ኮሚሽኑ በተሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ይሠራል

አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተሰጠው ተጨማሪ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ። በአማራ ክልል በቅርብ ጊዜ ውስጥም በክልል ደረጃ አጀንዳዎችን ለመሰብሰብ እየተሠራ መሆኑን አመልክተዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የኮሚሽኑ የተፈቀደለት የሦስት ዓመታት ጊዜ በመጠናቀቁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኮሚሽኑ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በቅርቡ የአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶታል። በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ቀሪ ሥራዎችን ለማጠናቀቅም እየሠራን ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል በአራት ክላስተር በመከፋፈል በዞን ደረጃ አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ መሠራቱን ጠቁመው፤ ባህር ዳር ክላስተር፣ ጎንደር ክላስተር፣ ደሴ ክላስተርና ደብረብርሃን ክላስተር በመከፋፈል የአጀንዳ ማሰባሰብና በክልል ደረጃ ለሚካሄደው ምክክር የሚሳተፉ ሰዎች መመረጣቸውን አውስተዋል።

በቅርብ ጊዜ ውስጥም በክልል ደረጃ አጀንዳዎችን ለመሰብሰብ እየሠራን ነው ብለዋል።

በትግራይ ክልል የተባባሪ አካላት ሥልጠና፣ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፎችን ማካሄድ በቀጣይነት እንደሚከናወኑ ጠቅሰው፤ ለዚህ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ከክልሉ አመራሮች እንዲሁም ምሁራን ጋር ውይይት ተደርጓል ነው ያሉት።

በፌዴራል ደረጃ ከሚገኙ ተቋማት እና ማህበራት ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰቢያ መድረክን ማዘጋጀት፣ ከዲያስፖራው ተሳታፊዎችን መለየት እና አጀንዳ ለመሰብሰብ እየተሠራ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፤ በተለያየ መልኩ የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን ማጠናከር፣ መለየት፣ በየጭብጡ ማዘጋጀት፣ ቅደም ተከተል እንዲይዙ ተደርጎ ለኮሚሽኑ ምክር ቤት እንደሚቀርብ ጠቁመዋል።

ተለይተው በተደራጁ አጀንዳዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት፣ አጀንዳዎችን በኮሚሽኑ ምክር ቤት በመቅረጽ ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፣ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አወያዮች እና አመቻቾችን መለየት፣ ማሠልጠን እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባዔው ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግም የኮሚሽኑ ቀጣይ የቤት ሥራዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ሀገር አቀፍ ንቅናቄን በማካሄድ የግንዛቤ ሥራዎችን በማስፋት የነቃ ተሳትፎ እንዲኖር ማስቻል ብሎም የሕዝብ ባለቤትነትን ማረጋገጥ፣ አሳታፊና አካታች የሆነ የሀገራዊ ምክክር ጉባዔን ማካሄድ፣ ከምክክሩ የሚገኙ ምክረ ሃሳቦችን ማጠናቀር እና ምክረ ሃሳብ ማቅረብም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አመላክተዋል።

ተገቢውን ምክክር አድርጎ የኢትዮጵያን ሰላም እንድታገኝ ማድረግ የዘመናችን ዓድዋ አድርገን ልንወስደው እንደሚገባ የጠቆሙት ዮናስ (ዶ/ር)፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኙ አካላት ወደ ምክክሩ መጥተው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎችም በጸሎት፣ በምክርና ሌሎችም ሀገራዊ እሴቶች በመጠቀም በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖችን ወደ ሰላማዊ ምክክር መድረክ እንዲመጡ የጀመሩትን ሥራ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም በጠራው አስቸኳይ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሶስት ዓመታት የሥራ አፈፃፀም በማዳመጥ የኮሚሽኑን የሥራ ዘመን ለአንድ ዓመት ማራዘሙ ይታወሳል።

ፋንታነሽ ክንዴ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You