“ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ ” ይላሉ አበው ሲተርቱ፤ አዎ ምንም ነገር ቢሆን ከተረዳዱበት ሸክሙ ይቀላልለ፤ ውጤቱ ያማረ ይሆናል:: አንድ ሰው ምን ጠንካራ ቢሆን፣ ገንዘብ፣ ሃብት፣ ንብረት፣ ጉልበትና እውቀት ያለው ቢሆን፤ አንድ ሰው አንድ ነው፤ ብቻውን ምንም ማድረግ አይችልም፤ ላድርግ እንኳን ቢል ውጤቱ ላይ መንገራገጮች አያጡትም:: ነገር ግን ያ አንድ ሰው የተሸከመውን ሸክም ሲካፈሉት ነገሩ ይቀላል፤ ስራው ይቃናል፤ ውጤቱም ያማረ ይሆናል::
ወይዘሮ በቀለች ተሾመ እድሜያቸውን ሙሉ የኖሩት አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ አዋሬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው:: እዛው አግብተው ሰባት ልጆችን ወልደዋል:: ዛሬ ላይ ሶስቱ በህይወት ባይኖሩም የተቀሩት አራቱ ልጆቻቸውን አንዲሁም የልጅ ልጆቻቸውን ይዘው ይኖራሉ:: ወይዘሮ በቀለች ከባለቤታቸው ጋር አቅማቸው የፈቀደውን የቀን ስራ እየሰሩ ልጆቻቸውን ያሳድጉ ቤታቸውን ያስተዳድሩ ነበር:: ኋላም ባለቤታቸው በሞት ሲለዩዋቸው ጉሊት በመነገድ የቤተሰቡን ጉሮሮ መሙላት የኑሯቸው መንገዱ ነበር::
ዛሬ አቅማቸው ደክሟል ለዘመናት የኖሩባት ቤትም እንደእሳቸው አርጅታ በላያቸው ላይ ልትወድቅ ተቃርባ ነበር፤ በምኑም በምኑም እየተጠገነች ግን ዛሬ ላይ ደርሳለች:: ወይዘሮ በቀለች ከልጆቻቸው እንዲሁም ከልጅ ልጆቻቸው ጋር በጋራ የሚኖሩባት ደሳሳዋ ጎጇቸው ዛሬ ላይ ቀን ሊወጣላት ብርሃን ልታይ እሷም እንደ ሌሎች ቤቶች ቤት ተብላ ልትጠራ ተራዋ ደረሰና እነሆ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አይን ውስጥ ገባች::
“….እኔ የዘንድሮውን ክረምት ከነልጆቼ እንዴት እወጣዋላሁ ብዬ ሰግቼ ነበር ግን ጥሎ የማይጥለው አምላክ ተመለከተኝና ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መጥተው ቤታችንን ቀና ሊያደርጉልን፤ ከብርድ ከዝናብ ከውሃ ሊታደጉን ፈቀዱ፤ ይህ ለእኔ እንደገና መወለድ ነው ” ይላሉ:: አዎ ምንም ለሌላቸው ለወይዘሮ በቀለች ከእንደገና መወለድም በላይ ነው:: የሚያፈስ ጣሪያ የፈረሰ ግድግዳ የጨቀየ መሬት ቀና ብሎ ሊሰራ መሆኑን ማሰብ በራሱ ትልቅ ነገር ነው::
እንደ ወይዘሮ በቀለች ሁሉ ወይዘሮ ባዝወርቅ ፍትሃተ በዚሁ በአዋሬ ላይ እድሜያቸውን ሙሉ የኖሩ እናት ናቸው:: ወይዘሮ ባዝወርቅ እንደ ዛሬው ጉልበታቸው ሳይደክም ማየትም ሳይሳናቸው በፊት ከመርካቶ የታሰረ ቆጮ እያመጡ አዋሬ ገበያ ላይ በመነገድ ታዋቂም ነበሩ:: ዛሬ ግን ያ ሁሉ ነገር የለም በልጆቻቸውና የልጅ ልጆቻቸው እጅ ላይ ወድቀዋል፤ ማየትም ስለማይችሉ እንደ ልባቸው ወጥቶ መግባት ተስኗቸዋል::
ወይዘሮዋ ለዓመታት የኖሩባት ቤት እንደሳቸው አርጅታ አቅም ቢሳናት ማፍሰስም፤ ብርድ ማስገባትም ጀምራ ነበር:: ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሚያድሷቸው ቤቶች ውስጥ የእሳቸውም አንዱ ሆኗል:: በዚህም በጣም ደስተኛ ናቸው::
” …..ቤቴ በላዬ ላይ ሳይወድቅ በፊትም መንግስት ደርሶልኛል:: በዚህም ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ:: አሁን የምፈልገፈው ነገር የለም” ይላሉ::
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር ነውና ብሂሉ መንግስት በዚህም መልኩ የችግረኛ እናቶችን ቤት ሲያድስ ልበ ቀና ኢትዮጵያውያን ደግሞ ቤቱ ታድሶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ሰዎቹ ማረፊያ እንዳይቸገሩ በማለት በራሳቸው ተነሳሽነት ወጪ እያወጡ ቤት እየተከራዩ እያስቀመጧቸው ነው::
አዎ! ኢትዮጵያዊነት ምስጢሩ ጥልቅ ነው የሚባለው ለዚህ ነው:: ኢትዮጵያዊ ወገኑ ተቸግሮ ብቻውን አይበላም፤ እንዲህ ባለው ሁኔታ ደግሞ እንኳን አዛውንቶች ሌላውንም ቢሆን ለመርዳት ከችግሩ እንዲያገግም ድጋፍ ለማድረግ ምንም የሚሳነው ነገር የለም::
ወይዘሮ በቀለች እንደሚሉት ዶክተር ዐቢይ መጥተው ቤቶቹን ሊያድሱልን ስራውን ሲያስጀምሩ በጣም ደስተኛ ሆነን ነው የጠበቋቸው:: ለማረፊያ ይሆነን ዘንድም እዛው አካባቢ ቤት እንድንከራይ ነግረውናል፤ ነገር ግን እኔ ቤት ተከራይቼ መቆየት አቅም አልነበረኝም:: እናም እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሉ ደግ ልብ ያላቸው ወጣቶች በተለይም አቶ ዮሃንስ እና ጓደኞቹ መጥተው እኛስ ምን እናግዛችሁ ሲሉ በጣም ነው የተደሰትኩት ይላሉ::
ወይዘሮ በቀለች ደጋግ ኢትዮጵያውያንን ያቆይልን ቤታችን ለእድሳት ቢፈርስም ማረፊያ አላጣንም አራት ሺ ብር እየከፈሉልን እየኖርን ነው፤ ከዚህ በላይ ደግነት ከወዴት ይመጣል ይላሉ:: ምናልባት እነዚህ ወጣቶች ልበ ቀና ሆነው ይህንን ባያደርጉልን ኖሮ ቤታችን ታድሶ እስከሚያልቅ እንቸገር ነበር፤ አሁን ግን ስራውም ቶሎ ቶሎ እየተሰራ ነው እኛም እስከ አሁን የሚሞቅ ቤት ውስጥ ቁጭ ብለናል በማለት ከብዙ ምርቃት ጋር ሃሳባቸውን ይገልጻሉ::
ወይዘሮ ባዝወርቅም በበኩላቸው አይናቸው የማያይ ደካማ ከመሆናቸው ጋር ቤታቸው በጠቅላይ ሚኒስትሩ መታደሱ ደስ ቢያሰኛቸውም ስራው እስኪጠናቀቅ ድረስ የት አርፋለሁ? የሚለው ነገር አሳስቧቸው እንደነበር ይናገራሉ::
ሆኖም አቶ ዮሃንስና ጓደኞቹ እኛም የበኩላችንን በማድረግ የራሳችንን ችግር በራሳችን እንፈታለን ብለው መጥተው ሲያናግሯቸው ድርብ ደስታ እንደተሰማቸውም ይናገራሉ:: ዛሬ ምንም ስጋት የለብኝም የሚሉት ወይዘሮ ባዝወርቅ ቤቴ ታድሶ እስከሚጠናቀቅ ከነልጆቼ በሞቀ ቤት ውስጥ እንድቆይ ተደርጌያለሁ፤ ለእኔ ከዚህ በላይ እንደገና መወለድ የለም፤ ለሰጪዎቻችን ሁሉ ፈጣሪ ብድሩን እጥፍ አድርጎ ይስጣቸው፤ አገራችንን ሰላም ያድርግልን በማለት ሃሳባቸውን ይገልጻሉ::
አቶ ዮሃንስ እርገጤ በአዋሬ አካባቢ የሚኖርና የእነ ወይዘሮ በቀለች ጎረቤት ነው:: አቶ ዮሃንስ አንድ ቀን ጠዋት ወደስራ ሲወጣ ዶክተር ዐቢይ አካባቢው ላይ ደርሰው የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት እያስጀመሩ መመልከቱን ይገልጻል:: ሰዎቹንና ቤታቸውን እንዲሁም ኑሯቸውን በቅርብ የሚያውቀው አቶ ዮሃንስ አዛውንቶቹ የዚህ እድል ተጠቃሚ መሆናቸው እጅጉን እንዳስደሰተው ይናገራል::
አቶ ዮሃንስ እንደሚለው አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ወርዶ እንደዚህ አይነት ልብ የሚነካና አርዓያነት ያለው ተግባር ሲፈጽም ከእኔ ከተራው ዜጋስ ምን ይጠበቃል ? ማለቱንም ያስታውሳል::
ቤቱ ለእድሳት በፈረሰበት ወቅትም ወደአዛውንቶቹ በመሄድ እንኳን ደስ አላችሁ ማለቱን የሚናገረው አቶ ዮሃንስ ሆኖም አዛውንቶቹ በተደረገላቸው ነገር ላቅ ያለ ደስታ ቢሰማቸውም ቤቱ ተገንብቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ግን የሚያርፉበት ቦታ አሳስቧቸው እንደነበር ያስታውሳል::
“……በወቅቱ ሄጄ እንኳን ደስ ያላችሁ! ስላቸው በከፍተኛ ደስታና ምርቃት ውስጥ ሆነው መደሰታቸውን ገለጹልኝ፤ ሆኖም ግን አዛውንቶች ገቢያቸውም ቤት ተከራይቶ ለአንድ ወር እንኳን ለመቆየት የሚያስችል ባለመሆኑ ስጋት ውስጥ እንዳሉም ገለጹልኝ፤ ይህ እኔስ በአቅሜ ምን ላደርግና ይህንን ስራ ልደግፍ እችላለሁ የሚል ሃሳብ ወደአእምሮዬ እንዲመጣ አደረገኝ” ይላል::
በቀጥታ ከአዛውንቶቹ ቤት ወጥቼ ያደረኩት የምቀርባቸው ጓደኞቼ ጋር መደወል ነበር የሚለው አቶ ዮሃንስ በዚህም ለደወልኩላቸው ሁሉ ያለውን ነገር አስረድቻቸው ስጋቱንም ነገርኳቸው፡፡ እነሱም መንግስት ይህንን ያህል ርቀት ሄዶ ስራዎችን በተለይም አቅመ ደካሞች የሚታገዙበትን ነገር ሲያደርግ እኛ የሁለትና የሶስት ወር የቤት ኪራይ መክፈል አያቅተንም ቤት ፈልገህ አስገባቸው በማለት ወዲያውኑ አዋጥተው 19 ሺ ብር ላኩልኝ በማለት ይናገራል::
በወቅቱ አቶ ዮሃንስ ወይዘሮ ባዝወርቅን ብቻ ነበር ለመርዳት ይህንን ገንዘብ ያሰባሰበው ነገር ግን ወይዘሮዋ እንደኔ አቅም የሌላት አብራኝ የኖረች እኔ ያለእሷ እሷም ያለእኔ መኖር የማንችል ጎረቤቴ አለች እሷን ጨምረህ አግዘን በማለታቸው ወይዘሮ በቀለችም የእድሉ ተጠቃሚ መሆን ቻሉ::
አቶ ዮሃንስ እንደሚለው ሰው ከተረዳዳ እንኳን ይህች ትንሽ ነገርና ብዙ ተዓምራትን መስራት ይችላል፤ እኔም ያደረኩት ይህንን ነው :: ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየሰሩ ያለው የበጎ ተግባር ስራ ሁላችንንም ሊያነቃቃ ይገባል፡፡ እሳቸው አንድ ሲያደርጉ እኛ ደግሞ ከስር ስንደግፍ ብዙ ችግሮቻችን ውሃ ይበላቸዋል ሲል ይናገራል::
‹‹እኔና ጓደኞቼ ከቤተሰብ ርቀን ያለን ነን፡፡ እኛ እዚህ አቅመ ደካሞችን ባለችን ነገር ስንደግፍ የእኛ ቤተሰቦች ባሉበት የሚደግፉ ሌሎች ሰዎች ፈጣሪ ያዘጋጃል:: በሌላ በኩል እኔ እዚህ ጋር መልካም ስራ ስሰራ የሚያየኝ ልጄ ነገ እሱም ሲያድግ አገሩ ላይ ችግር ፈጣሪ ሳይሆን የመፍትሔ አካል ይሆንልኛል፡፡ እናም ሁሉም ሰው በየአቅራቢያው ያለውን አንድም ሁለትም ሰው ቢያግዝ ከእኛ የሚተርፍ ችግር አይኖርም ››በማለት ይናገራል::
ከአቶ ዮሃንስ ጋር በበጎ ስራው ከተሳተፉት አምስት ጓደኞቻቸው መካከል ኢንጂነር መስፍን ውብሸት አንዱ ናቸው:: ኢንጂነር መስፍን ስለ ስራቸው ስጠይቃቸው አይ እኔ ሳልሆን ባለቤቴ ናት መናገር ያለባት አሉኝ፡፡ ባለቤታቸው ወይዘሮ ብሩክታዊት ጌታሁን እንዳሉት በጎነት ለራስ ነው:: አንድ ሰው ሰው ነው ለመባል የሚበቃውን አጠገቡ ያለውን ችግር በሚችለው አቅሙ ማቃለል ሲችል ነው ይላሉ::
በጎነት በገንዘብ ብቻ የሚገለጽ አይደለም የሚሉት ወይዘሮ ብሩክታዊት ሰው ጊዜውን ጉልበቱን እንዲሁም ቀና ሃሳቡንም በመስጠት በጎነቱን ማረጋገጥ ይችላል:: እኛም ካለችንና ከተሰጠችን ላይ መንግስት ይህንን የአቅመ ደካሞችን ቤት በዚህ መልኩ ሲሰራ እኛ ደግሞ ቤቱ እስኪያልቅ ማረፊያ ብንከራይላቸው ችግሩን ተካፈልን ማለት ነው በሚል በአቶ ዮሃንስ አነሳሽነት እንደተሳተፉም ይናገራሉ::
“ምናለኝና ምን እሰጣለሁ” ይላል አንዳንድ ሰው ያሉት ወይዘሮ ብሩክታዊት መስጠት ከሀብት ጋር የሚገናኝ አይደለም፡፡ መልካምነትና ንጹህ ህሊና ያለው ሁሉ ያልተሰጠው ነገር የለም፤ በመሆኑም እሱን ማካፈል ላይ ነው ስራ መሰራት ያለበት:: በሌላ በኩልም ለምሳው የያዛት አንድ ዳቦ ግማሿን ቢያካፍል ያ ሰው ያለውን አካፍሏል፡፡ ስለዚህ ደግነትን ከመኖር እና አለመኖር ጋር ማገናኘት አያስፈልግም ይላሉ::
ኢትዮጵያውያን ሲፈጥረን መልካም ነን፡፡ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ችግርን እስከታች ወርዶ የሚያይ መንግስት ሲኖር ደግሞ ተደጋግፎ ሁኔታዎችን ለማለፍ መጣር ነገ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነውና ሁሉም ያለውን ቢያካፍል ችግሮችና መከራዎቻችን ታሪክ ይሆናሉ ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሰኔ 24/2022