አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን በሦስት ነጥብ 12 ቢሊዮን ብር እየተገነባ ያለው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ከውል ጊዜው አምስት ወራት ዘግይቶ በሰኔ ወር 2011 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ኮርፖሬሽኑ አስታወቀ።
የኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ቱሉ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ወረዳ እየተገነባ ያለው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ ልምድ አለመኖርና በዲዛይን ችግር ምክንያት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታው ቢዘገይም በመጪው ሰኔ ወር ይጠናቀቃል።
የፓርኩ ግንባታ በሦስት ምዕራፎች ተከፍሎ የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት አቶ ከፍያለው፤ በመጀመሪያው የግንባታ ምዕራፍ ላይ ስምንት የአስተዳደር ሕንፃዎች፣ የመሸጫ ሱቆች፤ የማሰልጠኛ ማዕከላትና መጋዝኖች ግንባታ የአፈጻጸም ደረጃ ውል ከተገባው 60 ነጥብ 57 በመቶ በላይ ማከናወን ተችሏል። በሁለተኛው ምዕራፍም፤ የመንገድ፤ የውሃ፤ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችን ያካተተ የመሠረተ ልማት ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፤ ይህም ውል ከተገባው አፈጻጸሙ 46 ነጥብ 94 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።
በሦስተኛው ምዕራፍ ከሚገነቡት መካከል ክሊኒክ፤ የመኖሪያ አፓርታማዎችና እሳት አደጋ መቆጣጠሪያ እንደሚገኙበት ገልጸዋል። አጠቃላይ የግንባታው አፈጻጸምም ከ50 በመቶ አይበልጥም ብለዋል። በዚህ ረገድ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዴት ሊጠናቀቅ ይችላል? ብለን የጠየቅናቸው አቶ ከፍያለው፤ ‹‹ዝቅተኛ አፈጻጸም የታየባቸው የግንባታ ክፍሎች አብዛኛዎቹ የግንባታ ጥሬ ዕቃዎቹ ከውጭ ነው የሚመጡት። የውጭ ምንዛሬ ዘግይቶም ቢሆን ስላገኘን መሣሪያዎቹ ከውጭ ተገዝተው መጥተው እየተገጣጠሙ ስለሚገኙ በሁለት ወር ውስጥ ይጠናቀቃሉ›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የካቲት 2010 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ በስሩ ለፓርኩ ስምንት ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከላት እንደሚኖሩት ገልጸው፤ የሻሸመኔ የገጠር ትራንስፎርሜሽን ማዕከል ግንባታም በተፋጠነ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
በ271 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈውን የቡልቡላ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የሚያካሂደው ወላቦ የግንባታ ሥራዎች ድርጅት ሲሆን፤ በፓርኩ ግንባታ ወቅትም ከ3,500 በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንና ለግንባታው ጥሬ ዕቃ የሚያቀርቡ 13 ማህበራት መኖራቸውን አቶ ከፍያለው አክለው ተናግረዋል።
አቶ ከፍያለው አያይዘውም፤ በፓርኩ ውስጥ 11 ባለሀብቶች በቡና፤ በወተት፤ በአትክልት ፍራፍሬና ማቀነባባሪያዎች ሥራ ለመሰማራት የንግድ ዕቅዳቸውን እንዳስገቡ ገልጸው ኮርፖሬሽኑ ከአራቱ ባለሀብቶች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት መፈራረሙን ተናግረዋል። ከባለሀብቶቹ መካከልም ሞዴል አርሶ አደሮች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች ይገኙበታል ብለዋል።
በአራት ክልሎች በአንድ ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ እየተካሄደ ሲሆን፣ የፓርኮቹ ግንባታ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅማቸው ሲሠሩ ከቡሬ ፓርክ በዓመት 558 ሺህ ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱና 14 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ፤ ከባኸር ፓርክ 700 ሺህ ቶን መጠን ያላቸው የተለያዩ ምርቶች እንደሚመረቱና 18 ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንደሚገኝ፤ ከቡልቡላ ፓርክ 591ሺህ ቶን ምርትና 14 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚገኝ፤ ከይርጋለም ፓርክ 233ሺህ ቶን ምርትና ስድስት ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንደሚገኝ መረጃዎች ያመለክታሉ። እያንዳንዳቸው ፓርኮች 419ሺህ ቀጥተኛ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት18/2011
በጌትነት ምህረቴ