያለው ሀቅ አንድ ነው። ነገር ግን ከብሄራችን ፤ ከሃይማኖታችን ፤ ከፍላጎታችን ወዘተ አንጻር ነገሮችን እያየን ለኛ ብሄር ለኛ ሃይማኖት ለኛ ፍላጎት የሚሆን አዲስ ሀቅ ልንፈጥር ስንማስን የምንውል ሆነናል። በዚህ መንገድም ነው ብዙ የጀግንነትም የውርደትም ታሪክ ያዋለድነው። ብዙዎቻችን ያለን መብት በጉዳዩ ላይ አስተያየት የመያዝ ብቻ እንደሆነ ረስተን ለኛ የሚስማማ አዲስ ሀቅ ለመፍጠር ነው ጥረታችን።
ከዚህ ጋር የሚመሳሰል አንድ ታሪክ አለ። የአሜሪካ የቀድሞ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ አማካሪ የነበሩት ኬሊ አን ኮንዌይ የተጠቀሙት አማራጭ እውነት (alternative truth) የተሰኘ ገለጻ ነው። በወቅቱ ወይዘሮዋ በአሜሪካ ሚዲያ በከፍተኛ ደረጃ የተተቹ ሲሆን እውነት አንድ ነው አማራጭ እና ሁለተኛ እውነት ሊባል የሚችል ነገር የለም ተብለው ሞግተዋል። በኋላ ላይ እሳቸውም ይቅርታ ጠይቀዋል። አማራጭ እውነት ያልኩት ሌላ አዲስ እውነት ለመፍጠር ሳይሆን ተጨማሪ መረጃ ለማለት ነው ብለው አስተባብለዋል። ለሁሉም ነገር የራሳቸውን አማራጭ እውነት መፍጠር የሚፈልጉ እኛም ጋር ብዙዎች አሉ። የሚያርማቸው ሰው ያስፈልጋል።
ከላይ እንዳልኩት ብዙዎቻችን በተለይ በፖለቲካው ጉዳይ የኮንፈርሜሽን ባይዝ ተጠቂ ነን። በዚህም የተነሳ እኛ ላመንበት ነገር የሚስማማ አዲስ እውነት ስንፈጥር እና ያመኑ ሰዎችን ስናፈላልግ ነው የምንውለው። እኛ መስማት የምንፈልገውን ከተናገረ ማንንም ቢሆን ለመቀበል ዝግጁ ነን። እስኪ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ የተከሰቱትን ነገሮች እንኳን እንመልከት። በመንግሥት ላይ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ሙዚቃ ሲያወጣ በምን አይነት ስሜት እንደተቀበሉት። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ሰው በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ስላለው ጭፍጨፋ የሰጡትን አስተያየት እና ያን ተከትሎ የመጣላቸውን አድናቆትም እዩ ። በተቃራኒው እነዚህ ሰዎች የመንግሥት ደጋፊ በሆኑ ሰዎች የደረሰባቸውን ትችትም እዩ። ይህን ያየ ሰው እንደ ሕዝብ ምን ያህል የኮንፈርሜሽን ባያዝ ተጠቂ እንደሆንን በበቂ ሁኔታ መገንዘብ ይችላል። ይህ ባህሪያችንም ነው መጠቀሚያ የሚደርገን። ማንም መስማት የምንፈልገውን እየነገረ በተግባር ግን ከዚያ በተቃራኒ እያደረገ ሊጫወትብን ይችላል።
እና መፍትሄው ምንድን ነው? መፍትሄው ቀላል ነው። እኛ የምንፈልገውን እውነት ሳይሆን እውነት የሆነውን እውነት መፈለግ መጀመር አለብን። ምክንያቱም የሀገራችን ችግር በእኛ የእውነት ፍላጎት እና አረዳድ ልክ ሳይሆን በነባራዊው እውነታ ላይ ተመስርቶ ነው ሊፈታ የሚችለው። እገሌን ጀግና ነው ብለን ስለተስማማን ጀግና አይሆንም። እገሌ ጨፍጫፊ ነው ስላልንም እንዲሁ ጨፍጫፊ አይሆንም። እኛ ሆኗል ብለን ስላመንን አይሆንም ፤ አልተፈጸመም ብለን ስለካድንም ነገሩ አይሰወርም። እውነቱ በቦታው ነው ያለው። ስለዚህ የሁላችንም ጉዞ ወደ እውነቱ ነው መሆን ያለበት። መድከም ያለብን እውነቱ ላይ ለመድረስ ነው እንጂ የራሳችንን እውነት ለመፍጠር አይደለም። ማመን ያለብን ጆሯችንን ሳይሆን የሚታይ የሚዳሰሰውን ሀቅ ነው። አካሄዳችን ከመረጃ እና ማስረጃ ተነስቶ ወደ ድምዳሜ መጓዝ እንጂ ድምዳሜ ይዞ ከዚያ ለዚያ የሚሆን መረጃ እና ማስረጃ ወደ መሰብሰብ አይደለም። በተለይም የኢትዮጵያን ችግርን መፍታት የሚፈልግ ሰው ድካሙ በሙሉ እውነትን በማግኘት ላይ መሆን አለበት። ምክንያቱም አሁን የገባንባቸው ችግሮች በሙሉ ዋነኛ ማጠንጠኛ በሀሰት የተፈበረኩ ትርክቶች ናቸውና።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም