የአስራ አንድ ዲግሪ ባለቤት
ትምህርት ከ1900 ዓ.ም በፊት በአብዛኛው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጋር የተሳሰረ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ። መደበኛ የሚባለው የትምህርት ሂደትም ከሃይማኖት ጋር ተዳብሎ የሚሰጥ ነበር። በተለይም በዘመኑ አንድ ልጅ እስከ ዳዊት መድገም የደረሰ ትምህርት ካለው በቂ ተደርጎም ይቆጠር እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ከ1900 ዓ.ም በኋላ ጥቂት ሕፃናት ዘመናዊ ትምህርት ማግኘት ችለዋል። ለዚህ ደግሞ የዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት በዘመናዊው ትምህርት ፈር ቀዳጅ ሆኗል። ሪቻርድ ፓንክረስት በኢትዮጵያ ትምህርት ላይ በፃፉት ጽሑፍ በ1924 ዓ.ም ከ 3ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በዘመናዊ ትምህርት ቤቶች መማር መጀመራቸውን ይገልጻል ። 150 የሚሆኑ ሕፃናትም ወደ ትምህርት ቤት መምጣት ችለው እንደነበርም ነው ጽሑፉ የሚገልጸው።
በ1925 ዓ.ም 20 የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ቢከፈቱም የተማሪዎች ቁጥር ግን ከ 8 ሺህ መብለጥ ያልቻለ እንደነበርም መረጃዎች ያሳያሉ። የአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን በትምህርት ዘርፉ በርካታ ትምህር ቤቶች የተከፈቱበት በተቃራኒው ደግም በርካቶች ከትምህርት ገበታ በተለያዩ ምክንያቶች የተገለሉበት ዘመንም እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናጋራሉ። በተለይም ከጣሊያን ወረራ በኋላ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ የሌሎች ሀገራት ዜጎች የሚያስተናግዱ ትምህርት ቤቶች ብቅ ብለዋል። ራስ ተፈሪ መኮንንና መነን ትምህርት ቤቶች ለዚህ የሚጠቀሱ ናቸው። የእቴጌ መነን ትምህርት ቤት በጊዜው ሴቶች ተማሪዎች ብቻ የሚማሩበት ነበር። ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበሩ ሴት ተማሪዎች የነበረባቸው የባሕል ተፅእኖ እጅግ ከፍ ያለ ስለነበር ቁጥራቸው እጅጉን ዝቅተኛ ነበር ።
ታዋቂው ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ ደግሞ የመማርን ጥቅም በስንኝ አዋዶ በዜማ ማስደመጡ ዜጎች ለትምህርት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል፤
ጊዜው ካፊያ ነበር ትንሽ ጨለም ብሎ
አባቴ ሲጠራኝ እያለ “ና ቶሎ”
ምንም ትንሽ ብሆን ምስጢሩ ባይገባኝ
አባቴ እንባ አውጥቶ አልቅሶ መከረኝ
እንዲህ ሲል መከረኝ:-
“ተማር ልጄ ተማር ልጄ
ወገን ዘመድ የለኝ ሃብት የለኝም ከጄ
ስማኝ ልጄ ሌት ፀይ ነው
ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው።”
አዎ ! ላልተማረ ሰው ቀኑ ጨለማ ነው። ምክንያቱም ነጋዴም ዘፋኝም የቱም ሙያ ቢሆን በትምህርት ሲታገዝ ውጤቱ ከፍ ያለ በመሆኑ ነው፡፡ የዛሬ የሕይወት ገጽታ አምድ እንግዳችንም የመማርን ጥግ ያሳዩ መማር ከባድ መስሎ ለሚታያቸውም ትልቅ አርዓያ መሆን የሚችሉ አምስት የመጀመሪያ እንዲሁም አምስት ሁለተኛ ዲግሪና አንድ ዲፕሎማን በ 24 ዓመታት ውስጥ ያገኙ ሰው ናቸው፡፡
አቶ ሀብታሙ አበበ ተወልደው ያደጉት በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በደጀን ከተማ ነው ፡፡ ለቤተሰቦቻቸው አራተኛ ልጅ ሲሆኑ ፤ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም እዛው ደጀን ከተማ ነው የተከታተሉት፡፡ በትምህርታቸው ሰነፍም በጣም ጎበዝም ያልሆኑ መካከለኛ ተማሪ እንደሆኑ ነው የሚናገሩት፡፡
