የእግር ኳሱን ችግር ለመፍታት ታዳጊዎች ላይ ይሠራል

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ስፖርት ታሪክ በተለይም በእግር ኳስ የቀዳሚነት ድርሻ ያላት ሀገር ብትሆንም እንደ አጀማመሯ ግን መቀጠል አልቻለችም፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ይነሱ እንጂ በመፍትሄው ላይ ሲሠራም አይስተዋል፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውጤታማነት ችግርን ለመፍታት በብሄራዊ ቡድን ላይ ከመሥራት ይልቅ ታዳጊዎች ላይ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በማመን እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል፡፡

የአፍሪካ ዋንጫ እና የኮንፌዴሬሽኑ መሥራች የሆነችው ኢትዮጵያ እንደቀድሞ በመድረኩ ተከታታይ ተሳታፊና ተፎካካሪ እንዲሁም ከዚያ ያለፈ የመድረኩ ዐሻራ እንዲኖራት የእግር ኳስ ተሰጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች ላይ መሥራት አስፈላጊ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየክልሉ ያሉ የታዳጊ ወጣት ፕሮጀክቶችን ከመደገፍ ጎን ለጎን ከፊፋ ጋር በመሆን በፕሮጀክት የታቀፉ የታዳጊ ወጣቶች ውድድርን በማስጀመር ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሲዳማ ክልል ፌዴሬሽኖች ጋር ያደረገው ስምምነትም የዚሁ ውጤት ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ የእግር ኳስን ችግር ከመሠረቱ ለመፍታት የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና ክለቦች በታዳጊዎች ሥልጠና ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡ ፌዴሬሽኑ በቅርቡ ይፋ ባደረገው አዲሱ የኢትዮጵያ ታዳጊ እና ወጣቶች እግር ኳስ ልማት ፖሊሲ መሠረት በክልል ፌዴሬሽኖች የሚመሩ ከ17 ዓመት በታች ውድድሮችን ለማካሄድ ይፋ ያደረገው ፕሮጀክትን በሚመለከትም ገለጻ ተደርጓል፡፡ በታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ልምድ ያላቸውና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የታዳጊዎች እግር ኳስ ልማት አማካሪ የሆኑት ኢንስትራክተር አምሳሉ ፋንታሁን ለተሳታፊዎች ስለሚከናወነው ሥራ ሰነድ አቅርበው በተሳታፊዎች ሃሳብና አስተያየት ተሰጥቶበታል።

በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጥናትና ምርምር እና የማማከር አገልግሎት ዳይሬክተር በተዘጋጀው መድረክ ላይም የኢፌዴሪ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሃመድ፣ የአካዳሚው ከፍተኛ አመራሮችና አሠልጣኞች፣ ተመራማሪዎች፣ የቀድሞ የብሄራዊ ቡድን አሠልጣኞችና ተጫዋቾች አንዲሁም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ባስተላለፉት መልዕክትም ስፖርት ውስብስብ የሀገሪቱን ችግሮች የመፍታት ትልቅ አቅም እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ የሀገሪቱን የስፖርት ስብራቶች ለመጠገን ምን መሥራት እንደሚገባ ከብሄራዊ ፌዴሬሽኖች ጋር በመሆን ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል፡፡ መንግሥት አሸናፊ ሀገር ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት በስፖርቱም ዘርፍ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው፤ ፌዴሬሽኖችም ከግል ጥቅም ይልቅ ሀገርን እና ሥራን በማስቀደም ስፖርቱን ለማሳደግ ታዳጊ ወጣቶች ሥልጠና ላይ በማተኮር የመጡትን እድሎች በአግባቡ በመጠቀም ስፖርቱ በዕውቀትና በቅንጅት እንዲመራ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ከመደገፍ ባሻገር የአሠራር ሥርዓቶችን እንደሚዘረጋም አመላክተዋል፡፡

የአካዳሚው ዋና ዳይሬክተር አቶ አምበሳው እንየው በበኩላቸው፤ በሠልጣኞች ምልመላ፣ መረጣ፣ ሥልጠና እና የውድድር ሞዴሎች ለአካዳሚው የተሻለ ልምድ በመውሰድ ለመተግበር ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም የታዳጊ ወጣቶች ስፖርት ሥልጠና ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት፣ ብሄራዊ ፌዴሬሽኖች እና ክለቦች በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።

ታዳጊዎችን በሳይንሳዊና ዘመናዊ ሥልጠና በማብቃት ለክለቦችና ብሄራዊ ቡድኖች ከሚያፈሩ ተቋማት መካከል አንዱ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አካዳሚው ሠልጣኞችን ከፕሮጀክቶች እንዲሁም ሌሎች ሥፍራዎች በማወዳደርና ታለንታቸውን በመመዘን የሚመለምል ሲሆን፤ ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች መካከል አንዱ እግር ኳስ ነው፡፡ በዚህም በዕድሜ እርከን የሚደረጉ ብሄራዊ ቡድኖችን ጨምሮ በተለያዩ ውድድሮች ላይ በመሳተፍ ውጤታማ ታዳጊዎችን በማሠልጠን ላይ እንዳለ ማስመስከር ችሏል፡፡ ከሥልጠናው ባሻገር በጥናትና ምርምር ክፍሉ ሙያዊ አገልግሎቶችንም በመስጠት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ብርሃን ፈይሳ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You