የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበርን ከመሰረቱት ሴት ጋዜጠኞች አንዷ ነች። ለጋዘጠኝነት ሙያዋ ከሴቶች ጉዳይ መምሪያ ኃላፊነቷ እስከ መነሳት ተሰውታለታለች። ሙያውን በክፉ ወቅቶች ሳትሸሸው ለዛሬ ያበቃችው በመሆኗ ከሌሎቹ ትለያለች ተካበች አሰፋ። በቅርቡም የሴት ጋዜጠኞች ማህበር ለውለታዋ ዕውቅናና ምስጋና የቸራት ተካበች የተወለደችው አዲስ አበባ ከተማ ካዛንቺስ አካባቢ በ1939 ዓ.ም ነው።
ለወላጆቿ ከ11 ልጆች መካከል ሦስተኛ ልጃቸው ነች። በተለይ ለስድስቱ እህቶቿ እንደወንድምም ሆና ነው የኖረችው። ሊተነኩሳቸው የከጀለ ሁሉ ጋሻና መከታቸው ናት።
ለመምህራኖቿና ለአለቆቿ በአጠቃላይ ለሰው ልጆች ክብር ትሰጣለች። ሆኖም የማትፈራ ደፋርም ነች። ባላመነችበት ጉዳይ እስክታሳምን መከራከር ትወዳለች። እግር ኳስ ባትጫወትም ጨዋታ በሚካሄድባቸው ቦታዎች ሁሉ ተገኝታ ትመለከታለች። በስፖርት የተገነባው ቁመቷ መካከለኛ፤ የፊቷ ቀለም ብስል ቀይ፤ ገጽታው ስልክክ ያለ ሳቢና ማራኪ ቢሆንም የተቆጣ የሚመስለው ንግግሯ ከአካሄዷና ሱሪና ኮት አለባበሷ ጋር ተዳምሮ ወንዳወንድ ያስመስላታል።
ከሰው ባትጣላም በዚህ ሁኔታዋ እንኳን ሴቶቹ ወንዶቹም ሲፈሩና ሲያከብሯት፤ እሷም ስትመካበትና የደፈራትን ሁሉ አፈር ድሜ እያስጋጠች አሸናፊነት ስትጎናፀፍበት ኖራለች። ሁሌም አሸናፊ ነች። እህቶቿን ከለከፉ የትኞቹንም ወንዶች ሳትደበድብ አትለቅም። ዱላዋን የቀመሰ ጎረምሳ ሁለተኛ ቀና ብሎ እንኳን አያያቸውም። የማያውቅ ሊነካቸው ከሞከር ‹‹አንተ የዛች የእንትና እህት እኮነች ዋ! ይባባላሉ። ወንድሜን ሲያገኙት ያቺ እህትህ ደህና ነች አቤት እንትናን እኮ እንዴት አድርጋ እንደደበደበችው ይሉታል። ድብድቡን የተወችው ዕድሜዋ 20ዎቹን አልፎ ወደ 30ዎቹ ሲንደረደር ነው። ትምህርት ጨርሳ ሥራ ይዛለች። ወቅቱ ደርግ የመጣበት በመሆኑ ሁኔታውን ለማየት ወደ አራት ኪሎ ስትሄድ አንዱ ተከሻዋን ይመታታል።
ሆኖም በዕድሜዋም በስላ ፤ ትምህርቷን አጠናቃ ሥራ ይዛለችና የሰውየውን ድርጊት አይታ እንዳላየ አለፈችው። ‹‹ዞር ብዬ አይቼው ዱሮ ቢሆን ይሄኔ እንኳን ነክቶኝ ቢናገረኝ እንደማለቀው እያሰብኩ ሳቅኩና ሄድኩ›› ትላለች።
ለእሷ ባይመስላትም ንግግርዋ ጠንከር ያለ የወንዳወንድ በመሆኑ አንዳንዶች ለምን ትቆጭያለሽ ይሏታል። ሆኖም ጨዋታ አዋቂ፣ ሩህሩህ ፣ቀልደኛና የዋህም ነች። ውስጧን ሳያዩ ሲፈሯት የቆዩ ሰዎች ይሄን ባህሪዋን የሚያውቁት ሲግባቧት ነው።
የጋዜጠኝነትን ስራ ሀሁ ብላ ለጀመረችበት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጥሩ አመለካከት አላት፡፡ ትወደዋለች፡፡ ‹‹የሚያካሂዳቸውን ግንባታዎችና የሥራ እንቅስቃሴውን ሳልፍ ሳገድም ሳየው ደስ ይለኛል›› ትላለች፡፡የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አስተማሪዬ፣ መመኪያና የዓይኔ ብሌን ስትልም ታሞካሸዋለች። ከድሮ ጀምሮ ፕሬስ ውስጥ ሰላም ነበር። የተሻለ መተሳሰብና መቀራረብም ይታያል። ሌሎች ሚዲያዎች እርስ በእርስ የሚናቆሩበት ነበር። ማህበራዊ ሕይወታቸውም የላላ ነው። ፕሬስ ሥራውም ቢሆን አርአያነት ያለው፤ ዘመን ተሻጋሪና ታሪካዊ አሻራ የሚያሳርፍ ነው ትላለች። 44 ዓመታት ከሚጠጋው የሥራ ዘመኗ ከ30 በላዩን በዚሁ ድርጅትና በኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር በጋዜጠኝነትና በአመራር ሙያ በማገልገል ነው ያሳለፈችው።
