አዲስ አበባ፦ በሀገሪቷ የሚገነቡ አዳዲስ ግንባታዎችም ሆኑ ነባሮቹ ሲሻሻሉ አጠቃላይ የህብረተሰቡን ደህንነት፤ በተለይም አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ እንዳልሆኑ ተገለጸ።
አቶ ሲሳይ ደርቤ የቀድሞው ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት መረጃ፤ በአገሪቷ የሚካሄዱ ግንባታዎች ከደህንነት አንፃር የህብረተሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ በመላው የሀገሪቱ ክፍል ተፈፃሚ የሚሆን አዋጅ 624/2001 ተደንግጓል። ይሁን እንጂ አዋጁ ተግባራዊ ባለመደረጉ አጠቃላይ የህብረተሰቡን በተለይም የአካል ጉዳተኞችን ደህንነት ማረጋገጥ አልተቻለም ብለዋል።
በአዋጁ ከተቀመጡት የደህንነት መጠበቂያዎች መካከል በተለይም ለአካል ጉዳተኞች በማንኛውም የሕዝብ መገልገያ ህንፃ ውስጥ በተሽከርካሪ ወንበር ለመንቀሳቀስና ደረጃ ለመውጣት የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች እንዲፈጠሩላቸውና መፀዳጃ ቤት ሊሰራባቸው በሚገቡ በማናቸውም ህንፃዎች ውስጥ ለአካል ጉዳተኞች የሚመቹና ሊደርሱባቸው የሚችሉ በቂ መጠን ያላቸው መፀዳጃ ቤቶች መኖር አለባቸው። ከመሬት ወለል ከ20 ሜትር በላይ
ከፍታ ያለው ማንኛውም ህንፃ የአሳንሰር ወይንም ተመሳሳይ አገልግሎት ሊኖረው ይገባል ብለዋል። ነገር ግን እነዚህና መሰል አዋጆች ተግባራዊ ባለመሆናቸው ዜጎች በተለይም አካል ጉዳተኞች በየጊዜው ደህንነታቸው አደጋ ላይ ሲወድቅ ይታያል።
የየዕለት እንቅስቃሴዎቹ ሁሉ በዊልቸር እገዛ የሆነው አካል ጉዳተኛ ወጣት አቤኔዘር እዝቅኤል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ተማሪ ነው። ወጣቱ እንደገለፀውም፤ በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥም ሆነ ከግቢ ውጪ ያለው እንቅስቃሴ በተለይም ለአካል ጉዳተኞች እጅግ ፈታኝ ነው። አጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ብዙ ችግሮች አሉ። አካል ጉዳተኞች በየትም ቦታ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ
የላቸውም። በተለይም መንገድ፣ ትራንስፖርትና ህንፃዎችን በዊልቸር ለመጠቀም እጅግ ፈታኝና የማይሞከር ነው። ስለዚህ መንግስት ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት ሰጥቶ በአዋጅ የተቀመጠውን ህግ ተፈፃሚ በማድረግ አካል ጉዳተኞች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ሰፊ ስራ መስራት ይጠበቅበታል ይላል።
አዋጁን በትክክል መሬት ላይ የማውረድና በጥብቅ ስነምግባር የመምራት ችግር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው የሚሉት አቶ ሲሳይ በበኩላቸው፤ አዋጁን ለማስፈፀም በዋነኝነት ስልጣንና ሃላፊነት የተሰጠው ለከተሞች የህንፃ ሹም ነው። የህንፃ ሹሙ ከዲዛይን ጀምሮ ግንባታው ተጠናቆ እስከ እርክክብ ድረስ ያለውን ስራ የሚሰራ ቢሆንም፤ አዋጁን በአግባቡ መተግበር አልቻለም። ለዚህም የሰው ኃይልና የአደረጃጀት ችግር የነበረባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በኮንስትራክሽን ግንባታ ውስጥ ያሉት ባለድርሻ አካላት እጅግ በርካታ መሆናቸው ሌላው ተግዳሮት መሆኑን እና የጥፋቱ መጠንም በዛው ልክ ሰፊ እንደሆነ የተናገሩት ኃላፊው፤ ሁሉም አካል ለህግና ለሥርዓት ተገዢ በመሆን የአስተሳሰብ ለውጥ በማምጣት አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን መስራት ይገባዋል። ይህ ካልሆነ ግን ችግሮችን በመቅረፍ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አይቻልም ብለዋል።
የቀድሞው የኮንስትራከሽን ሚኒስቴር መስሪያ ቤትም የተሰጠው ስልጣንና ተግባር የተወሰነና የተቀነበበ መሆኑን ያስታወሱት ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት አዲስ የተቋቋመው የኮንስትራክሽን ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን መስሪያ ቤት የተሻለ ተግባርና ስልጣን የተሰጠው በመሆኑ በቀጣይ የተሻለ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃልም ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት18/2011
በፍሬህይወት አወቀ