የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፣‹‹የአስተሳሰብ ልዩነት ፣ፉክክርና የሚጋጭ ፍላጎት (Conficting Interest) ባለባቸው አገራት ውስጥ ችግሮች በአንድ ፓርቲ ፣በአንድ ቡድን ወይንም በጥቂት ሰዎች አይፈቱም።ጥቂቶች በር ዘግተው ቢጨነቁና ቢጠበቡም መፍትሄ ሊሆኑና ሊያመጡም ፈፅሞ አይቻላቸውም። በመሆኑም ልዩነቶችን ለማጥበብ ሆነ ለማስታረቅ፣ ከተናጠል ይልቅ የጋራ ውይይት ባህልና ልምድ የግድ ነው››ይላሉ።
በተለይ በግሎባላይዜሽን ዘመን ከአግላይ Exclusive ይልቅ አሳታፊ Inclusive መሆን የግድ እንደሚልና አንደኛው ሌላውን ከሚያገል ጠባብ አስተሳሰብ ነፃ ወጥቶ‹‹የጋራ ውሳኔያችን ትክክል ነው፣አንድ ስንሆን እንጂ ስንለያይ በቀላሉ እንወድቃለን‹‹Divided we fail United we Stand››ወደ ሚል መርህ መምጣት እንደሚያስፈልግም ያሰምሩበታል።
ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተፈጠሩና ከዘመን ዘመን እየተሸጋገሩ የመጡ ያልተቋጩ ሃሳቦች፣በይደር የቆዩ አለመግባባቶች እንዲሁም አገር ትቀጥል ዘንድ ቅድሚያ ተነስቷቸው የቆዩ የማያግባቡ አጀንዳዎች የተሸከመች አገር ናት።አገሪቱ ልዩነቶችን በውይይት የመፍታት የአሳታፊነት ባህልና ልምድ የሌለባት መሆኑ ደግሞ ችግሮች በቀላሉ ፈጣን ምላሽ እንዳያገኙ፣ውስጥ ውስጡን እንዲብላሉና ከትላንት እስከ ዛሬ እንዲከተላት ምክንያት መሆኑ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል።
‹‹እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ሞቼ እገኛለሁ››እኔ የማስበው ሁሌም ትክክል ነው››የሚል የአመለካከትና የባህሪ ችግርም ረጅም ጊዜ ሲያደክም ከርሟል።‹‹ችግር ካለም እኛው የስርአቱ ባለቤቶች እንናገር እንጂ ሌላው ምን ቆርጦትና ምንስ አግብቶት ነው በስርአቱ ላይ ትችት የሚሰነዝረው?››የሚለው ከእኔ እና ከእኛ ውጭ ላሳር አመለካከትና ተግባርም ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን በሁሉ ረገድ ሊቀይሩ የሚችሉ የተለያዩ ገንቢ አስተያየቶችና መፍትሄዎች ሳይቀር ከስመው እንዲቀሩ ምክንያት ሲሆን ታይቷል።
ትላንትም ሆነ ዛሬ እየተመላለሰ የሚደቁሰንና አዙሪት ሆኖብን ወደፊት አላንቀሳቅስ ያለን ችግራችንን ተነጋግረንና ተወያይተን ፍቱን የሆነ መፍትሄ ማስቀመጥ አለመቻላችን ነው። አጀንዳችን መጋጨት እንጂ መግባባት አይደለም።ለውጥ በአንድነት እንጂ በመለያየት እውን አይሆንም።ለውጥ ትናንትን ገድሎ፣ ዛሬን ብቻ አንጠልጥሎም አይሳካም።
ይሑንና ከህልውና ባሻገር ስለ አንድ አገር ስለመፅናትና መቀጠል እንዲሁም ስለ ሁለንተናዊ እድገት ሲታሰብ ለዚህ ስንክሳር መፍትሄ መስጠት የግድ ይላል።ኢትዮጵያ አንድነቷ ተረጋግጦ፣ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የህዝቧን ቁሳዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካት የምትችለው በአንድ በኩል ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ሲኖራት ነው። ይህ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ምን አይነት ቅርጽ መያዝ አለበት? ምን አይነት የዲሞክራሲ፣የፖለቲካ፣ የህግ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ተቋሞች ያስፈልጉናል የሚሉ ትልልቅ አገራዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ደግሞ በጠረጴዛ ዙሪያ ሊመከርበት ይገባል።
ለበርካታ አመታት በተለይ ባለፉት አራት አስርት አመታት የውይይት እሳቤ በኢትዮጵያ ምድር እውን ይሆን ዘንድ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ከተለያዩ አካላት ሲነሳ ቆይቷል።‹‹ይሁን››የሚል መልስ የሰጠ መንግስት ግን አልነበረም። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግስት በአንጻሩ ይሕን ታሪክ ለመለወጥ በተለይ ስለ ኢትዮጵያ ቁጭ ብሎ ለመምከር በሩን ክፍት አድርጓል።ውይይቱ እውን ይሆን ዘንድ በሁሉ ረገድ ፈቃደኛ መሆኑን የሚያመላክት እርምጃዎችን እየተራመደ ይገኛል።
ፈፅሞ ሊቀራረቡና ሊታረቁ አይችሉም የተባሉ ሃሳቦችና ከግለሰብ አንስቶ እስከ አገራት የተቀራረቡት እንዲሁም ከልዩነት ይልቅ በአንድነት ለጋራ አላማ የተሰለፉት በምክክር ነው።ደቡብ ኮሪያ ለዚህ እሳቤ ጥሩ ምሳሌ ናት። ደቡብ ኮርያውያን ዛሬ ላይ በብልፅግና ጎዳና የመራመዳቸው ዋነኛው ምክንያት ከአምስት አስርት አመታት በፊት ከሁሉ በላይ ለውይይት ቅድሚያ መስጠታቸው እንደሆነም ታሪክ አሳይቶናል።
በአካታች አገራዊ ምክክሩ ኢትዮጵያ ታተርፋለች እንጂ አትከስርም።ከሌሎች አገራት አንፃር ሲታይም የኢትዮጵያ አብዛኞቹ ችግሮች በውይይት ፈር ሊይዙ የሚችሉ ናቸው።የምክክር መድረኩ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ለተሻለ የፖለቲካ ባህል ግንባታና ለሁለንተናዊ እድገትም እጅግ ወሳኝ ነው።
የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት የሚለው ላይ ግልፅ አቅጣጫን ያስቀምጣል።የተረጋጋችና በኢኮኖሚ የዳበረች ዲሞክራሲያዊት አገር ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ ነው።ይሑንና ምክክሩ እንዴት ውጤታማ ሊሆን ይችላል ከማንስ ምን ይጠበቃል የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው።
የተለያዩ የስነ ልቦናም ሆነ የፖለቲካ ምሁራንም አንድን ውይይት ምክክር ውጤታማ ለማድረግ ይረዳሉ የሚባሉ መሰረታዊ ነጥቦችን ሲያስቀምጡ፣ ከወገናዊነት ነፃ በመሆን ሚዛናዊ አስተሳሰብን ማራመድ፣ሁሉም እኩል የሚያሸንፍበት/ Win-Win Resolution/መንገድ መከተል፣ግልጸኝነት፣ ትዕግስት፣ መደማመጥ እና የሌሎችን ሀሳብ ማክበር የግድ እንደሚል አፅንኦት ይሰጡታል።
በውይይት በምክክር ወቅት በሰዎች መካከል የአመለካከት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል።የሃሳብ ልዩነቶች ደግሞ አላማንና ግብን የማያስቱ እስከሆነ ድረስ ተፈጥሯዊ ሰውኛ /Humanistic/ ናቸው።የሃሳብ ልዩነቶችን አቻችሎ ለመቀጠል ከሁሉም በላይ ውይይትን ውጤታማ ለማድረግ ግን በተለይ የሰጥቶ መቀበል መርህ እጅግ ወሳኝ ነው።
ሚዛናዊ ሆኖ የሌሎችን ሀሳብ ለማዳመጥ የራስንም ለሌሎች ለማስረዳት መዘጋጀት ይገባል። አንድ ጥግ ይዘን የሌሎችን ሀሳብ በጥርጣሬ መመልከት ለስህተት ይዳርጋል።ይልቁንም የሀሳብ ልዩነቶችን በቅንነት በመመልከት ሌላው የሚያስበውን በሌላው ጫማ ውስጥ ሆኖ ማየትን የሚጠይቅ ነው ።
አገራዊ የምክክር መድረኩ ውጤታማ እንዲሆን ከተፈለገ ከሁሉ በላይ በሁሉ ረገድ አካታች መሆን ይኖርበታል። ስለኢትዮጵያ ያገባኛል፣ ይመለከተኛል ወይም ደግሞ ጥያቄ አለኝ የሚሉን በትምህርት ደረጃ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በፖለቲካ አመለካከትና በጾታ ሳይገደቡ ማሳተፍና ሃሳቦችን መውሰድ ለውይይቱ ፍሬያማነት ትልቅ ጠቀሜታ አለው። የተለያዩ ሃሳቦች ሊነሱ ቢችሉም ለምክክሩ የሚቀረጹት አጀንዳዎች በዋናነት ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረጉና ዘላቂ ሠላምን የሚያመጡ መሆን ይኖርባቸዋል።
ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት ከሁሉ በላይ ከግልና ከቡድን ይልቅ የአገርና የሕዝብን ጥቅም ማስቀደም የግድ ይላል። በዚህ ረገድ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። የአገር ህልውና የገዢ ፓርቲ አሊያም የአንድ ፓርቲ ጉዳይ አይደለም።እንደ ዜጋ ወይም እንደ ፓርቲ መንቀሳቀስ የሚቻለውም አገር ስትኖር ብቻ ነው።የአገርን አንድነት የሚጠብቁና የአገርን ጥቅም በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ደግሞ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ልዩነት ሊኖረው አይገባም።
ለምክክሩ ውጤታማነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምሁራን ሚና የላቀ ነው።በተለያዩ አገራት የተካሄዱ አገራዊ ምክክሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማይተካ ሚና ተጫውተዋል።እንደአገር ሳያግባቡ የቆዩ ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ በመለየትና የሚፈቱበትን መንገድ በማመላከት ውይይቶቹ ለውጤት እንዲበቁ ማድረግ ችለዋል።ይህን መንገድ የአገራችን ምሁራንም ሊራመዱበት ይገባል።መገናኛ ብዙሃኑ መድረኩን የሚዘግቡበት መንገድ በራሱ በጥንቃቄና በአግባቡ ሊቃኝና ከወዲሁ ተገቢው ዝግጅት ሊደረግበት የሚገባው ነው።
አንድ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር አገራዊ የውይይት መድረኮች ሲካሄዱ ሁሉም ጥያቄ ፈጣን መልስ ይኖረዋል ብሎ ማሰብም አግባብ አለመሆኑ ነው።የእያንዳንዱ ምክክር መልስ የሂደት ውጤት መሆኑን ጠንቅቆ መገንዘብ ያስፈልጋል። ‹‹ጥያቄው ላይ ዛሬ ተወያይተናል መልሱን ዛሬ ካልሆነም ነገ እንፈልጋለን››ብሎ ማሰብም ግዙፍ ስህተት መሆኑን መረዳት ይገባል።
በአጠቃላይ አገራዊ ምክክሩ እንደሌሎች የውይይት መድረኮች ተድበስብሶ የሚቀር ሳይሆን የሚዳሰስ ውጤት ማምጣት በሚቻልበት መልክ ሊቃኝ ይገባል።ለዓመታት ስንጠይቅ የመጣን ከመሆናችን አንፃር በጣም በጥንቃቄና በጥሩ ዝግጅት መካሔድ ይኖርበታል።ለዚህ እጅግ ወሳኝ ታሪካዊ ሁነት ሁለንተናዊ መሳካትም ሁሉም የበኩሉን መወጣት የነገ ሳይሆን የዛሬ ተግባሩ መሆን አለበት።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም