ኃይለማርያም ወንድሙ
የሙካሽ አልባሳት በነገሥታቱ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ይዘወተር የነበረ የክብር ልብስ ነው። በወቅቱ እንደ ካባ ተደርጎ በለበሱት ልብስ ላይ ጣል የሚደረግ። ነገር ግን እንደ ሌሎች ካባዎች ባለመሆኑ እንዲሁም በአንገታቸው ዙሪያና ጫፋቸው ዘርፍ ተበጅቶለት በወርቅማ ወይም በብርማ ጌጣጌጦች በወርቅ ዘቦ ስፌት ተሰፍቶ ለክብር እና ለፕሮቶኮል አገልግሎት ይለበስ ነበር።
ሙካሽ የሚለበሰው በነገስታቱ አካባቢና በቤተክርስቲያን አስተዳዳሪዎች ደረጃ ለክብራቸውና ለማዕረጋቸው መታያ በመሆኑ ተራው ሰው ሊለብሰው አቅሙም አይፈቅድም ። አቅሙ ቢፈቅም ይለብሰው ዘንድ እንደማይፈቀድለት በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ያወጋሉ።
የሙካሽ ካባ ልብስን የከሳቴ ብርሃን ተሰማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ ካባ፣ ላንቃ፣ የቤተክርስቲያን፣ የቤተመንግሥት የማዕረግ ልብስ፣ ላንቃ ያለው የመኳንንት ልብስ በሚል ይፈታዋል። ላንቃ ካባ ማለትም ዘርፍ ዘርፍ እየተደረገለት በለምድና በካባ ላይ በወርቅና በብር ጉብ ጉብ የሚጠለፍ ለምድ የማዕረግ መለዮ ልብስ ሲለው፣ የሙካሽ ጨርቅን አጥላስ ከሩጥ ሐር የተሰራ በልዩ ልዩ ዓይነት ቀለማት እያጥበረበረ የሚታይ የሐር ልብስ በማለትም ይገልጸዋል።
ከላይ እንደተገለጸው ካባ ከአጥላስ ፣ከሐር የሚሰፋ ክብ ወይም ባለኳስ ካባ ማለት መሆኑን መዝገበ ቃላቱ ያስረዳል። ካባ በልብስ ላይ ለክብር ለማዕረግ የሚደረብ ልብስ እንደመሆኑ፤ ካባ የሚለው የአማርኛ ቃላትም ፍቺው በምስጋና ላይ ምስጋና ደረበ፤ ከፍ ከፍ አደረገ እንደመሆኑ (ዝኒ ከማሁ)የሚለው የግዕዝ ቃልም ምናልባት ካባ ከሚለው ቃል ተመዞ ሊሆን ይችላል።
ሙካሽ በካባ መልክ የሚለበስ ልብስ እንደነበር ሁሉ ማሞካሸት የሚለውን ቃል ስናስበውም ሙካሽ ከሚለው ቃል የመጣ ሊሆን ይችላል። በነገሥታቱ ዘመን ለክብር ለማዕረግ፤ ለፕሮቶኮል የሚለበሰው ሙካሽ ደርግ ሲመጣ ቦታ እንዲያጣ ተደረገ። በአብያተ ክርስቲያናት፣ በዓላት አልፎ አልፎ ተለብሶ የሚታይ ሲሆን ሰዎች ለሰርግም ለብሰው ይገለገሉበታል።
በደርግ የአድኃሪያን ልብስ ነው ተብሎ ቦታ ያጣው ካባ አሁን አሁን የተወሰነ ቦታ እያገኘ ይመስላል። በዚህም ሙካሽ እንደ ፋሽን ሲለበስ ይታያል። ከበዓል ቀናት በተጨማሪ በሰርግ፣ በልደት፣ በጋብቻ፣ በበዓል፣ ትልልቅ ሽልማት ሥነሥርዓቶች ላይ መታየት ጀምሯል። የአጸደ ሕጻናት ተማሪዎች ሳይቀሩ ሲሸለሙ እንዲሁም ልደታቸውን ሲያከብሩ ሙካሽ መልበሳቸው በዘመናችን ዳግም ፋሽን ሆኖ ለመምጣቱ አንዱ ማሳያ ነው።
ሙካሽ የሚሰራበት ጨርቅ ከሌላው ጨርቅ ለስለስ ያለ በመሆኑ አንዳንዶች የሐር ጨርቅ ነው ይላሉ። አንዳንዶች ደግሞ የሙካሽ ጨርቅን ወላንሳ ይሉታል። አይነቱ ጥሩና በጣም ለስላሳ የሆነ የማይጎረብጥ ማለፊያና የሚመች ጨርቅ እንደማለት ነው። የማይጎረብጥ፣ ሰውን የማይበድል አመለ ለስላሳ ሰውም ወላንሳ ይባላል። የሙካሽ ጨርቆች በብዛት ነጭ፣ ቀይ፣ ጥቁር፣ ሰማያዊና አረንጓዴ አይነት ናቸው።
