
አርባ ምንጭ፡- ኢትዮጵያውያን በመቻቻልና በመተባበር ሰላማችንን ጠብቅን ጊዜንና ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀም በትጋት ከሰራን የሀገራችንን እድገትና ክብር ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ እንችላለን ሲሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ተናገሩ።
የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ቅዳሜ ለ35ኛ ጊዜ ተማሪዎችን ባስመቀረበት ወቅት የዩኒቨርሲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በሀገሪቱ የሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ድርሻቸው የጐላ ነው፡፡
ተመራቂዎች በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በቆዩባቸው ዓመታት ሰላምን ለማደፍረስ ከሩቅ የሚሰራጩ እኩይ ተልእኮዎችን ባለማስተናገድ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በፍቅር የሚኖርባት ትንሿ ኢትዮጵያ የመሆኗን ባህል አጥንክረው የወጡ መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ መልካም ስነምግባራቸውን በማስቀጠል በሚሄዱበት አካባቢ ሁሉ ለኢትዮጵያ ሰላም ፣ ልማትና ዴሞክራሲ ቅድሚያ ሰጥተው የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ1979 ዓ.ም በውሃ ቴክኖሎጂ በኢንስቲትዩት ደረጃ ተቋቁሞ ስራ እንደጀመረ የገለጹት ፕሬዘዳንቱ፣ በ1996 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ አድጓል ብለዋል። አሁን በ59 የትምህርት ክፍሎች በ82 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በ114 የ2ኛ ዲግሪ እና በ28 የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርት ፕሮግራሞች አጠቃላይ ከ29ሺ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው የእለቱ ተመራቂዎችን ጨምሮ እስከ አሁን 72ሺ 624 ሙያተኞችን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ሀብት ልማት አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ጠቁመዋል።
በአዲሱ የሀገራችን የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ መሰረት ዩኒቨርሲቲው የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ እንዲሰራ የተለየ መሆኑን ተከትሎ ለሀገሪቱ ልማት ተፈላጊ የሆኑ ፕሮግራሞችን ከፍቶ የማስተማርና የምርምር ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በ2014 በጀት አመት 747 (64 በመቶ) የሚሆኑ መምህራን በምርምር ስራ ታሳታፊ እንደነበሩ ጠቅሰው፣ 114 ሚሊዮን ብር ለምርምር ስራ መዋሉንም ገልጸዋል።
በመጨረሻም ተመራቂዎች ከዩኒቨርሲቲው ያካበቱትን እውቀት፣ ክህሎትና መልካም አስተሳሰብ በመጠቀም በተቋማት ውስጥ ተቀጥረውም ይሁን በግላቸው ስራ ፈጥረው አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ጥሪ አቅርበዋል።
ሌላው በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ክቡር አቶ ፈጠነ ተሾመ የብሄራዊ ሜትሮዎሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ አባል ሲሆኑ እውቀት የማይከስር ሀብትና የሁሉም ነገር መሰረት ሆኖ ማህበረሰብን የሚያሽጋግር እንደሆነ ገልጸዋል። ተመራቂዎች በትምህርት ቆይታቸው ወቅት በንድፈ ሃሳብና በተግባር ያገኙትን እውቀት በሚሰማሩበት የስራ ዘርፍ ሁሉ ለዘላቂ እድገትና ሽግግር እንዲጠቀሙበትም አሳስበዋል።
የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ያሳደሩብንን ተጽእኖዎች እንዲሁም በሀገራችን ላይ የተቃጣውን ጦርነት በመመከት የጀመርናቸውን ሁሉን አቀፍ ልማት ለማከናወን እየተጋን ባለንበት ወቅት የተመረቃችሁ መሆናቸሁ ልዩ ያደርጋችኋል ብለዋል። ችግር ፈቺ ሙያተኞች፣ ሕዝባችሁና ሀገራችሁ የሚጠብቁባችሁን አደራ የምትውጡ፣ በቅንነት የምታገለግሉ፣ ለሀገራችሁ እንቆቅልሽ የመፍትሄ አካል በመሆን በምትሰለፉበት የስራ መስክ ሁሉ የበኩላችሁን የምትውጡ እንድትሆኑ አሳስባለሁ ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የጋሞ ዞና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ፣ ከኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴርና ከሌሎች የፌዴራልና የክልል መስሪያ ቤቶች የተጋበዙ እንግዶች ፣ የሃይማኖት አባቶች ፣ ግጭትን በእርጥብ ሳር የማብረድ እሴትን ያኖሩት የጋሞ ሽማግሌዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል። የአርባ ምንጭ ከተማ የኪነት ቡድን የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ዘፈኖችን በመጫወት የአዳራሹን የደስታ ድባብ አድምቀዋል።
በእለቱ በተከናወነው የምረቃ መርሃ ግብር በመጀመሪያ ዲግሪ 2062፣ በ2ኛ ዲግሪ 490 እና በ3ኛ ዲግሪ 9 በድምሩ 2ሺ 561 ተማሪዎች መመረቃቸው ታውቋል።
ኢያሱ መለሰ
አዲስ ዘመን ሰኔ 27/2014