
ሐዋሳ:- በሲዳማ ክልል ከዚህ ቀደም ስር ሰድደው የቆዩና በሕዝቡ ዘንድ ጥያቄ ሲያስነሱ የቆዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየት እየተቀረፈ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።
የሲዳማ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት የእኩልነትና የመልማት ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቶ በአገሪቱ በመጣው የለውጡ ሥርዓትና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ አግኝቷል ያሉት አቶ ደስታ፤ ከሕዝቡ የመልማት ፍላጎት ጋር ተያይዞ ይነሱ የነበሩት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ከዚህ ቀደም ለዘመናት ስር ሰድደው የቆዩት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እያገኙ የሕዝቡን ፍላጎት በመለየት እየተሠራ ሲሆን፤ በቀጣይም የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የማይነሳበት ክልል እንዲሆን ይሠራልም ነው ያሉት።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ምሥረታ 2ኛ ዓመት ትናንት በይፋ የተከበረ ሲሆን ይህ ቀን በሲዳማ ሕዝብ ዘንድ የድል ቀን ሆኖ በየዓመቱ እንደሚበከር ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብ የእኩልነትና የመልማት ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ምላሽ እያገኘ መምጣቱን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግሥት ከተመሠረተ በኋላም ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች አመርቂና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት፤ የሲዳማ ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደርና ለመልማት ለዘመናት መራራ ትግል ሲያደርግ ቆይቶ ባገኘው ድል ሳይኩራራ በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ልማት አዙሯል።
የሕዝቡ ፖለቲካዊ ጥያቄ ምላሽ ካገኘበት ማግስት አንስቶም በክልሉ የተረጋጋና አስተማማኝ ሠላም የሠፈነበት ሁኔታ በመፈጠሩ በአሁኑ ወቅት ለቱሪዝም፣ ለኢንቨስትመንት እንዲሁም በተለያዩ ዘርፎች በበርካቶች ዘንድ ተመራጭ ክልል እየሆነ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
የክልላዊ መንግሥት መመሥረት ዕውን ከሆነ በኋላም ባለፉት ሁለት ዓመታት የሕዝቡን ፍላጎት በመለየት በተለይም በመንገድ፣ ውሃ፣ መብራት እንዲሁም ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማሟላት ቅድሚያ ተሰጥቶ መሠራቱንም አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ለሕዝቡ ፍላጎትና ጥያቄ በአንድ ጀምበር ምላሽ መስጠት አይቻልም ያሉት አቶ ደስታ፤ በቀጣይ ትግላችን የሚሆነው ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ሥራ አጥነትና ድህነት በመቅረፍ እንዲሁም ብልሹ አሠራሮችን መታገልና የሕዝቡን የኑሮ ሁኔታ ማሻሻል ነው ብለዋል።
የሲዳማ ሕዝብ ባህላዊ የእርቅና የግጭት አፈታት የአፊኒ ሥርዓትን በመጠቀም በክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ሠላምና ጸጥታ በመስፈኑ በቀጣይም ይህንን ዕሴትና ልማት አጠናክሮ ማስቀጠል የሁሉም ድርሻ እንደሚሆንም አስገንዝበዋል።
የክልሉን ሕዝብ ኑሮ በማሻሻል ወደ ለውጥ ጎዳና የማምራት ዕድሉ በእጃችን በመሆኑ ያለንን ሀብት በአግባቡ ተጠቅመን ለመልማት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።
በክልሉ ለሥራ አጥ ዜጎች በተፈለገው መጠን የሥራ ዕድል ለመፍጠር አለመቻሉን እንደ ተግዳሮት ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዜጎች ሥራ ወዳድና ፈጥረው መሥራት የሚችሉበትን የአመለካከት ለውጥ እስከሚያመጡ የክልሉ መንግሥት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንደሚያደርግም አመልክተዋል።
በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በፖለቲካዊ ዘርፎች የተከናወኑ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠልና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝቡ ፍላጎትና ጥያቄ ምላሽ በመስጠት የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የማይነሱበት ክልል ለማድረግ በየደረጃው ከሕዝቡ ጋር በመቀናጀት ይሠራልም ብለዋል።
አምሳሉ ፈለቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 28 /2014