” ….በአንደኛ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴ መካከለኛ ደረጃ ላይ የምቀመጥ ተማሪ ነበርኩ፡፡ ያኔም ሆነ እስከ አሁን የምወደው የሒሳብ ትምህርትን ነው። በነገራችን ላይ ቤተሰቦቼ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ነበሩ እነሱ የመማር እድልን ባያገኙም ለትምህርት ግን የሚሰጡት ዋጋ ከፍ ያለ ነበር። በዚህም ለእኔ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ልጆቻቸውን አስተምረው ጥሩ ደረጃ ላይ ለማድረስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ ነበር” ይላሉ ።
የቤተሰቦቻቸው ጥረት እንዲሁም የራሳቸው የትም ህርት ፍቅር ታክሎበትም አቶ ሀብታሙን ጨምሮ ሌሎቹም እህት ወንድሞቻቸው ከፍ ባለ ደረጃ የተማሩ በበርካታ ኃላፊነቶች ላይ የሚገኙ ስለመ ሆናቸው ይናገራሉ።
አቶ ሀብታሙ በዚህ ጥረታቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳ ጠናቀቁ በ1988 ዓ.ም ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ተመደቡ። እርሳቸው ይፈልጉ የነበሩት ሌላ ቦታና ሌላ ትምህርት ነበር። በመሆኑም አቶ ሀብታሙ ከኮንስትራክሽን ጋር የተያያዘ ትምህርት ቢማሩም ነበር የሚፈልጉት።
“….አዎ 12 ክፍል ብሔ ራዊ ፈተና ከተፈተንኩ በኋላ ምድቤ ኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ሆነ ፤ ይህ ደግሞ እኔ ከምፈልገው የኮንስትራክሽን ሙያ ጋር ምንም የማይገናኝ ነበር። እኔ እፈልግ የነበረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕንፃ ኮሌጅ የሚባለው ትምህርት ቤት መግባት ነበር። ሆኖም አልተሳካም ኮተቤ ገባሁ” ይላሉ።
ሳይፈልጉ ወደ ኮተቤ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሄዱት አቶ ሀብታሙ ወደ ኮሌጁ አልሄድም ብለው ሁሉ ትምህርታቸውን ሊያቋርጡ ፈልገው ነበር። ነገር ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አምስት ኪሎና ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲዎች ይማሩ የነበሩት እህትና ወንድሞቻቸው በፍጹም ማቋረጥ የለብህም ተማርና ትቀይራለህ በማለታቸው የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርትን ለመማር ገቡ።
“….እንደነገርኩሽ የእኔ ፍላጎት ሕንጻ ኮሌጅ ገብቼ የኮንስትራክሽን ሙያን መማር ነበር ፤ሆኖም አልተሳካም። እዚህ ደግሞ የደረሰኝ የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ሆነ፤ እኔ ምንም ደስ ሳይለኝ ቀረ ፤ ነገር ግን ትምህርቱን እንድከታተል ካደረጉኝ አሳማኝ ምክንያቶች መካከል ደግሞ ትምህርት በምስራቅ አፍሪካ በዲግሪ ደረጃ የሚሰጠው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ መሆኑ ነበር ፤ እናም ይህንን ትምህርት ተምረህ ጥሩ ውጤት ማምጣት ከቻልክ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ በመምህርነት የመቀጠል እድሉ ይኖርሃል ሲሉኝ አመንኩና ትምህርቴን ቀጠልኩ” ይላሉ።
የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርቱን ለሌሎች የሕይወት ጉዟቸው እንደመንደርደሪያ አድርገው ለመጠቀም ያሰቡት አቶ ሀብታሙም የአራቱን ዓመት ትምህርት በከፍተኛ ጥረትና በጥሩ ውጤት ለማጠናቀቅ ቻሉ።
“….ወንድሞቼም ሌላውም የሚያውቀኝ ሁሉ በመከረኝ መሠረት በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የጀመርኩትን የሰውነት ማጎልመሻ ትምህርት ጠንክሬ በመማር አብረውኝ ካሉት ሁሉ ላቅ ያለ ውጤትን ለማምጣት ቻልኩ። በዚህ ውጤቴም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ለመቀጠር ቻልኩ ” ይላሉ።
ይህ አቶ ሀብታሙና የወዳጅ ዘመዶቻቸው እቅድ የመሳካቱ አንዱ ማሳያ ሆነ ፤ ምክንያቱም ሌላ ትምህርትን ተምረው ቢሆን ኖሮ በመምህርነት ገጠር ይገቡ ይሆናል እንጂ ዩኒቨርሲቲ ላይ የመመድብ እድላቸው ጠባብ ስለነበር ነው።
“…..መጀመሪያ ላይ እኔ መምህርነት አልፈልግም የትምህርት መስኩንም አልወደድኩትም ስል ቤተሰቦቼ አይ ጥሩ ነው ትምህርቱም በስፋት በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ባለመሆኑ ዩኒቨርሲቲ ገብተህ የማስተማር እድል ታገኛለህ ፤ እሱን ካገኘህ ደግሞ የትምህርት መስክህንም ትቀይራለህ፤ ሌሎች ትምህርቶችንም ትማራለህ ሲሉኝ ተስማምቼ ነው ትምህርቱን በጥሩ ውጤት ተምሬ ያጠናቀቅሁት” ይላሉ።
ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ተቀጥረው የሄዱት አቶ ሀብታሙ እዛም ብዙ ሳይቆዩ ሌላ ሥራ አግኝተው የቢሮ ሠራተኛ ሆኑ ፤ ነገር ግን የትምህርት መስካቸውን የመቀየር ሌላ ትምህርትን የመማር እቅድ የሰነቁ በመሆኑ ሥራውን እየሠሩ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርታቸውን ጀመሩ።
” ….ማስተማር ብዙም ፍላጎቴ ስላልነበረ የትምህርት ዓይነቱንም ስላልወደድኩት ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሄድኩ በኋላ ብዙም ሳልቆይ ሌላ መሥሪያ ቤት አመልክቼ በመግባት የቢሮ ሥራ ነው የቀጠልኩት። ነገር ግን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርቴንም ቀጥዬ ነበር “ይላሉ።
ምንም እንኳን ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቆይተው እስከ ፒኤች ዲ ዲግሪ ድረስ የመድረስ እድል ቢኖራቸውም ይህንን ማድረግ አልቻሉም። ቢሆንም ግን እሳቸው ከመማር ያገዳቸው አንዳችም ነገር አልነበረም። እንደውም መማር ሱስ እስኪሆንባቸው ድረስ ትምህርትን ከሥራቸው ጎን ለጎን አስኬዱት።
“….በወቅቱ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አካውንቲንግን ትምህርትን መስጠት የጀመረው ለመጀመሪያ ጊዜ ያውም በዲፕሎማ ነበር። እኔም እየተማርኩ ባለሁበት ወቅት ሥራዬ ወደ ደብረማርቆስ በመዘዋወሩ 3መቶ ኪሎ ሜትሮችን እየተመላለስኩ በቅዳሜና እሁድ ተምሬ ነው የጨረስኩት ” ይላሉ።
ከ1988 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት ላይ ያሉት አቶ ሀብታሙ አካውንቲንግን እንደጨረሱ የማኔጅመንት ትምህርታቸውን እዛው ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ጀምረው ነበር፤ሆኖም ትምህርቱን ሳይጨርሱት አዲስ አበባ የሚመጡበት አጋጣሚ ተፈጠረና መጡ።
“…. ከ 1988 ዓ.ም ጀምሮ ለ24 ዓመታት ያለማቋረጥ የተለያዩ ትምህርቶችን ተምሬያለሁ እንደው ከእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሙሉውን ቢደመር አንድ ዓመት እንኳን የማይሞላ ነው ከትምህርት ውጪ ሆኜ ያሳለፍኩት በዚህም ያሰብኩበት ከመድረሴም በላይ በጣም ደስተኛ ነኝ “ይላሉ።
