የኤች አይ ቪ መከላከያ ክትባት ወሳኝ የደህንነት ማረጋገጫ ሙከራን አለፈ

የኤች አይ ቪ ቫይረስን ይከላከላል የተባለው እና በየዓመቱ የሚሰጠው ክትባት ከደህንነት አኳያ አስተማማኝ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችለውን የመጀመሪያ ደረጃ ወሳኝ ሂደት ማለፉን ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡ ሌናካፓቪር የተባለው ይህ የጸረ ኤች አይ ቪ ክትባት ቫይረሱ በሰዎች ህዋስ ውስጥ እንዳይባዛ የሚያደርግ አቅም ያለው መሆኑን ላንሴት በተባለ የህክምና ጋዜጣ ያወጣው ሪፖርት ገልጿል፡፡

ወሳኝ የተባለውን ይሄን የመጀመሪያ ደረጃ የደህንነት ማረጋገጫ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ ያለፈው ክትባቱ ወደፊት የሚደረጉ ሙከራዎችን ማለፍ ከቻለ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግል የመጀመሪያው የኤች አይ ቪ የቅድመ መከላከል ክትባት መሆን እንደሚችል ተገልጿል፡፡ ኤች አይቪ የሌለባቸው አርባ ሰዎች ተለይተው የጎላ ተጓዳኝ ችግር ወይም አስጊ የደህንነት ስጋት የለበትም የተባለው ሌናካፓቪር ክትባት በጡንቻቸው ላይ ተሰጥቷቸው የደህንነት ሙከራው እንደተደረገ ታውቋል፡፡

የሙከራ ክትባቱ ለሰዎቹ ከተሰጣቸው ከ56 ሳምንታት በኋላ የመከላከያ መድሃኒቱ በሰውነታቸው ውስጥ እንዳለ ለማወቅ መቻሉ የክትባቱን አስተማማኝነት ያመላከተ መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ለዚህ ዓመት በተዘጋጀው በቫይረስ እና በሌሎች በሽታዎች ዙሪያ በተካሄደው ጉባዔ ላይ የተሳተፉ የክትባቱ ተመራማሪዎች ወደፊት የሚደረጉት የሙከራ ሂደቶች የተለያየ ሁኔታ ላይ ስላሉ በርካታ ሰዎችን ሊያካትቱ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በየዓመቱ የሚሰጠው ይህ የኤች አይ ቪ መከላከያ ክትባት አንድ ጊዜ የሚወሰድ በመሆኑ የቅድመ መከላከያውን የሚወስዱ ሰዎችን ቁጥር ከፍ እንዲል ሊያደርገው ይችላል ብለዋል፡፡ ቴሬንስ ሂጊንስ የተባለው የኤች አይ ቪ በጎ አድራጎት ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሪቻርድ አንጌል በየእለ ይወሰድ የነበረው የቅድመ መከላከል እንክብል ታላቅ ለውጥ ተብሎ እንደነበር አስታውሰው በመርፌ የሚሰጠው ዓመታዊ ክትባት ሊመጣ መሆኑ ደግሞ የተሻለ ለውጥ የሚያመጣ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሙከራ ላይ ካለው ከዚህ ክትባት ሌላ በአሁኑ ሰዓት ሰዎች ለበሽታው ከመጋለጣቸው በፊት ለመከላከል የሚረዱ በየእለቱ የሚወሰድ እንክብል እና በየስምንት ሳምንቱ የሚሰጥ ክትባት በአገልግሎት ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ የኤች አይ ቪ ቅድመ መከላከያ እንክብሎች በሽታውን ከመከላከል ረገድ በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ ቢሆኑም በየቀኑ መወሰድ ስላለባቸው ለተጠቃሚዎች አስቸጋሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው የተገለጸው፡፡

በ2023 የወጣ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያመላክተው በመላው ዓለም 39.9 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ እንደሚገኝ ሲገልጽ ከነዚህም ውስጥ 65 በመቶ ያህሉ በአፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ መግለጹ ይታወሳል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት፣ ግሎባል ፈንድ እና የተባበሩት መንግሥታት የኤች አይ ቪ ኤይድስ ፕሮግራም የበሽታውን መከላከያ አቅርቦት ማሻሻልን ጨምሮ ኤች አይ ቪ በሽታን በአውሮፓውያኑ 2030 ለማጥፋት በጋራ እየሠሩ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

ኤች አይ ቪ እስከዛሬ ድረስ ዘላቂ ፈዋሽ መድሃኒትም ሆነ ክትባት ካልተገኘላቸው በሽታዎች መካከል አንዱ ሲሆን በየእለቱ የሚወሰዱ እንክብሎች እና የአጭር ጊዜ የቅድመ መከላከያ ክትባት ቢኖሩትም ተደራሽነታቸው ውስን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን በሽታው በደማቸው እንደሚገኝ ያወቁ ሰዎች ጤናማ እና የተስተካከለ ሕይወትን እንዲመሩ የጸረ ኤች አይ ቪ ህክምና መድሃኒቶች በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ በስፋት ጥቅም ላይ በመዋል ለበርካቶች የመኖር ዋስትናን በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በተመራማሪዎች ዘንድ በየጊዜው ተስፋ እየታየበት ያለው የኤች አይ ቪ መድሃኒት የማግኘት ሂደት በሌናካምፓቪር ውጤታማነቱ እየታየ ይገኛል፡፡ መረጃውን ከቢቢሲ አገኘን፡፡

ዘላለም ተሾመ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You