
ገና ልጅ ሳለች በአንድ ዓይኗ ላይ የደረሰባትን ክፉ አጋጣሚ አትረሳም፡፡ ክብነሽ ኬሬ ከቀናት በአንዱ ሠፈራቸው ከሚገኝ አንድ ዋርካ ሥር አረፍ አለች፡፡ ዋርካው ትልቅና ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ጥላ ሥር ዘወትር በርካታ የቀዬው ልጆች ይሰበሰባሉ፡፡ በቦታው በተገኙ ጊዜም ዋርካው የውስጡን ፍሬ አይነፍጋቸውም፡፡ በቅርንጫፎቹ ያዘለውን የበዛ በረከት ያወርድላቸዋል፡፡ የበሉትን በልተው የተረፋቸውን ጌጥ መሥራት ልማዳቸው ነው፡፡ ጌጡን ሠርተው በአንገት በእጃቸው ይዋቡበታል፡፡
የዛን ቀን ትንሽዋ ክብነሽ በጥላው ስር ስትገኝ የዋርካውን ፍሬ አስባ ነው፡፡ ጥቂት ከቆየች ትልቁ ዋርካ በሳሉን፣ ከጥሬ እያለ ፍሬዎች ያወርድላታል፡፡ እንደ ሁሌው ከጣፋጩ በረከት እየለቀመች ትበላለች፡፡ ዕለቱን በቦታው ስትደርስ ዋርካው ብዙ ፍሬዎችን አዝንቦ ጠበቃት፡፡ ክብነሽ መሬቱን የሞሉትን የበዙ ፍሬዎች ስታይ ፈገግ አለች፡፡ አሁን ያሻትን እየለቀመች መብላት፣ ማጣጣም ትችላለች፡፡
ፍሬዎቹን ሰብስባ ለቅማ ስትጨርስ ዓይኖቿ ከመበላት ያለፉትን ልዩ ፍሬዎች አስተዋሉ፡፡ እነዚህ ፍሬዎች መሀላቸው ተበስቶ ለጌጣጌጥ ይሆናሉ፡፡ ሁሌም በፍሬዎቹ መዋብን የምትሻው ክብነሽ አጋጣሚውን ልትጠቀም አሰበች፡፡ ልጅ ብትሆንም ፍሬውን መብሳት እንደማያቅታት ገምታለች። እንዲህ ለማድረግ ግን አስተካክሎ የሚበሳላትን ሹል ነገር ማግኘት አለባት፡፡ እጆቿ መሀል ያሉትን ፍሬዎች አጥብቃ ወደ አንድ አቅጣጫ አመራች፡፡ በዚህ ሥፍራ ያየችው የጃርት እሾህ ፍሬውን በወጉ እንደሚበሳው ተማምናለች፡፡ ደስ እያላት እሾሁን አንስታ ተመለሰች፡፡ ጥቂት ቆይታ ፍሬዎቹን በተነችና መሀላቸውን ለመብሳት አዘጋጀች ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ እሾሁ እየበሳ ጌጥ ይሠራላታል፡፡ ይህን ስታስብ ፊቷ በፈገግታ ተሞላ፡፡
ትንንሽ እጆቿ የቻሉትን ያህል እየተጫኑ የፍሬውን መሀል ልብ ለመብሳት ታገሉ፡፡ እንዳሳበችው ሆኖ ፍሬው በዋዛ አልተበገረም፡፡ ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ ደጋግማ እየታገለች ሞከረች፣ ሞከረች፡፡ ለውጥ የለም፡፡ ንድድ እያላት እግሮቿ ላይ አስቀምጣ የእጆቿን እሾህ ወደፊት ተጭና በሀይል ገፋችው፡፡ እሾሁ ፍሬውን ስቶ አቅጣጨውን ቀየረ።
በአፍታ ፍጥነት የሾለው እሾህ አፍንጫዋን አልፎ ከዓይኖቿ ደጃፍ ደረሰ፡፡ አመጣጡ ቅጽበታዊ የሚባል ነበር። ግራ ዓይኗ ከመርዛሙ የጃርት እሾህ ጥቃት ማምለጥ አልቻለም። የሾለው ጫፍ የዓይኗን ጠርዝ አልፎ መሀል ብሌኗ ላይ ተመሰገ፡፡ ሁኔታው አስደንጋጭና ፈጣን ሆነ፡፡ ዓይኗ በጃርቱ እሾህ መጎዳቱ እንደታወቀ አባቷ አዲስአበባ ምኒልክ ሆስፒታል አምጥተው አሳከሟት፡፡