የተማሪዎች ረብሻ ደስታ ስለሚነሳት መምህር መሆንን አትፈልግም ነበር፡፡ ሆኖም እየማለችና እየተገዘተች ትጠላው በነበረው በመምህርነት ሙያ ተሰማራች። ቀድሞ በየነ መርድ አሁን ዕድገት በሕብረት በተሰኘው ትምህርት ቤት ለ13 ዓመታት የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎችን በፍቅር አስተምራለች ።ተማሪዎቿ በልጅነቷ እንደፈራችው ባህርያቸው የሚያውክ አልነበረም። ይወዷትና ያከብሯት እንደነበረም ታወሳለች። ለውጤታማነቷ በመምህርነት ሥራ ጀምረው እስከ ትምህርት ሚኒስቴር በኃላፊነት ያገለገሉት አባቷ ልምድ መቅሰሟ ረድቷታል።
አባቷ በልጅ አስተዳደግ ላይ ቀልድ አያውቁም። ሁልጊዜ ማታ ማታ በየተራ ደብተራቸውን መፈተሻቸውና የፈተና ወረቀት ማየታቸው ግድ ነበር። እሷና እህቶቿ አንድ ኤክስ ከተገኘባቸው እንዴት ሆኖ ገባ ፤ ለምን አስተማሪያችሁን አልጠየቃችሁም ይባላሉ። ኮርኮም መደረጋቸውም አይቀርም። እናታቸውም እንዲሁ የልጆቻቸው ትኩረት ትምህርታቸው ላይ እንዲሆን ይፈልጋሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ካዛንቺሽ በሚገኘው በቀድሞው አስፋወሰን በአሁኑ ምስራቅ ጎህ ፤የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ በአሁኑ ኮኮበ ጽባህ ት/ቤት ያጠናቀቀችው በዚህ መልኩ ነው። በ13ቱ ዓመት ቆይታዋ ተማሪዎቿን እንደዚሁ ስትቀርጽም ኖራለች። የጋዜጠኝነቱን ትምህርት ቀስማ በሙያው ለመሰማራት የበቃችውም የመምህራን ማህበር የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ገንዘብ ያዥ በነበረችበት ሰዓት ባገኘችው የነፃ ትምህርት ዕድል ነው።
በ1976 ዓ.ም በውድድሩ አሸንፋ ወደ ችኮዝላባክያ በማቅናት ለአምስት ዓመታት የጋዜጠኝነት ትምህርት ተምራ የማስተር ኦፍ አርት ሁለተኛ ዲግሪዋን ይዛ ተመልሳለች። ፈጥናም ለማስታወቂያ ሚኒስቴር አመለከተችና 1983 ጥቅምት አንድ ቀን ፕሬስ ድርጅት ተመደበች፡፡ የጋዜጠኝነት ሥራንም አሀዱ አለች። ድርጅቱ በሚያሳትማቸው በአዲስ ዘመን ጋዜጣና በየካቲት መጽሔት እስከ 1986 ዓ.ም ስትሰራ ቆየች። በየመሥሪያ ቤቱ የሴቶች መምሪያ ይቋቋም ሲባል ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በዚሁ በ1986 አጋማሽ ተዛወረች።
ተካበች አሁን ላይ አሜሪካ ከምትኖረው ከፍፁም አለማየሁ ፣ ከአባይነሽ ብሩ ከቅድስት ክፍለዮሐንስና ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበርን የመመስረቱ ሃሳብ የመነጨላትም ይሄኔ ነው። ይግባቡና ይቀራረቡ ከነበሩትና ተመሳሳይ ሃሳብ ከነበራቸው ባልደረቦቿ ፍፁም አለማየሁ አባይነሽ ብሩ ፣ ስርጉት አስፋው፣ ኢሌኒ መኩሪያ፣ ከአሜሪካ ኤምባሲዎቹ ወይዘሮ አለምሰገድና ወይዘሮ ታቦቱን ጨምሮ ከፋና ሬድዎዋ ቅድስት ክፍለዮሐንስ፣ ከፕሬሷ ኤልሳቤጥ እንድሪያስ፣ ከፖሊስና እርምጃው ጋዜጣ ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ በቀለና ከሌሎች ሴት ጋዜጠኞች ጋር እየተገናኘች ሃሳቡን ስታብላላ ቆየች።
በዚሁ ወቅትም ዓለም አቀፍ የሴቶች ጉባኤ በየአህጉሩ ሲደረግ አፍሪካ ሴኔጋል ዳካር በተካሄደው ተሳተፈች። ከዚህ መልስም ዓለም አቀፍ ጉባኤ በቤጂንግ ቻይና ተካሄደ። እዚህ ደግሞ በወቅቱ የሴቶች ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ ታደለች ኃይለሚካኤል ተካፈለች። ከቤጂንጉ ጉባኤ 12 ዋና ዋና ነጥቦች አንዱና ዋናው ሴቶችና ሚዲያ የሚል ነበርና እነተካበች በስብሰባው የተሳተፈችውን ወይዘሮ ታደለችን በየሚዲያው ለሚሰሩት ሴቶች እንድታስረዳ ስብሰባ አዘጋጅተው ጋበዟት። ሴት ጋዜጠኞቹ የራሳችን ማህበር እንመስርት የሚል ሃሳብም አነሱ።
ሆኖም ስብሰባው የግማሽ ቀን በመሆኑና ሰዓት በመድረሱ ሃሳቡ መቋጫ ሳያገኝ መድረኩ ተበተነ። አንዳንድ ሴት ጋዜጠኞች ሃሳቡን ለአለቆቻቸው በመንገራቸው የምስረታ ውጥኑ በስፋት እየተሰማ መጣ። በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር የነበሩት ጆሮም ገባ። በትላልቆቹ አለቆች ዘንድ የኢትዮጵያ ጋዜጠኖች ማህበር እያለ ለብቻው ሌላ ማህበር መመሥረት ለምን አስፈለገ? የሚል ጥያቄና ቅሬታም አስነሳ። እነተካበች ለዚህ በየሚዲያ ተቋማቱ ለተነሳ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ምክክር አደረጉ።
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ቢኖርም ለሴት ጋዜጠኞች ሰፊ ዕድል የሚሰጥ አለመሆኑን አስረዱ። በተለይ በወቅቱ ሴት ጋዜጠኞች አገር ውስጥ በሚሰጡ አጫጭር የጋዜጠኝነት ስልጠናዎች እንደወንዶች ቀርቶ በጥቂቱ እንኳን እየተሳተፉ እንዳልሆነም ተናገሩ። በዚህ የተነሳ በመገናኛ ብዙሃኑ ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ ውሱን ሆኖ ለመቆየት መገደዱንም አነሱ። በተለይ ኢትዮጵያ ውስጥ ራሱን ችሎ የጋዜጠኝነት የሚሰጥ ተቋም ባለመኖሩ ማኅበሩ መቋቋሙ ሴት ጋዜጠኞች ለመብታቸውና ለጥቅማቸው እንዲታገሉ ከማድረጉ ባሻገር በርካታ ሴቶችን በአገር ውስጥና በውጪ በሚሰጡ አጫጭር የጋዜጠኝነት ሙያ ኮርሶች በማሰልጠን በስፋት ሴት ጋዜጠኞችን ማፍራት እንደሚያስችልም ጠቀሱ። ማህበሩን በዋንኛነት መመስረት የፈለጉት ለዚህ መሆኑንም አፍረጠረጡት።
ሆኖም ምላሹ በስርዓቱ አቀንቃኞች በበጎ ዓይን አልታየላቻም። እንደ አሳዳሚ ተቆጥሮባቸው እነተካበችን ካድሬ ጥርስ ውስጥ አስገባቸው። ይባስ ተብሎ በዓመት አንዴ በሚከበር የመገናኛ ብዙሃን በዓል ላይ ዕውቋ የሬዴዎዋ ጋዜጠኛ አባይነሽ ብሩ ሴቶችና ሚዲያ የሚል ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅታ አቀረበች። በጽሑፏ በሚዲያው ላይ ብዙ ሴቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ፤ያሉትም በበርካታ ተፅዕኖዎችና ችግሮች ላይ መሆናቸውንም አመላከተች። ችግሩን ለመፍታት ማህበሩ መመስረት መፍትሄ እንደሚሆንም በውይይቱ ጎልቶ ወጣ። ይሄ የአመራሮቹን ቅሬታ አባባሰው። አባይነሽ አመራሮች ፊት ማህበሩ መመስረቱ እንደማይቀር መናገሯም በጥሩ አልተወሰደም።
በዚህ ወቅት ማስታወቂያና ባህል ሚኒስቴር አንድ መሥሪያ ቤት ሆኖ ተቋቋመ። ይሄው ሰበብ ሆነና በማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ የነበረው የሴቶች ጉዳይ መምሪያ በ1988 ዓ.ም ፈረሰ። ተካበችም ከሴቶች መምሪያ ኃላፊነቷ ተነሳች። ወደመጣችበት ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትም ተመለሰች። አብረዋት ይሰሩ የነበሩትም ሁለት ባለሙያዎች ወደየመጡበት የሚዲያ ተቋም ተመለሱ። በወቅቱ የነበሩት የፕሬስ አለቆቿ ፊት አልነሷትም። አንዳንድ የዘመኑ ካድሬዎች ከደረጃዋ ዝቅ ብላ እንድትሰራ ምኞት ቢኖራቸውም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ኃላፊዎች ተሟግተው የድርጅቱን የዜና ማዕከል በዋናነት እንድታስተባብር አደረጓት።
የፎቶግራፍ ባለሙያ ከመመደብ ጀምሮ ጋዜጠኞችን በማሰማራት ለማኔጅመንቱ አባላት ኤዲቶሪያል ላይ የዕየለቱን አፈፃፀም በማቅረብ ከድርጅቱ ኃላፊዎችና ከላይ እስከታች ካለው ሰራተኛ ጋር ተግባብታና ተመካክራ ስታገለግል ለዓመታት ቆየች። ወቅቱን ባታስታውሰውም ወደ አዲስ ዘመን አምዶች ዝግጅት ክፍልም ተዛውራ ስትሰራ ቆይታለች። ዛሬ ላይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚ ፣ ፖለቲካና ሕግ ተብሎ በመከፋፈል እየተሰራበት ያለው ልምድ ከዚሁ መመዘዙንና እየጎለበተ መምጣቱን ታወሳለች። ምን እንጠይቅሎት የሚሉና በርካታ የሕክምና፣ የሕግና ሌሎች የውጪ ባለሙያዎች ከየሙያቸው አንፃር ሰፊ ትምህርታዊና አዝናኝ ማብራሪያ የሚሰጡባቸውም አዳዲስ ዓምዶች ላይ የመስራት ዕድሉን አግኝታ ጡረታ እስከ ወጣችበት 2003 ዓ.ም መጨረሻ አገልግላለች።
አንጋፋዋ ጋዜጠኛ በዚህ ሁሉ መካከል የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር መመስረት ውጥኗን አልዘነጋችም። በራሳቸው ወጪ ሻይ ቡና እያዘጋጁ በሚያደርጉት ውይይት ትገኝ ነበር።
እንዳወጋችን በሥራ ጫና እሷ ባትገኝም በተለይ የኒዘርላንድ ኤምባሲ አንደኛ ፀሐፊ የሆነው ሚስተር ቦካንሰን ለምስረታው ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ቦካንሰን በራሱ ወጪና በራሱ ቤት የራት ግብዣና ሻይ ቡና እያዘጋጀ የተወሰኑ ሴት ጋዜጠኞችን በማሰባሰብ ስለ ማህበሩ ምስረታ ሲያወያይ ቆይቷል። ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበት የኢትዮጵያ መገናኛ ባለሙያዎች ሴት ማህበር (ኢትመባሴማ ) በ1991 ዓ.ም በታህሳስ ወር ተመሰረተ። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የእንግሊዝኛው ክፍል ባልደረባ ፍፁም አለማየሁም በፕሬዚዳንትነት ፣ ተካበች አሰፋ በገንዘብ ያዥነት ተመረጡ። እስከ ፕሬዚዳንትነትና ሥራ አስፈፃሚነት ደጋግማ በመመረጥ አገልግላለች።
