በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ለአርሶ አደሩ ፈርጀ ብዙ ጥቅም እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፡- በትግራይ ክልል 62 ሺ ሄክታር መሬት ላይ ሲሠራ በቀየው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ለምግብነት እና ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ የሥነ-ሕይወት ተክል ምርቶች እየለሙ መሆኑን የክልሉ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለፀ፡፡

በትግራይ ክልል የግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሚኪኤለ ምሩፅ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በክልሉ በሁሉም ወረዳዎች ላይ በዘመቻ ሲሠራ በቆየው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ፤ የአፈርና ውሃ አጠባበቅ ዘዴ በጥሩ አፈፃፀም ላይ ይገኛል፤ ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃው ሥራ ጎን ለጎን አዳዲስ እና ለየት ያሉ ለምግብነት እና ለእንስሳት መኖ የሚያገለግሉ የሥነ-ሕይወት ተክል ምርቶችን የማምረት ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

ቀደም ሲል በሴፍቲኔት እና በተለያዩ የልማት ፕሮጀክጀክቶች የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎች ሲሠሩ እንደነበር የጠቀሱት አቶ ሚኪኤለ፤ በተለይ በአሁኑ የዘመቻ ሥራ ህብረተሰቡ ከሕይወቱ ጋር በማስተሳሰር በንቃት መሳተፉን አስታውሰዋል፡፡

ዘመቻው በሙያተኞች እየተደገፈና ፅርአ፣ አጉላዕ፣ አፅቢ በተባሉ አካባቢዎች ማህበረሰቡ በነቂስ ወጥቶ አካባቢው የሚገኙት ወንዝ እና ተፋሰሶችን በመጠቀም የተለያዩ አዳዲስ ተክሎች ማለትም የዝሆን ሳር፣ ቢሾ ሳር የመሳሰሉትን እያለማ ይገኛል ብለዋል፡፡ በሓውዜን፣ ፃዕዳ እምባ፣ ክልተ አውላዕሎ እና ሓይቂመስሓል አካባቢዎች የመኖ ምርት በስፋት ለማምረት በዘመቻ እየተሠራ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

የመኖ ምርት ላይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ የሚገኘው በዋናነት የወተት ተዋፅኦን ለማሳደግ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሩ የተሻለ የወተት ምርት ሲያገኝ ቤተሰቡን ተጠቃሚ ለማድርግ የማይቸገር መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ አሁንም ከአካባቢው ማህበረሰብ ወደ መቐለ ከተማ በቀን አራት ሺህ ሊትር ወተት ድረስ ሲሸጥ መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ የወተት ምርትን ከፍ ለማድረግ እና በተለይ በፆም ወቅት የወተት ተዋፅኦ ገበያ ስለሚቀዘቅዝ ከተለያዩ ፕሮጀክቶች ጋር በመሆን የወተት ማቀነባበሪያዎች በክልል ደረጃ በስፋት እንዲፈጠሩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በተባይ ጠፍቶ የነበረው የበለስ ተክል አሁን በአዲስ መልክ እየተተከለና በስፋት እየለማ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ምርቱ ለሰው እና ለእንስሳት በምግብነት የሚያገለግል ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

በእንስሳት ሀብት ላይ በትኩረት እየሠራ ነው ያሉ ሲሆን፤ ኢኮኖሚን ለማሳደግ በዋናነት ዶሮ ለማርባት፣ በግ ፣ ፍየል እና ከብት ለማድለብ በሚመቹ ቦታዎች ላይ ህብረተሰቡ እንዲሳተፍ በሀገር ደረጃ በተቀመጡ አቅጣጫዎች መሠረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

በየዓመቱ በዘመቻ መልክ በሚሠራው የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገብን ቆይተናል ያሉት ኃላፊው፤ አፈርና ውሃ ስንገድብ በዛውም ለእንስሳት መኖ የሚሆን ምርት በማምረት ውጤታማ ሆነናል ብለዋል፡፡

በክልሉ የተሳካ የግብርና ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው ፤ በተለይም ማህበረሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሙሉ ቀልቡን ወደ ሥራ እና ወደ ልማት በማድረግ በክልሉ የሚፈጠሩ የተለያዩ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ሳይገድቡት በልማት ሥራው ላይ በመሳተፍ አካባቢውን መለወጥ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

ሔርሞን ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You