እንዲያም ሆኖ የዓይኗ መዳን ጉዳይ ተስፋ አስቆራጭ ነበር፡፡ የሕክምናው ውጤት አንድ ዓይኗ ከብርሃን እይታ መጋረዱን አረጋገጠ፡፡ ክብነሽ የልጅነት ዕድሜዋን በተሰበረ ስሜት ያዘች፡፡ የወላጅ አባቷ መሞትና የአንድ ዓይኗ መጥፋት ለውስጧ ኀዘን እያቀበለ ወጣትነቷ ላይ አደረሳት፡፡
ከዓመታት በፊት ከአገሯ ርቃ ወደ ከተማ ስትዘልቅ ኑሮን አሸንፋ እንደምትኖር እርግጠኛ ሆና ነበር፡፡ እንዳሰበችው ሆኖ ከአዲስ አበባ ሕይወት ጋር በሥራ ተዋወቀች፡፡ የዛኔ ለትዳር አጋር የሆናት ባለቤቷ ጎኗ ነበር፡፡ እሱ ሁሌም የጎደለውን እየሞላ ‹‹አይዞሽ›› ይላታል፡፡ ጥንዶቹ በአዲስ አበባ ጎጆን ቀልሰዋል፡፡ በሃሳብ እየተረዳዱ በኑሮ እየተጋገዙ ሕይወትን ሲመሩ አብሮነታቸው ከልብ ነው፡፡
ባልና ሚስት የጋራ ልጅ አላቸው፡፡ ሁሌም ከእነሱ አልፎ ስለአንድዬዋ ልጃቸው ዓለም ይጨነቃሉ፡፡ ሁለቱም ዛሬን ከተጉ ነገ መልካም እንደሚሆን አይጠፋቸውም፡፡ ይህ እውነት ጥንዶቹን በሥራ ሲያተጋ ፣ ሲያበረታ ይውላል፡፡ ክብነሽ ራሷንና ቤተሰቧን ለማገዝ መተዳደሪያ አላጣችም፡፡ በትንሹ የጀመረችው ቁርስ ቤት ጥቂት የማይባሉ ደንበኞችን አፍርቶላታል፡፡ ከሥራዋ የምታገኘው ገቢ ለቤት ኪራይና ለዕለት ወጪ አሳምሮ ይበቃታል፡፡
ሶስቱ ቤተሰቦች በፍቅርና በደስታ እየኖሩ ነው፡፡ ዛሬን በመተሳሰብ መዝለቃቸው የነገን መሠረት ለመገንባት ያግዛል። ከቀናት በአንዱ ግን ይህ በጎ ጅምር እንቅፋት ገጠመው። የቤቱ ምሰሶና አባወራ ድንገት በሞት ተቀደመ። ይህ እውነት ለወይዘሮዋ እጅግ ከባድና አስደንጋጭ ነበር፡፡ ከባሏ ሞት በኋላ አንድ ልጇን ያለ አባት ማሳደጉ፣ ኑሮን በብቸኝነት መግፋቱ ፈተናት፡፡ ከጊዜያት በኋላ ልጇን ሀገርቤት ልካ አዲስ አበባ ተመለሰች፡፡ ቤተሰቦቿ አቅመ ደካማ ናቸው፡፡ልጇን በወጉ ለማሳደግ የእሷን እጅ ይጠብቃሉ፡፡ ክብነሽ ለዚህ አልሰነፈችም። የጀመረችውን ሥራ አጠንክራ ራሷን፣ ልጇንና ቤተሰቧን ታግዛለች፡፡
ጊዜያቶች ነጎዱ፣ዓመታት አለፉ፡፡ እናት አዲስ አበባ፣ ልጅ ደግሞ ሀገርቤት እየኖሩ ነው፡፡ ሁለቱ በተገናኙ ጊዜ የልባቸውን ያወጋሉ፡፡ ልጅ አሁን አስራሶስት ዓመት ሆኗታል፡፡ ማደግ መለወጧን ስታስብ ግን ጎዶሎዋን አትዘነጋም፡፡ ሁሌም ብቸኛ ልጅ መሆኗ ያስከፋታል፡፡ እናቷን ባገኘቻት ቁጥር እህት አልያም ወንድም እንድትወልድላት ትለምናታለች፡፡