ከምስረታው በኋላ በስፋት ድጋፍ ይገኝና ስልጠና ይሰጥ ስለነበረ ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር ማለት ይቻላል። በተለይ ምንም ዓይነት የጋዜጠኝነት ስልጠና ባልነበረበት ወቅት ፍሬደሪክ ኤቨርት የተሰኘው የጀርመን ድርጅት በርካታ አጫጭር ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ማስ ሚዲያ ኢንስቲትዩትም የተቋቋመው ከዚህ በኋላ በመሆኑ አበርክቶው ቀላል አልነበረም። ከዚሁ ጎን ለጎንም ማህበሩ በተለይ ኢንስቲትዩቱ ገብተው የመማር ዕድል ላላገኙ አባላቱና ሴት ጋዜጠኞች በየመገናኛ ብዙሃን ዘርፉ የውጭና የአገር ውስጥ አጫጭርና ረጃጅም ሙያዊ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል። ብዙዎቹ በዘርፉ የራሳቸው የሥራ ዕድል ለመፍጠርና የተሻለ ደረጃ ለመድረስ በቅተዋል።
1997 ዓ.ም ሞቅ ደመቅ ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ባለሙያዎች ሴት ማህበር (ኢትመባሴማ ) እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ መጣ። ምክንያቱ በወቅቱ ስልጣን ላይ የነበረው ኢህአዴግ ከፍተኛ ሽንፈት ስለደረሰበት ያወጣው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራትን የሚያስር አዲስ አዋጅ ነበር። አዋጁ ሁለት መልኮች ሲኖሩት አንዱ በማህበሩ አባላት ላይ ብቻ የሚሰራ ከሆነ ከውጪ አገር 90 በመቶውን 10 በመቶውን ደግሞ ከአገር ውስጥ ማግኘት እንደሚችል ይደነግጋል። ለሶስተኛ ሰው የሚሰራ ከሆነ 90 በመቶውን ከአገር ውስጥ 10 በመቶውን ድጋፍ ከውጪ እንደሚያገኝም ያስቀምጣል። ከፍተኛ ገንዘብ የነበራቸውንና ለማህበሩ ድጋፍ ያደርጉ የነበሩትን ገንዘባቸውን ሁሉ ወረሰ። ለአብነት የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና የነ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ሰብዓዊ መብት ድርጅት ይጠቀሳል።
የውጪ ድርጅቶችም ቢሆኑ ከመንግስት ጋር መጋጨት አይፈልጉምና ሸሹ። የማህበሩ እንቅስቃሴ እጅግ ተቀዛቀዘ። ከ16 በላይ ሰራተኞቹ ውስጥ አብዛኞቹ ደመወዝ ሊከፍላቸው ባለመቻሉ ተበተኑ። በተለይ ጡረታ ወጥታ ሙሉ ጊዜዋን ለማህበሩ ባደረገችበት 2005 ዓ.ም የነበሩት ፀሐፊ፣ ሂሳብና ጽዳት ሰራተኞች ገቢው ሲነጥፍ ለቀቁ። ብዙ መስዋዕትነት ከፍላ ለምስረታ ያበቃችው የክፉ ቀን ወዳጁ ተካበች አሰፋ ብቻ ቀረች። ቢሮው እንዳይዘጋ፤ የማህበሩ ስም እንዳይዘነጋ፤ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ባዶ ቤት መዋል ጀመረች።
ረጃጅም መንገዶችን በእግር በመጓዝ፤ በልመና ፊት በመገረፍ ለዓመታት ገንዘቧንና ጊዜዋን እየሰዋች ህልውናውን አሰነበተችው። የኢትዮጵያ መገናኛ ባለሙያዎች ሴት ማህበር (ኢትመባሴማ) አሁን ላይ በተካበች ጥረት ውዝፍ የቤት ኪራዩን ዘግቷል። ቢሮውን አዘምኖና የራሱ ስቱዲዮ ገንብቷል። ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ አዲስ የቦርድ አመራሮችንም መርጦ ወደ ሥራ ገብቷል። ተካበች በዚህ ውስጥ የቀድሞ ሥራ አስፈፃሚ አባል የሶሎሜ ደስታ አስተዋፅኦ ጎልቶ መውጣቱን በመግለፅ ሃሳቧን አሳርጋለች።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014