አዲስ አበባ፤ ‹‹ብርሀን ለሁሉም›› ብሄራዊ የኤሌክትሪፊክሽን ፕሮግራም በመተግበር ብርሃን ላልደረሳቸው 56 በመቶ የህብረተሰብ ክፍሎ በ2017 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ተፈጻሚ ለማድረግ 6 ቢሊዩን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገለጸ፡፡
የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ‹‹ብርሀን ለሁሉም›› ፕሮጀክት፤ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የሚገኝ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ አቅምን በማሰባሰብ አገራዊ የማስፈጸም አቅምን በማቀናጀት ሁሉንም ኢትዩጵያዊ ተጠቃሚ ማድረግ አላማው ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ለሁለተኛው ዙር ትግበራው፤ ለግሪድ ስራዎች ሶስት ነጥብ ሁለት ቢሊየን ውስጥ፤ ተጠቃሚው 35፣ መንግስት15፣ ልማት አጋሮችና አበዳሪዎች 50 በመቶ፤ ለኦፍ ግሪድ የሚያስፈልገው ሁለት ነጥብ አምስት ቢሊየን ውስጥ 40 በመንግስትና ተጠቃሚዎች ቀሪው ከልማትና አበዳሪ ተቋማት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
ለሶስት ቀናት የሚካሄደው የአካባቢያዊ ኢነርጂ ትብብር ጉባኤ ዛሬ በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲጀመር ሁለተኛው ዙር ‹‹ብርሀን ለሁሉም›› ብሄራዊ የኤሌክትሪፊክሽን ፕሮግራምም ይፋ ተደርጓል፡፡ በወቅቱ እንደተገለጸው፤ ኤሌክትሪክ ላልደረሳቸው 56 በመቶ ለሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ለማዳረስ ርብርብ ይደረጋል፡፡
በእስካሁን ትግበራ 44 በመቶ የህብረተሰብ ክፍሎችን ማዳረስ መቻሉን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ዜጎችን የዘመናዊ ኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግና ለሁሉም ኤሌክትሪክን ለማዳረስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ በመርሀ ግብሩ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጣቸውና ልዩ ትኩረትና ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይተገበራልም ብለዋል፡፡
ተጨማሪ የማመንጨት አቅም ለመገንባት የግሉን ዘርፍ በዘርፉ ለማሳተፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ስለሺ፤ የእንፋሎት፣ የሃይድሮ፣ የሶላርና የነፋስ ሃይል ማመንጫዎች በግል ዘርፍ እንደሚለሙ ተናግረዋል፡፡ የኔት ወርክ ይል ማስተላለፍ አቅም አሁንም በሚፈለገው ደረጃ እንዳልተፈታ በመጠቆምም፤ እያደገ ያለውን የሃይል ፍላጎት ለማሳካት ያልተቆራረጠና ጥራቱን የጠበቀ የሃይል አቅርቦት እንዲኖር የነባር የሃይል ትስስሩን የማስተላለፍ፣ የማከፋፈልና አቅም የማሳደግና የማሻሻል ስራዎች ስራዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በቴክኖሎጂ ዑደትና በዋጋ ቅናሽ ወዳዳሪነታቸው እየተሸሻለ የመጡ እንደ ጸሃይ ሃይል አማራጭ የሃይልና ታዳሽ ምንጮች በስፋት እንዲተገበሩ ይደረጋል፡፡ የሃይል ዘርፍ ግቦችን ለማሳካት ሃገራዊ የፋይናንስ፣ የቴክኖሎጂ ምርት፣ የተቋማትና የሰለጠነ የሰው ሃብት አቅምን በማጎልበት በቀጣይ ለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ከውጭ ባለሃብቶች ጋር ትብብር በማድረግ የአቅም ግንባታ ስራ ይጠናከራል፡፡
የኢትዩጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው፤ በቀጣይ የሶላር ሃይል በስፋት ጥቅም ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል፡፡ በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ የሶላር ሃይል ጥቅም ላይ ለማዋል 12 የሙከራ ስራዎች በትግበራ ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ በመጠቆም፤ የሶላር ቴክኖሎጂ ከጊዜ ጊዜ እያደገና እየሰፋ እንደመሆኑ በዓለም ገበያም ብቃት ያላቸው አምራቾች ምርታቸውን እያቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
‹‹ብርሃን ለሁሉ›› የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለሰፊው ህብረተሰብ ለማዳረስ የተደረሰበትን ውጤት በመገምገም ለተሻለ አፈጻጸምና ውጤታማነት የሚያበቃ ስልት በመቀየስ፤ እየተተገበረ ይገኛል፡፡ የመጀመሪያው መርሃ ግብርም ህዳር ወር 2010 ዓ.ም ይፋ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ዘላለም ግዛው