
ሩስያ በ2016ቱ የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ጣልቃ ስለመግባቷ ለማጣራት በልዩ መርማሪ ሲካሄድ የቆየው ምርመራ ውጤቱ ይፋ ሆኗል፡፡ የምርመራ ውጤቱም ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሩስያ ባለስልጣናትና ድርጅቶች ጋር ንክኪ እንደነበራቸው የሚያሳይ ማስረጃ አለመገኘቱን አሳይቷል፡፡ የአሜሪካ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ለኮንግረሱ በጻፉት ደብዳቤ፤ በልዩ መርማሪው ሮበርት ሙለር ሲካሄድ የቆየው ምርመራ የፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫ ቡድን ከሩስያ ባለስልጣናት ጋር ግንኙነት እንደነበረው የሚያመለክት በቂ ማስረጃ እንዳልተገኘ አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ‹‹የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ከሩስያ ጋር በመመሳጠር በ2016ቱ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ተፅዕኖ ስለማሳደሩ የሚያመለክት ማስረጃ እንዳልተገኘ የልዩ መርማሪው የምርመራ ውጤት ያሳያል›› በማለት ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዝደንት ትራምፕ ፍትሕ እንዲዛባ ስለማድረጋቸው የሚያሳይ በቂ ማስረጃ እንደሌለም ጠቁመዋል፡፡
የልዩ መርማሪው ሪፖርት ይፋ መሆኑን ተከትሎ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ‹‹ከሩስያ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ አልነበረንም፤ ምንም ዓይነት የፍትህ መዛባት አልፈፀምንም፤ ከተጠያቂነትም ነፃ ሆነናል፤ አሜሪካን ታላቅ የማድረግ ተግባራችንን እንቀጥላለን›› በማለት በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ይሁን እንጂ፤ የልዩ መርማሪው ሪፖርት የፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ከሩስያ ባለስልጣናትና ተቋማት ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ማስረጃ ማግኘት አለመቻሉ ፕሬዝደንቱ ሙሉ በሙሉ ከተጠያቂነት ነፃ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በደብዳቤያቸው አመልክተዋል። ፕሬዝደንቱ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉባቸው ጉዳዮች ስለመኖራቸውና ስላለመኖራቸው በግልፅ የታወቀ ነገር የለም ብሏል፡፡
ከሩስያ መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸው በርካታ ግለሰቦች ለትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ድጋፍ ለማድረግ ጥያቄ አቅርበው እንደነበርና የትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን አባላት ድጋፉን ስለመቀበላቸውና ከሩስያ መንግሥት ጋር ስለመተባበራቸው የሚያሳይ ማስረጃ እንዳልተገኘ የልዩ መርማሪው ሪፖርት ያሳያል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ባር፤ ልዩ መርማሪውሮበርት ሙለር ምርመራውን በሚያካሂዱበት ወቅት የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ፍትሕን ለማዛባት ጫና ስለማድረጉ የሚያመለክት በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ እርሳቸውና ምክትላቸው ሮድ ሮዝንስቴይን ፕሬዝደንቱ የሕግ ጥሰት ፈፅመዋል ብለው እንደማያምኑም ገልጸዋል፡፡
የልዩ መርማሪው ሪፖርት የፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ቡድን ከሩስያ ባለስልጣናትና ተቋማት ጋር ንክኪ እንደነበራቸው ማስረጃ ማግኘት እንዳልተቻለ ቢያመለክትም፤ ፕሬዝደንቱ ሙሉ በሙሉ ከተጠያቂነት ነፃ ይሆናሉ? ወይስ አይሆኑም? የሚለው ጉዳይ ግን አወዛጋቢ ሆኗል፡፡
የምርመራው ውጤት ፕሬዝደንቱ ሙሉ በሙሉ ከተጠያቂነት ነፃ ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ ቢያመለክትም፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ግን የፕሬዝደንት ትራምፕ አስተዳደር ልዩ መርማሪው ሮበርት ሙለር ምርመራውን በሚያካሂዱበት ወቅት ፍትሕን ለማዛባት ጫና ስለማድረጉ የሚያመለክት በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ፕሬዝደንቱ የሕግ ጥሰት እንዳልፈጸሙ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል፡፡ ይህም ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትልቅ ፖለቲካዊ ፋይዳ እንዳለው ተገልጿል፡፡
በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር የአሜሪካ ፍትሕ መስሪያ ቤት (Department of Justice) ቃል አቀባይ የነበሩት ማት ሚለር፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር የልዩ መርማሪው ሪፖርት ከደረሳቸው ከ48 ሰዓታት በኋላ ፕሬዝደንቱ የሕግ ጥሰት አለመፈጸማቸውን በራሳቸው መወሰናቸው ከፍትሕ መስሪያ ቤቱ አሰራር ያፈነገጠ አካሄድ እንደሆነ ለአልጀዚራ ተናግረዋል፡፡
‹‹በልዩ መርማሪው ሪፖርት ላይ የተካተተ ምክረ ሃሳብ የለም፡፡ ልዩ መርማሪው ለ22 ወራት ያህል መጠነ ሰፊ ምርመራ አድርገው ለማካተት ያልፈጉትን ማጠቃለያና ምክረ ሃሳብ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ግን ሪፖርቱ ከደረሳቸው ከ48 ሰዓታት በኋላ ፕሬዝደንቱ የሕግ ጥሰት እንዳልፈጸሙ የሚያመለክት ማጠቃለያ መስጠታቸው ያልተለመደና ተገቢ ያልሆነ አሰራር ነው፡፡ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ውሳኔ አጠራጣሪ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ውሳኔዎች ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ በኃላፊነት የሚሰጡ አይደሉም›› ብለዋል፡፡
ዴሞክራቶቹ ናንሲ ፔሎሲ እና ቸክ ሹመር የልዩ መርማሪው ሙሉ ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ጉዳዩን በያዙበት መንገድ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ሁለቱ አንጋፋ ዴሞክራቶች በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የልዩ መርማሪው ሪፖርት ፕሬዝደንቱን በሕግ ጥሰት ከተጠያቂነት ነፃ እንደማያደርጋቸው መግለፁ የሪፖርቱ ሙሉ ሃሳብ በአስቸኳይ ለሕዝብ ይፋ መሆኑ እጅግ አስፈላጊ ስለመሆኑ እንደሚጠቁም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ገለልተኛ የሆኑ ሰው እንዳልሆኑና ጉዳዩን ፍትሐዊ በሆነና ከወገንተኛነት በጸዳ መልኩ ያዩታል ተብሎ እንደማይጠበቅም ፔሎሲ እና ሹመር ተናግረዋል፡፡
ናንሲ ፔሎሲ የኮንግረስ አባላት የሆኑ ዴሞክራቶችን ሰብስበው ‹‹የአሜሪካ ሕዝብ እውነቱን የማወቅ መብት አለው፡፡ ግልፅነት የአሜሪካ ፖለቲካ ዋነኛ መርህ ነው›› በማለት የልዩ መርማሪው ሪፖርት ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡
በአሜሪካ ምክር ቤት የደህንነት ኮሚቴ ሊቀ- መንበር አዳም ስቺፍ ሪፖርቱ በአስቸኳይ ለሕዝብ ይፋ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹የአሜሪካ ሕዝብ ልዩ መርማሪው ለሁለት ዓመታት ገደማ ያህል ያከናወኑትን ምርመራ ውጤቱን የማወቅ መብት አለው፡፡ ሁሉም ሰው ስለእያንዳንዱ ጉዳይ ያለውን ጥያቄና ጥርጣሬ ግለሰቦችን በተናጠል የመጠየቅ ግዴታ ስለሌለበት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ የሪፖርቱን ሙሉ ሃሳብ ለሕዝቡ ይፋ ማድረግ አለባቸው›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ከልዩ መርማሪው የተላከላቸውን ሪፖርት ከፍትሕ መስሪያ ቤቱ ባለስልጣናትና ባለሙያዎች ጋር እንደተመለከቱትና ግልፅነት ባለው ሁኔታ ለኮንግረሱ እንደሚያቀርቡም ቃል ገብተዋል፡፡
በእርግጥ፤ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዊሊያም ባር ለኮንግረሱ የፃፉት ደብዳቤ ፕሬዝደንት ትራምፕና ረዳቶቻቸው በቀጣዮቹ ጊዜያት ሌሎች ምርመራዎች እንደሚጠብቋቸው የሚያመለክት ፍንጭ አለው። ለአብነት ያህል የኒውዮርክ ዓቃቢያነ ሕግ በቶማስ ባራክ የተመራው የትራምፕ በዓለ ሲመት ኮሚቴ ለበዓለ ሲመቱ ካዋለው ገንዘብ መዋጮ ጋር በተያያዘ ምርመራ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል፤ ኤሊዮት ብሮይዲ የተባሉ የካሊፎርኒያ የደህንነት ባለሙያና በ2016ቱ የሪፐብሊካን ፓርቲ ጉባዔ ምክትል የፋይናንስ ኃላፊ የነበሩት ግለሰብ ያስተባበሩት የገንዘብ መዋጮ መርሃ ግብርም ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል፡፡ ፕሬዝደንት ትራምፕ ስቶርሚ ዳንኤልስ ከተባለች ሴት ጋር የነበራቸው ግንኙነትም ሌላ ምርመራ ሊያስከፍትባቸው እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡
አሜሪካዊው የሕግ ባለሙያ ሮበርት ስዋን ሙለር፤ ሩስያ እ.ኤ.አ በ2016 በተካሄደው አወዛጋቢው የአሜሪካ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ጣልቃ በመግባት የሪፐብሊካን ፓርቲ ተወካይ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ምርጫውን እንዲያሸንፉ አድርጋለች የሚለውን አቤቱታ ለ22 ወራት ያህል ሲመረምሩ ቆይተዋል፡፡ የሙለር ምርመራ በሕግ ባለሙያዎች፤ በአሜሪካ የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (Federal Bureau of Investigation – FBI) ሰራተኞች፤ በስለላና እንደጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ገለፃ በወንጀል ምርመራ ሰራተኞች የተደገፈ ነበር። የምርመራ ቡድኑ 500 የዓይን ምስክሮችን ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል። ከ500 በላይ የፍተሻ ትዕዛዞችን አውጥቷል፤ ሁለት ሺህ 800 ሰዎች የምስክርነት ቃላቸውን እዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፤ ለ13 ጊዜያት የውጭ መንግሥታትን ትብብር ጠይቋል፡፡ በምርመራው ወቅት ሮበርት ሙለር የፕሬዝደንት ትራምፕ የምርጫ ዘመቻ ኃላፊ ፖል ማናፎርት እና የግል ጠበቃ ማይክል ኮኸንን ጨምሮ በ34 ሰዎች ላይ ክስ መስርተዋል፡፡
በ2018 ከተካሄደው የአሜሪካ አጋማሽ ዘመን ምርጫ ወዲህ ብቻ አምስት የምክር ቤቱ ኮሚቴዎች በፕሬዝደንት ትራምፕ ላይ ምርመራዎችን ማካሄድ መጀመራቸው የሚታወስ ነው፡፡ ለአሁኑ ‹‹ከተጠያቂነት ነፃ ነኝ›› ብለው ያወጁት ፕሬዝደንት ትራምፕ በቀጣይ ጊዜያት ምን ሊገጥማቸው እንደሚችል በግልፅ የታወቀ ነገር የለም፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 18/2011
በአንተነህ ቸሬ ��b�x