የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ ቢሆንም በመገናኛ ብዙሃን ተገቢው ሽፋን እየተሰጠው እንዳልሆነ ይነገራል። ሆኖም ከኢትዮጵያ ሕዝብ 17 በመቶው በሰው ሰራሽ አደጋም ሆነ በተፈጥሮ አካሉ የተጎዱ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ። የትምህርት፤ የጤና፤ የሥራ ዕድልና የሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዳልሆኑም ጥናቶቹ ያመላክታሉ።
በቅርቡ የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባዘጋጀው የምክክር መድረክ የአዲስ አበባ ሴቶች ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አሉላ ሲሳይ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ እንደገለፁት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኞች አብዛኞቹ ያሉት ከ19 እስከ 59 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ነው። ከነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የትምህርት ተሳትፏቸው ዝቅተኛ ሲሆን 44 በመቶዎች ጭራሽ ምንም ዓይነት የትምህርት ዕድል አላገኙም። 89 በመቶው እስካሁን ምንም ዓይነት የገቢ ማስገኛ ሥራ እንደሌላቸውና የሰው ሰራሽ አካል ድጋፍ አለማግኘታቸው በጥናቱ ታይቷል። ከመሰረታዊ ማህበራዊ ጉዳዮች ተጠቃሚነት አንፃር ሲቃኝም በትምህርት፤ በጤና፤ በትራንስፖርት ያላቸው ተሳትፎ እጅግ ዝቅተኛ መሆኑ ተቃኝቷል።
ችግሩን መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በስፋት ገብተው የሚቀርፉበት ሁኔታ መመቻቸቱን አቶ አሉላ መግለፃቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የቺሻየር ፋዎንዴሽን የአዲስ አበባ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ፀጋዬ ዘለቀ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ ይሄንኑ ነው የተናገሩት። እሳቸው እንደሚሉት መገናኛ ብዙሃን ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደመሆናቸው መጠን በአካል ጉዳተኞች አካቶ ልማት ትግበራ ወይም ሁለንተናዊ ተሳታፊና ተጠቃሚነት ላይ ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ በተገቢው መንገድ መሰራት አለበት። መስኩ 17 በመቶ በሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ላይ የሚሰራ መሆኑንም ማጤን ይኖርበታል።
‹‹እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በተለይ ልማት ተሳትፎ ውስጥ በቸልታ ሊታዩ አይገባም›› ይላሉ አቶ ዘለቀ። የመገናኛ ብዙሃኑ ባለሙያ ይሄን ተገንዝቦ ከዚህ ቀደም ሲሰራበት ከነበረው በበለጠ ሁኔታ በኢትዮጵያ ልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የአካል ጉዳተኞች ተሳትፎ ጎልቶ እንዲወጣ መሥራት እንደሚጠበቅበትም ያስገነዝባሉ። የአካል ጉዳተኞች እንደማንኛውም የሕብረተሰብ ክፍል የጤና፤ የትምህርት፣ የሥራ ዕድልና የሌሎች የልማት ጥያቄዎች አሏቸው እነዚህን ጥያቄዎቻቸውን አጉልተው ማውጣት የመገናኛ ብዙሃኑ ሚና ሊሆን ይገባል።
ሕብረተሰቡም ሆነ ተቋማት አካል ጉዳተኛ ላይ ያላቸውን አመለካከት በጥሩ መልኩ እንዲቃኝ የማድረግ ሥራ ከመገናኛ ብዙሃን ይጠበቃል ሲል የተናገረው ደግሞ በምክክር መድረኩ የአካል ጉዳተኞች አካቶ ትግበራ የሚዲያው ሚና ምን መሆን እንዳለበት የሚያመላክት የዳሰሳ ጥናት ያቀረበው የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋዜጠኛና የመረጃና ግንዛቤ ስነ አካል ጉዳተኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ዮሴፍ ኃይለማርያም ነው።
እንደ ጋዜጠኛው ጉዳያቸው ከ10 ደቂቃ የአየር ሰዓት ጀምሮ እስከ 30 ደቂቃ ብሎም እስከ አንድ ሰዓት አድጎ በመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ማግኘት መቻሉ ይበረታታል። ሆኖም ትልቁ በሚባለው አንድ ሰዓት የሚሰሩት የግል መገናኛ ብዙሃን ናቸው። የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ሥራውን የሚሰራው በጩኻት ነው። አካል ጉዳተኛ ያልሆነው ጋዜጠኛ የሴቶች ፤የሕግ የህፃናት፤ የኢኮኖሚ ፤የትምህርት ተብሎ ፕሮግራም እንደሚሰራው የአካል ጉዳተኛን አለመሥራቱ የአመለካከት ችግር መኖሩን ያመለክታል።
‹አስፈፃሚ አካላት እንዴት አካል ጉዳተኞችን አካተው መሥራት እንዳለባቸው በሕግ ተቀምጧል› የሚለው ዮሴፍ አንድ ፕሮግራም ሲሰራ፤ ሲታቀድ አካል ጉዳተኛውን ታሳቢ የማድረግ ግዴታ ሊኖር ይገባል ይላል ጋዜጠኛ ዮሴፍ። ጋዜጠኛው ለአካል ጉዳተኛ መረጃ እንዴት እንደሚያደርስና ስለ አካል ጉዳተኛው መብት እንዴት እንደሚያወራም በህግ አግባብ የተቀመጠ ቢሆንም እስካሁን ወደ መሬት አውርደው እየሰሩበት ያለው ጥቂቶች ናቸው።
አካል ጉዳተኞች 17 በመቶ የአገሪቱን ዜጎች ቁጥር ሽፋን የያዙ ናቸው። በአገሪቱ ልማት በተለይ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ያላቸው ተሳትፎ ምን መሆን እንዳለበት አሳይ ፤አስነብብ፤ አስደምጥ ፤አሳውቅ ፤ይላል። ብቻም ሳይሆን ይሄን መሰረት አድርጎ መረጃን ለአካል ጉዳተኛው፤ ለመንግስት የሥራ ኃላፊ፤ አካል ጉዳተኛ ላልሆነው ሕብረተሰብ ንገር እንደሚልም ያክላል።
ሆኖም መገናኛ ብዙሃኑ ይሄን መተግበሩ ላይ ገና የሚቀሩ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉባቸውም ጋዜጠኛ ዩሴፍ ይጠቁማል። እንደጋዜጠኛው ቋንቋ አጠቃቀም ላይም ችግር አለ። አካል ጉዳተኛውን አካለ ስንኩል ወይም ጎዶሎ ብለው የሚጠሩ ጋዜጠኞች እንዳጋጠሙት ዮሴፍ ያስረዳል። እንዲሁም አካሉ የጎደለና ያልጎደለ የሕብረተሰብ ክፍል በንጽጽር ሲያስቀምጡ አካሉ ያልጎደለውን ጤነኛው ብሎ የማሰብ የአካል ጉዳት ያለበትን ደግሞ በሽተኛ ብሎ የማሰብ አባዜ እንዳለ ዮሴፍ ያብራራል።
ይሄን ዓይነቱ የተዛባ አተያይ በበርካታ ጋዜጠኞች ዘንድ እንደሚንጸባረቅና ሊስተካከልም እንደሚገባ በውይይት መድረኩ ላይ ግንዛቤ ተይዞበታል። አቶ መኮንን ማናየ ይባላሉ። የዊይማ (WEEMA) ኢንተርናሽናል የትምህርትና የማህበራዊ አካታችነት ፕሮግራም ማናጀር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት አካል ጉዳተኞች በትምህርትም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች በስፋት ተሳታፍና ተጠቃሚ አይደሉም።
ተጠቃሚ አለመሆናቸውና ተጠቃሚ መሆናቸውን ሕብረተሰቡም ሆነ ራሳቸው የሚገነዘቡት በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት ነው። ሆኖም አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ በማድረጉ በኩል መገናኛ ብዙሃን ክፍተት አለበት። ለማሳያ እንደጠቀሱትም ህትመት ዘርፉ ላይ የሚወጡትን ጽሑፎች ዓይነ ስውራን አያነቧቸውም። እንዲሁ በሬዴዮ የሚተላለፈውን መስማት የተሳናቸው አይከታተሉትም።
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተለይ በአዲስ አበባ የሚመረቁ ፕሮጀክቶች አካል ጉዳተኛውን ያካተቱ መሆን አለመሆናቸውን የተመለከተ ሽፋን መስጠት አለባቸው። እኛም መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አካል ጉዳተኞችን ተሳታፊና ተጠቃሚ በማድረጉ፤ መገናኛ ብዙሃን ደግሞ ይሄን በማስተጋባቱና በመፈተሹ ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን መገንዘብ ይገባል አልን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2014