
አዲስ አበባ፡- የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን በፍጥነትና በሙሉ አቅም በተግባር በመተርጎም አፍሪካ ከስምምነቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በላቀ ትኩረት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ። 57ኛው የአፍሪካ የገንዘብ፣ ፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው መክፈቻ ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሰመሬታ ሰዋሰው እንደተናገሩት፣ ስምምነቱ አፍሪካውያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነታቸውን ለማረጋገጥ የያዙት የጋራ ህልም በመሆኑ በፍጥነትና በሙሉ አቅም ወደ ተግባር በመለወጥ አፍሪካ ከስምምነቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በከፍተኛ ትኩረት መሥራት ይገባል። 55 ሀገራትንና ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ሕዝብን የሚያጠቃልለው የዓለም ትልቁ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት የተፈረመው ለአዲስ የምጣኔ ሀብት እድገትና ተጠቃሚነት ጠንካራ መሠረት ለመገንባት ነው። ከዚህ አኳያም ስምምነቱ ተጨባጭ የሆነ ተግባራዊ ትርጉም ይፈልጋል።
እንደእሳቸው ገለፃ፣ ስምምነቱን ወደ ተግባር በመለወጥ የስምምነቱን ሙሉ አቅምና እቅድ መጠቀም ይገባል። በዚህም የአፍሪካውያንን የልማት አቅምና የመልማት ፍላጎትን ማሳካት ያስፈልጋል። የስምምነቱ ትግበራ ሁሉን አቀፍ ጥረት፣ ትብብርና ቁርጠኛነት ይፈልጋል።
‹‹የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት ሕጋዊ ማዕቀፍ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካን የምጣኔ ሀብት ትስስር የሚያጎለብት ታላቅና አሻጋሪ ርምጃ ነው። በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረግን የንግድ ልውውጥ በማመቻቸት፣ ፖሊሲዎችን በማጣጣም እና የንግድ መሰናክሎችን በማስወገድ የአህጉሪቱን የምጣኔ ሀብት አቅም ለመጠቀም የሚያስችል መሣሪያ ነው›› ብለዋል። ከስምምነቱ ትግበራ የሚጠበቁት የኢንዱስትሪያላይዜሽን፣ የሥራ ፈጠራና የድህነት ቅነሳ ስኬቶች ለአጀንዳ 2063 እውን መሆን ወሳኝ ማሳያዎች እንደሆኑም ገልጸዋል።
የመሠረተ ልማትና የፖሊሲ ክፍተቶች፣ የፋይናንስ እጥረት እና በአባል ሀገራት መካከል ያሉ የአቅም ልዩነቶች ስምምነቱን በመተግበር ሂደት የሚያጋጥሙ ፈተናዎች እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ችግሮቹ የተቀናጁና በፈጠራ የታገዙ መፍትሄዎችን እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ጠንካራ ምጣኔ ሀብታዊ ትስስር ያላት አፍሪካን የማየት ታሪካዊ ፍላጎት ያላት በመሆኑ ለስምምነቱ ትግበራ ቁርጠኛ መሆኗንም ወይዘሮ ሰመሬታ ገልጸዋል። ሀገሪቱ ለመሠረተ ልማት ግንባታ የሰጠችው ትኩረት እና ለስምምነቱ መሳካት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ትግበራ የዚህ ፍላጎት ማሳያዎች መሆኑንም በአብነት አንስተዋል።
የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የፕሮግራም ድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ፔድሮ በበኩላቸው፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት አፍሪካውያን በአንድ ድምፅ እንዲናገሩ የሚያግዝ የምጣኔ ሀብትና የፖለቲካ መሣሪያ ነው። ይህን ለማሳካት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ሁሉ ማሟላት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የነፃ የንግድ ቀጣናው ስምምነት ትግበራ መሰናክል ከመረጃ እጥረት እንደሚጀምር የተናገሩት ምክትል ዋና ጸሐፊው፣ ‹‹የአፍሪካ የግል ዘርፍ በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ስለ ንግድ ቀጣናው በቂ መረጃና ግንዛቤ የላቸውም። የግሉ ዘርፍ መረጃ ሳይኖረው በሀገራት መካከል ያለው የንግድ ልውውጥ እንዲሻሻል መጠበቅ የለብንም። ስለሆነም ትግበራው ሁሉን አቀፍ የሆነና የተቀናጀ ተግባር ይፈልጋል›› ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ የባለብዙ ወገን የንግድ ስምምነቶች ብዙ ፈተናዎች እያጋጠሟቸው እንደሚገኙ ጠቁመው፣ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት መሰል ችግሮችን ለመቋቋም እንደሁነኛ አማራጭ ሊወሰድ የሚችል መሣሪያ እንደሆነ ገልጸዋል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም