አዲስ አበባ ከተማ ከንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት አኳያ ክፍተት ይስተዋልባታል። የከተማ አስተዳደሩ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ግድቦችን በመገንባትና በማስፋፋት፣ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች አያሌ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር የነዋሪዎችን የውሃ ጥያቄ ለመመለስ ጥረት ቢያደርግም፣ ፍላጎቱን ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት አልቻለም። በከተማዋ አብዛኞቹ አካባቢዎች የሚታየው ውሃ በፈረቃ ማዳረስ ሥራም የሚያመለክተው ይህንኑ ነው።
የባለሥልጣኑ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ ከከተማዋ ወረዳዎች ስድስቱ ብቻ ናቸው 24 ሰአት ውሃ የሚያገኙት። የተቀሩት በፈረቃ ውሃ የሚያገኙ ናቸው። ከአስር እስከ አስራ አምስት ቀን ውሃ የሚጠብቁ አካባቢዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ደግሞ ውሃ የሌላቸው መሆናቸውን ነው።
ውሃ በማይመጣበት ጊዜ ላለመቸገር ውሃ በጀሪካን፣ በበርሜል፣ በሮቶ ማጠራቀም የግድ ነው። ሳይደግስ አይጣልም እንዲሉ ዘይት ይዞ ሀገራችን የገባው ቢጫ ጀሪካን ለውሃ ቀጂዎችና ሻጮች እንዲሁም አጠራቃሚዎች ባለውለታ ሆኗል። ጀሪካኑ በብዛት ለውሃ መቅዳት የተሰለፈበት፣ በመሀል ከተማዋ ጭምር በጋሪ በብዛት ተጭኖ የሚታይበት ሁኔታም የችግሩን አሳሳቢነት ይጠቁማል። ጀረኪና፣ በርሜል፣ ሮቶ አምራችና ሻጮች ገበያ ደርቶላቸዋል። ውሃ በጀሪካን በውሃ ቦቴ መሸጥ እንጀራ ሆኗል። ባለሃያ ሊትር አንድ ጀሪካን ውሃ ከሃያ ብር በላይ እየተሸጠ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ አርጋው በቅርቡ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ባለሥልጣኑ የውሃ ቆጣሪ የተገጠመላቸው 600 ሺ ደንበኞች አሉት። ንጹህ ውሃ የሚጠይቁ የመሀል ከተማዋ ነዋሪዎች የቆጣሪ ጥያቄ እየቀነሰ ቢመጣም፣ በጋራ መኖሪያ ቤቶችና ማስፋፋያ አካባቢዎች ግን ፍላጎቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በከተማዋ በየአመቱ ከ10 ሺ እስከ 15 ሺ የውሃ ቆጣሪዎች ይቀጠላሉ፤ የሪል ስቱቶችም የዚሁ ተጠቃሚዎች ናቸው። 24 ሰአት ውሃ የሚያገኙት ስድስት ወረዳዎች ብቻ ናቸው።
የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለሥልጣን በቅርቡ አንድ ግዙፍ የውሃ ፕሮጀክት አስመርቋል፤ ይህም በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች ይታይ የነበረውን የውሃ እጥረት በተወሰኑ መልኩ ለማቃለል እንደሚያስችል ታምኖበታል።
ይህ የለገዳዲ ክፍል ሁለት የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክት ባለፈው እሁድ በተመረቀበት ወቅት የባለሥልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዘነበ አባተ እንዳሉት፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በአሁኑ ወቅት ከሶስት ግድቦችና በተለያዩ ቦታዎች ከተቆፈሩ ከሁለት መቶ በላይ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች በቀን 674 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ ያመርታል። በከተማዋ ከ8ሺ 255 ኪሎ ሜትር በላይ የውሃ ማስተላለፊያና ማሰራጫ መስመሮችን በመዘርጋት በ51 ጣቢያዎች በተተከሉ 151 የግፊት መስጫ ፓምፓች በመጠቀም አገልገሎቱን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ነው።
የከተማዋ ወደ ጎንም ሆነ ወደ ላይ እጅግ በፈጠነ መልኩ መስፋፋት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፤ የሆቴሎች፣ የዩኒቨርሲቲዎችና ሆስፒታሎች እየተበራከቱ መምጣት፤ ውሃን እንደ ግብአት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች፣ በከተማዋ እዚህም እዚያም የሚገነቡ ህንጻዎችና የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች በአጠቃላይ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤው ከፍ ያለ የውሃ ፍላጎት እንዲኖር መጠየቃቸው በገሀድ የሚታይ ሀቅ ነው። ስርጭቱን ፍትሃዊ ለማድረግ ሲባል ባለሥልጣኑ ውሃ በፈረቃ ለማደል ተገድዶ እየሰራ ይገኛል።
ባለሥልጣኑ የከተማዋን የውሃ ፍላጎት ለመመለስ ይቻል ዘንድ የአጭር፣ የመካከለኛ እና የረጅም ጊዜ አቅዶችን አውጥቶ እየሰራ እንደሚገኝም ዋና ስራ አስኪያጁ ጠቅሰው፣ በአጭር ጊዜ ለሕብረተሰቡ ለማድረስ ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከል ባለፈው እሁድ የተመረቀው የለገዳዲ ክፍል ሁለት የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክትና በከተማዋና በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን የተገነቡ የውሃ ጉድጓዶች ተጠቃሾች መሆናቸውን ያብራራሉ።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ማብራሪያ፤ የለገዳዲ ክፍል ሁለት የጥልቅ ውሃ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን በበረክ ወረዳ በተለያዩ አካባቢዎች በተቆፈሩ 16 ጥልቅ ጉድጓዶች በቀን 86 ሺ ሜትር ኩብ ውሃ ማምረት ያስችላል። ፕሮጀክቱ የባለሥልጣኑን በቀን ውሃ የማምረት አቅም ከ674 ሺ ወደ 760 ሺ አሳድጎታል።
ፕሮጀክቱ ባለሥልጣኑ እስከ አሁን ካለማቸው ፕሮጀክቶች ትልቁ ነው። ከ860 ሺ በላይ የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል። ለየካና ጉለሌ ክፍለ ከተማ የሚያገለግል ሲሆን፣ ለእነዚህ አካባቢዎች ከለገዳዲ ግድብ ይገፋ የነበረውን ውሃ ወደ ሌሎች አካባቢዎች በመውሰድም የውሃ እጥረትን ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አቅም ሊሆን ይችላል።
በ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የመንግሥት በጀት የተገነባ ሲሆን፣ ከሁለት ሺ እስከ አምስት ሺ ሜትር ኩብ ውሃ መያዝ የሚችሉ 10 የውሃ ማጠራቀሚያ ጋኖችም ተገንብተውለታል። ከ200 እስከ 800 ሚሊ ሜትር ዳያሜትር ስፋት ያላቸው 185 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመሮች፣ ሁለት የግፊት መስጫ ጣቢያ እና የ38 ኪሎ ሜትር የመዳረሻ መንገድ ግንባታዎች ተካሂደውለታል።
የአዲስ አበባ ከተማ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ውሃ የሚያገኘው ከኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ነው ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲቻል ውሃው የተገኘባቸውን የዚሁ ዞን አካባቢዎች ማሕበረሰብም ንጹህ ውሃና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገኙም ያስቻለ መሆኑን ይገልጻሉ።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ፤ በዚህ ሶስት ዓመት ውሰጥ በልዩ ዞኑ ለሚገኙ ወረዳዎችና የገጠር ቀበሌዎች 30 ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክቶችን እና 37 ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችን ባለሥልጣኑ ገንብቷል። 105 ኪሎ ሜትር ለውሃና ለሕብረተሰቡ መዳረሻ የሚሆን መንገድ ተሰርቷል፣ ዘጠኝ የአቃቂ ቀበሌዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው።
ከዚህ ጎን ለጎን ከገጸምድር ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በልማት ተጽእኖ ለሚደርስባቸው ለወልመራና ሱሉልታ ወረዳዎች ሁለት ዘመናዊ ጤና ጣቢያዎች፣ ሶስት ትምህርት ቤቶች፣ አምስት የእንስሳት ክሊኒኮችና ሌሎች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው።
ኢንጂነሩ የውሃ መሰረተ ልማቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥና ረጅም አገልግሎት አንዲሰጥ ለማድረግ የጥገናና የኦፕሬሽን ስራ የእለት ተእለት ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፣ ሥራው ከፍተኛ በጀትና ብቁ ባለሙያ የሚጠይቅ ስለመሆኑም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል። ባለሥልጣኑ ለውሃ ኦፕሬሽንና ጥገና ሥራ ብቻ በቀን አስከ ሶስት ሚሊዮን ብር እያወጣ መሆኑን፣ የኦፕሬሽንና ጥገና አቅሙን ለማሳደግ፣ የውሃ ስርጭት ሥርዓትን ለማዘመን የሚያስቸል የሀይድሮሊክ ሞዴሊንግ ሥራ እያጠናቀቀ መሆኑን ያብራራሉ።
የለገዳዲና የድሬ ግድቦችን የጥገና ሥራ ጨምሮ በአጠቃላይ ከዓለም ባንክ በተገኘ 40 ሚሊዮን ዶላር ብድር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። እነዚህ ፕሮጅክቶች ሲጠናቀቁ ለባለሥልጣኑ ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ እምነቱ እንዳላቸውም ነው የተናገሩት።
እንደ ዋና ስራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ ከፍተኛ የውሃ ችግር አለባቸው ተብለው ለሚታወቁት በከተማዋ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ለሚገኙት አካባቢዎች የሚደረገውን የውሃ አቅርቦት አቅም ያሳድጋል። በተለይ በየካ ክፍለ ከተማ ከፍተኛ የውሃ ችግር ይታያል። ፕሮጀክቱ የካ ላይ በሁለት ሳምንት አንዴ በአስር ቀን አንዴ የሚያገኙትን ነዋሪዎች ችግር ይፈታል። በአስራ አምስት ቀን አንዴ ውሃ የሚያገኙ የጉለሌ ክፍለ ከተማ አካባቢዎችም አሉ። የዚህን ክፍለ ከተማ የውሃ አቅርቦትንም ያሳድጋል። ከለገዳዲ ወደ ጉለሌና የካ የሚገፋውን ውሃ ደግሞ ወደ መሀል ከተማና ቦሌ አራብሳ መግፋት የሚያስችል በመሆኑም አዎንታዊ ተጽኦኖው ከፍተኛ ነው።
ያም ሆኖ ግን ከተማዋ በስፋት እና በፍጥነት እያደገች እንደመሆኗ ችግሩን ግን ከመሰረቱ ሊፈታ አይችልም ያሉት ዋና ስራ አስኪያጁ፣ በቀጣይ የከተማዋን ውሃ ፍላጎት ለማሳካት እንደሚሰራም ነው ያረጋገጡት። የአስር አመቱን መሪ እቅድ ጠቅሰውም ከከርሰ ምድር የውሃ ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን ሌሎች የገጸ ምድር ውሃ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
የውሃ ፕሮጀክቱን መርቀው የከፈቱት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአንኳን ደስ አላችሁ ነው ንግግራቸውን የጀመሩት። ከንቲባዋ በለገዳዲ ቁጥር ሁለት የጥልቅ ውሃ ፕሮጀክት የተቀዳጀነው ድል ትርጉሙ ብዙ ነው ይላሉ።
ፕሮጀክቱ በአንድ በኩል በንጹህ መጠጥ ውሃ እጥረት የሚሰቃየውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ችግር የሚያቃልል መሆኑን ጠቅሰው፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ ፕሮጀክቱ በሚለማበት አካባቢ የሚኖር ሕብረተሰብ ውሃ ሰጥቶ ውሃ እንዲጠማው የሚያደርግ አለመሆኑንና የጋራ ተጠቃሚነት የተጠበቀበት መሆኑንም ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የፕሮጀክት ታሪክ በራስ አቅም በራስ ወጪ ይህን የሚያህል ፕሮጀከት ስንገነባ በታሪካችን የመጀመሪያ ነው ያሉት ከንቲባዋ፣ ጥቅሙን እጅግ በጣም ትልቅ የሚያደርገው ደግሞ ያለምንም የገንዘብ ጭማሪ፣ የዋጋ ለውጥ በተያዘለት አቅድ እንዲያውም ከተያዘለት የእቅድ ጊዜ ቀድሞ በመጠናቀቁ መሆኑን አብራርተዋል።
ከንቲባዋ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ክልል አጎራባች ሕዝቦች አንዱ ያለሌላው መኖር እንደማይችሉ ተናግረው፣ የልማት ስራዎችን ስንሰራ አብሮ መልማትን የጋራ ተጠቃሚነትን ታሳቢ በማድረግ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