ቀይ ከፋይ ወይም አረንጓዴ ባለወርቅ ዘርፍ፤ በዙፋንና በመከዳ ላይ የሚዘረጋ የሚነጠፍ ነው። በቲሸርት መልክ ወርቀ ዘቦ ተጠልፎበት ወጣቶችና ጎልማሶች ሲለብሱትም ይታያል። ኮረዶችና እናቶችም በጉርድ ቀሚስ መልክ ያለጥልፍ ጨርቁን የሚለብሱት ሲሆን፤ በብዛት ልክ እንደጥበብ አልባሳት ወይም ቀሚሶች ወርቀ ዘቦ ተጠልፎበትም በበዓላትም ሆነ በአዘቦት ቀናት ሲለብሱት እየታየ ነው። ይህም ለማዕረግ ብቻ የሚለበሰው የሙካሽ አልባሳት በአዘቦት ቀንም ጭምር እየለበሱት መታየቱ ልብሱ እንደ ፋሽን ለመምጣቱ ማሳያ ነው።
በመርካቶ አውቶቡስ ተራ አካባቢ በሙካሽ ጥልፍ ስራ የተሰማራው ወጣት ያሲን ተሾመ፣ የሙካሽ ስራ አድካሚ እንደሆነና ትዕግስትን እንዲሁም ጥበብን እንደሚጠይቅ ይናገራል። ስራውን በልጅነቱ በመርካቶ አካባቢ ከሚኖሩ ሰዎች እያየ መማሩንም ያስረዳል። በሙያው አምስት ዓመት እንደሆነውና በአጋጣሚ በአካባቢው የሚሰሩ ሰዎች ስለነበሩ ጥበቡንና ሙያውን ወዶት እየሰራበት እንደሆነም ይናገራል። የጥልፍ ስራውና ጉብ ጉብ ማለትም አንገት ላይ እና ደረት ላይ ጫፍ ጫፉ እንደ ዘርፍ የሚጠለፉት ብርማም ሆነ ወርቅማ ጌጣ ጌጦችም ጭምር ስላሉበት ስራው አድካሚ መሆኑን ያስረዳል። ብዙ ትጋት ይፈልጋል የሚለው ወጣቱ፤ የሙካሽ ስራው በብዛት ከፋይ ጨርቅ ላይ ቢሰራም ጥበብ ላይ ከፋይ ጨርቁ አንገት ላይና በሴቶች ቀሚስ ጫፉ ዙሪያውን ከፋይ ተደርቦበት እንሚሰራ ያስረዳል።
ከፋይ የሙካሽ ጨርቆቹ ቀሚስ፣ ካባ እና የወንዶች ቲሸርት እንደሚሰራበትና በተለይ ቀሚስና ቲሸርቱ እንደ ጥበብ ወርቀ ዘቦ ብቻ ተጠልፎበት በብዛት ሰዎች እንደሚገዙትና ተወዳጅ እየሆነ መምጣቱን ይናገራል። በአካባቢው ብዛት የሙካሽ ስራ እንደሚሰራ የሚጠቁመው ወጣት ቀደም ሲል አልባሳቱ ለንጉስና መሳፍንት ቤተሰቦች ይሰራ እንደነበር በመግለፅ የሚሰሩትም ትልልቅ ሰዎች መሆናቸውን ያስረዳል። እነዚህ ሰዎችም ሙያውን አውርሰው ስለሄዱ ወጣቶች እንደቀጠሉበት ይናገራል።
አሁን አሁን ዜጎች የሀገራቸውን ልብስና ባህል መጠቀም በመጀመራቸው ሙካሽ እንደጥበብ አልባሳት መለበሱ እየተዘወተረ ነው። ሙካሽ በብዛት የሚሰራው በካባ ብቻ ስለነበር አሁን ወጣቶችና ኮረዶች በስፋት እንደፋሽን አድርገው እያስጠለፉ ሲለብሱት ይታያል። ባህላዊው ከዘመናዊው ጋር እየተቀላቀለም ልዩ ውበት ባለው መልኩ እየተሰራ ይገኛል።
ለሙካሽ ስራ የሚያገለግሉት ወርቅማ እና ብርማ ጉብ ጉብ ጌጣ ጌጦች በተለይ ለካባው ስራ ወሳኝ በመሆኑ በብዛት ከዱባይ፣ ከቻይና እና ከህንድ፤ ጨርቁም ከቻይናና ከዱባይ እንደሚመጣ ወጣት ያሲን ይናገራል። የሙካሽ ካባዎች ዋጋቸው ውድ ስለሆነና ስለማይዘወተሩ ሰዎች በብዛት በኪራይ መልክ በዓል ሲኖርባቸው መጠቀምን እንደሚመርጡም ያስረዳል። በዚህም ልብሱን የሚሸጡ ሱቆች የበለጠ ተጠቃሚ ሆነዋል። እነዚህ ነጋዴዎች ከማከራየት በዘለለም ለደንበኞቻቸው እያዘጋጁ በመርካቶ፣ ሽሮሜዳ፣ ኮልፌና ቦሌ እንደሚሸጡና እንደሚያስረክብም ያስረዳል።
በአምስት ኪሎ አካባቢ የቤተ ክህነት አልባሳትን በማዘጋጀት ስራ የሚተዳደረው አብርሃም ይበቃል፤ ሙካሽ ለሠርግ፣ ለልደት፣ ለጋብቻ፣ ለበዓል፣ ለሽልማት ሥነሥርዓት የሚያገለግል የማዕረግ ልብስ እንደሆነ ይናገራል። ዋጋው ውድ ስለሆነ ሰዎች በብዛት ተከራይተው መገልገልን እንደሚመርጡም ያስረዳል። ነገር ግን በዘመናችን ጨርቁ ወጣቶች እና ኮረዶች እየተወደደ በመምጣቱ በወርቀ ዘቦ እያስጠለፉ ሲገለገሉበት ማየት የተለመደና ጨርቁ ከካባ በዘለለ እያገለለ እንደሚገኝ ይናገራል። ይህም ዳግም እንደፋሽን ሆኖ ስለመምጣቱ ማሳያ መሆኑን ያስረዳል።
አዲስ ዘመን ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም