ልዑል በተባለ ስም የሚታወቅ የሰፈር ውስጥ ደላላ ነው። በድለላ ስራው የተወደደና ውጤታማ ደላላ። የድለላ ስራውን በሚሰራበት ጊዜ ምክንያት ፈጥሮ የሚናገረው አንድ ነገር፤ የስሙን ታሪካዊ አመጣጥ ነው። ስሜ ልዑል ይባላል፤ አባቴ ልዑል ያለኝ ለራሴ ትልቅ ቦታ እንድሰጥ በማሰቡ ነው። ትልቅነት ደግሞ ሎሌነት ነው።
ሌሎችን ማገለገል። የምሰራው ስራ የድለላ ስራ በማሕበረሰቡ ዘንድ ክብር የሚያሰጥ ባይሆንም፤ እኔ ግን በአገልጋይነቴ ክብር አሰጠዋለሁ። ደንበኞቼ የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ መሄድ ያለብኝ እርቀት ድረስ እሄዳለሁ። እውነተኛ መረጃ ስለምሰጣቸው ደንበኞቼ ይወዱኛል። ለራሴ ጥቅም ብቻ ብዬ ደንበኞቼን አላንገላታም። ወዘተ እያለ ልዑልነትንና ደላላነትን ለማስታረቅ ይሞክራል።
የአካባቢው ሰዎችም የሚናገሩት ልዑል የተዋጣለት ሃቀኛ ደላላ መሆኑን ነው። ሰዎች ወደ እርሱ ሲሄዱ መፍትሔ ፍለጋ ነው። ከእርሱም ዘንድ መፍትሔ እንደሚያገኙ ያምናሉ። ደንበኞቹን እንደ ቤተሰቦቹ አድርጎ የሚያይ፤ ሁልጊዜ በእነርሱ ቦታ ሆኖ የሚጨነቅ ነው። ልጆች ይዛ ቤት በመፈለግ የምትንገላታ እናትን ማሳረፍ እንዴት አያስደስት ይላል። አንዳንዴም የሰዎቹን አቅም ትቶ የድለላ ክፍያም አይቀበለም። እርካታው ማገልገሉ ነው፤ ይህ ለእርሱ ልዑልነት ነው። ልዑልነትን በሎሌነት ውስጥ።
አንድ ቀን ይታመምና ለህክምና ካለበት አካባቢ ተነስቶ ጉዞ ለማድረግ የታክሲ ሰልፍ ላይ ይሰለፋል። የታክሲ ተሰላፊዎችም ልዑልን እንዴ ልዑል አንተማ አትሰለፍም ብለው ወደ ፊት ያመጡታል፤ ሁሉንም አመስግኖ ታክሲ ውስጥ ይገባል። ታክሲው ጉዞ ሲጀምር የታክሲው ሊከፍል ሲልም አይታሰብም ይሉታል። የተባለው የህክምና ቦታ ሲደርስም የህክምና ባለሙያዎች በተለየ ሁኔታ አስተናገዱት። ህክምናውን ጨርሶ እቤቱ ሲመለስ ሎሌ ሆኖ ማገልገል ኑሮን እንደ ልዑል ያደርገዋል ሲል ለቤተሰቡ ነገራቸው። ዝቅ ብሎ ማገልገል ከፍ ያደርግ ይሆናል እንጂ፤ በፍጹም አያሳንስም ሲል በትልቁ ጽፎ መኝታ ቤቱ ውስጥ ሰቀለ። ሎሌነት፤ ልዑልነት።
ሎሌነትን ስናስብ
ሎሌነትን ስታስብ የምታስበው በአነስተኛ የስራ መደብ ላይ ተመድበው የሚሰሩ ሰዎችን ይሆን? ከሆነ የተሳሳተ ምልከታ አለህ ማለት ነው። ሎሌነት ስለ የስራመደብ ሆነ ችሎታ አይደለም። ስለ አተያይ እንጂ። በእርግጠኝነት በአገልግሎት መስጫ ተቋማት ውስጥ ስለ ሎሌነት ዝቅተኛ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች ገጥመውህ ይሆናል። በመንግሥት ተቋም ውስጥ የሚሰራ ሥርዓት የሌለው ሰራተኛ፣ ትእዛዝህን ለመቀበል ቸልተኛ የሆነች የካፍቴሪያ አስተናጋጅ፣ ስልክ ከጓደኛው ጋር እያወራ አገልግሎት ሊሰጥ የሚሞክር ግምጃ ቤት ሰራተኛ ወዘተ የሎሌነት አገልግሎት ያልተረዱ ሰዎች ማሳያዎች ናቸው።
ሰራተኞች ሰዎችን ለመርዳት ሳይፈልጉ ሲቀሩ እንደምትረዳው እንዲሁ የሎሌነት ልብ የሌለውንም መሪ እንዲሁ ትረዳዋለህ። ምርጥ የሚባሉ መሪዎች እራሳቸውን ሳይሆን ሌሎችን ለማገልገል ፍላጎቱ ያላቸው ናቸው።
እውነተኛው ሎሌ ማንነው?
የእውነተኛው ሎሌ ማሳያዎች መካከል የተወሰኑትን ነጥቦች እናንሳ፤
- እውነተኛ ሎሌ ከራሱ አጀንዳ በፊት ሌሎችን የሚያስቀድም ነው፣
የሎሌነት መገለጫ መካከል የመጀመሪያ መገለጫ ሌሎችን ከራስ እና ከግል ፍላጎት በፊት የማስቀደም አቅም ነው። ይህ የራስን አጀንዳ አቆይቶ ሌሎችን በማስቀደም የሚገለጽ ነው። ይህ ማለት በታሰበበት ደረጃ የሰዎችን ፍላጎት ማጤን መቻል፣ ለመርዳት መሞከር እናም ፍላጎታቸው አስፈላጊ መሆኑን መረዳት በመቻል ነው። ከራስ ማስቀደም ባይቻል እንኳን ሌሎችም እንደ እኛ ፍላጎት እንዳላቸው መረዳት መቻል ነው።
- እውነተኛ ሎሌ ለማገልገል የልብ መተማመን ያለው ነው፣
እውነተኛ የሎሌነት ልብ መነሻው በራስ ላይ ትምምን መኖር ነው። አገልግሎት ለማግኘት እርሱ በጣም የተገባው ሰው መሆኑን የሚረዳ ሰው ካየህ እርሱ በራሱ ላይ ትምምን የሌለውሰው ነው። ሌሎችን ለመያዝ የምንሞክርበት መንገድ ስለእራሳችን የምናስብበትን መንገድ የሚያሳይ ነው። ፈላስፋ ፖት ኢሪክ ሆፈር እንዲህ ብሎ ነበር ሊታሰብበት የሚገባው ነገር ራሳቸውን በምንወድበት መንገድ ጎረቤታችንን የምንወድ መሆናችንን፣ በራሳችን ሊሆን እንደምንፈልገው በሌሎች ማድረግ፣ እራሳችንን ስንጠላ ሌሎችን እንጠላለን፣ እራሳችንን መታገስ በቻልነው ልክ ሌሎችንም እንታገሳለን። እራሳችንን የቅር ካልን ሌሎችንም ይቅር እንላለን። የችግሮች ሁሉ ምንጭ ሆነ ዓለምን ያስቸገረው ራሳችንን መውደዳችን ሳይሆን ራሳችንን መጥላታችን ነው። ብለዋል ።ትምምን ያላቸው ሰዎች ለሌሎች ሃይል የሚሆኑ መሆናቸውን ልንረዳ ይገባል።
- እውነተኛ ሎሌ ለሌሎች የሚሰጥ አገልግሎትን የሚፈጥር ነው፣
አንዳንዱ ማገለገል ስራው ስለሆነ ሊያገለግል ይችላል። ሌላው ደግሞ በድንገተኛ ጊዜ እንዲሁ ድንገቴውን ነገር ለመከላከል ወይንም ለመቆጣጠር ለሆነ ጊዜ ያህል ሊያገለግል ይችላል። ነገር ግን ስለ ሌሎች አገልግሎትን የሚፈጥሩ ሰዎችን መመልከት ያስፈልጋል። ታላላቅ መሪዎች የአገልግሎት ፍላጎትን ያያሉ፣ እድሉን ይፈጥራሉ እንዲሁም ምንም አይነት ምላሽ ሳይጠብቁ አገልግሎቱን ይሰጣሉ። እውነተኛ ሎሌዎችም ለሌሎች ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት በመፍጠር ችግር ፈቺነት መለያቸው ነው።
- እውነተኛ ሎሌ ሥልጣን ተኮር ያልሆነ ነው፣
ሥልጣን ያሰቡትን ሃሳብ ለመተግበር እድል ይሰጣል። ሥልጣን ማግኘን ማንም አይጠላም። ሎሌ መሪዎች በደረጃ እና በሥልጣን ላይ አያተኩሩም። ሎሌም ሥልጣን ተኮር ሳይሆን ሰው ተኮር በሆነ ቁጥር በሎሌነት ውስጥ ተጽእኖን መፍጠር ይችላል። በሎሌነት ውስጥ የሚፈጠረው ተጽእኖ ደግሞ በሥልጣን ከሚፈጠረው ብዙ እርቀት መሄድ ይችላል። በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሥልጣን መልቀቅ የማይፈልጉ አካላት ሥልጣን የግል እርስታቸው አድርገው የሚያስቡ በመሆናቸው ነው። ሥልጣን ግን አገልግሎት መስጫ ነው። እውነተኛ ሎሌ ደግሞ ከሥልጣንም በላይ ሄደው በመልካም ተጽእኖ አገልግሎት የሚሰጡ ናቸው።
- እውነተኛ ሌሎች ከፍቅር የሚያገለግል ነው፣
ስለ ደሞዝ ብለው የሚያገለግሉ አሉ። ስለ ፍቅር ብለው የሚያገለግሉም አሉ። እናት ለልጇ የምትሰጠው አገልግሎት ከፍቅር የሚመነጭ ነው። ሎሌነት እራስን በማስተዋወቅ ውስጥ የሚረካ ስሜት አይደለም። በፍቅር የሚቀጣጠል እንጂ። በስተመጨረሻ የተጽእኖ መፍጠርህ ጥግ የሚለካው ለሌሎች ባለህ ጥልቅ እሳቤ ነው። ለእዚያ ነው ሌሎችን ለማገልገል ፍላጎት ያለን መሆን ያለበት።
- እውነተኛ ሎሌ ስለ ሌሎች ድምጽ የሚሆን ነው
ድምጽ መሆን ሲባል በእኛ ላይ እንዲሆን የማንፈልገውን በሌላው ላይ ባለማድረግ፤ እንዲሁም በእኛ ላይ እንዲሆን የማንፈልገው በሌላው ላይ ሲሆን እኛ ላይ ቢሆን የምናደርገውን በማድረግ አስተዋጾ ማድረግ ማለት ነው። የተራበ ሰው ስናይ በተራበው ሰው ቦታላይ ሆነን ስንመለከት ያኔ ድምጽ የመሆንን አቅም እናገኛለን። መንገድ ላይ የሚተኙ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ተመልክተን ራሳችንን እነርሱ ቦታ ላይ አድርገን ስንመለከት ያኔ ድምጽ መሆን እንችላለን።
በአጭሩ ድምጽ መሆን ሁለት ነገሮችን ከእኛ ይጠይቃል። የመጀመሪያው በሌላው ጫማ ውስጥ መሆን ሲሆን ሁለተኛው በራሳችን ጫማ ውስጥ መሆንን።
በሌላው ጫማ ውስጥ ሆኖ መመልከት እኛ ጋር ያለው ነገር ብቸኛ ሃሳብ አድርገን እንዳናይ ምናልባትም ከፍረጃ ወጥተን ነገሮችን በሚዛን መመልከት የምንችልበትን እድል ይሰጠናል። በዙሪያችን ያሉ ሰዎች ሁሉ ካደመጥናቸው ሊናገሩ የሚፈልጉት ድምጽ አለ፤ ወይንም እየተናገሩት ያሉት። በሌላው ጫማ ውስጥ ተሁኖ እንቅስቃሴን ማድረግ ድምጽ የመሆንን እድልን ይሰጣል። ሁልጊዜ ነገሮችን ከራስ ጫማ ብቻ መመልከት የተዛባ እይታ እንዲኖረን ያደርጋል። በሌላው ጫማ ውስጥ ተሁኖ ነገሮችን የመመልከት አካሄድ ነገሮችን በእውቀትና በመረዳት ወደማድረግ ደረጃ ያወጣል።
በራሳችን ጫማ ውስጥ ተሁኖ መመልከት መቻል ደግሞ ማድረግ የምንችለውን ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ እንቅስቃሴ ማድረግ እንድንችል እድል የሚሰጠን ይሆናል። በምድራችን ላይ ያለውን ችግር ልንፈታ አንችልም። በሀገራችን ያለውን ችግር እንደ ግለሰብ ልንፈታ አንችልም። የአንድ ሰውን ችግር በራሳችን አቅም ብቻ ልንፈታም አንችል ይሆናል። በራስ ጫማ ውስጥ ስንሆን ድምጽ መሆን በምንችልበት ደረጃ ላይ ድምጽ መሆን እንድንችል ያደርገናል። መጽሐፉ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚለውም ለእዚህ ነው። ከራሳችን በላይ ልንወደው የምንችል ባልንጀራ የለም። እንደ ራሳችን የመንወድ ከሆነ እርሱ ትልቅ አምላካዊ ጥሪን ተቀብሎ መፈጸም ነው። ድምጽ መሆን ማለት በራስ ጫማ ሆኖ ማለትም ይኸው ነው።
ለሌሎች ድምጽ መሆን በሚዛኑ ቢሆን ምድርን መለስተኛ ገነት ማድረግ በቻልን ነበር። በሌላው ጫማ ውስጥ መሆን አለመቻል በሌሎች ስቃይ ውስጥ የምንደሰት፤ የሌላው ህመም የማይሰማን ሆነን እንገኛለን። በምድራችን እንዲሁም በዓለማችን ውስጥ እጅግ አስከፊ ፈተና ውስጥ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሉ። በተቃራኒው ደግሞ ችግር ፈጣሪ ሆነው ነገር ግን በነጻነት ሕይወታቸውን እየመሩ ያሉም ይገኛሉ። ሌሎቹ ደግሞ የራሳቸውን አጥር ሰርተው በሞቀው ቤታቸው ውስጥ አሉ። አንዱ ለአንዱ ድምጽ መሆን አላስፈላጊ አድርጎ በመውሰድ አጥርን አጥብቆ መኖር። ይህን ቤትም አንድ ቀን የፈተና ማእበል ሲነካው እንዲሁ ሌላው ቤት አጥሩን አጥብቆ ያይም ይሆናል።
እንደ አንድ ህያው ፍጡር ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆንን በሚገባ ተረድተን የእለት ተእለት እንቅስቃሴያችን አካል ማድረግ አለብን፤ በሎሌነት መንፈስ።
እውነተኛ ሎሌ ከራሱ በላይ የሚኖር መሆኑ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ስለ ሌሎች ድምጽ መሆኑ አንዱ ነው። መልካም ስብዕና ለእያንዳንዱ ሰው የሚያስፈልግ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው። መልካም ስብዕና ለባለቤቱም ለሰዎቹም መልካም ነው። ድምጽ መሆን የመቻል አቅም ከመልካም ስብዕና ጋር ያለውን ግንኙነት መረዳት ይገባል።
በመልካም ስብዕና የተገነቡ ሰዎች ድምጽ መሆን ሲችሉ የመሰማት እድላቸው ከፍተኛ ነው። መደመጥ ሁሉም ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚያገኘው አለመሆኑን አስቀድመን ያነሳነውም ለእዚህ ነው። ሁሉም ሰው የመሰማት መብት አለው፤ ሁሉም ሰው ድምጽን የማሰማት ግዴታ አለበት፤ ነገርግን ሁሉም ሰው እኩል አይሰማም።
በአካባቢያችን የተጣሉ ሰዎችን ለማስታረቅ የሚፈለገው ምን አይነት ነው? ለጋብቻ ጥያቄን ለማቅረብ የሚላኩትስ? በተመሳሳይ ሁኔታ በሀገርም ሆነ በለዓምአቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያለው ሰው በመሆን ውስጥ መልካም ስብእና ቦታ ይኖረዋል።
የመልካም ወጣት የስብዕና ማእከልን የመገንባት ሥራን በምንስራበት ጊዜ አሻግረን የምናየው ኢትዮጵያ በመልካም ስብዕና የታነጹ ዜጎች መኖሪያ እንድትሆን ነው። የዜጎች ምርታማነት እንዲሁም የእርስበርስ ፍሬያማ የሆነ መስተጋብር ከስብዕና ውስጥ የሚመነጭ ስለሆነ።
በጭንቅላት ምጥቀት የቱንም ያህል የደረሰ ሰው፣ በገንዘብ አያያዙ የቱንም ያህል ሀብታም የሆነ ሰው፣ በማንኛውም መለኪያ አንቱታን ያተረፈ ሰው ስብዕናው የተገነባ ካልሆነ ውጤት የለውም። የስብዕና ግንባታ አስፈላጊ የሚሆነው ለእዚህ ነው። መልካም ስም፤ ከመልካም ስብዕና ይመነጫል፤ ድምጽ ለመሆንም እድልን ይሰጣል።
በስብዕናቸው ጠንካራ የሆኑ ዜጎች ባሉበት ሀገር ውስጥ ሀገራዊ ምርታማነት እንዲሁም በምእራቡ ዓለም የባህል ወረራ ተጽእኖ ውስጥ የመግባት እድላቸው አነስተኛ ሆኖ እንመለከታለን። ሀገራችን በስብዕና ላይ አተኩራ ከሰራች፤ የሚደመጡ ሽማግሌዎች ይኖሯታል። ካልሆነ ግ አሁን ያለንበት የስብዕና ማሽቆልቆል ቀጥሎ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሊከተን ይችላል።
ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆንን እንደ ማሕበረሰብ ማስፈን ብንችል በሴቶች ላይ የሚደርሰውን አላስፈላጊ ጾታዊ ጥቃት መመከት በቻልን ነበር። በየመስሪያቤቱ እንደ ነዳጅ የሥራ ማንቀሳቀሻ የሆነውን ሙስናን ትርጉም ባለው ሁኔታ በቀነስን ነበር። በየቤተእምነቱ ከእምነት የሆነ ተጽእኖ ፈጣሪ የሆኑ ምእመናንን ማፍራት በቻልን ነበር። በኢትዮጵያ ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን እንደሚገባ መዘርዘር አንባቢውን ማድከም ነው። በየአካባቢው ድምጻችንን የሚሹ ዜጎች አሉ። ድምጽ በመሆን ውስጥ መልካም ስም ስራውን ይስራ።
የተግባር እርምጃን እንራመድ፣
በተግባር ተፈትኖ ውጤታማ ሆኖ መገኘት በሎሌነት መንገድ ውስጥ አለ። ልምምዱ ግን በአንድ ቀን የሚመጣ አይደለም። ስለሆነም፤
- በትንሹ መተግበር ጀምር – ለሌሎች መልካም ነገርን ያደረከው ለመጨረሻ ጊዜ መቼ ነበር? ከአንተ ጋር በቅርበት ካሉት ጋር ጀምር፤ ከትዳር አጋርህ፣ ከልጆችህ፣ ከቤተሰቦችህ። ትንሽ ነገርን ዛሬ ላይ በማድረግ ሰዎች እንደምታስብላቸው ማሳየት ትችላለህ።
- በመንጋው መካከል በዝግታ መራመድን ተማር – ከስራ ባለደረቦችህ፣ ደንበኞችህ፣ የቅርብ አለቃህ ወይንም ከሌሎች ሰዎች ጋር በቅርበት ለመተዋወቅ እድልን በሚሰጥ ሁኔታ አግኛቸው። በምትገናኙበት ጊዜ ግብ ማድረግ ያለብህ እኒህን ሰዎች ማወቅ ባለብህ ልክ ለማወቅ መሆን እንዳለበት አተኩር። ወደ ቤት በተመለስክ ጊዜ ያገኘሃቸውን ሰዎች ማን ምን እንደሚፈልግ ለማሰላሰል ሞክርና ግምሽ ለሚሆኑት የሚጠቅም ነገር ለማድረግ ምን ማድረግ እንደምትችል አስብ።
- ወደ ተግባር ቀይር – የሎሌነት አመለካከት አንተ ውስጥ ከሌለ ለማምጣት የተሻለው ነገር በትንሹም ቢሆን መጀመር ነው። በአካልህ፣ በአእምሮህ ባለህ ነገር ሁሉ ማገለገል ጀምር። ሌሎችን ለስድስት ወር በቤተክርስቲያን ውስጥ፣ በነጻ-አገልግሎት ውስጥ ወይንም በሌሎች ማህበረሰባዊ አገልግሎት ውስጥ ተካፈል። ይህን አድርገህ አሁንም አተያየህ እንደሚገባ ያልተቀየረ ከመሰለህ ደግመህ አድርገው። ልብህ ወደ ሎሌነት እስኪቀየር ድረስ ደጋግመህ አድርገው።
ዛሬ በሀገራችን ኢትዮጵያ ነገሮች ሁሉ ያለ እጅ መንሻ የማይሰሩበት ምእራፍ ላይ መድረሱ በሰፊው ይነገራል። ሎሌ የሆኑ መሪዎችን ማግኘት፤ ሎሌ የሆኑ ሰራተኞችን ማግኘት ወዘተ ቀላል ስራ አይመስልም። ልዑልነትን ፈልገን ግን በብዙ እንደክማለን። የመፍትሔው መንገድ ግን በአንድ እርምጃ ወደፊት መራመድ ነው። የአስተሳሰብ ለውጥን መነሻ የሚያደርግ እርምጃ። በሎሌነት ወደ ልዑልነት። ስለ ራስ ብቻ ሳይሆን ስለ ሌሎችም።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014