በደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ ዞን ሰባቦሩ ወረዳ ተወልደው አድገዋል። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከትምህርት መልስ ቤተሰባቸውን በሥራ አገልግለዋል። ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙ እንደመሆናቸው ታዲያ ቤተሰባቸውን በግብርና ሥራ እንዲሁም በከብቶች ጥበቃ በማገልገል የሚስተካከላቸው አልነበረም። ከጥጃ ጀምሮ ትላልቅ ከብቶችን በመጠበቅ ጎበዝ እረኛ እንደነበሩ ያስታውሳሉ።
‹‹ከከብት የበለጠ ሀብት የለም›› ብለው ከማመን ባለፈ ለከብቶች ጥልቅ ፍቅር ካላቸው አርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙት የዛሬው የስኬት እንግዳችን አቶ ውዴሳ ያቺሴ ናቸው። የጉጂ ሀይላንድ ኮፊ መስራችና ባለቤት እንዲሁም የቡአ አብሳ ማዕድን ልማት የቦርድ ፕሬዚዳንት ናቸው። እንግዳችን ከቡና እንዲሁም ከማዕድን ልማት በተጨማሪ በሆቴልና በሌሎች ዘርፎችም ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ችለዋል።
ገና በለጋ ዕድሜያቸው ከብቶች በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ሲጠብቁ የተመለከቱት ወላጅ አባታቸው ከብቶች እንዲያረቡና የከብቶች ባለጸጋ እንዲሆኑ ግፊት ያሳድሩባቸዋል። እርሳቸው ግን በከብት ሀብት ልማት ከሚገኝ ባለጸጋነት ያለፈ ራእይ ነበራቸው፤ የተለያዩ የንግድ ሀሳቦች በውስጣቸው ይንሸራሸሩ ነበርና አባታቸው ላቀረቡላቸው አርብቶ አደርነት ብቻ እጅ አልሰጡም። እንዲያውም እጅግ ዝቅተኛ ከሆነው የከረሜላ ንግድ የጀመሩት ስራ ዛሬ ፍሬያማ ሆኖ ትላልቅ ድርጅቶችን ማፍራትና መምራት አስችሏቸዋል።
ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ቤተሰባቸውን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ውዴሳ፤ ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር›› በሚባልበት በደርግ ዘመነ መንግሥት ገና አፍላ ጎረምሳ ነበሩ። ታዲያ በዚህ ወቅት ለውትድርና በጥብቅ ይፈለጋሉ፤ ትምህርታቸውን አቋርጠው በግዳጅ ወደ ምስራቅ ጎጃም ቢላኩም፣ ፍላጎታቸው ትምህርትና ንግድ በመሆኑ ጠፍተው ወደ ቀዬቸው ይመለሳሉ።
እንደተመለሱም 10ኛ ክፍል ተምረው በመፈተን ጥሩ ውጤት አምጥተው ወደ 11ኛ ክፍል ያልፋሉ። ይሁንና ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር›› የሚለው ድባብ ገና ያልጠፋ በመሆኑ ትምህርታቸውን መግፋት አልሆነላቸው አለ። ስለዚህ በውስጣቸው ያለውን የንግድ ፍላጎት ወደ ተግባር ለመለወጥ በመወሰን የከረሜላ ንግዳቸውን ቀጠሉ። ከከረሜላ ንግድ ቀጥለውም ዶሮ እየገዙ መሸጥ ጀመሩ። ‹‹ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሩ ይሄዳል›› እንደሚባለው የንግድ ሥራውን ወደ ትናንሽ ሸቀጣ ሸቀጦች በማሳደግ ሀሳባቸውን ዕውን ለማድረግ ይታትሩ ጀመር።
‹‹ከልጅነቴ ጀምሮ ለንግድ ከፍተኛ ፍላጎት ነበረኝ›› የሚሉት አቶ ውዴሳ፤ ተማሪ እያሉ ጀምረው ትናንሽ የተባሉ ነገሮችን በመሸጥ ልብሳቸውንና የትምህርት ቁሳቁሱን ለግላቸው ያሟሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም ቤተሰባቸውን ከማገዝ ባለፈ ራሳቸውን ለመቻል የነበራቸው ከፍተኛ ፍላጎትና ትጋት ለዛሬ ስኬት መሰረት የጣለላቸው እንደሆነም መገንዘብ ይቻላል።
በትንሿ የከረሜላ ንግድ ጀምረው ዶሮ፣ ፍየል፣ ከብቶችና በእህል ንግድም ሰርተዋል። ትምህርታቸውን 11ኛ ክፍል ላይ አቋርጠው ሙሉ ጊዜያቸውንም ለእዚህ ስራ ማዋል ውስጥ በመግባታቸው ስራው ይበልጥ ውጤታማ መሆን እየቻለ መጣ። ወዲያውም ዳጎስ ያለ ገንዘብ ከማግኘታቸውም በላይ አመርቂ ለውጥ ማምጣት እንደቻሉ ያስታውሳሉ።
ተወልደው ያደጉበት ደቡብ ኦሮሚያ ጉጂ ዞንም በወርቅ የታወቀ እንደመሆኑ ዘርፈ ብዙ ከሆነው የንግድ ሥራቸው በተጨማሪ በማዕድን ዘርፍ ተሰማርተው ወርቅ ገዝተዋል፤ ሸጠዋል። ወቅቱ ከፍተኛ ገንዘብ ማግኘት የቻሉበትና ውጤት ያስመዘገቡበት ቢሆንም የንግድ ሌላኛው ገጽታ የሆነው ኪሳራም ደርሶባቸው ነበር። ኪሳራው ከአስር ዓመት በላይ አታግሏቸዋል። መኖሪያ ቤታቸው ሳይቀር በባንክ ዕዳ ተይዞ ለጨረታ እስኪቀርብ ድረስ በብዙ ተቸግረዋል።
በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ታዲያ አንድም ቀን ተስፋ መቁረጥ ያልታየባቸው አቶ ውዴሳ፤ ለችግር እጅ ሳይሰጡ ተቋቁመው ለማለፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። ጥረታቸውም በፈጣሪ እገዛ ጭምር ፍሬያማ ሆነላቸው። አስር ዓመታትን ያስቆጠረው የኪሳራ ወቅት ታዲያ ትልቅ ትምህርት ያስተማራቸውና መሸጋገሪያ ድልድይ እንደሆናቸው ይናገራሉ።
በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ውስጥ ሆነው ሲታትሩ ባስተዋላቸው አንድ ወዳጃቸው አማካኝነት ወደ ቡናው ዘርፍ መግባታቸውን ያስታወሱት አቶ ውዴሳ፤ በወቅቱ የነበራቸውን ትጋትና ጥንካሬ የተረዳው አብሮ አደጋቸውም በቡና ልማትና ግብይት ላይ ትኩረት አድርገው ቢሰሩ ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ይመክራቸዋል። ለንግድ ሥራ ብቻ ልዩ ፍላጎት የነበራቸው አቶ ውዴሳም፤ ምክሩን ተቀብለው በአካባቢያቸው ቡናን ማልማት ጀምረዋል።
በጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ የመጀመሪያውን የቡና ኢንቨስትመንት ፈቃድ አግኝተው በ1992 ዓ.ም በ200 ሄክታር መሬት ላይ ዘርፉን የተቀላቀሉት አቶ ውዴሳ፤ አራት ጓደኞቻቸውን በማሳተፍ ሞርሞራ የቡና ተክል ልማትን አቋቋሙ። በወቅቱ በርካታ የቡና ችግኞችን በማዘጋጀት ልማቱን ተያያዙት። ምርቱ ፍሬ የሚሰጠው ከአራትና አምስት ዓመት በኋላ በመሆኑ በአምስት ዓመት ውስጥ ቡናው አፍርቶ ለገበያ ማቅረብ ቻሉ።
አራት ጓደኞቻቸውን አስከትለው የጀመሩት ሞርሞራ የቡና ልማት ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ያለና ሌሎች እህት ኩባንያዎችንም መውለድ የቻለ መሆኑን ያነሱት አቶ ውዴሳ፤ የተለያዩ ኩባንያዎችን ማቋቋም እንደቻሉም ይናገራሉ። በቀዳሚነት ልጆቻቸውን ጨምሮ በቤተሰባቸው ስም የተቋቋመው ጉጂ ሀይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን ቡናን አልምቶ ለውጭ ገበያ እያቀረበ የሚገኘው የግላቸው ኩባንያቸው ሲሆን በመቀጠልም በማዕድን ልማት ቡአ አብሳ ማዕድን ልማት የተባለውን ኩባንያ በ21 አባላት ማቋቋም ችለዋል።
በ21 አባላትና በ21 ሺ ብር ካፒታል የተቋቋመው ይህ የማዕድን ልማት ማህበር በአሁኑ ወቅት 315 አባላትን ያቀፈ ሞዴል የማዕድን ልማት ኩባንያ ሆኗል። በዋናነት ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማቅረብ ትልቅ ውጤት እያስመዘገበ የሚገኘው ይህ ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ከወርቅ በተጨማሪ ታንታለምና የተለያዩ የከበሩ ማዕድናትን በማልማት ከ43 ሚሊዮን ብር በላይ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ማፍራት ችሏል።
ከሌሎች ጋር ከተቋቋሙት የማዕድን ልማት እና የሞርሞራ ቡና ልማት በተጨማሪ በግላቸው የሚመሩት ጉጂ ሀይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን መስራችና ባለቤት የሆኑት አቶ ውዴሳ፤ በሻኪሶ ከተማ ባለአራት ኮከብ ሆቴል አላቸው። ሆቴሉ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝና ለከተማው ዕድገትም አስተዋጽኦ ማበርከት የቻለ ነው።
ባለሀብቱ በእነዚህ ኩባንያዎች በድምሩ ከአራት ሺ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል። በጋራ የመሥራት ጠንካራ ፍላጎት አላቸው፤ ለንግድ ሥራ ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት አብሮ አደጎቻቸውን ጭምር ወደ ዘርፉ መሳብ ችሏል፤ በግላቸው ካቋቋሙዋቸው ኩባንያዎች በተጨማሪ ከአብሮአደጎቻቸው ጋር በመሆንም በማዕድን ልማት ተሰማርተው ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
በግላቸው በሚያስተዳድሩትና በስፋት የሚታወቁበት ጉጂ ሀይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን በ150 ሄክታር መሬት ላይ ከሚያለማው ቡና በተጨማሪ ከ1000 በላይ ከሆኑ አጋር ገበሬዎች ጋርም አብሮ ይሰራል። ለገበሬዎቹ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እና አስፈላጊውን ግብዓት በማቅረብ የሚያለሙትን ቡና ይገዛል። ለጉጂ ሀይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን በራሱ ቦታ የሚያለማውንና አርሶ አደሮቹ የሚያለሙትን ቡና ጨምሮ ለውጭ ገበያ ያቀርባል።
በጉጂ ዞን የሚመረተውን ቡናም ዱከም አካባቢ በሚገኘው የቡና ማቀነባባሪያ ፋብሪካ ውስጥ በማስገባት በመቀሸርና በማበጠር ለውጭ ገበያ ዝግጁ በማድረግ ይልካሉ። የቡና ማቀነባባሪያ ፋብሪካው የተለያዩ ማሽኖችን የያዘ እንደመሆኑ ድርጅቱ ከራሱ አልፎ በአካባቢው የሚገኙና ቡናን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የጀመሩ ገበሬዎችን ቡና የመፈልፈል፣ የመቀሸርና የማበጠር አገልግሎት ይሰጣል።
ቡናን አልምቶ ለውጭ ገበያ እያቀረበ የሚገኘው ጉጂ ሀይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን በአማካኝ በዓመት ከሰባት እስከ ስምንት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለአገር ያስገኛል፤ በተመሳሳይ ሞርሞራ የቡና ልማትም እንዲሁ በዓመት ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገኛል። በድምሩ በዓመት እስከ 10 ሚሊዮን ዶላር ለአገሪቷ ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙት አቶ ውዴሳ፤ በዋናነት አውሮፓ አገራትን ጨምሮ አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ደቡብ ኮርያና ቻይና የገበያ መዳረሻዎቻቸው እንደሆኑ አጫውተውናል።
ዘንድሮ በቂ ዝናብ ያልነበረ መሆኑን አስታውሰው በፈለጉት መጠን ማምረት እንዳልቻሉ አንስተዋል። ይሁንና በአሁን ወቅት በአካባቢው አጥጋቢ ዝናብ እየታየ ያለ በመሆኑ ከጉጂ ሀይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን እና ከአጋር ገበሬዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት ይጠበቃል። በመሆኑም በቀጣይ ዓመት የሚኖራቸው አፈጻጸም ካለፉት ዓመታት የተሻለ እንደሚሆን ነው ያመላከቱት።
‹‹የትኛውም ኩባንያ ሥራውን በሚሠራበት አካባቢ ተቀባይነትን ካላገኘ ውጤታማ መሆን አይችልም›› የሚሉት አቶ ውዴሳ፤ በማህበረሰቡ ውስጥ ገብቶ ለመሥራት ከመንግሥት ቀጥሎ የማህበረሰቡ ፈቃደኝነት ወሳኝ ነው ይላሉ። በመሆኑም በአካባቢው ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን በመሥራት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደቻሉም ነው የሚናገሩት።
ለአብነትም በማዕድን ልማት ዘርፍ በተሰማሩበት አካባቢ በሰባቦሩ ወረዳ የሰቢቾና ሲሬ ቡቄ ቀበሌዎችን የሚያገናኝ መንገድ በመሥራት የማህበረሰቡን የዘመናት ጥያቄ መመለስ ችለዋል። በተጨማሪም ደንቢውዶ ቀበሌ የውዶአዳማ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እድሳት የማድረግና የነበረባቸውን የክፍል ጥበት ለማቃለል የህንጻ የማስፋፋያ ሥራ ሠርተዋል። በዚሁ አካባቢም የመንገድ ሥራን ጨምሮ በዞንና በወረዳው ዙሪያ በርካታ የልማት ሥራዎችን አከናውነዋል።
አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይም እንዲሁ ተሳታፊ በመሆን ይታወቃሉ። ገበታ ለአገርን ጨምሮ ለመንግሥት ጥሪዎች ሁሉ ምላሽ ሰጥተዋል። ከሶማሌ ክልል ተፈናቃይ ለነበሩ ዜጎችም እንዲሁ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። ዱከም ላይ ባቋቋሙት ኢንዱስትሪ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ያልነበራቸው በመሆኑ ከግቢያቸው ውስጥ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ንጹህ የመጠጥ ውሃ በማውጣት ህብረተሰቡ እንዲጠቀም አስችለዋል።
በርካታ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት አቶ ውዴሳ፤ በተለይም እስካሁን ቡናን በጥሬው ለውጭ ገበያ እያቀረበ የሚገኘው ድርጅታቸው ጉጂ ሀይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን በቀጣይ እሴት በመጨመር ተቆልቶ የተፈጨ ቡናን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ዝግጅቱን አጠናቅቋል። ለዚህ ሥራቸውም ቀደም ሲል በግዢ ካገኙት የአምስት ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በተጨማሪ ስድስት ሺ ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ ከመንግሥት ያገኙ በመሆኑ የማስፋፋያ ሥራቸውን እያጠናቀቁ የሚገኙ ሲሆን፤ ሰፊ የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ እንደሆነም አጫውተውናል።
አቶ ውዴሳ ዝቅተኛ ከሆነው ከከረሜላ ንግድ ተነስተው በዶሮ፣ በፍየል፣ በከብቶችና በእህል ንግድ በመሰማራት አድካሚውን የንግድ ዓለም አቆራርጠው ተጉዘዋል። ዛሬ ላይ በቡና እንዲሁም በማዕድን ልማት ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ከከፍታው ማማ ላይ ደርሰዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ የታደለቻቸው በርካታ ጸጋዎች ያሏት፤ በተለይም በአፈር ለምነት፣ በደን፣ በማዕድን፣ በአየር ጸባይ እጅጉን የታደለችና የተባረከች ምድር ስለመሆኗ የሚገልጹት አቶ ውዴሳ፣ “ኢትዮጵያውያን በተሰጡን የበዙ ጸጋዎች መጠቀም አልቻልንም” ሲሉ አቶ ውዴሳ ይገልጻሉ። “ወደ ምድር የመጣንበትን ዓላማ እየሳትን ነው” በማለትም “ለተፈጠርንበት ዓላማ እንኑር። በተሰጠን ተፈጥሯዊ ጸጋ ተጠቅመን መልካም ፍሬን እናፍራ” የሚል ጠንካራ መልዕክት አስተላልፈዋል። እኛም የእርሳቸውን ሀሳብ በመጋራት የኢትዮጵያን ሀብትና ፀጋዎች ጥቅም ላይ ለማዋል መትጋት አንደሚያስፈልግ በማስገንዘብ እናበቃለን።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014