የግንቦት 2010 ዓ.ም ትውስታ
በአገሪቱ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጥሮ የነበረው የፖለቲካ አለመረጋት በተለያዩ አካባቢዎች ተስፋፍቶ የሰላም እጦት ማስከተሉ ይታወሳል። አለመረጋጋቱ ቀጥሎም ዜጎች እንደልብ እንዳይዘዋወሩ፣ የቱሪስት ፍሰቱ እንዲስተጓጎልም አድርጓል። ለሦስት ዓመታት የዘለቀው የሕዝብ ቁጣና ተቃውሞ ዶክተር አብይን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲመጡ አድርጓል።
የእርሳቸውን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ አዳዲስ ለውጦች ተካሂደዋል። ተግዳሮቱን ወደ መልካም ዕድል በመቀየር አፋጣኝ የለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ በአገሪቱ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ተችሏል። አምና በግንቦት ወር የተከሰቱ አንኳር ጉዳዮች እንደሚከተለው ልናስታውሳችሁ ወደድን።
እስረኞችን የመፍታት እርምጃው ቀጥሏል
መንግስት በፍትህ ሥርዓቱ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እየወሰደ ባለው እርምጃ በሽብር ክስ የተከሰሱትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ 740 ሰዎች በክስ ማቋረጥና በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የገለጸው ግንቦት18 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር። የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ በዕለቱ ሰጥተውት በነበረው መግለጫ፤ በሽብር ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው በክርክር ሂደት ላይ
የነበሩ 137 ሰዎች እንዲሁም በሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው በክርክር ላይ የነበሩ 27 ሰዎችና አራት ድርጅቶች በህግ አሰራሩ መሰረት ክስ እንዲቋረጥ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ተወስኖ ለፍርድ ቤቶች ቀርቧል።
በተለያዩ ወንጀሎች ተከስሰው በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጣቸው ፍርደኞችም በይቅርታ ቦርድ ታይቶ 576 ያህል ሰዎች የተፈቱ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ 18 ያህሉ ሴቶች ናቸው። የክስ ማቋረጡና ይቅርታ ውሳኔው በምንም ሁኔታ ቢሆን መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኝነት የማይነካ መሆኑም ተገልጾ ነበር።
ኢህአዴግ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ወሰነ
• የመንግሥት ትላልቅ ኩባንያዎች ወደ ግል ሊተላለፉ ነው
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የአልጀርሱ ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የወሰነው በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም ነበር።
የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ መንግሥት የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱም ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም በወጣው መግለጫ አስታውቋል።
‹‹የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪውን ተቀብሎ የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ›› ኮሚቴው ጥሪውን አቀርቧል።
በሌላ በኩል፤ ኮሚቴው በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙትም ሆነ በግንባታ ላይ የሚገኙ የባቡር፣ የስኳር ልማት፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የሆቴልና የተለያዩ የማኑፋክቸሪንግ ድርጅቶችም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል በአክስዮን ሽያጭ ወደ ግል ዘርፍ እንዲተላለፉ ወስኗል።
ኢትዮ ቴሌኮም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችና የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ትልቁን የአክስዮን ድርሻ መንግሥት ይዞ ቀሪው አክስዮን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ባለሀብቶች እንዲተላለፍ አቅጣጫ አስቀምጧል። አፈፃፀሙም የልማታዊ መንግሥትን ባህሪያት በሚያስጠብቅ፤ የኢትዮጵያን ፈጣንና ተከታታይ ዕድገት በሚያስቀጥልና የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲመራ ገልጾ፣ ዝርዝሩ በባለሙያዎች ተደግፎ በጥብቅ ዲስፕሊን ተግባራዊ እንዲደረግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ወስኗል።
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦ.ዴ.ግ) አዲስ አበባ ገባ
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦ.ዴ.ግ) የኢፌዴሪን መንግስት የሰላም ጥሪ ተከትሎ አዲስ አበባ የገባው ግንቦት 15 ቀን 2010 ዓ.ም ነበር። የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ሌንጮ ለታ በወቅቱ በመንግስት በኩል ያለው ሁኔታ የተሻለ በመሆኑ ሌሎች በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ጥሪውን ተከትለው በሰላማዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ አቅርበዋል። ኦ.ዴ.ግም በቀጣይ ከመንግስት ጋር ውይይት ካደረገ በኋላ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታልም ብለዋል።
ለመከላከያ ሰራዊት ኃላፊዎች በንድፈ ሃሳብ የታገዘ ገለጻ ተሰጠ
የመከላከያ ሰራዊት የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲ ግቦች ማሳካት እና የአገሪቱን ህዝቦች ክብር እና የሀገር ሉዐላዊነት ማስከበር ተልዕኮውን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የገለጹት በዚሁ ወር ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመከላከያ ሰራዊት ሃላፊዎች በንድፈ ሃሳብ የታገዘ ገለጻና ከሃላፊዎቹ ጋር በአገራዊና ወቅታዊ ጉዳች ዙሪያ ባደረጉት ውይይት፤ የመከላከያ ሰራዊት የአገሪቱን ብሄራዊ ጥቅሞች ለማስከበር የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የቴክሎጂ፣ የዲፕሎማሲና የወታደራዊ አቅሞችን አቀናጅቶ አገራዊ ክብርንና ልዕልናን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የማይተካ ሚና እንዳለው አረጋገጠዋል።
ሰራዊቱ በመርህ የሚገዛ፣ ለወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ተፅእኖ በቀላሉ እጅ የማይሰጥ፣ የህዝብን ፍላጎትና ጥቅም የሚያስከብር፣ ሙያውን በየጊዜው እያሳደገ የሚሄድና ኃላፊነትን የመወጣትና የተሟላ ስብዕና የሚላበስ መሆን ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት18/2011