እንደ ከንቲባዋ ገለጻ፤ የአዲስ አበባ ከተማ ከ85 እጅ በላይ የሚሆነውን የውሃ አቅርቦት የሚያገኘው በዙሪያው ከሚገኘው የኦሮሚያ ልዩ ዞን አካባቢዎች ነው፤ በአንጻሩ የሚወገደውም ፍሳሽ ወደዚሁ አካባቢ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ይደርስ የነበረውን ጉዳት በመቀነስ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዲገነቡ መደረጉም የዚሁ መሰረታዊ እሳቤ ውጤት ነው።
በዚህ አግባብ እየተሻሻለ በመጣው ግንኙነታችን የለገዳዲ ክፍል ሁለት የጥልቅ ውሃ ጉድጓድ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ፣ የገርቢ የድሬ የሲቪሉ የውሃ ፕሮጀክትንም በአጋርነት በትብብር መንፈስ ለሚቀጥለው ግንባታ እውን መሆን ዝግጁ ተደርገዋል ሲሉ እሳቸውም ቀጣዩን የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ ጠቁመዋል ።
የአዲስ አበባን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት የምናደርገውን ጥረት አጠናክረን የምንቀጥለው እንደዚህ አይነቱን ሰፊ ኢንቨስትመንት፣ ቴክኖሎጂና እውቀትን የሚጠይቁ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር የውሃ ፕሮጀክቶችን በማስፋትና የጋራ ርብርብ በማድረግ ነው ብለዋል።
ይህ ፕሮጀክት የታቀደው ለሶስት አመት ቢሆንም በሁለት አመት መጨረስ ተችሏል። ለይስሙላም ሳይሆን የጀመርነውን እንጨርሳለን የሚለውን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ቃል በተግባር እንዲሉ የጀመርነውን ፕሮጀክት በውጤታማነት በተያዘለት ጊዜ መጨረስ ችለናል ሲሉ ተናግረዋል። ፕሮጀክቱ በፍጥነቱም ሆነ በግዝፈቱ በአይነቱ አዲስ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ብዙ ልምድ አግኝቶበታል፤ ብቃቱንም አሳይቶበታል ይላሉ።
‹‹ከንቲባዋ፤ ፕሮጀክቱ በፈተና ወቅት የተሰራ ነው፤ ከዚህ ፕሮጀክት የምንማረው ትልቅ ነገር ፈተና እንደማያስቆመን ይልቁንም ተጠናክረን ብርቱ መስፈንጠሪያ አድርገን የምንጠቀምበት መሆኑን ነው›› ሲሉ ገልጸው፣ ጠንክረን ከሰራን የሕዝባችንን ችግር መቅረፍ አንችላለን›› ብለዋል።
በትናንት ስንቅነት በዛሬ አቅምነት በነገ አሻግሮ ተመልካችነት እንጓዛለን ያሉት ከንቲባዋ፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነታችንን የሚያረጋግጡትን እነዚህንና የጋራ ሀብታችን የሆኑትን የተገነቡ ፕሮጀክቶችን ሁሉ በጋራ ከተንከባከብንና በጋራ ከተጠቀምንባቸው ለትውልድም ማሸጋገር እንችላለን ሲሉም አስገንዝበዋል።
ከንቲባዋ ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ እንዳሉት፤ ፕሮጀክቱ ብዙ ፋይዳ አለው፤ አንደኛ የአዲስ አበባን የውሃ ሽፋን ማሳደግ ያስችላል። ከመሰረቱ የሁሉንም የከተማዋን አካባቢዎች የውሃ ችግር ይፈታል ባይባልም በተለይ የየካና የጉለሌ ከፍለ ከተማዎችን ከ800 ሺ በላይ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።
ብዙ ቴክኖሎጂዎች ስራ ላይ የዋሉበት፣ ለረጅም ጊዜ እንዲያገልግል ተደርጎ በጥራት የተገነባ የውሃ ፕሮጀክት መሆኑንም ተናግረው፣ በዚህ ሀገር ፈተናና ጦርነት ውስጥ በቆየችበት ጊዜ በራስ በጀት ይህን ያህል ፕሮጀክት በተባለው ጊዜ ገንብቶ ማቅረብ ፕሮጀክቱን ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል።
መንግሥት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየሰራ ነው፤ የአንድነት፣ የእንጦጦና የወዳጅነት ፓርኮችን በተያዘላቸው ጊዜ በማጠናቀቅ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ እንደሚቻል አሳይቷል፤ ይህ የመንግሥት ቁርጠኝነት የመንግሥት ቤቶች ኮርፖሬሽን በገርጂ በገነባው የመኖሪያ መንደርም ተደግሟል። ይህንን የውሃ ፕሮጀከትም በተያዘለት በጀት፣ ከተያዘለት የጊዜ ሰሌዳም አስቀድሞ በማጠናቀቅ የመንግሥት የፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ ሌላው ማሳያ ነው ማለት ይቻላል።
ኃይሉ ሣህለድንግል
አዲስ ዘመን ሐምሌ 2 ቀን 2014 ዓ.ም