ለሚመለከተው ሁሉ…
እንሆ ግለሰባዊ አቋም…
እኔ ከዚህ ትውልድ አይደለሁም ከዚያኛው ከአባቶቼ ትውልድ ነኝ። ከዛኛው አብሮ እየበላ፣ አብሮ እየጠጣ ኢትዮጵያዊነትን በፍቅር ቀለም ከቀለመው አብራክ ነኝ። ከዛኛው..በጨዋነት አገር ካቆመው፣ በፍቅር ጥልን ከገደለው፣ በአንድነቱ ታሪክ ከሠራው ከዛ ትውልድ ዘንዳ ነኝ። እኔ በባዶ እግሩ እየሄደ ጫማ ካለበሰኝ፣ ሳይማር በፈርዐ እግዚአብሔር ሁሉን ካወቀው፣ ፊደል ሳይቆጥር ዘመናዊነትን ካስተማረኝ ከዛ ብሩክ አብራው የበቀልኩ ነኝ።
እኔ ብሔር ሳይል ሃይማኖት፣ ዘር ሳይል ጎሳ ፊደል ቀርጾ፣ የቀን መቁጠሪያ ሠርቶ ታሪክና ቀዳማይነትን ያለበሰኝ የዛ የባለታሪክ ጽንስ ነኝ። ራሴን በገዛ ፍቃዴ አሁን ካለው ከስሜታዊው ትውልድ አገለልኩ። በብሔር ስም ፍቅር ካጣው፣ በእኔነት ጽንፍ አንድነት ካጣው፣ በራስ ወዳድነት ኢትዮጵያዊነትን ከሻረው ከዚህ ትውልድ ተለየሁ። እናም እኔ አባቶቼን ነኝ ስል ሁሉም እንዲሰማኝ ጮኽ ብዬ ተናገርኩ።
እኔ ሰው ነኝ..አባቶቼ ያስተማሩኝ ሰውነትን ነው። እናንተም ሰው ናችሁ ያኛው ትውልድ የነገራችሁ ሰውነትን ነው። ታዲያ ሰውነት በዚህ ዘመን የት ገባ? ዛሬ ላይ የምንባላባቸው ብሔርና ቋንቋ፣ ዘርና በምን ሚዛን ከሰውነት በለጡ? ለዚም ስል ራሴን ከእናንተ አገለልኩ..እኔ ኢትዮጵያዊ ነኝ፣ እኔ የእውነተኛዎቹ የአባቶቼ ፍሬ ነኝ ስል ተነሳሁ። ይሄ ሰው ምን ነካው እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። ደግሞም እናንተ እንጂ እኔ አላበድኩም።
ሰው የሚያብደውና ከተፈጥሮ ሚዛን የሚጎድለው ሰውነትን በሌላ ሲቀይር ነው። ሰው ኋላ ቀር የሚባለው የአባቶቹን የአንድነት ምድር በመለያየት የእኔ..የእኛ ሲል ነው። አገር ድሀ የምትባለው ፍቅርን ያጡ ሕዝቦች ሲኖሩባት ነው። ብዙ የጋራ ታሪኮች እያሉ ሕዝብ ያን የጋራ ታሪክ መጠቀም ሳይችል ሲቀር ነው። የእኛ ድህነት ባለመሥራት የመጣ የሚመስለው ሞልቷል። የእኛ ድህነት የኢኮኖሚ ችግር ብቻ የሚመስለው ብዙ ነው። የእኛ ድህነት የኢኮኖሚ ድህነት አይደለም። የእኛ ድህነት የፍቅር ማጣት፣ የአንድነት ማጣት የወለደው ነው። የእኛ ኋላ መቅረት የከሸፈ የፖለቲካ ሸር የፈጠረው ነው። ዛሬ ላይ ጎልተው የምናያቸው ኢኮኖሚያዊም ሆኑ ማህበራዊ ችግሮቻችን አንድነት በማጣት የተፈጠሩ ናቸው።
ሰው አንድ ከሆነ፣ ሕዝብ በፍቅርና በአንድነት ከቆመ አይደለም ድህነትን፣ አይደለም ኋላ ቀርነትን ሌላም አይበግረውም። ትልቁ ችግራችን የአንድነት ማጣት ችግር ነው። ትልቁ ችግራችን ስልጣን እጃችን ሲገባ አብሮ የተረኝነት ስሜት መሰማቱ ነው። የትኛውም የዓለም ስልጣኔ በሕዝቦች የአንድነት መንፈስ ተጠንስሶ ፍሬ ያፈራ ነው። ሩቅ ሳንሄድ በቀላሉ እንኳን የአድዋን ድል ብናይ አንድነት የፈጠረው ሆኖ እናገኘዋለን።
አስቡት እስኪ..ዓለም ላይ በስልጣኔ ፊት አውራሪ የሆነች፣ በሎጂስቲክና በጦር ኃይል አካዳሚ አንቱታን ያገኘች፣ ከዚህ ሁሉ በላይ በአየርና በየብስ የሚምዘገዘጉ ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀች አገር በአንድ ድሀና ባህላዊ መሣሪያ ባነገቡ ሕዝቦች ስትሸነፍ። ይሄን እውነት ምን ትሉታላችሁ? ይሄ እውነት የአንድነት እውነት ነው። ይሄ እውነት ታሪክ የቀየረ፣ ኢትዮጵያዊነትን ከአጽናፍ አጽናፍ ከፍ ያደረገ የአባቶቻችን የአንድነት ክንድ ነው። እኛም ከፍ ለማለት፣ ከኋላቀርነትና ከድህነት እንድንወጣ አንድነት ነው የሚያስፈልገን።
እኔ በምክንያት የተፈጠርኩ፣ በምክንያት የምኖር ወጣት ነኝ። እኔ የአገሬ ድሀ መሆን፣ የወገኔ በቀን ሦስት ጊዜ አለመብላት የሚያሳስበኝ፣ ብሔር ምን እንደሆነ የማላውቅ፣ በፖለቲካ ቅራኔ ጥላቻ የማላውቅ ምክንያታዊ ወጣት ነኝ። ለአገሬ ምርጡን የማስብ፣ ለድሀው ወገኔ የምጨነቅ ባለ ራዕይ ወጣት ነኝ። እኔ የኢትዮጵያን ስም በመልካም ከሚያስተጋቡት ምርጦች ውስጥ ነኝ። በዘርና በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ከሚባሉት ውስጥ አይደለሁም። የሚያግባቡንና አንድ የሚያደርጉን ብዙ ነገሮች እያሉ በለያዩን ጥቂት ነገሮች የምሸነፍና ድንጋይ ከሚያነሱት ውስጥ አይደለሁም።
እንደ እኔ ትውልዱን የጠላ፣ እንደ እኔ በምክንያትና በማሰብ የሚኖር ካለ ይከተለኝ። እንደ እኔ ሰውነትን ያገነነ፣ እንደ እኔ ፍቅርና ይቅርታን አንድነትንም ለመልበስ የተሰናዳ ካለ ጎኔ ይቁም። እንደ እኔ ወገኖቹን ሁሉ የሚያፈቅር፣ ኢትዮጵያን ያለ ታማኝ ዜጋ ካለ አብሮኝ ይቁም። በእኔና በእናንተ መካከል የቆመ የማንነት ድንበር፣ ብሔርተኝነትን የሚሽር የህልውና አጥር፣ የአንድነት ምሰሶ ኢትዮጵያዊነት ነው። በዚህ ስም ካልተግባባን በሌላ በምንም አንግባባም። እግዜር ስንት ጊዜ ታዘበን.. አጋንንት ስንት ጊዜ ቀናብን። ሁሉ ነገራችን በእጃችን ያለ ሕዝቦች ነበርን። ፍቅር ቢኖረን የጎደለን አንዳች እንደሌለ እንደርስበት ነበር። አንድነት ቢኖረን በዚህ ልክ በርሀብ፣ በዚህ ልክ በመገፋፋት ባልነወርን ነበር።
ሕዝቤ ሆይ ስማኝ ካለ ፍቅር የምንራመደው መንገድ ወደ ሞት ካልሆነ ወደየትም አያደርሰንም። ስለዚህ ፍቅርን እንወቅ። ኢትዮጵያ መግባቢያ ቋንቋችን ናት። በእያንዳንዳችን ነፍስ ላይ፣ በእያንዳንዳችን ከንፈር ላይ ያለ ቅዱስ ቃላችን ናት። ይሄን እውነት ስላልተረዳነውና ስላልተቀበልነው ነው ዛሬ ላይ በብሔር ስም ብዙ ነገር እየሆንን ያለነው።
ሰውነት ከዘር ቢበልጥብን ኖሮ፣ ኢትዮጵያዊነት ከብሔር ቢልቅብን ኖሮ ዛሬ ላይ እነዚህን ሁሉ የሞትና የጦርነት መርዶዎች ባልተጋፈጥን ነበር። እንደ እኔ ትውልዱን ሽሹና ወደ አባቶቻችን መንፈስ እንመንን። በአባቶቻችን የአንድነት ገዳም ውስጥ ፍቅርን ተምረን በቅተን ስንመለስ ምናልባት ያኔ አገርና ሕዝብ ምን ማለት እንደሆኑ ይገባን ይሆናል። እኔ ትውልዱን ሸሽቼዋለሁ..እናንተም ሽሹትና ይሄን ብሔርተኛ ትውልድ ባዶውን እናስቀረው..ከዛም ኢትዮጵያን የሚል ትውልድ እንፍጠር።
በደምና በአጥንት የተቀለመ ኢትዮጵያ የሚል የአንድነት ሐውልት እኮ አለን። በሞትና በጀግንነት የተፈጠረ ሀበሻ የሚል ድንቅ የወል ስም እኮ አለን። ታዲያ ኦሮሞነት፣ አማራነት፣ ትግሬነት ምን አመጣው? በየትኛው መስፈርት ነው ብሔር ከኢትዮጵያዊነት ሊልቅ የሚችለው? አትሳቱ.. ኢትዮጵያዊነት መሪያችን ነው። የተጠለልነው በኢትዮጵያዊነት ትልቅ ዋርካ ስር ነው። ኢትዮጵያዊነትን ሸሽቶ ብሔርተኝነትን መትከል ይሄን ትልቅ የጋራ ዋርካ መገንደስ ነው ።
እኛነትን ሽሮ እኔነትን መትከል ለዘመናት በአባቶቻችን እንባና ደም የጸደቀችውን፣ ጸድቃም የለመለመችውን፣ ለምልማም ሰላሳና ስልሳ መቶም ያፈራችውን ኢትዮጵያን ማሳነስ፣ ማጠውለግ፣ ማምከን ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያዊነት ምንድነው ስንባል የምንመልሰው የጋራ እውነት ሊኖረን ይገባል። እኔ ግን እላለሁ ከኢትዮጵያዊነት ውጪ ሌላ ብሔር፣ ሌላ ማንነት የለኝም።
የእኔ ብሔር፣ የማንነቴ ጥላ፣ ዋርካዬ ኢትዮጵያ ናት። እናንተም አይኑራችሁ.. መማያችሁ ኢትዮጵያ ትሁን። አገራችን ኢትዮጵያ ለሁላችን የምትበቃ ማህጸነ ለምለም አገር ናት። እኛ ለእሷ እንመቻት እንጂ እሷ ለእኛ የሚሆን ብዙ ነገር አላት። እኛ በፍቅር፣ በአንድነት እጅ ለእጅ ተያይዘን እንቁም እንጂ ማጀቷ ሙሉ ነው። ሌማቷ ጎድሎ አያውቅም። አይደለም ለእኛ ለሌሎች የሚሆን ብዙ ነገር ያለን ሕዝቦች ነን። ግን ይሄ ሁሉ ሙላት፣ ይሄ ሁሉ መትረፍረፍ ያለፍቅር፣ ያለአንድነት ምንም ነው።
በብሔር ሳይሆን በሰውነት አገር እንሥራ። በነውር ሳይሆን በኢትዮጵያዊነት ትውልድ እንቅረጽ። የሚበጀን ይሄ ነው። አገራችንን እያሳነስናት ያለነው ራሳችን ነን። ወጣቱ ራሱን ለአፍታ ቢመለከት እየሄደበት ያለው መንገድ ልክ እንዳይደለ ይደርስበታል። እኔ አማራ ብቻ፣ ኦሮሞ ብቻ ወይም ትግሬ ብቻ አይደለሁም፣ እኔ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ደግፎ ያቆመኝ የብሔረሰብ ልጅ..የብሔረሰብ ቅይጥ ነኝ።
እኔ እዚህ ቦታ ሰው ሆኜ እንድቆም አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ሱማሌው፣ ሲዳማው፣ ወላይታው፣ ጋሞው፣ ጉራጌው፣ አርጉባው ሁሉም ብሔር አስተዋጽኦ አድርጓል። እንዴት ራሴን በክብር ካቆመኝ ከዚህ ሕዝብ መገንጠል እችላለሁ? እንዴትስ ውለታውን ረስቼ ኦሮሞ ነኝ፣ አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ እላለሁ? እንዴት በኩራት ካቆመኝ ብሔርብሔረሰብ ተለይቼ ሲዳማ ነኝ፣ ጉራጌ ነኝ እላለሁ? እኔ ሁሉንም ብሔርብሔረሰብ ነኝ።
የእኔ የምለው ብሔር የለኝም። የእኔ ካልኩም ኢትዮጵያዬን ነው የእኔ የምላት። የእኔ ብሔር እሷ ናት። ከእንግዲህ ባለው ታሪካችን፣ ከእንግዲህ ባለው ሕይወታችን ኢትዮጵያን እገርም ብሔርም አድርገን እንድንኖር እፈልጋለሁ። ከእንግዲህ ባለው ማህበራዊ ሕይወታችን፣ ከእንግዲህ ባለው ፖለቲካችን ኢትዮጵያን ርስትም መመኪያም አድርገን እንድንኖር እሻለሁ። አገሩን ብሔሩ ያደረገ ትውልድ በዚህ ዘመን እንዲፈጠር እሻለሁ። አገሩን ሁሉ ነገሩ ያደረገ መንግሥትና ሕዝብ በዚህ ዘመን እንዲበዛ እሻለሁ። ያለዛ አትመልሱኝም። ያለዛ ከምናኔዬ አልመለስም። አገራችሁን ብሔራችሁ አድርጋችሁ ካልጠበቃችሁኝ እየሄድኩበት ካለው የምናኔ ጉዞ አልመለስም።
ብቻችንን ተዐምር የለንም። ብቻችንን አገርና ሕዝብ መሆን አንችልም። ብቻችንን አስፈሪ የመሆን አቅም የለንም። ኃይላችን አንድነታችን ነው። እድገታችን ብዙሀነታችን ነው። አንድ መሆን ከኃይልና ከውበት ባለፈ አስፈሪነትም ነው። ግርማ ሞገስ ነው። አንበሳነት ነው..ኩራት ነው። ታዲያ ወንድማማችነት አይሻልም ትላላችሁ? ታዲያ ፍቅርን ያገነነ፣ አንድነትን የወደደ አገርና ሕዝብ ቢወጣን ምኑ ነው ችግሩ? ልዩነታችንን ለውበት እንጂ ለመለያየት አንጠቀመው። ብዙሀነታችንን ለልማት እንጂ ለሁከት አናድርገው።
ከጉዞዬ ትመልሱኝ ዘንድ..አብሬአችሁም በወንድምነት እቆም ዘንድ በኢትዮጵያዊነት ታረቁኝ። በኢትዮጵያዊነት ማሉልኝ። ከእንግዲህ ኢትዮጵያዊ ነኝ በሉኝ። ያለዛ በዚህ ዘመን ተፈጥሬ የዛ ዘመን ትውልድ እሆናለሁ። ያለዛ እናንተን ትቼ ኢትዮጵያን አፍቅረው ወደሞቱት የዋህ ነፍሶች አዘግማለሁ። ያለዛ ርቄአችሁ በኢትዮጵያዊነት ገዳም ውስጥ ለብቻዬ እመንናለሁ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 30/2014