በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስር የነበሩትን የምዕራብ ኦሞ፣ የቤንች ሸኮ፣ የካፋ፣ የዳውሮና የሸካ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳን በአንድነት በመያዝ በኅዳር ወር 2014 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲዊ ሪፐብሊክ 11ኛው ክልላዊ መንግሥት ሆኖ የተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል፤ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ከፍተኛ አቅም ያለው በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አካባቢ ነው።
በተለይም ክልሉ ያለው የቡና፣ የሻይ ቅጠል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የማዕድናት ሀብት ሀገርን የሚያኮራ፣ ባለሀብቶችን በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያነሳሳ እና የሕዝብን የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የፀጋዎች ባለቤት ነው።
የክልሉ ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ ክልሉ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት ባለፀጋ ነው። ከወርቅ ማዕድን በተጨማሪ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የድንጋይ ከሰል በክልሉ በዳውሮ እና በኮንታ አካባቢዎች በስፋት ይገኛል። ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚሆን የብረትና የድንጋይ ከሰል ማዕድናትም ሌላው በክልሉ የሚገኙ ሀብቶች ናቸው።
በአስር ዓመቱ ሀገራዊ የልማት ዕቅድ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል የማዕድን ዘርፍ አንዱ መሆኑ ይታወቃል። የዘርፉ እምቅ የማእድን ሀብት በዚህ በኩል ጉልህ ስፍራ ይኖረዋል። ዘርፉ በሀገራዊ ኢኮኖሚ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዲኖረው በክልሉ ያለውን እምቅ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
ክልሉ ወርቅን ጨምሮ የተለያዩ ማዕድናት ባለፀጋ ቢሆንም ልማቱ እየተከናወነ ያለው በባህላዊ መንገድ በመሆኑና ቀደም ሲል ጀምሮ ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶ፣ ሀብቱ ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል የሚፈለገውን ያህል ጥረት ባለመደረጉ ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ አላስገኘም። ለአብነት ያህል እስካሁን ባለው ሂደት ወርቅ የማምረት ሥራው በባህላዊ መንገድ፣ በአካፋና በዶማ በመቆፈር፣ የሚከናወን ነው።
ስራውን የሚያከናውኑት በማሕበር የተደራጁ የአካባቢው ነዋሪዎች በመሆናቸው የማዕድን ሀብቱን በዘመናዊ አሰራር ለማልማት ብዙ ሥራዎች ይጠበቃሉ። ስለሆነም የማዕድን ሀብቶችን ለይቶና አደራጅቶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ የክልሉ ቀጣይ የቤት ሥራ እንደሆነ ግንዛቤ ተይዞ ከወዲሁ እየተሰራ እንደሆነም የኤጀንሲው መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለይም ለውጭ ገበያ ቀርቦ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት ረገድ ትልቅ ድርሻ ባለው በወርቅ ማዕድን ልማት ላይ በስፋት እንዲሰራና በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ በግዥ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለውን የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ መተካት እንዲቻል ትኩረት ተሰጥቷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘት የሀገር ኢኮኖሚን በብርቱ የሚደግፉ ምርቶች መገኛ ነው። ከፍተኛ የቡናና የማዕድን ሀብቶችን የያዘው ይህ ክልል፤ ሀብቱ ከክልሉ አልፎ ለሀገርም የሚተርፍ ፀጋ ነው። ክልሉ አስደናቂ የሆነ መልከዓምድራዊ አቀማመጥ፣ ልምላሜና የተፈጥሮ ሀብት ያለው በመሆኑ የባለሀብቶችን ትኩረት እንደሚስብ ይጠበቃል።
በዚህ ረገድ ስለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የኢንቨስትመንት ሀብትና የዘርፉ የሥራ እንቅስቃሴዎች የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ፣ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ይደነቅ ወልደሰንበት በተለይ ለ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ የሰጡትን ማብራሪያ እንደሚከተለይ አቅርበነዋል።
የክልሉ የኢንቨስትመንት አቅም
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በተለያዩ ዘርፎች እምቅ የኢንቨስትመንት አቅም አለው። ዓመታዊ ሰብል፣ ቡናና ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ኢንዱስትሪ እና አገልግሎት ዘርፎች በክልሉ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት የሚያስችሉ የምጣኔ ሀብት መስኮች ናቸው።
በማዕድን ዘርፍም ሰፊ አቅም እንዳለ አመላካች ነገሮች አሉ። ክልሉ በአዲስ መልክ የተደራጀ በመሆኑ ያሉትን የማዕድን ሀብቶች ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በስፋት በማጥናት ለኢንቨስትመንት ዝግጁ የሚያደርግ ይሆናል። የክልሉን ሀብቶች ለመለየት የሚደረጉ ተጨማሪ ጥናቶች እንደተጠበቁ ሆነው፤ እስካሁን በተካሄደ ጥናት 88ሺ 786 ሄክታር ለዓመታዊ ሰብሎች፣ አራት ሺ 875 ሄክታር ለቡናና ቅመማ ቅመም እና 20ሺ 565 ሄክታር ለአትክልትና ፍራፍሬ፤ በአጠቃላይ 134ሺ 126 ሄክታር መሬት ለግብርና ዘርፍ ምቹ እንደሆነ ታውቋል።
በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎችም ክልሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻና አማራጭ መሆን የሚችል አካባቢ ነው። በክልሉ ዞኖችና ከተሞች 69 ነጥብ ሰባት ሄክታር መሬት በአገልግሎት ዘርፍ እንዲሁም 64 ነጥብ ስድስት ሄክታር ደግሞ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ተለይቷል።
ባለሀብቶችን የመሳብ ጥረት
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ በመሳብ ክልሉና ሕዝቡ ከሀብቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል፤እያከናወነም ይገኛል። ለባለሀብቶች ጥሪ ተደርጓል፤ባለሀብቶችን ለመቀበል በዞን የአስተዳደር መዋቅሮች አማካኝነት ግንዛቤ እንዲፈጠር ተደርጓል። ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ሲመጡ ያለምንም መስተጓጎል ወደ ስራ እንዲገቡ በየጊዜው ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ተሰርተዋል። የባለሀብቶች ጥያቄዎች ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል። ባለሀብቶች ምንም ዓይነት የቢሮክራሲ ችግር ሳይገጥማቸው ወደ ስራ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ ነው።
የባለሀብቶች ፍላጎትና ተሳትፎ
ክልሉ ከተደራጀ ወዲህ ባለሀብቶች በክልሉ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት አሳይተዋል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተሰሩ የንቅናቄ ተግባራት አማካኝነት ብዙ ባለሀብቶች በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ላይ ለመሰማራት ፍላጎት እንዳላቸው ማወቅ ተችሏል። በቅርቡ በግብርና፣ በአገልግሎትና በኢንዱስትሪ ዘርፎች ከአንድ ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ያስመዘገቡ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቻቸውን አቅርበው ፕሮጀክቶቹ ተገምግመውና በሚያስፈልገው መስፈርት መሰረት ተመዝነው በአስፈፃሚው አካል ውሳኔ አግኝተዋል። ፕሮጀክቶቹ አቅማቸው ታይቶና በቴክኒክ ኮሚቴ ተገምግሞ አስፈፃሚው አካል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ወደ ስራ እንዲገቡ እየተደረገ ነው።
ባለሀብቶቹ ለመሰማራት ጥያቄ ያቀረቡባቸው ዘርፎች ግብርና (ዓመታዊ ሰብሎች፣ ቡና፣ ሻይ ቅጠል፣ ቅመማ ቅመም፣ አትክልትና ፍራፍሬ)፣ አገልግሎት (ሆቴልና ቱሪዝም) እና ኢንዱስትሪ ዘርፎች ናቸው። ባለሀብቶቹ ፈቃድ ወስደው ስራ የጀመሩባቸው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ለሁለት ሺ 457 ዜጎች ቋሚ እንዲሁም ለ21ሺ939 ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ እድሎችን መፍጠር ችለዋል።
የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች
ክልሉ የባለሀብቶችን ፍሰት ለመጨመር የሚያደርጋቸው ማበረታቻዎች በአዋጅና በመመሪያ በተደነገጉ የማበረታቻዎች (Incentives) አሰጣጥ መሰረት የሚፈፀሙ ይሆናል። ቦታዎችን አዘጋጅቶ ለባለሀብቶች ማቅረብን ጨምሮ ክትትልና ድጋፍ የማድረግ ተግባራትን ያከናውናል። ባለሀብቶች በፍጥነት ወደ ስራ እንዲገቡ ቅድመ ሁኔታዎችን ያመቻቻል።
ተገማች መሰናክሎች
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በክልልነት ከተደራጀ ገና ጥቂት ወራት የተቆጠሩ በመሆኑ ባለሀብቶችን ወደ ክልሉ ለመሳብ በሚደረገው ጥረት ላይ መሰናክል ይፈጥራሉ ተብሎ የሚገመቱ ችግሮች ይኖራሉ።
በክልሉ ገና በጥናት ያልተለዩ ብዙ ሀብቶች አሉ። ወርቅ፣ ኦፓልና ሌሎች ማዕድናት በክልሉ ይገኛሉ ተብሎ ይገመታል። እነዚህ ሀብቶች በትክክል ተጠንተው ወደ ስራ አለመገባቱ ባለሀብቶችን በብዛትና በፍጥነት ወደ ክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለማስገባት ችግር መፍጠሩ አይቀርም። ከዚህ አንፃር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የክልሉን ሀብቶች በጥናት በመለየት ለኢንቨስትመንት ክፍት ማድረግ አስፈላጊ ነው።
ክልሉ አዲስ በመሆኑ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ተግባራት ለማቀላጠፍ በሚያስችል የሰው ኃይልና ሌሎች ግብዓቶች ማጠናከር ያስፈልጋል። የኢንቨስትመንት ስራዎች ቀልጣፋና ውጤታማ እንዲሆኑ ብቁ የሰው ኃይል አስፈላጊ በመሆኑ አደረጃጀቶችን የማጠናከርና ግብዓት የማሟላቱን ስራ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ መስራት ይገባል።
የመሰረተ ልማት ችግሮችም በክልሉ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ችግር ይፈጥራሉ። አርብቶ አደሮችና አርሶ አደሮች የሚኖሩባቸው የክልሉ አካባቢዎች የመሰረተ ልማት ተደራሽ ካልሆኑ ባለሀብቶች ወደ አካባቢዎቹ ገብተው በኢንቨስትመንት ላይ ለመሰማራት ይቸገራሉ። ስለሆነም የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማጠናከር የመሰረተ ልማት አቅርቦቶችን ማሟላት ይገባል።
ሰላምና ፀጥታ እና ኢንቨስትመንት
ሰላምና ፀጥታን ማስጠበቅ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታዎችን ከሚፈጥሩ ግብዓቶች ዋነኛው እንደሆነ ይታወቃል። የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከተመሰረተ በኋላ በሰላም እጦት የሚታወቁ አካባቢዎች ሰላም ሰፍኖባቸዋል። ለአብነት ያህል የፀጥታ ችግሮች የነበሩባቸው የአርብቶ አደር አካባቢዎች እየተረጋጉ ይገኛሉ። የክልሉ የፀጥታ መዋቅርም የተጠናከረና ችግሮችን መፍታት የሚችልበት ቁመና ላይ ይገኛል። በመሆኑም ከዚህ ቀደም ተደራሽ ያልነበሩ አካባቢዎች ጭምር የኢንቨስትመንት ፍላጎት እየታየባቸው ነው። በአጠቃላይ የክልሉ መንግሥት ሰላምና ፀጥታን ከማስፈን አንፃር የተሻለ ስራ እየሰራ ይገኛል።
እቅዶች
ክልሉ አስደናቂ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ልምላሜና ሀብት ያለው በመሆኑ ይህን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ያስገባ እቅድ ተግባራዊ ይደረጋል። በግብርና፣ በቱሪዝምና በኢንዱስትሪ ዘርፎች በስፋት ለመስራት የተዘጋጁ እቅዶች አሉ። የክልሉን የማዕድን ሀብቶች በጥናት በመለየት ለኢንቨስትመንት ምቹ ማድረግም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል።
አቶ ይደነቅ ወልደሰንበት እንደሚናገሩት፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች አሉት። አካባቢው ገና ያልተነኩ ብዙ ሀብቶች አሉት። ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሌላው አካባቢ የሚበቃ የተትረፈረፈ ሀብት ያለው አካባቢ ነው። የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሀብቶች ወደ ክልሉ በመምጣት በኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ ቢሰማሩ ጥሩ ውጤቶችን ያገኛሉ፤ራሳቸውንም ሀገርንም መጥቀም ይችላሉ።
በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ወደ ክልሉ ቢመጡ ክልሉ ባለሀብቶቹን ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሆነ ተናግረዋል።
አንተነህ ቸሬ