የሰው ኃይል ክህሎት ግንባታ-ለአምራች ኢንዱስትሪው ምርታማነት

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ እንደ ሀገር ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራባቸው ከሚገኙ ዘርፎች መካከል የኢንዱስትሪ ዘርፍ አንዱ ነው፡፡ ዘርፉ ከግብርናው ቀጥሎ ሰፊ የሰው ኃይል የሚሸከም እንደመሆኑ ለሀገር የኢኮኖሚ እድገትም ሆነ ለዜጎች ኑሮ መሻሻል ወሳኝ ሚና እንዲጫወት ይጠበቃል፡፡ በቀጣይ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ በሚደረገው መዋቅራዊ ሽግግርም በምጣኔ ሀብቱ ውስጥ ትርጉም ያለው ድርሻ እንዲኖረው ይፈለጋል፡፡ መንግሥት ይህን ሁሉ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ እየሠራ ይገኛል፡፡

በዘርፉ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባሮች መካከል ለሰው ኃይል ክህሎትና አቅም ማጎልበት ሥራ የተሰጠው ትኩረት ይጠቀሳል፡፡ በእዚህ ሥራም ከአምራች ኢንዱስትሪው ባሻገር መንግሥትና የሚመለከታቸው ተቋማትና የግሉ ዘርፍ በቅንጅት ርብርብ እያደረጉም ናቸው፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ አምራች አንዱስትሪዎች የሚወዳደሩት በቴክሎጂያቸው፣ ባላቸው የሰለጠነ በፍጥነትና በሚፈለገው መጠን ማምረት በሚችል የሰው ኃይላቸው እንደሆነ ይታመናል፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሰለጠነ የሰው ኃይል በሌለበት ምርታማነት፤ ምርታማነት በሌለበትም ተወዳዳሪነት እንደማይታሰብም የዘርፍ ምሁራን ያነሳሉ፡፡ ተወዳዳሪነት ከሌለ በቀጣይነት እያደጉ የመሄድ አቅም አይኖርም፡፡

በዚህ ረገድ አምራች ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸውን የሰው ኃይል ለማፍራት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ይታመናል፡፡ ይህንን ሚናቸውን ይበልጥ ለማጠናከርና በኢንዱስትሪና በስልጠና ተቋማቱ መካከል ያለውን ትስስር በማጎልበት ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችል ያለመ የውይይት መድረክ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በጋራ አካሂደዋል፡፡

በዚህ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሚያዘጋጀው ሁለተኛው ምዕራፍ ሦስተኛው ዙር የስለኢትዮጵያ መድረክ “ክህሎት ስለኢትዮጵያ” በሚል በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ በአምራች ዘርፍ ያለውን የሰው ኃይል በማብቃት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ማጎልበት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩ የአምራች ኢንዱስትሪውን ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሳደግ የሰው ኃይሉን አቅም ማሳደግና ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ ማብቃት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር ተካሂዷል፡፡ በመድረኩ ላይ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡልልታ እንደተናገሩት፤ መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪውን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ መርሃ ግብሮችን በመንደፍና የአሠራር ሥርዓቶችን በማሻሻል እየሠራ ይገኛል፡፡

በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የምጣኔ ሀብቱ ምሰሶዎች የተባሉትን አምስት ዋና ዋና ዘርፎችን በመለየት ሲሰራ መቆየቱን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰው፤ በዚህም የማኑፋክቸሪንግ (አምራች) ኢንዱስትሪው ያለማቋረጥ እያደገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ወደ ሙሉ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ በመግባት የአምራች ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ማነቆ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲፈታ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡ ማሻሻያው ከነባሮቹ ባሻገር አዳዲስ የዘርፉን አንቀሳቃሾች ጭምር መሳብ እያስቻለ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በ2015 በጀት ዓመት የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ከሰባት በመቶ እንደማይበልጥ አስታውሰው፤ በ2016 በጀት ዓመት 10 ነጥብ 01 እድገት ማስመዝገብ መቻሉን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ዘርፉ እያደገ እና ተስፋ ሰጪ የሆኑ ውጤቶች እያስመዘገበ ስለመሆኑ ማሳያ እንደሆነ ተናግረው፤ ከዚህ በመነሳትም በተያዘው 2017 በጀት ዓመት ከ11 በመቶ በላይ እድገት ለማስመዝገብ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ይህን እድገት ለማስቀጠል አምራች ኢንዱስትሪው ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካትና በዘርፉ የዳበረ ክህሎት ያለው ሰፊ የሰው ኃይል ለማፍራት እየተሠራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳሉት፤ መንግሥት ገቢ ምርትን በመተካት ረገድ ትልልቅ ውሳኔዎችን አሳልፏል፤ በተለይም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ሀገር ውስጥ እንዲመረቱ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባሮች ተኪ ምርቶችን በማምረት በኩል ከፍተኛ ለ ውጥ እየመጣ ይገኛል ፡፡

ይህንንም ለአብነት ጠቅሰው ሲያብራሩ፤ ‹‹የፀጥታ አካላት ልብስ መቶ በመቶ ከውጭ ይገባ ነበር፤ አሁን ግን ይህን ምርት በሀገር ውስጥ መቶ በመቶ ማምረት ተችሏል፤ ሀገሪቱ ከራሷ ፍጆታም አልፋ ለጎረቤት ሀገራት ለመሸጥ ንግግር ጀምራለች፤ ለሀገሮቹ ምርቱን እያሳየን አወንታዊ ምላሽ እየሰጡን ይገኛሉ›› ብለዋል፡፡ ይህም መንግሥት ቁርጠኝነቱን ወስዶ ምርቱ በሀገር ውስጥ እንዲመረት በማድረግና ተቋማቱን ከአምራች ኢንዱስትሪው እንዲገዙ አቅጣጫ በማስቀመጡ የተገኘ ለውጥ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

እሳቸው እንዳብራሩት፤ በተመሳሳይ የቆዳና ቆዳ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በጥራትና በስፋት እንዲያመርትና ገቢ የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን ለማስቀረት እየተሠራ ነው። በአሁኑ ወቅት በተለይም የትምህርት ቤት ጫማዎችን መቶ በመቶ በሀገር ውስጥ ለማምረት እየተሠራ ነው፡፡ ሀገሪቱ ያላትን ሰፊ የእንስሳት ሀብት ታሳቢ በማድረግም መንግሥት የቆዳ ኢንዱስትሪውን ቁርጠኝነቱን ወስዶ እየደገፈ ይገኛል። ይህም ሀገሪቱን በዓለም ገበያ ላይ ጭምር ተወዳዳሪ እንደሚያደርጋትም ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ልምድ በመቀመርም የምርት ማሸጊያዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ከረጢት አምራች ኢንዱስትሪ፣ ከስታራትአፕ ኤጀንሲና ከደረጃዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለማምረት ስምምነት ተፈጥሮ በአሁኑ ወቅት የማምረት ሥራው ተጀምሯል›› ይላሉ፡፡ ይህንን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባም ያስገነዝባሉ፡፡

እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ዘርፉን ለማሳደግ በመንግሥት እየተሠሩ ካሉ ሥራዎች መካከል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅምና አጠቃቀምን ማሳደግ የሚለው አንዱ ነው፡፡ በዚህ ረገድም በ2014 በጀት ዓመት የኢንዱስትሪው የማምረት አቅም 46 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛነት በወቅቱ ከሰው ኃይል፣ ግብዓት አቅርቦትና መሠረተ ልማት ጋር በተያያዘ የነበሩት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡

ሚኒስቴሩ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና የኢንዱስትሪውን የማምረት አቅም ለማጎልበት ሰፊ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፤ እያደረገም ይገኛል፡፡ በተለይ ከሰው ኃይል ክህሎት ጋር የተያያዘውን ችግር ለመፍታት ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ጋር በመሆን የክህሎት አቅምን ለማሳደግ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

ኢኮኖሚው በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ እንዲጓዝ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የሰለጠነ የሰው ኃይል አስፈላጊና ወሳኝ ነው፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለኢኮኖሚ ዕድገት ቁልፍ በመሆኑ በሰለጠነ የሰው ኃይል መደገፍ ይኖርበታል። የሥራ ዕድል መፍጠር ይገባዋል፡፡ የሰው ኃይል ክህሎት አቅምን ማጎልበት ግብርና፣ ቱሪዝምን፣ ማዕድን እና የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ለማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ ሚኒስቴሩ የኢንዱስትሪ አቅም ግንባታ ስትራቴጂ አዘጋጅቷል።

በዚህ ረገድ እንደ ሀገር በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች ቢኖሩም፤ አምራች ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን ክህሎት የሚያሟሉት ጥቂቶች እንደሆኑም ሚኒስትር ዴኤታው ይገልጻሉ፡፡ ‹‹የሰው ኃይሉን በተከታታይ ለማብቃት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ኢንዱስትሪው ከሚፈልገው ክህሎት አንፃር የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አለ፤ ለኢንዱስትሪው ክህሎት ያለው የሰው ኃይል በበቂ ሁኔታ እየቀረበለት አይደለም›› ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል የሥራ እድል የሚፈልጉ ወጣቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በአምራች ኢንዱስትሪው እና በሥራ አጥ ወጣቶች ችሎታ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ እንደሚያስፈልግም አቶ ታረቀኝ ይናገራሉ፡፡ ለዚህም ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሠራ ነው ብለዋል።

ከአምራቹ በተጨማሪ የኢንዱስትሪ አመራሩም የክህሎት ክፍተት እንዳለበት ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተው፤ ‹‹አምራች ኢንዱስትሪውን በሚፈለገው መልኩ ለማሳደግም ክህሎት ያለው አመራር ማፍራትን ይጠይቃል›› ብለዋል። የዘርፉን ባህሪ፤ የኢንዱስትሪ ምርት የሚጠይቀውን የጊዜ ገደብና ጥራት ማወቅ ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ሚኒስቴሩ ጥናት ማካሄዱንና ከዚህ በመነሳትም የኢንዱስትሪ አቅም ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ታረቀኝ ማብራሪያ፤ ባለፉት ዓመታት በአምራች ዘርፍ ከ2014 እስከ 2016 በአማካኝ 256 ሺ የሥራ እድል በየዓመቱ መፍጠር ተችሏል፡፡ በዚህም በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው አስረኛው ዓመት መጨረሻ ላይ 800 ሺ ለሚጠጉ ዜጎች የሥራ እድል ለመፍጠርና ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡

የሀገሪቱ ኢኮኖሚ በገቢ ምርቶች ላይ ተመስርቶ የቆየበት ሁኔታ የኢኮኖሚ እድገቱ በታሰበው ልክ ዘላቂነት ያለው እንዳይሆን አድርጎት መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ የግብርናው ዘርፍ ለኢኮኖሚው ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑንና በአንጻሩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ አስተዋፅኦ ከስድስት በመቶ እንደማይበልጥ አመልክተዋል፡፡ ይህም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር በጣም ዝቅተኛ በሚባል አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ እንደሚያመላክት አስታውቀዋል። ኢኮኖሚውን ከውጭ ጥገኝነት ለማላቀቅ አምራች ኢንዱስትሪውን መደገፍ እና የሚፈልገውን ችሎታ ማሟላት እንዲሁም በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ‹‹በክህሎት የበቃ የሰው ኃይል ለአንድ ሀገር ምን አስተዋጽኦ ይኖረዋል›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ጽሑፍ ያቀረቡት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተሻለ በሬቻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ‹‹የዕድገት ጉዟችንን ለማሳካት የክህሎት ሚና ትልቅ ድርሻ አለው›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ስብራትን መጠገን የሚያስችሉ በርካታ ክህሎት መር ሥራዎች ተሠርተዋል። በክህሎት የበለጸጉ ዜጎችን ለኢንዱስትሪዎች ለማቅረብ አቅርቦት መር የሆነው ሥርዓት ወደ ፍላጎት መር እንዲቀየር ተደርጓል፡፡

‹‹የብልፅግና ጉዞን ለማሳካት የክህሎት ሚና ትልቅ ነው›› ያሉት ተሻለ (ዶ/ር)፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ ኢኮኖሚያዊ ስብራትን መጠገን የሚያስችሉ ክህሎት መር ሥራዎች መሠራታቸውን አመልክተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው እንዳስታወቁት፤ የግሉ ዘርፍ የሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግም የተለያዩ ርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ፡፡ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና በባህሪው ተግባር ተኮር ሲሆን፤ ተግባር ተኮር ሥልጠናን እውን ለማድረግ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት የሚያስችል ሕጋዊ ማሕቀፍ ተዘጋጅቷል።

ብቁ የሰው ኃይል ማለት በእውቀቱ፣ በክህሎቱ፣ በአስተሳሰቡ እና በተነሳሽነቱም ለሥራ ዝግጁ የሆነ ኃይል ማለት ነው። የሥልጠና ጥራትን አስጠብቆ የሚፈለገውን ክህሎት የተላበሱ ዜጎችን ለማፍራት የኢንዱስትሪዎች እና የሥልጠና ተቋማትን ትስስር ለማጠናከር እየተሠራ ይገኛል፡፡

በቴክኒክና ሙያ ተቋማት በአጫጭር ሥልጠና ከሦስት ሚሊዮን በላይ፣ በመደበኛው ደግሞ ከ500 ሺ በላይ ዜጎች እየሠለጠኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ በዘርፉ ያለውን የባለሙያዎች የክህሎት ጥራት ለማምጣት የተደረገው ጥረት እና የማስተዋወቅ ሥራ በቂ ነው ተብሎ አይታመንም ብለዋል።

ለክህሎት ልማት ትኩረት መስጠት እና ለሙያና ሙያተኞች የሚሰጠውን ክብር ማሳደግ እንደሚገባም አስገንዝበው፤ ‹‹እንደ ሀገር የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ትርክትን መገንባት ቀዳሚ ተግባራችን ሊሆን ይገባል›› ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡ በተለይም አዳዲስ ትርክቶች ከሚፈጠርባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ክህሎት መሆኑን ይጠቅሳሉ። ይህም ከሙያና ሙያተኛ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የተዛቡ ትርክቶችን ለማስተካከል እንደሚያግዝ ያስረዳሉ።

እሳቸው እንዳስታወቁት፤ በዚህ ረገድ እንደ ሀገር ያጋጠመውን የትምህርት ጥራት ስብራት ለመጠገን (ለማደስ) አዲስ የትምህርት ሥርዓት ተቀርጾ እየተተገበረ ነው፤ በዚህ ሂደት ለውጥ ከተደረገባቸው ዘርፎች አንዱ የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ይዘትን ማስተካከል ነው፤ ለዚህም ተቋማትን ለማዘመን፣ ደረጃውን የጠበቀ የሥልጠና ሥርዓትና የበቃ ባለሙያ እንዲኖር ለማድረግ እየተሠራ ነው።

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና በባህሪው ተግባር ተኮር መሆኑን አንስተው፤ በሀገሪቱ በእውቀት፣ በክህሎት እና በአስተሳሰቡ ዝግጁ የሆነ ብቁ የሰው ኃይል ማፍራት ላይ እየተሠራ ስለመሆኑም ነው ያብራሩት፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በበኩላቸው፤ ‹‹እያንዳንዱ አምራች ኢንዱስትሪ የሚፈልገውን ብቁ የሰው ኃይል ለመገንባት በትብብር መሥራት ይገባዋል ይላሉ፡፡ ሚኒስቴሩ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ ‹‹ክህሎትን በማበልፀግ ረገድም እንደ ሀገር ልንንከባከባቸውና ልንጠብቃቸው የሚገቡ ሀገር በቀል እውቀቶች አሉ ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡ 26 የሚደርሱ ሀገር በቀል እውቀቶች ተለይተው በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተቱ ለማድረግ እየተሠራ ነው›› ሲሉም ያመለክታሉ፡፡

በቀጣይም በሀገር በቀል እውቀቶች የማሻሻያ ሥራ እንደሚሠራ ወይዘሮ ሙፈሪያት ጠቁመው፤ ይህም ሙያና ሙያተኞችን ለማክበር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ያስረዳሉ። አዳዲስና ነባር የሥራ ዘርፎችን ማጣመር እና ጀማሪ ሥራ ፈጣሪዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ፡፡ ኢትዮጵያን ከፍ ማድረግ የሚቻለው ሥራ በክህሎት ሲመራ መሆኑንም አስገንዝበው፤ ‹‹ያለውን እውቀት ያለምንም ቁጠባ ሀገር ላይ ማዋል ያስፈልጋል›› ብለዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You