እናት ክብነሽ ከአባወራዋ ሞት በኋላ በብቸኝነት ኖራለች።አሁን ግን ይህን ታሪክ ቀይሮ የልጇን ጥያቄ የሚመልስ ምዕራፍ ላይ ልትገኝ ጊዜው ደርሷል፡፡ ባል አግብታ አዲስ ሕይወት እንደጀመረች ፤ወንድ ልጅ ወልዳ የልጇን ጥያቄ መለሰች፡፡ ልጆቿ ከአንድ ሁለት ሲሆኑላት ውስጧ ተደሰተ። ይህ መሆኑ ግን ሕይወቷን በመልካም አላቀናም፡፡ ከአዲሱ አባወራዋ ጋር እንዳሰበችው መግባባት አልቻሉም፡፡ አጋጣሚው የቀድሞ ኑሮዋን አዛብቶ የእጇን ሲሳይ በተነው፡፡ ልጅ እያሳደገች ኑሮን መግፋት፣ ሕይወትን መምራት ከበዳት። የነበረው እንዳልነበር ሆኖ ፈተናት፡፡
ትናንት ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትተርፈው ወይዘሮ ዛሬ የሰው እጅ ልታይ ግድ ሆነ፡፡ ለዓመታት በስኬት የቆየችበት የምግብ ሥራ ለኪሳራ ተዳርጎ አስጨነቃት፡፡ ክብነሽ ሕይወት በሌላ መልኩ ቢያገኛት ኑሮዋ ተቀየረ፡፡ የአንድ ዓመት ልጇን ይዛ የቤት ኪራይ መክፈል እስኪሳናት ተቸገረች፡፡
በአንድ አጋጣሚ ወደሰፈሯ የደረሱ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 04 አካላት በድንገት ከብነሽን ጎበኝዋት፡፡ ሕይወትና ኑሮዋ ግልጽ ነበር፡፡ የመሥራት አቅም ቢኖራትም ለመኖር የሚያስችል በቂ ጥሪት ከእጇ የለም፡፡ የክፍለ ከተማው ሰዎች ሁሌም እንዲህ አይነት ወገኖችን ማገዝና መደገፍ ዓላማቸው ነው፡፡
ክብነሽን የመሰሉ ብርቱ ሴቶች በየቤቱ ያለሥራ መቀመጣቸውን ያውቃሉ፡፡ ሴቶቹ ለመሥራት የሚያስችል ድጋፍ ከተቸራቸው ከራሳቸው አልፈው ለሌሎች እንደሚበጁ ከእስከዛሬው ልምዳቸው አረጋግጠዋል፡፡ እነዚህ አካላት በርካታ ሴቶችን በጥናት ለይተው ካገኙ በኋላ ለሥራ ያዘጋጇቸውን የተስማሚ ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመለገስ ሥራ እንዲጀምሩና ራሳቸውን በወጉ እንዲችሉ ዕድሉን ይከፍታሉ፡፡
ክብነሽ ይህ እውነት ሲነገራት ራሷን በሥራ የምታበረታበትን ምርጫ ለይታ ወሰነች፡፡ ለእሷ ኑሮና ሕይወት የሚበጀው የቺፕስ መጥበሻ ማሽን መሆኑ አልጠፋትም፡፡ ይህ ቁስ በእጇ ቢገባ የቀድሞ ሙያዋን ተጠቅማ ራሷን ለመርዳት ይቻላታል፡፡
ውስጠቷን በወጉ የተረዱት አካላት ያሰበችውን ለመፈጸም አልዘገዩም፡፡ የእሷን ፍላጎት ይሞላል፣ ራሷን በሥራ ያበረታል ያሉትንና የመረጠችውን ማሽን በስጦታ አበረከቱላት፡፡ ዛሬ ክብነሽ በሕይወት መንገድ ላይ የገጠማትን ፈተና ታግላ ለማሸነፍ ጉዞ ጀምራለች፡፡ ትናንት አንገቷን ያስደፋት ችግር ነገም እንዳይከተላት እየጣረች ነው፡፡
ክብነሽ በልጅነቷ በደረሰባት ጉዳት ዛሬ ድረስ አንድ ዓይኗ አያይላትም፡፡ እንዲያም ሆኖ እጅ አትሰጥም፡፡ በተሰጣት የተስማሚ ቴክኖሎጂ ውጤት ራሷን ችላ ልጆቿን ለማሳደግ ርምጃዋ አይዘገይም፡፡ ሕይወት በየአጋጣሚው ቢፈትናትም ከወደቀችበት ልትነሳ ጥንካሬዋን ደርባለች፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም