የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት የተገኙበት ችሎት ነው። በአንድ መንግስታዊ ተቋም እና በአንድ ኢትዮጵያ ውስጥ በአስጎብኚነት በተመዘገበ ድርጅት መካከል አለመግባባት ተፈጥሯል። ጉዳዩን በአጭሩ መቋጨት ባለመቻሉ ከስር ፍርድ ቤት እስከ ሰበር ድረስ አምርቷል። የሰነድ መለያ ቁጥር 86817 ለመስከረም 22 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞለት የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህን ጨምሮ አራት የፌዴራል ዳኞች በችሎቱ ተሰይመዋል።
አመልካች የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አቃቢ ህግ አቶ ቢኒያም አብርሃም ሰአቱን ጠብቀው በችሎቱ ፊት ቀርበዋል። በሰነዱ ላይ ተጠሪ የሆነው ግሎሪ ኢትዮጵያ አስጎብኚና የጉዞ ወኪል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ጠበቃ ጫንያለው ከበደ የተባሉትን ግለሰብ ይዞ ከችሎቱ ዘንድ ተገኝቷል ። ለረጅም ጊዜ ሲያከራክር የቆየው፤ ግራ ቀኝ ሲመረመር የቆየው ዶሴ ውሳኔ የሚያገኝበት ቀን ነው። ፍትህ ሊሰፍን ግድ ነውና ዳኞች ቦታ ቦታቸውን ይዘው፤ የችሎቱ ታዳሚዎችም ጉዳዩን እየተከታተሉ የመጨረሻውን ውሳኔ ሊሰሙ ጓጉተዋል። ዳኞች በእጃቸው የሚያነሷትና በመጨረሻም ጠረጴዛውን ድው! የሚያደርጉባት አጭሯ መዶሻ ለሁለቱም ተቋማት ልዩ ትርጉም አላት።
ጉዳዩ
ጉዳዩ ከአስጎብኚና የጉዞ ወኪል የንግድ ፈቃድ ሥራ ጋር በተያያዘ ለአንድ ተሽከርካሪ የጉምሩክ ቀረጥ የሚከፈልበትን አግባብ የሚመለከት ነው። የግራ ቀኙ ክርክር የተጀመረው በፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሲሆን የአሁኑ ተጠሪ ከሳሽ፣ የአሁኑ አመልካች ደግሞ ተከሳሽ ሆነው ተከራክረዋል። የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች በሚል ይህን ጉዳይ በ2006 ዓ.ም በቅጽ 15 የታተመ እውነታ ነው።
ተጠሪው ምን አሉ?
ተጠሪው ለፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረበው የክስ ማመልከቻ ይዘት በአጭሩ ድርጅታቸው በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፐብሊክ የኢንቨስትመንት ባለስልጣን የማስጎብኝት አገልግሎት ፈቃድ የተሠጠው መሆኑን፣ በዚሁ መሰረት መንግስት በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች የሰጠውን ከቀረጥ ነጻ መብት ተጠቅሞ በደንብ ቁጥር 146/2000 አግባብ በተሠጠው መብት መሰረት ከሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች አስፈላጊውን ሁኔታ ሁሉ አሟልቶ፣ ተሽከርካሪዎችን ገዝቶ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የአሁኑን አመልካች በመጠየቅ ሐምሌ 15 ቀን 2002 ዓ.ም በተፃፈ ደብዳቤ መኪኖቹ ከማናቸውም ቀረጥና ታክስ ነጻ ሆነው እንዲገቡ በፈቀደው መሰረት ተሽከርካሪዎቹ አስፈላጊ ፎርማሊቲዎችን አሟልተው ቀረጥ ሳይከፈልባቸው መግባታቸውን፣ ተጠሪ መኪኖቹን ወደ ሥራ ካሰማራ በኋላ ከሶስቱ መኪኖቹ አንዱ ከ10 ሰው በታች የሚጭን ስለሆነ ቀረጥና ታክስ መክፈል አለብህ በማለት አመልካች መጠየቁን፣ ተሽከርካሪዎቹን አስመልክቶ መሟላት የሚገባቸውን መስፈርቶች የመግለፅና የማሳወቅ ስልጣን የተሠጠው ለትራንስፖርት ባለስልጣን መሆኑ እየታወቀና ይኼው ባለስልጣን ማብራሪያ ተጠይቆ ሚኒባስ ማለት አሽከርካሪውን ሳይጨምር ከ7-14 ሰው የሚጭን መሆኑን ገልፆ ማብራሪያ መስጠቱንና በዚህ አግባብ አመልካችም ሲያስተናግድ ቆይቶ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ ቀረጥና ታክስ ካልከፈልክ ማለቱ ያላግባብ መሆኑን ዘርዝሮ ሁከቱ ተወግዶ የአመልካች የቀረጥ ክፍያ ጥያቄ ውድቅ ሆኖ እንዲወሰን ዳኝነት መጠየቁን የሚያሳይ ነው።
የአመልካች መቃወሚያ
የአሁን አመልካች ቀርቦም ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን በቀጥታ ለማየት የሚችልበት አግባብ የሌለ መሆኑን በመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያነት ያነሳ ሲሆን በፍሬ ነገር ደረጃ ደግሞ እርምጃው በሕጉ የተሰጠውን ስልጣን መሰረት አድርጎ የተከናወነ መሆኑን በመጥቀስና ለጉዳዩ አግባብነት አላቸው ያላቸውን የህግ ማዕቀፎችን ዘርዝሮ ክሱ ውድቅ ሊሆን ይገባል በማለት ተከራክሯል።
የስር ፍርድ ቤት…
የሥር ፍርድ ቤት አመልካች ስልጣንን መሰረት አድርጎ ያነሳውን ክርክር በተመለከተ የተጠሪ ጥያቄ ከቀረጥ ነጻ መብት የተያያዘ እንጂ ከቀረጥና ከታክስ አከፋፈል ጋር የተያያዘ አይደለም በሚል ምክንያት ውድቅ አድርጎታል። ፍሬ ጉዳዩን በተመለከተም የግራ ቀኙን ክርክርና ማስረጃ በመመርመር የአመልካች ጥያቄ ሕጋዊ አይደለም በማለት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ የአሁኑ አመልካች ቅር በመሰኘት ይግባኙን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም።
የአሁኑ የሰበር አቤቱታ የቀረበውም ይህንኑ ውሳኔ በመቃወም ለማስለወጥ ነው። የአመልካች የሰበር አቤቱታ መሰረታዊ ይዘትም የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን በቀጥታ ማየቱ በሕጉ ከተዘረጋው ስርዓት ውጪ መሆኑንና በአከራካሪው መኪና ላይ የአመልካች የቀረጥና የታክስ ይከፈል ጥያቄ በሕጉ በተፈቀደው አግባብና ስልጣኑን መሰረት አድርጎ የተከናወነ ሆኖ እያለ ተጠሪ የሁከት ይወገድልኝ ክስ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ተገቢውን ጭብጥ ሳይመሰርትና አግባብነት ያላቸውን ህጎች በአግባቡ ሳይመለከት የአመልካች ጥያቄ አግባብ አይደለም ብሎ መወሰኑ መሰረታዊ የሆነ የሕግ ስህተት ነው በማለት መከራከሩን የሚያሳይ ነው። አቤቱታው ተመርምሮም በሰበር ችሎቱ እንዲታይ በመደረጉ የግራ ቀኙ ክርክር በፅሑፍ እንዲደረግ ተደርጓል።
የጉዳዩ አመጣጥ አጠር አጠር ባለመልኩ ከላይ የተገለጸው ሲሆን ይህ ችሎትም የግራ ቀኙን ክርክር ለሰበር አቤቱታው መነሻ ከሆነው ውሳኔ እና ለጉዳዩ ቀጥተኛ አግባብነት ካላቸው የህጉ ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ ጉዳዩን በሚከተለው መልኩ መርምሮታል። እንደመረመረውም የስር ፍርድ ቤት ጉዳዩን በቀጥታ ክስ ማስተናገዱ ተገቢ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ነጥብ በጭብጥነት ሊታይ የሚገባው ሁኖ አግኝተናል ይላል ሂደቱን ከመረመረ በኋላ።
ከክርክሩ መገንዘብ የተቻለው የአሁኑ ተጠሪ ባለው የኢንቨስትመንት ፈቃድ በኢንቨስትመንት ሥራ ላይ በመሰማራት ለስራው የሚገለገልባቸው ተሽከርካሪዎችን ከቀረጥና ከታክስ ነጻ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ፈልጎ ይህንኑ በማመልከት ስለተፈቀደለት አስፈላጊ ዶክመንቶችን በማሟላት መኪኖችን ገዝቶ ከአስገባና ስራ ላይ ከአሰማራ በኋላ ከገቡት ተሽከርካሪዎች ውስጥ አንዱ ከአስር ሰው በታች የሚጭን በመሆኑ ቀረጥ ሊከፈልበት ይገባል በማለት አመልካች መስሪያ ቤት መጠየቁን ገልጾ ጥያቄው ሁከት በመሆኑ ሊቆም ይገባል በማለት ዳኝነት መጠየቁን፣ የአመልካች ዋና የመከራከሪያ ነጥብ ደግሞ ለተጠሪ የቀረበው አይነት ጥያቄ በአመልካች መቅረቡ በሕጉ የተፈቀደና በጥያቄው ቅሬታ ያለው ወገንም በአዋጅ ቁጥር 622/2001 አግባብ በአመልካች መስሪያ ቤት በተዘረጋው ስርዓት ቅሬታውን ማቅረብ፣ በሚሰጠው ውሳኔ ቅሬታ ካደረበትም ጉዳዩ ለግብር ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ከሚቀርብና በስርዓቱ መሰረት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትና ለበላይ ፍርድ ቤቶቸ ቅሬታው ታይቶ ከሚስተናገድ በስተቀር በቀጥታ ክስ ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት ጉዳይ አይደለም፣ ከአስር በታች የሆነ ሰው የሚጭን መቀመጫ ያለው ተሽከርካሪ ደግሞ ‹‹ሚኒባስ›› በሚለው ትርጉም አይካተትም በሚል መሆኑን ነው።
ከላይ ከተገለፀው የግራ ቀኙ ክርክር መረዳት የሚቻለው፤ ተጠሪ የቀረጥና የታክስ ነጻ መብት አለኝ በማለት ከመጥቀሱ ውጪ አከራካሪው ተሽከርካሪ ከቀረጥና ታክስ ነጻ ተብሎ በሕጉ አግባብ ሊመደብ የሚችል መሆን ያለመሆኑ የክርክሩ መሰረታዊ ጭብጥና ግራ ቀኙን የሚያከራክር ጉዳይ መሆኑ ነው። እንዲህ ከሆነ ከእቃው አመዳደብ፣ የጉምሩክ ሥነ-ስርዓት፤ ከቀረጥና ታክስ አከፋፈል ጋር ተያይዞ ቅሬታ መነሳቱን የሚያመላክት በመሆኑ በአዋጅ ቁጥር 622/01 አንቀጽ 87(1) ሥር በግልጽ እንደተመለከተው፤ በእቃዎች አሰያየም፣ አመዳደብ ወይም በታሪፍ ልክ ላይ ተቃውሞ ካለ እንዲሁም በተጠቃሹ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3(ሐ) ስር እንደተመለከተው ማንኛውም ከጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በሚሰጡ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ ያለው አካል አቤቱታውን ማቅረብ ያለበት ቀጥታ ለፍርድ ቤት ሳይሆን በተጠቃሹ አዋጅ በተዘረጋው የይግባኝ ሥርዓት መሆኑ ተመልክቷል።
የይግባኝ አቀራረብ ስርዓቱም ጉዳዩ ከአመልካች መስሪያ ቤት የጉምሩክ ጉዳዮች አቤቱታ አጣሪ ኮሚቴ ቀርቦ ከታዬ በኋላ ቅሬታ ያለው ወገን በአንቀጽ ንዑስ ቁጥር 5 መሰረት ለግብር ይግባኝ ሰሚ መቅረብ እንዳለበት፣ ከዚያም በአንቀጹ ንኡስ ቁጥር 9 መሰረት ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት፣ በዚህ ውሳኔ ቅሬታ ያለው ወገንም በአንቀጹ ንዑስ ቁጥር 10 ድንጋጌ አግባብ በአዋጅ ቁጥር 286/1994 አንቀጽ 112 እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 80(3(ሀ) እና አዋጅ ቀጥር 25/1988 አንቀጽ 10 ድንጋጌዎች አግባብ ለበላይ ፍርድ ቤት እንደየቅደምተከተሉ ይግባኙንና የሰበር አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችል የድንጋጌዎች አቀራረጽና ይዘት ያሳያል።
ይህ ከሆነ ደግሞ የአመልካች የቀረጥና የታክስ ክፍያ ጥያቄ አግባብነት የለውም የሚለው የተጠሪ ክርክር በእነዚሁ አዋጆች በተዘረጋው ስርዓት መሰረት ታይቶ እልባት ከሚያገኝ በስተቀር በቀጥታ ለመደበኛ ፍርድ ቤት የሚቀርብበት እና ፍርድ ቤቶች ጉዳዩን በቀጥታ አይተው ውሳኔ የሚሰጡበት አግባብ አይኖርም። የበታች ፍርድ ቤቶችም ጉዳዩ ሲቀርብላቸው ጉዳዩን በቀጥታ የማየት ስልጣን እንደሌላቸው በመገንዘብ በፍትሃብሄር ሥነ- ሥርዓት ቁጥር 9፣231(1(ለ)) እና 244(2(ሀ)) መሰረት መመለስ ሲገባቸው ክሱን በመቀበልና በማከራከር ውሳኔ መስጠታቸው የህጉን አካሄድ የተከተለ ሆኖ አላገኘነውም ሲል ወደ መጨረሻው ብያኔ ተንደረደረ።
ክርክሩ ሲጠቃለል
ታዲያ ጉዳዩ ሲጠቃለል፤ የበታች ፍርድ ቤቶች ተጠሪ ባቀረቡት የቀረጥ እና የታክስ ክፍያ ጥያቄ ላይ ስልጣን ሳይኖራቸው የሰጡት ውሳኔ የሕግ መሰረት የሌለው ነው። ክርክሩን አጠቃላይ ይዘት አግባብነት ካላቸው ድንጋጌዎች ጋር ያላገናዘበ መሆኑን ተጠቅሷል። በመሆኑም መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ስለተገኘ ተከታዩን ወስነናል ሲል የመጨረሻውን ውሳኔ አሳርፏል።
ው ሳ ኔ
1. በፌዴራሉ መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 176250 ነሐሴ 13 ቀን 2003 ዓ.ም ተሰጥቶ በ07/02/2004 ዓ.ም የተገለጸውና በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመለያ ቁጥር 117291 ጥር 06 ቀን 2005 ዓ.ም የፀናው ውሳኔ በፍትሃብሄር ሥነ ሥርዓት ቁጥር 348 (1) መሰረት ተሽሯል ሲል ይደመድማል።
2. የመደበኛ ፍርድ ቤት ተጠሪ ያቀረበውን ጥያቄ በቀጥታ ክስ በመቀበልና በመመልከት ውሳኔ ለመስጠት የሥረ-ነገር ስልጣን የለውም ሲል ወስኗል።
3. በዚህ ችሎት በተደረገው ክርክር በግራቀኙ ለደረሰው ወጪና ኪሣራ የየራሳቸውን ይቻሉ፤ ፍርዱም ተፈፃሚ ይሁን ሲል በሁለቱ ወገኖች መካከል የነበረውን ክርክር ተቋጭቶ መዝግቡ እንዲዘጋ ተወስኗል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ሰኔ 25/2014