አቶ ሀብታሙ በባህር ዳር የጀመሩትን የማኔጅመንት ትምህርት መቀጠል ባይችሉም በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ በመግባት የኮምፒውተር ሳይንስ ትምህርታቸውን ቀጥለዋል ። ከዛም በኋላ ያለማቋረጥ እስከ ዛሬ ድረስ አምስት የመጀመሪያ ዲግሪ፤ አምስት ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም አንድ ዲፕሎማን በተለያዩ የትምህርት መስኮች ለማግኘት ችለዋል። አቶ ሀብታሙ የተማሯቸው የትምህርት አይነቶች ፦ MA Construction Management ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፣MA Human Resources Management ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ፣ MA Social Psychology ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣MA Human Resource & Organization Development In Education ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ MA Logistics & Supply Chain Management አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ፣ Bsc Civil Engineering ከአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ፣ BA Finance & Economics ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ ፣ BA Development Management ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ፣Bsc Computer Science ከቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፣BE Health & Physical Education ከኮተቤ የመምህራን ትምህርት ኮሌጅ፣ diploma Accounting ከባህርዳር ከዩኒቨርሲቲ ናቸው። አብዛኛው ሰው የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ ሁለተኛ ሶስተኛ ዲግሪ ድረስ ሊደርስ ይችላል ። እርስዎ ግን በተለያዩ መስኮች ይህ ሁሉ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ የመማርዎ ምክንያት ምንድን ነው? ግቡስ የቱ ጋር ነው ? ብዬ ላነሳሁላቸው ጥያቄ ሲመልሱ ፤
” …….የዚህ የትምህርት ሂደት መነሻው ከፍተኛ የሆነው የትምህርት ፍላጎቴ ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ የዲፕሎማ ትምህርቴን ለመጨረስ ሶስት መቶ ኪሎ ሜትሮችን እመላላስ ነበር ። የተለያዩ የትምህርት አይነቶችን ለመማሬ ምክንያቱ ደግሞ በተለያዩ ተቋማት የምሠራባቸው ብሎም በኃላፊነት የሚሰጡኝ የሥራ መደቦች ናቸው” ይላሉ ።
አቶ ሀብታሙ በሚመደቡበት የሥራ መስክ ላይ በተለይም ሙያ ነክ በሚሆኑ ጊዜ ከባለሙያዎች ጋር ሙያዊ ቃላቶችን እየተጠቀሙ ለመነጋገር ተግባብቶም ሥራ ለመሥራት እነሱ የሚሠሩትን ሙያ መማር ያስፈልጋል ብለው ያምናሉ ለዚህም ነው አራት ያህሉ ትምህርቶቻቸው በሚሠሩባቸው ሥራዎች ዙሪያ ያደረጉት።
“…..ትምህርቶቹን እየተማርኩ በተለያዩ መስኮችም የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎቼን እየተቀበልኩ ስመጣ አስር ዲግሪዎችን መያዝ የሚል ግብ አስቀመጥኩ። የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርቴንም የማስበው ከዚህ በኋላ ነው” ይላሉ ።
ከዚህ በኋላ ግቤን አሳክቻለሁ የመጀመሪያም ሆነ ሁለተኛ ዲግሪን ከዚህ በኋላ አልማርም የሚሉት አቶ ሀብታሙ የትምህርት ፍላጎቴን አይቶ የሚያግዘኝና የሚደግፈኝ ባገኝ ግን ሶስተኛ ዲግሪ (ፒኤች ዲ) የመማር ሕልም አለኝም ይላሉ።
እንኳን አስር ዲግሪ አንድና ሁለትም ለመማር ከፍተኛ የገንዘብ የጊዜና የጉልበት ወጪ ይኖረዋል። አቶ ሀብታሙም ለትምህርታቸው ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለዋል። ለእኔ ገንዘብ ከትምህርቴ አይበልጥም የሚሉት አቶ ሀብታሙ ከመጀመሪያና ከአንድ ሁለተኛ ዲግሪ ውጪ ያሉትን በሙሉ በራሳቸው ወጪ ስለመማራቸው ይናገራሉ ።
ለሁለት ዓመታት ያህል ሁለት የዲግሪና አንድ የማስተርስ ዲግሪ ትምህርቶችን በተመሳሳይ ዓመት በመጀመር ተምሬያለሁ የሚሉት አቶ ሀብታሙ በተለይም ፈተና በሚደርስበት ጊዜ ከፍተኛ መጨናነቅ ውስጥ እንደሚገቡ ይናገራሉ።
” ….የሚገርመው በአንድ ዓመት ውስጥ ሁለት ዲግሪና አንድ ሁለተኛ ዲግሪ እየተማርኩ ነበር ፤ በጣም ጊዜ ከማጣቴ የተነሳ ከእንቅልፍም ከሰውም ተቆራርጬ ነበር ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ፈተናዎች በአንድ ላይ ገጥመውብኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሜርስ ላዳ ታክሲ ተከራይቼ በማቆም ፈተና ተፈትኜ ጨርሼ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሄጄ የተፈተንኩበት ጊዜ የማልረሳው ነው። ከዛ በኋላ ግን እንደዚህ አድርጌ አላውቅም “።
ትምህርት ሲደራረብ በውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ አያሳድርም ወይ? ብዬ ላቀረብኩላቸው ሲመልሱም “….አዎ ተጽዕኖ አለው። ነገር ግን እኔ ለመመረቅ ሳይሆን ፍላጎቴን ለማርካት ብቻ ነበር የምማረው። የመጀመሪያውንና የመጨረሻውን ዲግሪዬን አንኳን ሁለቱንም በከፍተኛ ውጤት ነው የጨረስኩት። የምስክር ወረቀትም ተሰጥቶኛል” ይላሉ።
ሌሊት ተኝቼ አላውቅም የሚሉት አቶ ሀብታሙ ቀን ግን በምንም ተዓምር ትምህርቴ በሥራዬ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳርፍ አላደርግም፤ እንደውም ምንም ዓይነት የትምህርት ጥናት በቢሮ ውስጥ አላጠናም። ሰዎችም ስለመማሬ አያውቁም ይላሉ። እንደዚህም ሆነው ተምረው አሁን የመጨረሻው ዲግሪያቸውን ሲያገኙ እንኳን ከአንድ “ኤ-“(ኤ ማይነስ) ውጪ ሁሉንም “ኤ+” ነው ያመጡት።
“…. .ውጤቶቼ ሁሉም ማለት ይቻላል በጣም ጥሩ ናቸው ። አንድም የትምህርት ዓይነት ወደሌላ ዓመት ተዘዋውሮብኝ አያውቅም። ይህ ደግሞ ሁለትም ሦስትም ትምህርት በምማርበትም ጊዜ የሚሆን ነው። በመሆኑም ተጽዕኖ ቢኖረውም እኔ ለመመረቅ ሳይሆን ለፍላጎት የምማር በመሆኔ ውጤቴ አይቀንስም። በነገራችን ላይ አብረውኝ ከዓመት ዓመት የሚማሩትም ልጆች ቢሆኑ ሁለት ሶስት ዲግሪ ይዤ የምማር መሆኔን አያውቁም” ይላሉ።
“ትምህርት ለእኔ ሱስ ነው” የሚሉት አቶ ሀብታሙ አሁን የዚህን ዓመት ትምህርት ጨርሼ ተመርቄያለሁ ፤ ሌሊት ግን ምን እንደምሠራ ከወዲሁ በጣም ተጨንቄያለሁ” ይላሉ።
ከትምህርት ውጪ ብዙም የሚያስደስታቸው ነገር የሌለው አቶ ሀብታሙ ትዳር ባይመሰርቱም ሁለት ልጆች አላቸው ፤ ነገር ግን ልጆቻቸውን እንደ አባት የትም መዝናኛ ቦታ ወስደው አዝናንተው ብሎም ትምህርታቸውን አስጠንተው እንደማያውቁ ይናገራሉ። እህትና ወንድሞቻቸውም አዲስ አበባ ከተማ ላይ ቢሆኑም በዓመትና በሁለት ዓመት ብቻ እንደሚያገኟቸው ነው የሚናገሩት። ይህ የሆነው ግን ጊዜ በማጣቴ ነው ቤተሰቦቼም ተረድተውኛል ለእኔም ቢሆን ከትምህርት የሚበልጥብኝ አንዳችም ነገር የለም ይላሉ።
“….እኔ ከትምህርት ውጪ ለሌላ ነገር ጊዜ ሰጥቼ አላውቅም ፤ ሕጋዊ ትዳርንም ያልመሠረትኩት በዚህ ምክንያት ነው። በገንዘብም በኩል ቢሆን ብዙዎቹን ትምህርቶቼን በራሴ ከፍዬ ነው የተማርኳቸው። ተጽዕኖ ግን አለው። በነገራችን ላይ ልጆቼን እንደ አባት ተከታትዬ ስለ ትምህርታቸው ጠይቄ አስጠንቼ አላውቅም ፤ምክንያቱም ጊዜ የለኝም። የትምህርት ወጪው ብዙ ስለሆነም የመንግሥት ሥራዬንም ሳላጓድል ትምህርቴንም እየተማርኩ ከ2005 እስከ 2010 ዓ.ም ድረስ የግል ኮሌጆች ላይ በመምህርነት እሠራ ነበር። ግን ደግሞ ልጆቼን ስመረቅ ይዣቸው እሄዳለሁ ፤አንዳንድ ጊዜ የሕይወት ልምዴን እመክራቸዋለሁ ፤በተቻለ መጠን ቀናውን ጎዳና ለማሳየት እሞክራለሁ ፤ እነሱም ግን በጣም ጎበዝ ናቸው ባይባልም መካከለኛ ተማሪዎች ናቸው። እኔ ግን ደግፌያቸዋለሁ ለማለት አልችልም” ይላሉ።
አቶ ሀብታሙ ሥራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በሠሩባቸው መሥሪያ ቤቶች በሙሉ ውጤታማ ስለመሆናቸው ይናገራሉ ።በጣም ካልተቸገሩ በቀርም ትምህርትን በሥራ ሰዓት ለማጥናትም ሆነ የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት እንደማይሞክሩም ነው የሚናገሩት፤ ምን ጊዜም ቢሆን ቅድሚያ የምሰጠው ለሥራዬ ነው ይላሉ።
“…. ብዙ ትምህርት መማር ጥቅም አለው ምክንያቱም በማንኛውም የሥራ መስክ ላይ ለመሥራት ያስችላል። በአንድ የሥራ ዘርፍ ላይ ስፔሻላይዝድ ከማድረግ ይልቅ በተለያዩ መስኮች እውቀት መሸመት ውጤታማ ያደርጋል። እኔም የተለያዩ ትምህርቶችን መማሬ በተመደብኩበት ዘርፍ ሁሉ ውጤታማ ለመሆን አስችሎኛል ” ይላሉ። አቶ ሀብታሙ እንዳሉትም ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት ለትምህርታቸው ነው ። በዚህም ሰርግ የሚባል ነገር ሄደው አያውቁም ። ዘመድ መጠየቅም እሳቸውን የሚመለከት አይደለም። ለቅሶ ግን በጣም የቅርብ የሆኑ ወሳኝ ቤተሰቦች ሲሆኑ እንደሚሄዱ ይናገራሉ።
“……የቅርብ ሰዎቼ ማለትም እህት ወንድሞቼ እንዲሁም ጓደኞቼ እስከዚህ እድሜ ድረስ ለትምህርት መልፋት ፋይዳው ምንድን ነው እያሉ ይጠይቃሉ። ነገር ግን እኔ ትምህርት ስጀምር ለማንም አልናገርም ሊያልቅ ሲል ነው የምናገረው፤ እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን አብዛኞቹ ቤተሰቦቼ ደስተኞች ናቸው በጋዜጣ ላይም እንዲወጣ የሚያደርጉት እነሱ ናቸው። ግን ደግሞ እንዳልለፋ ይፈልጋሉ” ይላሉ።
ትምህርት በመማሬ አጣሁት የምለው ነገር ባይኖረኝም ልጆቼን አለመደገፍ። ሰርግ። ለቅሶ አለመድረስ በተለያዩ ማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይ አለመሳተፍ ጉድለት ነው፤ ነገር ግን በመማሬ ያገኘሁትን ነገር ደግሞ አይተካልኝም፤ በገንዘብም በኩል ቢሆን ብዙ ዋጋ እከፍላለሁ በመንግሥት ደመወዝ ነው ይህንን ሁሉ ትምህርት የምማረው። ነገር ግን ለትምህርት ያወጣሁት ወጪ ምንም አይመስለኝም ይላሉ።
መልዕክት
ለአንድ ዓመት የትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ሠርቻለሁ ፤ሁሌም የምበሳጭበት ነገር ደግሞ የተጭበረበረ የትምህርት ማስረጃ በሚያቀርቡ ሰዎችና በሚሰጡ የትምህርት ተቋማት ላይ ነው። እነዚህ ሰዎች አንድ ትምህርት መማር አቅቷቸው ነው በተጭበረበረ ሰነድ እንጀራ ለመብላት የሚሄዱት ነገር ግን አይደለም አንድ አስራ አንድና ከዛ በላይ ትምህርት መማር እንደሚቻል ከእኔ መማር ይችላሉ ።
መማር ደግሞ በራስ መተማመን ይጨምራል፤ ተቋማትም ሊገነዘቡ የሚገባው ነገር ሐሰተኛ ማስረጃ በሰጡ ቁጥር ሰውዩውን ብቻ ሳይሆን ሀገርን እየገደሉ መሆኑን ነው። ሁሉም ሰው አንድ አይደለም ከዛ በላይ መማር እንደሚቻል ማወቅ ያስፈልጋል። ለወጣቶችም የምመክረው ጊዜን ባልባሌ ከማጥፋት በትምህርት ላይ ቢያተኩሩም ለሀገርም ለራሳቸውም ጥቅሙ የጎላ ነው ሲሉ መልዕክታቸውን ይቋጫሉ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ን 2014 ዓ.ም