የዘመናችንን ቅድመ መደበኛ ትምህርት ጨርሰን (ሀ…ሁ እና ኤ.ቢ.ሲ.ዲ ቆጥረን)፣ አንደኛ ክፍል ተብለን የመጀመሪያ ደረጃ መደበኛ አስኳላ ትምህርታችንን “ሀ” ብለን በጀመርንበት የልጅነት ጊዜያችን “ልጅነቴ ልጅነቴ ማርና ወተቴ” ከሚለው የመዝሙርና ሙዚቃ ክፍለ ጊዜ ትምህርታችን ጎን ለጎን አስተማሪዎቻችን የተለያዩ ቁም ነገር ያላቸው የግብረ ገብ ሞራል ዕውቀቶችንም በተረት መልክ እያዝናኑ ያስተምሩን ነበር።የነዚህ ልዩ ልዩ ይዘት ያላቸው የግብረ ገብ ትምህርቶች የመምህራን ማስተማሪያ መጽሐፍ(Teachers’ Guide Book) “ታሪክና ምሳሌ” የተባሉ ትልልቅ መልዕክትን የተሸከሙ የክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ትንንሽ መጽሐፎች መሆናቸውን አስታውሳለሁ።
በእነዚህ መጽሐፎች ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ዘመን አይሽሬ ታሪኮችና የሞራል ዕውቀቶች በግጥም የተጻፉ ናቸው።ታሪኮቹ በግጥም ይቀርቡና መጨረሻ ላይ ደግሞ “የሞራል ትምህርት” በሚል የታሪኩ አንኳር መልዕክት በአጭሩ በአንድ ወይንም በሁለት ዓረፍተ ነገር ተጨምቆ ይቀመጣል። የተጻፈበት ስልት ግጥም መሆኑ በእርግጥም ልጆችን እያዝናኑ ለሕይወታቸው የሚበጃቸውን ቁም ነገር ለማስጨበጥ በማስተማሪያነት መመረጣቸው የዚያኔዎቹ መምህራን ትክክለኛ የትውልድ ቀራጺ፣ እውነተኛ የቀለም አባቶች መሆናቸውን ያመላክታል፡፡
እውነተኛዎቹ የቀለም አባቶቸ ካሳወቁኝ እውነተኛ እውቀቶች መካከል አንደኛው መልካም ያደረጉ ሰዎችን አለማመስገን ንፉግነት፣ ንፉግነት ደግሞ የመስጠትና የደግነት ተቃራኒ በመሆኑ በራሳችንና በሌሎች ሰዎች ላይ የደግነት እጥረት እንዲኖር የሚያደርግ አጥፊ ጠባይ መሆኑን ነውና ሳላመሰግናቸውና ሳላደንቃቸው ባልፍ ጥፋት ነውና አመሰግናቸዋለሁ። ታዲያ ከክቡር ዶክተር ከበደ ሚካኤል ታሪክና ምሳሌ መጽሐፎች ወስደው አዋቂዎቹ መምህራኖች በልጅነቴ ካስተማሩኝ የማልረሳቸው ታሪኮች ውስጥ አንደኛው “የብረት ድስትና የሸክላ ድስት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ ነበር። ይህም በግጥም የተተረከ ታሪክ ሲሆን ሸክላ ድስት ከብረት ድስት ጋር የመሠረተውን ጓደኝነትና ውጤቱን የሚገልጽ ነው።የታሪኩ ዋነኛ ነጥብና ማስተላለፍ የሚፈልገው የሞራል ወይንም የግብረ ገብ መልዕክትም ሰዎች ጓደኞቻቸውን ሲመርጡ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸውና ከእነርሱ ጋር በባህሪይና በስብዕና የማይገጥም ያለአቻ ጓደኛና ጓደኝነት ሊያስከትል የሚችለውን ራስን እስከማጣት ሊደርስ የሚችል ከፍተኛ ጉዳት ነው፡፡
የረጅም ዘመን ወዳጃችንና ጎረቤታችን ሱዳን በአሁኑ ሰዓት እየተከተለችው ያለችው የጓደኝነትና የወዳጅነት መንገድ በልጅነቴ የተማርኩትን የሸክላ ድስትና የብረት ድስት ታሪክ ያስታውሰኛል። ይህን ያልኩበትን ምክንያት ቀጥዬ ላብራራ።እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ እና ጎረቤት አገር ሱዳን የረጅም ዘመን የአገርነትና የአገረ መንግሥትነት ታሪክ ያላቸው፤ የተጠቃሽ ጥንታዊ ስልጣኔዎች ባለቤቶች የሆኑ ቀደምት አገራት ናቸው።ሠፊ ቦታን ከሚሸፍን የጋራ ድንበር ከመጋራትና ከተፈጥሯዊ ትስስርና መልክዓ ምድራዊ ጉርብትና በአሻገር አገራቱ ከአንድ ሐረግ የሚመዘዝ በደምና በእትብት የተሳሰረ የሥጋ ዝምድና ያላቸው ወንድምና እህትማማቾችም ናቸው።
በረጅሙ የአገረ መንግሥት ታሪካቸው ውስጥም በተናጠል ብቻ ሳይሆን በወል የሚጋሯቸው ታሪኮቻቸውም ከሌሎች ከማናቸውም ወዳጅና ጎረቤት አገራት በላይ እጅጉን ብዙ ናቸው። የአንዳቸው ለአንዳቸው ወካይ ሆነው ሊቀርቡ እስከሚችሉ ድረስ እጅጉን የተሰናሰሉና የተዋሃዱ ተመሳሳይ ማንነት፣ ባህልና የጋራ ታሪኮችን መገንባት የቻሉ ከአንድ ወንዝ የተቀዱ፣ ከአንድ ወንዝ የሚጠጡ ዘመዳሞችም፣ ጎረቤታሞችም ናቸው።እናም ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያና ሱዳን በረጅሙ የአገርነትና የመንግሥትነት ታሪካቸውና የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ሁሉም አልጋ በአልጋ ነው ማለት ባይቻልም አብዛኛውን ዘመናቸውን ግን ከልዩነት በላይ በአንድነት፤ ከፉክክር ይልቅ በትብብር ያሳለፉ መሆናቸውን ከታሪካቸው መረዳት ይቻላል፡፡
በተለይም እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1900 መባቻ ጀምሮ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ለመቀራመት መጡት የአውሮፓ ኢምፔሪያሊስቶች ጥለውት በሄዱት ተንኮል አዘል የድንበር ማካለል ሥራ የተነሳ የእኛና የታሪካዊቷን ዘመዳም ጎረቤታችን ሱዳንን ጨምሮ የመላው የአህጉራችን አገራት የእርስ በእርስ ግንኙነትና መልካም ጉርብትና ጥላ አጥልቶበት ቀርቷል። በዚህ ላይ ደግሞ በዓባይ ውኃ ላይ “ከእኔ ውጪ ማንም ተጠቃሚ ሊሆን አይገባም” በሚለው የቅኝ ገዥዎች ኢምፔሪያሊስታዊ የአስተሳሰብ ሌጋሲ የምትመራው አፍሪካዊቷ ምዕራባዊት ግብፅ የጥቅም ተጋሪዎቿን የማናከስና በጠላት ዓይን እንዲተያዩ የማድረግ የውጭ ፖሊሲ ታክሎበት ከጎረቤታችን ሱዳን ጋር ያለን መልካም ዝምድናና ግንኙነት የቀደመ ታሪካችንን በማይመጥን መንገድ በተደጋጋሚ በግጭትና በአምባጓሮ ሲፈተን ቆይቷል።
አሁን ላይ ደግሞ ከውስጣችን የበቀለውና በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የገዛ እናቱን ኢትዮጵያን ለማፍረስ ለግማሽ ምዕተ ዓመታት ያለእረፍት እየታተረ የሚገኘው ከሃዲውና አሸባሪው ሕወሓት ከግብጽና ከሌሎች የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋራ አብሮ ከሱዳን ጋር የፈጠረው ያለአቻ ጓደኝነት ተጨምሮበት ከሱዳን ጋር ያለን ታሪካዊ መልካም ግንኙነት ከምንጊዜውም በላይ እንዲሻክር ምክንያት ሆኗል።ነገሩን በውል ያስተዋሉ እውነተኛ የአፍሪካ ልጆች ሁሉ የሚመሰክሩትም ይህንኑ ነው።ታዋቂዋ ሱዳናዊት ጋዜጠኛ ሱሀይር አብዱራህማን አንዷ ናት።
