አዲስ አበባ፡- በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢ፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ፤ የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1 የስኳር ፕሮጀክት በአፋጠኝ ለአዲስ ተቋራጭ እንዲተላለፍና የግንባታው ሂደት እንዲፋጠን አሳሰበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው አንድ ቡድን ወደ ኦሞ ኩራዝ ቁጥር 1፣3 እና 5 ስኳር ፋብሪካዎች በመላክ ያደረገው የመስክ ምልከታ ሪፖርት ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡
የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ ከመጀመሪያው ተቋራጭ ጋር የነበረው ውል ከወራት በፊት እንዲቋረጥ የተደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ከአዲስ ተቋራጭ ጋር የግንባታ ውል አለመታሰሩን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ከአዲስ ኮንትራክተር ጋር ውል ታስሮ ወደ ግንባታ ስራ ባለመገባቱ ፕሮጀክቱ በዕቅዱ መሰረት እንዳይጓዝ እያደረገ መሆኑን የጠቆመው ቋሚ ኮሚቴው ይህም ሀገሪቷ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንዳታገኝ እያደረጋት መሆኑን አብራርቷል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአዲስ ተቋራጭ ተላልፎ ግንባታው በእቅዱ መሰረት እንዲከናወን ሲልም አሳስቧል፡፡
የስኳር ኮርፖሬሽን ተጠባባቂ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ዋዮ ሮባ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፊት ከነበረው ኮንትራክተር ጋር የነበረውን ውል አቋርጦ ከአዲስ ኮንትራክተር ጋር ውል ለመፈረም አዳጋች በመሆኑ ሊጓተት ችሏል፡፡
የፋብሪካው ግንባታ ስራ ያለበት ሁኔታ ለማድረግ ጥናት ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ረጅም ጊዜ የወሰደ ጥናት ተደርጓል፡፡ በቀድሞው የፕሮጀክቱ ኮንትራክተር (በሜቴክ) ተገዝተው ሀገር ውስጥ የገቡ ዕቃዎች ሳይት መድረስና የዕቃው ጥራት የማረጋገጥ ስራ ብዙ ጊዜ ሊፈጅ ችሏል፡፡ የዲዛይን ችግር ያለባቸው ፕሮጀክቶችን የመለየት ስራም ሲሰራ ነበር፡፡ ከኦሞ ኩራዝ ቀድመው ለአዲስ ኮንትራክተር መተላለፍ የነበረባቸው ፕሮጀክቶችን ለአዲስ ኮንትራክተር የማስተላለፍ ስራ ሲሰራ ቆይቷል፡፡
እነዚህ ስራዎች ግማሽ አመት ወስደዋል፡፡ ከአዲስ ኮንትራክተር ጋር ውል ከመታሰሩ በፊት መከናወን የነበረባቸው ስራዎች ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን ተከናውነው መጠናቀቃቸውን የገለጹት አቶ ዋዮ፤ በቅርቡ ከአዲስ ኮንትራክተር ጋር ድርድር እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡
ድርድሩ ከአንድ ሳምንት በላይ እንደማይፈጅ በመግለጽ በሁለት ሳምንት ውስጥ ከአዲስ ኮንትራክተር ጋር ውል ይገባል ብለዋል፡፡ ለአዲስ ኮንትራክተር ከተሰጠ በኋላ ግንባታው በስድስት ወር ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለምለም ሀድጉ በበኩላቸው እንደተናገሩት ከቀድሞ ኮንትራክተር ወደ አዲስ ኮንትራክተር በማስተላለፍ ሂደት ብዙ ጊዜ መውሰዱ ሀገሪቷና ህዝቦቿ ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እንዳያገኙ አድርጓል፡፡
ህዝቡ ኦሞ ኩራዝ አንድን ጨምሮ ግንባታ ላይ ያሉ የስኳር ፕሮጀክቶች በአፋጣኝ ተጠናቀው የስኳር ፍላጎቱ እንዲሟላለት ይፈላጋል፡፡
ሀገሪቷም ስኳር ወደ ውጭ ሀገር ልካ ሚኒዛሬ ማግኘት ባትችል እንኳ ስኳር ከውጭ ሀገር ለማስገባት የምታወጣውን ሚኒዛሬ ማዳን ትፈልጋለች፡፡ በመሆኑም ግንባታ ላይ ያሉ ፋብሪካዎችን በአስቸኳይ ለማጠናቀቅ ርብርብ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
መላኩ ኤሮሴ