የሀገሬ የመንግሥታት ሽግግር ዋና መለያው ነባር ተቋማትን አፈራርሶና አጥፍቶ “አዲስ” በሚሰኙ መዋቅሮች ማውገርገር ስለመሆኑ ታሪካችን የሚመሰክርልን “እያነባ” ጭምር ነው። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እጅግ ደክሞበትና ዋጋ ከፍሎበት ያቋቋማቸውን መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች የወታደራዊው የደርግ ሥርዓት ገና “በትረ ሥልጣኑን” በጨበጠ ማግሥት እንደምን እየናደ ወደ ፍርስራሽነት በመለወጥ ቅርስና ውርስ አልባ እንዳደረገን በብዙ ማስረጃዎች ማመላከት ይቻላል።
“በፊውዳሊዝም ሥርዓት ላይ ሶሻሊስት ኢትዮጵያን እንገነባለን!” በሚለው የርዕዮተ ዓለም የጉሽ ገፈት ፍልስፍው ሰክሮ ያሳከረን የደርግ ሥርዓት ሀገሬን ሀገር ያሰኟትን በርካታ ተቋማዊ እሴቶች እንክትክታቸውን ያወጣው ትዕቢትና እብሪት አሳብዶትና በንጉሣዊ አስተዳደር ጥላቻ ሰክሮ እንጂ በርግጥም በቂና አሳማኝ ምክንያት ኖሮት አልነበረም።
“ግፍ ያናወጠው ባሕር፤ ድንጋይ አንሳፎ ላባ ያሰጥማል” እንዲሉ፤ ወታደራዊው የደርግ ሥርዓትም እንዲሁ ዕድል ፊት ነስታው የወር ተራ ጀንበሩ ስታዘቀዝቅ “አጉራህ ጠናኝ” በማለት ተሸንፎ መንበሩን ለተረኛውና ከጫካ እያገሳ ለወጣው ወያኔ/ኢህአዴግ ያስረከበው በራሱ ስህተቶች እጁን ለካቴና አሳልፎ በመስጠት ነበር። አዲስ መጭው የወያኔ ሥርዓትም እንዲሁ ልክ እንደ ቀዳሚው የደርግ ሥርዓት በመጀመሪያ የወሰደው ርምጃ መንግሥታዊ ተቋማትን አፈራርሶ ቀብራቸውን ማስፈጸም ነበር።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜና ዐውድ ሲፈቅድልን ተመልሰን ብዙ ጉዳዮች እንደምንዳስስ ቃል በመግባት ለዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ምክንያት ሆኖ ሃሳቡን ያጫረብን በቅርቡ የታተመ አንድ መጽሐፍ ነው። የመጽሐፉ ርዕስ “የመረጃ ደኅንነት ሙያ እና የኢትዮጵያ ገፅታው፤ ትውስታና ትንታኔ ከ1965 – 1983 ዓ.ም” የሚል ሲሆን ደራሲው ደግሞ በላይ ገብረ ጻድቅ የሚባሉ ጎምቱ ምሁርና የሀገራችንን የደኅንነት መሥሪያ ቤት ለበርካታ ዓመታት ያገለገሉ የሀገር ባለውለታ ናቸው።
ባሕር ማዶኞች ከፈረሱ አፍ “straight from the horse’s mouth” እንዲሉ ደራሲው ያበረከቱልን ይህ መጽሐፍ ከራሳቸው ሙያና ታሪክ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ስለሆነ ስለማንነታቸው በአጭሩ ዘርዘር አድርጎ ማስተዋወቁ መጽሐፉን በጉጉት እንድናነብ ይገፋፋናል። ይህ ጸሐፊም ደራሲውን ከልጅነቱ ጀምሮ በሚገባ ስለሚያውቃቸውና መጽሐፉ በተመረቀበት ዕለትም በይዘቱ ላይ አጭር የዳሰሳ ጥናት አቅርቦ ስለነበር ማስተዋወቂያው ከመጻሕፍቱ የተወሰደ ብቻ ሳይሆን የረጂም ዓመታት ቅርበት ምስክርነትም የታከለበት ነው።
ደራሲው በላይ ገ/ጻድቅ አባዲና ፖሊስ ኮሌጅ ከሚባለው ዝነኛ ተቋም በ1965 ዓ.ም በምክትል መቶ አለቅነት ማዕረግ ተመርቀው በቀጥታ ሥራ የጀመሩት በንጉሠ ነገሥቱ የመረጃ ተቋም ይባል በነበረው የሕዝብ ፀጥታ ጥበቃ ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ሲሆን በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ተመድበውም አገልግለዋል።
ደርግ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላም ከመስከረም 1967 – 1983 ዓ.ም በበረራ ደህንነት ጥበቃ፣ በተለያዩ የመረጃ ሥራዎች፣ በሀገርና ሕዝብ ደኅንነት ጥበቃ ሚኒስቴር መ/ቤት ውስጥ የሚኒስትሩ ልዩ ረዳትና በኋላም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውረው በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንደኛ ጸሐፊ፣ በምሥራቅ ጀርመንና በእስራኤል ኤምባሲዎቻችን ውስጥ አማካሪና ላይዘን ኦፊሰር በመሆን ሀገራቸውን እስከ ሰኔ 1983 ዓ.ም በታማኝነት አገልግለው በመጨረሻም በሕወሓቱ የደኅንነት ኃላፊ ከሥራ በመታገዳቸው ላለፉት 30 ዓመታት ያህል በስደት የቆዩት በእንግሊዝ ሀገር ውስጥ ነው።
አሸማቆ ኖሮ ተሸማቆ የሚያልፈው ተቋም፤
ምክንያታዊነቱን ለማብራራት ቢያዳግትም በኢትዮጵያ የተቋማት ታሪክ ውስጥ ተፈርቶና አሽቆጥቁጦ ኖሮ፤ መንግሥታት በተለዋወጡ ቁጥር ዐይንህን ለአፈር ከሚባሉ ተቋማት መካከል አንዱ የደኅንነት መሥሪያ ቤት ነው። ስያሜው ከሥርዓት ሥርዓት ሲለዋወጥ ቢኖርም ሕዝቡ በነቂስ በሚስማማበት የተለመደ ስሙ “የደኅንነት ተቋም” እያልን መጥራቱን መርጠናል።
የደኅንነት ተቋም እንኳንስ ለእኛ መሰሉ በብዙ ጠላቶች ተከቦ ጥርስ ለገባ ሀገር ቀርቶ ለማንኛውም ሉዓላዊና የተረጋጋ ለሚመስል ሀገርም ቢሆን የእስትንፋስ ያህል እጅግ አስፈላጊ ነው። ያለ ሕግ ሥርዓት፣ ያለ መከላከያ ሠራዊትና ያለ ጠንካራ የደኅነት ተቋም አንድ ሀገር፣ ሀገር ተብሎ ተከብሮ ሊጠራ ከቶውንም አይችልም። በተለይም የደኅነቱ ተቋም ደካማና ልፍስፍስ ከሆነ የሀገር ገመና ተራቁቶ ለመዋረድ ቅርብና ቀላል ይሆናል። በትንሽ በትልቁ ጡንቻቸውንና ጉልበታቸውን እያሳዩ ሕዝብን ለማሸበርና ሰላምን ለማናጋት እንቅልፍ ለሚያጡ የውጭና የውስጥ ጠላቶችም የሠርግና የምላሽ ያህል የሚያስፈንድቅ ነው። መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር አደራውን በጫንቃው ላይ የተሸከመውን ያህል የደኅንነቱ ተቋም ደግሞ ተግቶ ኃላፊነቱን የሚወጣው “አራት ዐይናማ በረኛ” በመሆን ነው።
ያለመታደል ሆኖ በዚህ ሰሞን እንኳን ሕዝቡን እምባ ባራጩ የአሸባሪ ቡድኖች ተደጋጋሚ ድርጊቶች የተማረረው ሕዝብ “ለመሆኑ በየአካባቢዎቹ የተፈጸሙት የወገን ጭፍጨፋዎች፣ የንብረት ውድመቶችና መፈናቅሎች ሲፈጸም የደኅንነት ተቋሙ ምን ይሠራ ነበር?” እየተባለ በብዙዎች ሲጠየቅ መሰንበቱ የተቋሙን እጅግ አስፈላጊነት የሚጠቁም ነው። እርግጥ ነው አገልግሎቱ እጅግ የላቀ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ዛሬም ቢሆን ሕዝቡ በደኅንነት መ/ቤቱ ላይ ያለው አመለካከት ሙሉ ለሙሉ ከፍርሃት ቆፈን የተላቀቀ ነው ለማለት ያዳግታል። መ/ቤቱም ቢሆን ወደ ሕዝብ ልብ ውስጥ ጠልቆ ገብቶ ለመወደድና በአለኝታነቱ እንዲከበር ተገቢው ሥራ ተሰርቷል ለማለት ያዳግታል።
ለማንኛውም በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን ታሪክ ረጂም ዕድሜ የሚቆጠርለት የደኅንነት ሙያ መንግሥታዊ ሥርዓቶች በተፈራረቁ ቁጥር በፍርሃትና በጥርጣሬ ስለሚታይ የአዲስ መጭው ሥርዓት ዱላ ቀድሞ የሚያርፈው በተቋሙና በባለሙያዎቹ ላይ ነው። ይህን መሰሉ የረዥም ዘመናት ገድልና ታሪኩ በተጠቀሰው የደራሲ በላይ ገ/ጸድቅ መጽሐፍ ውስጥ በሚገባ ስለተተረከ የአስተማሪነቱ ዋጋ እጅግ ከፍ ያለ ነው።
ደራሲው ለሁለት ዓመት ያህል ያገለገሉበትን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የመረጃ ተቋማት የገለጹት፤ “የአገሪቱን ሰላምና ጸጥታ ከማስጠበቅ አኳያ ከፍተኛ ብቃት እንደነበራቸው ለመናገር ብዙም ምስክር አያሻም። ተቋማቱን ለማቋቋም የሚያስፈልጋቸውን መዋቅራዊ ድጋፍና የሙያተኞች ሥልጠና ያገኙ የነበረው ትናንትናም ሆነ ዛሬ በዓለማችን ውስጥ ታዋቂ በሆኑት በአሜሪካዊያንና በእስራኤላዊያን ተቋማት ነበር። ” በማለት ነው።
በዚህም ጠንካራ ድርጅታዊ መዋቅር የተነሳ በንጉሡ ዘመን በይፋ የሚታወቁት የመከላከያ መረጃ ተቋማት፡- የሕዝብ ፀጥታ ጥበቃ፣ የፖሊስ ሠራዊት ልዩ ቅርንጫፎችና ኤታማዦር በመባል ይታወቅ የነበረው የመገናኛ መረጃ ማዕከል በጥቅሉ ዘመኑ ባፈራቸው ብቁ ባለሙያዎችና ወጣት ወጣት ሙያተኞች የተገነቡ ስለነበሩና በአመራር ላይ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣናቱም በእውቀትና በልምድ አንቱ የመሰኘት አክብሮት የተጎናጸፉ ስለነበሩ ተቋማቱ በአህጉር ደረጃ ሳይቀር ጠንካራ እንደነበሩ በዝርዝርና በተጨባጭ የኦፕሬሽን ማስረጃዎች ለማመለከት ሞክረዋል።
በአንጻሩ “ንጉሣዊ አገዛዙን የተካው የደርግ መንግሥት በአብዮቱ መባቻ ላይ በአገሪቱ የነበሩትን የመረጃ ተቋማት እንደ ንጉሡ ንብረት አድርጎ ከሕዝብ ጋር ለመተዋወቂያነት እንደተጠቀመበት ታሪኩን በዝርዝር አስፍረዋል። ገና ሙሉ ለሙሉ ሥልጣኑ ላይ ከመንሰራፋቱ አስቀድሞም ተቋማቱን በጅምላ ፍረጃ ፀረ-ሕዝብና ሀገር፣ አፋኝ፣ ጨቋኝ፣ የንጉሡን ሥልጣን ብቻ ለመጠበቅ እንደተቋቋሙ በመቁጠር የሕዝብን ፍቅርና አመኔታ መሸመቻ አድርጎት ነበር” – ይሉናል። ከዚህም አልፎ ተርፎ ነባርና በእውቀታቸውና በልምዳቸው የተከበሩትን መሪዎቹን በመረሸን፣ በርካታ ነባር ባለሙያዎቹም ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እንዳደረገ ማስረጃው በዝርዝር ቀርቧል።