ሱሀይር “ሱዳን እንደ አገር ጉርብትናዋም ይሁን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷ ከኢትዮጵያ ጋር እንጂ ከትንሿ ትግራይ ክልል ጋር አይደለም” ትላለች።ይህ የሆነበት ምክንያት አብዛኞቹ የሱዳን ጀነራሎች ከሕወሓት ጋር በነበራቸው ሕገወጥ የመሣሪያና የኮንትሮባንድ ንግድ ምክንያት መሆኑንም ጋዜጠኛዋ ትጠቁማለች።“ግብፅን ጨምሮ ምዕራባውያን የፈለጉት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን ማንሳት እንጂ ኢትዮጵያ እንዴት ትሁን የሚል አቋም የላቸውም” ትላለች።የአንድን አገር መንግሥት በጉልበት ከስልጣን ለማስነሳት ይሄንን ሁሉ ዙሪያ ጥምጥም የተሄደበት ምክንያት የናይል ፖለቲካ ከእየሩሳሌም መስጊድና የፍልስጤሞች አገር አለመሆንና ታሪክ ሆኖ መቀረትን የያዘ እረጅም ታሪክ ያለው መሆኑንም ትናገራለች።
ጋዜጠኛዋ አሁን ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት የገጠመው ቡድን (ሕወሓት) እኛ ታግለን ከጣልነው የበሽር ኡመር ዘራፊ ቡድን በላይ ኢትዮጵያን ሲዘርፍና አሸባሪዎችን እየረዳ ለምዕራባውያን የተዳከመች አፍሪካን ለማቅረብ ሲሠራ የኖረ መሆኑንም ታመላክታለች። ሱሀይር አልፎ አልፎ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ስላለው ውጊያ ከጋዜጠኛ ካሊድ ሙሳ ጥያቄ ቀርቦላት በሰጠችው መልስ ላይ “በስደተኝነት ስም የመጡት አብዛኞቹ የትግራይና የቤኒሻንጉል ተወላጆች ወደሱዳን የገቡት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በተደረገው ስምምነት እንጂ በጦርነቱ ምክንያት ጦርነቱን ሽሽተው አይደለም” ትላለች፡፡
በስደተኞች ስም ወደ ሱዳን ገብተው ወታደራዊ ስልጠና እንዲሰለጥኑ ገና ከጦርነቱ በፊት ሕወሓትና የሱዳን ጀኔራሎች የግብፅ ደህነንቶች ስምምነት አድርገዋል።ጦርነቱ እንደተጀመረ ወደ ሱዳን ገብተው ስልጠና ከጨረሱ በኋላ ወደኢትዮጵያ ለመግባት ሲሞክሩ ከኢትዮጵያ መከላከያ በኩል ወደ ሱዳን ድንበር ጥቃት ያደርጋሉ ይህም ጦርነቱን የሚደግፉ የሱዳን ጀኔራሎች መኖራቸው ነው ብላለች። ከወራት በፊት ከአል አለሚ ሚዲያ ጋር ባደረገችው ቃለ መጠይቅ ሱዳናዊቷ ጋዜጠኛ፣ አሁን ያለው ባደረገችው ሰፊ ቃለ ምልልስ፤ “አሁን ያለው የሱዳን መንግሥት የወደፊቱን የኢትዮጵያና የሱዳንን ግንኙነት ወደቂም በቀል ሊቀይረው እየተንደረደረ ነው” ስትልም አስጠንቅቃ ነበር።
ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ በተመለከተ ሱዳን በድንበር አካባቢ የምታካሂደው የኃይል ጥቃትና ትንኮሳም የሱዳን ሕዝብ ፍላጎት አለመሆኑንና የሱዳን መንግሥት እያካሄደ ያለው የግል ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የዲፕሎማሲ ሥራ ኢትዮጵያና ሱዳንን ወደፊት ከጉርብት ሊለያይ እንደሚችል የሱዳንን መንግሥት አስጠንቅ ቃለች፡፡
እኛም ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚመሠረት ጓደኝነት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንም ለአፍሪካም የማይበጅና ጥፋትንም የሚያስከትል ነውና ታሪካዊ ዘመዳችንና ጎረቤታችን ሱዳን ከሕወሓት፣ ከግብጽና ከሌሎችም የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የሚደረግ እንዲህ ዓይነቱን “ያለአቻ ጓደኝነት” እንድታቆም ዘመንን በተሻገረው በታሪካዊው በመልካሙ ጓደኝነታችን ስም እንጠይቃለን።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ን 2014 ዓ.ም