እውነቱን ለመናገር በዚህ ቀውጢ ሰዓት ይቺ ሀገር ከምንም ነገር በላይ ሀገራዊ ምክክር ፣ እርቅንና ሰላምን የሚያስቀድም ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያለው አመራር ያስፈልጋታል። እንደመታደል ሆነ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት ብሔራዊ ምክክር፣እርቅ፣ሰላም፣ ይቅርባይነት ፣ ፍቅር፣ መሰባሰብ ፣ መደመር ሳይነሳ ውሎ ያደረበት ቀንም ሆነ አጋጣሚ የለም ማለት ይቻ ላል። ሆኖም በአመራሩም ሆነ በልሒቃኑና በሕዝቡ ዘንድ ያን ያህል ሕብር ፣ መናበብና መሰጠት አለ ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቸግራል። ይህን ክፍተት ሞልቶ ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑም ሆነ በእርቅና ሰላም ላይ ለሚሠሩ አካላት ተገቢውን ድጋፍና ትኩረት መስጠት ይገ ባል። በትውልዶች መካከል ከስንት አንድ እጃችን የገባን ይህን መልካም አጋጣሚ በፍጹም ጥበብና ማስተዋል ልንጠቀምበት ታሪካዊ ኃላፊነት አለብን ።
መንግሥት ለዚህ ነው ሰሞኑን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያረጋገጡት ። ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን አመራርና አባላት ጋር በተያዘው ሳምንት ውይይት አድርገዋል። መንግሥት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሥራ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ፤ ሁሉም አካላት በአካታችነት ወደምክክሩ እንዲመጡ ፍላጎቱን በተግባር ማሳየቱን ፤ በኮሚሽኑ ሥራ ጣልቃ የመግባት ፍላጎት እንደሌለውና ይልቁንም ለኮሚሽኑ ሥራ መሳካት የበጀትና ሌሎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ዶ/ር ዐቢይ አረጋግጠዋል። ኮሚሽኑ መጨረሻ ላይ ለሚያቀርበው ምክረ ሀሳብ ተግባራዊነት ብልጽግና ያለምንም ማቅማማት እንደሚሠራ ቃል ገብተዋል ። በተመሳሳይ ሁኔታ በሰሜኑ የሀገሪቷ ክፍል ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ፓርቲያቸው ብልጽግና የሚከተለው የሰላም አማራጭ ሀገራዊ ጥቅምን በሚያስከብር እና በአፍሪካ ኅብረት አመቻችነት መሆኑን ፤ ችግሩን ለመፍታት ፓርቲው የሚከተላቸው የሰላም አማራጮች ሕገ መንግሥታዊነትን ባከበረ ፣ ሀገራዊ ጥቅምን ባረጋገጠ መልኩ እንዲካሄድ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ እና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አቅጣጫ ማስቀመጡና በፌዴራል መንግሥት በኩል የሰላም ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙ ያለውን ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ያመለክታል። አሸባሪው ሕወሓት የጦርነት ነጋሪት ጉሰማውን ትቶ ወደ ውይይት የሚመጣ ከሆነ አንድምታው ሰፊ ነው ።
ስለ እውነተኛ እርቅ በተወሳ ቁጥር ከልዑል ፈጣሪ ለጥቆ መቼም ወደ አይነ ፣ እዝነ ሕሊናችን ግዘፍ ነስቶ የሚመጣው ፣ በግርማ ጮሆ የሚሰማን ኔልሰን ማንዴላ /ማዲባ/ ነው ። የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ ፣ ደቡብ አፍሪካ ፣ አፓርታይድ ፣ ኤፍ ደብሊው ዴክለርክ፣…፤ ከዚያ ይከተላሉ ። ስለ እርቅ ሲነሳ ማዲባ አብሮ ስሙ ይወ ሳል። ማዲባ ሲወሳ እርቅ አብሮ ይነሳል ። የእርቅ ምልክት ነው። በገዘፈው ሰብዕናው ገልጦ በተግባር አሳይቶናል። ኑሮታል። መስክሮታል ። እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1998 የእውነትና እርቅ ኮሚሽን ያጠናቀረውን ሪፖርት ማዲባ ከሊቀ መንበሩ ቀሲስ ዴዝሞንድ ቱቱ ከተረከበ በኋላ ባስተላለፈው መልዕክት ፤” በሕገ መንግሥታችን የተደነገገውን ዴሞክራሲና ሰብዓዊነት ለመጠበቅ እርቅ ያስፈልገናል ። “ ብሎ ነበር ። አዎ ! ተቀራርቦ መነጋገር ፣ እርቅና መግባባት ከሌለ ሰላም ሊሰፍን አይችልም ። ሰላም ከሌለ አይደለም ሰብዓዊነት ፣ ዴሞክራሲ ፤ የሀገር ሕልውና ላይ አደጋ መደቀኑ አይቀርም ። እንደኛ በውጥረት ፣ ውሉ በጠፋ ትብታብ እና ፅንፍ በረገጠ አቋም ላይ ለምትገኝና ለምትጠራወዝ ሀገር ተቀራርቦ መነጋገር ፣ መግባባትና መታረቅ የግድ ነው ። ሀገራችንን ትናንትም ሆነ ዛሬ ቁም ስቅሏን እያሳያት ያለው በፖለቲካዊ ልሒቁና በጭፍራው የሚጎነቆለው ልዩነትና ጥላቻ ከፍ ሲልም ዋልታ ረገጥነትና የፈጠራ ትርክት ነውና ፖለቲካዊ ዕርቅ በብርቱ ያሻናል ።
ለመሆኑ ፖለቲካዊ እርቅ Political Reconcilation ሲባል ምን ማለት ነው ?
ኮሊን መርፊ “ THE FORGIVENESS MODEL OF RECONCILIATION “በሚል ርዕስ ለንባብ ባበቃው ጹሑፉ ፤ “ ፖለቲካዊ እርቅን የተሰበረ ግንኙነት የመጠገን ሂደት ነው። “በታሪክ ምርኮኝነት ፣ ሆን ተብሎ ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል በተነዛ የፈጠራ ትርክት ፣ በማንነት ላይ በተዋቀረው ፖለቲካ፣ በግራ ዘመም አይዶሎጂ እና በሕዝበኝነት populism በተካረረ ልዩነት ፣ ቁጭት መፍጠር እንደማታገያ ስልት በመወሰዱ ፣ በሴራ ኀልዮት በተጎነቆለ ጥላቻ ፣ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲባል በሕዝቦች መካከል በተዘራ ልዩነት ፣ አንድን ሕዝብና ሃይማኖት በመለየት እንደጠላት መፈረጅ እና በሌሎች ገፊ ምክንያቶች የተነሳ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት እጅግ ሻክሯል ። በዚህ የተነሳ የአንዳንድ ፓርቲዎች አመራሮች አይደለም ቁጭ ብሎ ለመነጋገር አይን ለአይን እንኳ ለመተያየት ፍቃደኞች አይደሉም ።
ኮሊን ፖለቲካዊ እርቅ ሶስት ንጣፎች ወይም ንብርብር layers እንዳሉት ያትታል ። የላይኛው የፖለቲካ ፓርቲዎች ግንኙነት እንዲበላሽ ያደረጉ መግፍኤዎችን መለየት ፤ እነዚህን ምክንያቶች ከፍ ብዬ ለማሳየት የሞከርሁ ሲሆን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ግን ይበልጥ ዘርዝሮ ሊተነትናቸው ይችላል ። መካከለኛው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከሚፈጠር እርቅ የሚጠበቀውን ግብ ለይቶ ማስቀመጥ ነው ። የተቀመጠው ግብ ውስን ሊሆን ይገባል ። በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያሉ ልዩነቶችን ከማባባስ መቆጠብ ሊሆን ይችላል ። እንደ ብሔራዊ እርቅ ያሉ ጉዳዮች ግን ከፓርቲዎች አልፈው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩና ተዋናዮቹም በርካታ ስለሆኑ በዚህ የእርቅ ሒደት የሚካተቱ አይደሉም ። የታችኛው ንጣፍ እርቁ የሚሳካበትን ስልት መንደፍ ነው ። ከፍ ሲል የተነሱትን ሁለቱ የፖለቲካዊ እርቅ ንጣፎችን በጥንቃቄ መተግበር የእርቅ ሂደቱን ውጤታማ ያደርገዋል ተብሎ ይታ መናል። ኮሊን መርፊ በማስከተል ፤ “ ፖለቲካዊ እርቅ የሕግ የበላይነትን በስምምነት በጋራ የማረጋገጥ እንጂ ይቅር የመባባል ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም ። በእርቅ ሂደቱ ምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ መቀመጥ የለበትም ። …” የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ሊያካሂደው ያቀደውን እርቅ ከምንም አይነት ቅድመ ሁኔታ ጋር ሊያያይዘው አይገባም ። ሁላችንም ልብ እንደምንለው የዴስቲኒ ኢትዮጵያ አባላት የሄዱበት መንገድ ለዚህ ጥሩ አብነት ነው ።
ሆኖም ስለ ሰላምና ስለ ይቅርታ መነጋገር የራሱ የሆነ ሂደትና ቅደም ተከተል እንዳለው አበክሮ ማጤን ያሻል ።
እዚህ ላይ የሰላም ፣ የእርቅ ፣ የሽምግልና ዓላማ አቀፍ ረቡኒው እና በአሜሪካ በሀሪሰንበርግ በሚገኘው ኢስተርን መኖናይት ዩኒቨርሲቲ የዓለምአቀፍ ግልግልና ዕርቅ ፕሮፌሰር የሆኑት ፤ ሕዝቅያስ አሰፋ ፤ “ የሰላምና እርቅ ትርጉምና መንገዶች ፤ “ በሚለው መጽሐፋቸው ፤ ያነሷቸውን ቁም ነገሮች ፤ ሰላም ፣ ዕርቅ የራሱ መንገድ እና አካሄድ እንዳለው ያሳያሉ ።
“…ሰላም ለግጭቶች መነሻ የሆኑትን ልዩነቶች በሚገባ ከለየና ከመረመረ በኋላ ልዩነቶችን ለፈጠሩት ችግሮች ሁሉን ወገኖች የሚበጁ መፍትሔዎች መፈለግ ማለት ነው ። …፤ “ ገፅ 26 _ 33 ፤ ሲሉ ሰላምን ይበይኑታል ።
ቲጂ ፕረስ, [7/9/2022 3:01 AM]
[Forwarded from ሞሼ ዳያን]
ሰላም ግጭትን ማስወገድ አይደለም ። በኢሕአዴግ እንደሆነው በደህንነት ፣ በፀጥታ ኃይሉና በካንጋሮ ፍርድ ቤቶች ግጭትን ማስወገድ ይቻል ይሆናል እውነተኛውን ሰላም ግን አያረጋግጥም ። የአስቸኳይ ጊዜ አውጆ ግጭትን ተቃውሞን ፀጥ ለጥ ማድረግ ይቻል ይሆናል ዘላቂ ሰላምን ግን ማስፈን አይቻልም ። ለዚህ ነው ፕሮፌሰር ሰላም ለግጭቶች መነሻ የሆኑትን መርምሮ ለሁሉም ወገኖች የሚበጅ መፍትሔ መፈለግ ነው ያሉት ። አሁን በሀገራችን የሚከሰቱ ግጭቶች ከዚህ አንጻር ማየትን ይጠይቃል። ፕሮፌሰር ከላይ በጠቀስሁት መጽሐፋቸው የሰላም ሥራ የራሱ እሴቶችና መርሆዎች እንዳሉት ያመላክታሉ ።
ሀ. መሠረታዊ የግጭት መንስኤዎችን መርምሮ የአመለካከት አድማስን ማስፋት ፤
ለ. ፍትሕ፦ዘላቂ ሰላም ያለፍትሕ ሊገኝ አይችልም ። ማኅበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካው ፍትሕ ባልተረጋገጠበት ሰላምን ማምጣት አይቻልም ። ለዚህ ነው የለውጥ ኃይሉ ተቋማት ላይ እየሠራ ያለው ።
ሐ. መግባባት ፦ፕሮፌሰር መግባባትን ሲበይኑት ፤ አንዱ ሌላው ውስጥ ሲገባና ሌላውም መጀመሪያው ውስጥ ሲገባ ነው ይላሉ ፤ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ መግባባትን መፍጠር የማዕዘን ድንጋይ ነው ። በግጭቶች ተሳታፊ በሆኑ ኃይላት መካከል መግባባትን ለመፍጠር ደግሞ ፤ መጀመሪያ የግጭቱ አካላት ፣ የሚጋጩባቸው ምክንያቶች እና መፍትሔዎች ላይ መግባባት ይጠይ ቃል ።
መ . የሕይወት መተሳሰር mutuality
ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የሰዎች ሕይወት የተሳሰረ መሆኑን በጥልቀት መገንዘብ ፣ መረዳት ይጠይቃል ። የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎቶች ተመሳሳይ ፣ ተቀራራቢ መሆናቸውን መገንዘብ ማለት ነው ። ሰው መከበርን ፣ መወደድን ፣ መደመጥን ፣ ከፍ ከፍ ማለትን እንደሚሻ ሁሉ በተቃራኒው ውርደትን ፣ መገፋትን ፣ መጠላትን ፣ መናቅን ፣ መቆርቆዝን ፣ …፤ ማስወገድ ነው ። ፕሮፌሰር ሕዝቅያስ በዚሁ መጽሐፋቸው ስለ እርቅ ምንነትና መሠረታዊ አላባውያን fundamental elements እንደሚከተለው ይተነትናሉ ።
“ እርቅ ማለት በከባድ ጠብና ይህም ባስከተለው መጎዳዳት ፣ ጥላቻና መፈራራት ምክንያት ተለያይተው ፣ ተራርቀው ፣ ተቆራርጠው የነበሩ ሰዎች የወደመውን የጋራ ኑሮአቸውን እንደገና ለመገንባት የሚጓዙበት ሂደት ነው ። እርቅ ጥልቅ የሰላም ግንባታ ዘዴና ዓላማ ነው ። የእርቅ ሂደት የሚከተሉትን እርምጃዎች ያካትታል ። “
፩ኛ . በግጭቱ ተካፋይ የነበሩ ወገኖች በሌላው ላይ የፈፀሙትን በደልና ጉዳት በሐቀኝነት ማመን ፤
፪ኛ . በተፈፀመው በደል እውነተኛ ፀፀትን መግለፅ ፤
፫ኛ . የተበደለውን አካል ከልብ ይቅርታ መጠየቅ ፤
፬ኛ . የተበደለው አካል ከልብ ይቅርታውን በመቀበል ይቅር ማለት ፤
፭ኛ . ተበዳዩን ጉዳት ከመድረሱ በፊት ወደ ነበረበት ሁኔታ መመለስ ፤
፮ኛ . በደሉ እንደገና እንደማይፈፀም አስተማማኝ የሆነ ማረጋገጫ መስጠት ፤
፯ኛ . ከግጭቱና ካስከተለው ጉዳት በመማር የሁለቱንም ወገኖች ጥልቅ ፍላጎትና ጥቅም የሚያራምድ ፣ የሚያጎላምስና የሚያስተሳስር አዳዲስ ግንኙነቶችን መመሥረትና ዕቅዶችን መንደፍ ፤
እንደ መውጫ
ሀገራዊ ምክክር ፣ የእርቅና እውነት የማፈላለግ ሥራ በተወሳ ቁጥር ደቡብ አፍሪካውያንንና የአፍሪካ ናሽናል ኮንግረስ /ኤ ኤን ሲ/ ቀድመው ወደ አእምሮአችን ይመ ጣሉ ። እንደ ሕዝብ የባርነት ፣የግፍ፣ የጭቆና፣ የዘረኝነትን ቀንበርን እንደ ደቡብ አፍሪካውያን የተሸከመ የለም ማለት ይቻላል ። በገዛ ሀገራቸው ሁለተኛ ፣ ሶስተኛ ዜጋ ሆነ ዋል። ተዋርደዋል ። ተግዘዋል ። ታስረዋል ። በጅምላ ተገድለ ዋል ። ከፖለቲካ ፓርቲ ደግሞ እንደ ደቡብ አፍሪ ካዎች ኤ ኤን ሲ ፣ ኮሚኒስት ፓርቲ ፣ ኢንዲያን ኮንግረስ ፣ አፍሪካን ፒውፕልስ ኦርጋናይዜሽን የተሳደደ ፣ የታደነ ፣ የተጋዘ ፣ የታሠረ ፣ የታፈነ ፣ የተሰቃየ የለም ማለት ይቻላል። ይሁንና በማዲባ እና በፓርቲው ኤ ኤን ሲ ፊታውራሪነት እውነትን አፈላልገው ይቅር መባባል ችለዋል ። እርቅን አውርደዋል ። እነሱ ይሄን ካደረጉ የእኛዎቹ ፓርቲዎች ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ካላቸው እርቅ ለማውረድ ምን ይሳናቸዋል ! ?
ኔልሰን ማንዴላ ዘረኛውን የአፓርታይድ የነጮች አምባገነናዊ አገዛዝ ሰለተቃወመ ብቻ የእድሜውን ሲሶ ያህል 27 ዓመታት በአንድ ጠባብ ጨለማ ክፍል ከከባድ የጉልበት ሥራ ጋር በስቃይ በእስር አሳለፈ ። ሆኖም ይቅርባይነቱን አላስቀረውም ። ይቅርባይነት በግለሰቦች ከፍ ሲልም በማኅበረሰቡ ባህላዊ እሴቶች ፣ ወረቶች ላይ የታነፀ መሠረት ነው ። በአንዳንድ ግለሰቦችና ማኅበረሰቦች ይቅርባይነት የማንነታቸው አካል ሲሆን በሌሎች ደግሞ ይቅርባይነት የተሸናፊነት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል ። ትህነግ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል ። ደቡብ አፍሪካውያን ፣ ሩዋንዳውያን ፣ ኬንያውያን ፣ ኮሎምቢያውያን እንደ ሕዝብ በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው ። ወደ ግለሰብ ስንመጣ ግን ከመደጋገም አልፎ እሰልሰዋለሁ እንደ ኔልሰን ማንዴላ አርዓያነት ያለው ሰው የለም ። ከዚያ ሁሉ እስር ፣ ስቃይና እንግልት በኋላ በአፓርታይድ ላይም ሆነ በነጭ ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ቂም አልያዘም ። “ ከ27 ዓመታት እስር በኋላ ተፈትቼ ነጻነቴን ለመቀዳጀት ወደ እስር ቤቱ መውጫ በር እየተቃረብሁ እያለ ጥላቻን ፣ ቂምን እስር ቤት ትቼው ካልወጣሁ ምኑን ከእስር ተፈታሁት ብዬ አሰብሁ ። “ ከሀገራችን ፖለቲከኞች የኢዜማው አንዷለም አራጌ ያን ሁሉ በደል በይቅርታ የተሻገረ ከአንደበቱ ጥላቻ ቂም በቀል የማይወጣ የትውልድ አርዓያ ነው ። ሁላችንም የአካል እስረኞች ባንሆንም የአስተሳሰብ እስረኞች ነን ማለት ይቻላል ። ጥላቻን ፣ ዘረኝነት ፣ ቂም በቀለን በአእምሮአችን ጓዳ ይዘን ስለምንዞር ። እንደ ማዲባ ትተነው ስላልወጣን ።
” Long Walk to Freedom “ (1995) በተሰኘው ድንቅ የራስ የሕይወት ታሪክ መጽሐፉ ፤ “ በሀገሬ መጀመሪያ እንታሰራለን ከዚያ ፕሬዚዳንት እንሆናለን ። “ ያለው ትንቢታዊ ንግግር በደቡብ አፍሪካ ሆኖ ለመመስከር በቅተናል ። የቀደሙት ፕሬዚዳንቶች ታቦ ኢምቤኪ ፣ ጃኮብ ዙማ ሆኑ ስልጣን ላይ ያሉት ስሪል ራማፎዛ ጊዜው ይለያይ እንጂ እስርን ቀምሰዋታል ። የእኛ “ መሪዎችም “ በአካላዊ እስር ባይሆንም በፍርሀት ቆፈንና በማንነት እስር ላይ ናቸውም ፣ አልፈውማል ። በቀጣዩ 7ኛ ብሔራዊ ምርጫ በተለይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አሸንፈው ወይም በጥምር መንግሥት የሚመሠርቱ ከሆነ ብዙዎቹ በእስር አልያም በስደት ያለፉ መሆናቸውን ልብ ይሏል ። ማዲባ እንዳለው ከመንፈሳዊም ሆነ አካላዊ ምርኮም ሆነ እስር በዘላቂነት ነጻ ለመውጣት ይቅር መባባል ያስፈልጋል ።
የኢዜማው አቶ የሽዋስ አሰፋ በebs “የቤተሰብ ጨዋታ” ላይ ከኦነጉ ኦቦ ቀጀላ መርዳሳ ጋር በአንድ ቤተሰብነት ቀርቦ በነበር ጊዜ ፤ “ ብዙዎች ፖለቲከኛ ሆነን የተወለድን ይመስላቸዋል ። “ ብሏል ። እንደ ተቀረው ሰው መዝናናት ፣ መሳቅ መጫወት እንደሚችሉ ለማሳየት። በነገራችን ላይ ኦነግም ፣ ኢዜማም ሆነ ብልፅግና ወይም አብን ዴስቲኒ ኢትዮጵያ በሶስት ዙሮች ባዘጋጀው የምክክር አውደ ጥናት ከመጠራጠርና ከመወነጃጀል ወጥተው መቀራረብ በመቻላቸው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት መክረውና ዘክረው “የምንፈልጋት ኢትዮጵያ በ2032 “ይዘው መጥተዋል ። እንግዲህ የእነ አቶ የሽዋስና ኦቦ ቀጀላ ቤተሰብነት የተጀመረው ከዚህ ነው ። ተቀራርበው መነጋገራቸው ያመጣውን ለውጥ አቶ የሽዋስ ስሜትን በሚነካ የዋህነት ለArts tv ሲናገር ፤ “ ከዚህ በኋላ እነ ኦቦ ቀጀላን ጉንፋን እንኳ እንዲይዛቸው አልፈልግም ። “ ነበር ያለው ። ማዲባ ከፍ ብዬ በጠቀስሁት ተወዳጅ መጽሐፉ ሁሉም ጥላቻን ተምሮት እንጂ ከእናቱ ማህፀን ይዞት የተወለደ የለም ። ጥላቻን የተማረ አእምሮ ደግሞ ፍቅርንና እርቅን መማር አይቸግረውም እንዳለው የፖለቲካ ፓርቲዎቻችንም ምንም እንኳ በስተእርጅና ቢሆንም የይቅርታን አቡጊዳ መቁጠር አይከብዳቸውም ብለን እናምናለን ።
ፈጣሪ ለእውነተኛ ሀገራዊ ምክክር ፣ እርቅና ይቅርባይነት ያብቃን !!!
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ን 2014 ዓ.ም