እያደረ ግን በሥርዓቶቹ ሽግግር መካከል ዛሬም ድረስ ከታሪካዊ ጠላትነት ሊለዝቡ ያልቻሉ አንዳንድ የቅርብና የሩቅ መንግሥታትና በሀገር ውስጥ የመገንጠል ዓላማ አንግበው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖችና ገና ከእትብቱ ተላቆ ድክ ድክ ማለት ያልተጀመረው የወያኔ ቡድን በነባሩ ባለሙያዎች የረቀቀ ክትትል ተልእኳቸው መክሸፍ መጀመሩን የተረዱት አንዳንድ የአዲሱ የደርግ መንግሥት ሹማምንት ነባሮቹን የደኅንነት ባለሙያዎች በተመለከተ፤ “እነዚህ ሰዎች እኛ ስንለው እንደከረምነው ሳይሆን ሥራቸው የንጉሡን አልጋ ከመጠበቅ በላይ ነው። ” ብለው ምስክርነት መስጠታቸውም ተረጋግጧል።
ከደርግ በኋላ ጸጉሩን አጎፍሮ ከጫካ የወጣው የወያኔ/ኢህአዴግ “መንግሥት” ሥልጣን በያዘ ወር ባለሞላ ጊዜ ውስጥ በመጀመሪያ የወሰደው እርምጃ የደኅንነቱን ተቋም እንዳለ ማፍረስ፣ ኃላፊዎቹንና ሠራተኞቹን ማሳደድ፣ ማሰርና መግደል ነበር። በዚሁ ጭፍን ድንብር የበቀል ውሳኔም ሀገሪቱ መከራ ላይ ለመውደቅ፣ ሕዝቡም የስቅቅ ኑሮ እየኖረ ለማንባት ጊዜ አልፈጀበትም።
ደራሲው እጅግ ከረቀቁ ታሪካዊና ተጠቃሽ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገራት የኦፕሬሽን ስኬቶች ጋር እያዋዙና እያስደመሙ የዘረዘሯቸው ታሪኮች በእጅጉ የሚያስደንቁና ለተመራማሪዎችም እንደ አንድ ከፍተኛ ሰነድ የሚያገልግሉ ናቸው። መጽሐፉ ምናልባትም በዚህ ዘርፍ በቀዳሚነት የሚጠቀስ የመጀመሪያ ሥራ ተደርጎ ሊቆጠር እንደሚችል ይታመናል። ከዚህ በኋላም ሌሎች ጸሐፍት የደራሲውን ፈለግ ተከትለው በርካታ መሰል መጻሕፍትን ለንባብ እንደሚያበቁ ይጠበቃል።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በንባቡ መካከል እጅግ የተመሰጠባቸውና የተዝናናባቸው በርካታ እውቀቶች፣ መረጃዎችና ፈገግ የሚያስደርጉ ታሪኮች የተጠቀሱ ቢሆንም መጽሐፉ እንዲነበብ የሚያበረታቱትንና እንደ “ዲዘርት” የሚያገለግሉ ጥቂት ታሪኮችን ከመጽሐፉ ውስጥ ነቅሰን እንጠቁም። እንደማዝናኛነት ከጠቀሷቸው የይባላል ታሪኮች አንዱ ስለ ንጉሡ የተገለጸው በእጅጉ ፈገግ የሚያስደርግ ነው።
“ጃንሆይ ይደርሷቸው ከነበሩት ዕለታዊ መረጃዎች መካከል የሚያስደስቷቸው፣ የሚያዝናኗቸውና በጉጉት ከሚጠብቋቸው መካከል ሚኒስትሮቻቸውና የጦር አዛዦቻቸው በየጊዜው እርስ በእርሳቸውና ከሴቶች ጋር በስልክ ያድርጉ የነበረው ጭውውት፤ ዋናዎቹና የሚናፍቋቸው እንደነበሩ በሃሜት መልክ ይነገር ነበር። አልፎ አልፎም በድምጽ ተቀድተው የሚቀርቡላቸውን መረጃዎች ሲሰሙ የማያቋርጥ ሳቅ ይስቁ ነበር። ” በማለት ፈገግ የሚያሰኙ መሰል “እውነታዎችን” በየመሃል ጣል ጣል ያደርጋሉ።
“ድብቁ ሰው” በመባል ይታወቁና ይፈሩ የበሩትን የደርግን የደኅንነት መ/ቤት ሚኒስትር ሌ/ኮ ተስፋዬ ወልደ ሥላሴን፤ ታሪኮቻቸውን ጽፈው እንዳስነበቡን እንደ ብዙዎቹ የሚኒስትሩ የቅርብ ጓደኞች በደላቸውንና ፈጸመዋቸዋል የሚሉትን ግፎች ብቻ እየዘረዘሩ “የጦስ ዶሮ” ሊያደርጓቸው አልሞከሩም። ይልቁንስ እንደ ቅርብ አለቃና ልዩ ረዳታቸው ደራሲ በላይ ገ/ጻድቅ የሰጡት ምስክርነት በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው ነው።
“ኮ/ሌ ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ ጨዋ፣ ሰውን በባሕርይውና በችሎታው ብቻ የሚመዝኑ፣ ማሥራት የሚችሉና የሚያበረታቱ፣ ብዙ የሚያደምጡ፣ ችኩል ያልሆኑ፣ ሰዎችን የሚያቀርቡ እንጂ የማይገፈትሩ፣ ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ የበታቾቻውን በትዕግሥት የሚያደምጡ፣ መመሪያዎችን ሲሰጡ የተለየ ሃሳብ ሊኖር ይችላል በሚል የሚጠይቁ አዛዥ እንደነበሩ ጸሐፊው ያስታውሰል…በልምድም ሆነ በሙያ በሚፈለገው ትምህርት ከአንዳንዶች በስተቀር ኮ/ል ተስፋዬ የተሻሉ ነበሩ። ” በማለት የግላቸውን ምስክርነት ከሰጡ በኋላ ድካማቸውን የገለጹትም በጨዋነት ነበር። እንዲህ በማለት፤ “እርግጥ ነው የኮ/ል መንግሥቱን ዘለፋ ለመርሳት አልኮልና ከዚሁ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ነገሮችን ያዘወትሩ ነበር የሚል ሀሜትም ይሰማባቸው ነበር። ” ይህ ገለጻ በደልንና ጥፋትን ብቻ ከማጉላት ይልቅ የሰዎችን ጠንካራ ጎን ለመገለትም ኅሊናን ማድመጥ እንደሚገባ ጥሩ ማሳያ ነው።
ደራሲው እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እውቀቶችን፣ መረጃዎችን እያዋዙ በማቅረብ ለአንባቢያን እንደሚጠነቀቁ በመጽሐፉ ውስጥ በጉልህ ይስተዋላል። በየሥርዓተ መንግሥታቱ በደኅንነቱ ተቋምና በሠራተኞቹ አማካይነት ስህተት በፍጹም አልተፈጸመም፣ መሪዎቹም “ከደሙ ንጹሕ ነበሩ” ለማለት ሳይሆን ከድክመት ዝርዝር ጋር በሚቀራረብ መጠን ጥንካሬንም ማሳየቱ መልካም መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
ስለዚህም ይህ መጽሐፉ አንዴ ብቻ ተነቦ የሚቀመጥ ሳይሆን ብዙ ታሪኮችና እውነቶች እየተመዘዙለት የትናንቷንና የዛሬዋን ኢትዮጵያ በሚገባ ንጽጽር ማሳየት የሚችል ስለሆነ ደራሲውን በማመስገን አንባቢያን መጽሐፉን እንዲያነቡ ጸሐፊው ያበረታታል። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ሰኔ 29 /2014