
እርስ በእርስ የመደጋገፍና የእህት ወንድማማችነት እሴት ላይ ተንተርሶ ለተመሠረተው መቄዶንያ በጎ አድራጎት ማህበር እጁን የማይዘረጋ ኢትዮጵያዊ የለም። ሁሉም ዜጋ በዚህ በጎ ምግባር ላይ ተሳታፊ የሚሆነው እና ካለው ቀንሶ ለበጎ አላማው የሚያካፍልበት ሌላም ተጨማሪ ምክንያት አለው። ይህ ምክንያት በሕይወት ፈተና ወድቀውና ተስፋ ቆርጠው በጎዳና ቤታቸውን ላደረጉ ብርታት የሆነው ቢንያም በለጠ (የክቡር ዶክተር) በጎ ምግባር ምሳሌ በማድረግ እና የዓላማው ተጋሪ ለመሆን ነው፡፡
የበጎ ምግባር አምባሳደሩ ቢንያም በ2004 ዓ.ም 40 አረጋዊያንን እና አእምሮ ህሙማንን ከወደቁበት በማንሳት ማህበሩን መሠረተ። ለ13 ዓመታት ሙሉ ጊዜውን ብቻ ሳይሆን ሕይወቱን ሰጥቶ ዛሬ ላይ አድርሶታል፡፡ ማህበሩ አሁን ላይ 45 ከተሞች ላይ ቅርንጫፍ ያለው ትልቅ ተቋም ሆኗል፡፡ በ250 ተጨማሪ ቦታዎች አገልግሎቱን ለማስፋትም እየተጋ ይገኛል፡፡ ከስምንት ሺህ በላይ ደጋፊ የሌላቸውና የሌሎችን ብርቱ እንክብካቤና ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን በቋሚነት በመንከባከብና በማኖር ላይ ይገኛል፡፡
በመቄዶንያ ውስጥ በአስጎብኚነት የተሰማራውና ‹‹አባቴ መቄዶንያ ነው›› የሚለው ወጣት ምንዳ ጣሰው እንዳስቃኘን በዋናው ግቢ በቀን ከአራት እስከ ስምንት ጊዜ ዳይፐር የሚቀየርላቸው የኮሌስትሮን፣ የደም ግፊት፣ የጭንቅላት ካንሰር፣ የደም ካንሰር፣ የአእምሮ ህመም፣ የኩላሊት እጥበት የሚሹ፣ የተለያየ የአካል ጉዳት ያለባቸው ህሙማን ይገኛሉ፡፡ በጉብኝቱ ሂደት እንዳስተዋልነው ከነዚህ መካከል ጎንበስ ቀና ማለት ተስኗቸው በተለያዩ ክፍሎች በየጾታው ተለይተው በተኙበት አልጋ ላይ ክብካቤ የሚደረግላቸው ዳይፐር ተጠቃሚ ህሙማን ብቻ 2ሺ 500 ናቸው፡፡ እነዚህን አቅመ ደካሞች የሚመግባቸውም ሆነ ጎንበስ ቀና የሚያደርጋቸው ሰው ነው፡፡ ከጤና ችግራቸው አንፃር የፍራሽ ፍጆታቸው ሰፊ በመሆኑ በላስቲክ ሸፍኖ የሚሰፋላቸውም አለ፡፡
በሰፊው ግቢ ከእነዚህ ውጭ እንደሚሪንዳና ጁስ ያሉ ፈሳሾችን ተጠቃሚ ህሙማንም በርካታ ናቸው። የአእምሮ ህሙማኑ ቁጥር እጅግ ብዙ ነው፡፡ ከ2ሺ 500 በላይ የማህበሩ ተቀጣሪ ሠራተኞች ሁሉንም ህሙማን መንከባከብ ግዴታቸው ቢሆንም ለአእምሮ ህሙማኑ የሚሰጡት ትኩረት እጅግ ከፍተኛ ነው። ከወዲያ ወዲህ ሲሄዱ ነፃነታቸውን ሳይጋፉ በጥብቅና በትእግስት መከታተል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሠራተኞቹ በፈረቃ የህሙማኑንም ሆነ አጠቃላይ በግቢው ያለውን ተገልጋይ ጽዳት የመጠበቅና የመንከባከብ ኃላፊነትም ተጥሎባቸዋል፡፡ ሆኖም ከነሱ በላይ ቁጥር ባላቸው በበጎ ፈቃደኛ አገልጋይ ወገኖች ይታገዛሉ፡፡
እነዚህ ህሙማን ሕክምና የሚያገኙትም በነፃ በሚያገለግሉ በጎ ፈቃደኛ ሐኪሞች አማካኝነት ነው። ሐኪሞቹ ከሕሙማኑ ውስጥ በሪፈር ወደየሆስፒታሉ የሚልኳቸውም አሉ፡፡ በግቢው ውስጥ በተንጣለለ ቦታ ላይ የሰፈረው ባለ 12 ወለል እና ባለ ሁለት ምድር ቤት ሆስፒታል እንዲሁም ከ30 በላይ ክፍሎች ያሉት መኖሪያ በተለይ ለነዚህ ጽኑ ህሙማን ተስፋቸው ነው፡፡ አምስት ቢሊዮን ብሩ ተሰባስቦ የቀረው የግንባታ ሥራ ተጠናቅቆ ሥራ እስከሚጀምር በጉጉት የሚጠባበቁ ብዙዎች ናቸው፡፡
ወጣት ምንዳ በጉብኝቱ ያስቃኘን ብዙ ነው። በማህበሩ በተንጣለለ ግቢ ውስጥ ያልተሠራ ሥራ የለም። በግቢው ውስጥ የሚካሄዱ ግንባታዎች፤ እንክብካቤ የሚደረግላቸው ዜጎችና ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ይስተዋላሉ፡፡ ሥራዎቹ በፍጥነትና በቅልጥፍና ፤ በአጭር ጊዜም እንዲጠናቀቁ እቅድ ተይዞላቸዋል፡፡
የማህበሩ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢንያም ደጋግሞ ‹‹ፈጣሪ ነው የሚሠራው›› በሚል ትሁት ቃል ምላሽ ለመስጠት ቢሞክርም ማህበሩን ከምሥረታው አንስቶ እዚህ እንዲደርስ ራሱን መስዋዕት ከማድረግ ጀምሮ ብዙ ዋጋ መክፈሉን የግቢው ማኅበረሰብ ይመሰክርለታል፡፡ የሥራ ፍቅር፣ ቁርጠኝነት፣ ቅንነት፣ ጽናትና ፈሪሀ እግዚአብሔር ያለው፤ የሚሠራውን የሚያውቅ መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ለማህበሩ ድጋፍ የሚያደርጉ ዜጎችም የቢንያምን ሥነ ምግባር፣ የዓላማ ፅናት በማስተዋልና ፈለጉን በመከተል ከጎኑ ይቆማሉ፡፡
አሁን ላይ በማህበሩ ድጋፍ የሚደረግላቸው ወገኖች ወደማይቀረው ሞት ሲሄዱ አስቀድመው በሚያስቀምጡት ኑዛዜ መሠረት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንዲፈፀም አስከሬን ይዞ በየክልሉ በመሄድ ጭምር ከጎኑ ሳትለይ የምታግዘውን የትዳር አጋሩን ወይዘሮ እሌኒ ነች። ይህንን የበጎነት ተምሳሌት በማሰብ ለማህበሩ እጃቸውን የሚዘረጉና በጉልበት፣ እውቀት፣ በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ ድጋፍ የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው።
ይሁን እንጂ የማህበሩ ዘላቂ ህልውና በመሥራቹ ቢንያም መጣሉ ብዙ ዜጎችን እያሳሰበ ይገኛል፡፡ ከነዚህ ወገኖች አንዷ የሆኑትና ‹‹በግቢው ውስጥ ለጉዳይ መጣሁ›› ብለውን ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ወይኒቱ ስጦታው ይገኙበታል። እርሳቸው ለዝግጅት ክፍላችን የሚከተለውን ብለውናል።
የማህበሩ መሥራች ቢንያም ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ ነው የሚሠራው፡፡ ተገልጋዩን እየተዘዋወረ ሲንከባከብ፣ የመጣውን እንግዳ ሲያስተናግድ፣ ወዲያና ወዲህ ሲሯሯጥ ይውላል፤ እረፍት የሚባል የለውም፡፡ ሌሊቱን የሚያሳልፈውም በማህበሩ ጉዳይ ተጠምዶ መሆኑን አይቻለሁ፡፡ አረጋዊያንንና አቅመ ደካሞችን ከወደቁበት አንስቶ እያበላ እና እያጠጣ ከመንከባከብ ባሻገር በሞት በሚለዩበት ጊዜ የቀብራቸው ጉዳይ ሳይቀር ያስጨንቀዋል። ሰው በተኛበት ሌሊት እሱ ለብቻው ቁጭ ብሎ የሟቾቹን ኑዛዜ በማገላበጥ ቀብር ቦታቸውን ሲያመቻች ያነጋል፤ ለራሱ ጊዜ የለውም፡፡ ይሄ የብዙዎቻችን ተስፋ የሆነው የማህበሩ ህልውና በእርሱ እና በባለቤቱ ላይ ከመመስረቱ አንፃር በብርቱ ያሰጋኛል። በቂ እረፍትና እንቅልፍ በማግኘት ጤናውን መጠበቅ እንዳለበት ይሰማኛል፤ በማለት አስተያየታቸውን አጋርተውናል።
የዝግጅት ክፍላችን ሪፖርተር ወደ ማህበሩ ግቢ ዘልቆ እንዳስተዋለው ቢንያም ሙሉ ቀኑን በተባለው መልኩ ጊዜውን እንደሚያሳልፍ ለመታዘብ ችሏል፡፡ እረፍት ከማጣቱ የተነሳ ወንበር ተደግፎ፤ አንዳንዴም እግሩን ሸብረክ አድርጎና ጉልበቱን በወንበሩ ላይ ባለው ትራስ አሳርፎ ነው መቆሚያ እንደሌለው ጅረት ወደ ቢሮው የሚጎርፈውን ባለጉዳይ የሚያስተናግደው፡፡
ለብዙዎች ምሳሌ የሆነው ተግባሩ እረፍት ማጣቱን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ሕይወቱን ለማህበሩ መስጠቱን ያሳያል። ወራቤ ላይ እየተከፈተ ያለውን ጨምሮ በ45 ከተሞች ቅርንጫፍ ጭምር እየተገለገሉ ያሉ ከስምንት ሺህ በላይ ተረጂዎች አሉ። ይህ ጉዳይ እንደ ወይዘሮ ወይኒቱ ከውጭ ሆነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሰጡትን እንዲሁም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ያሳስባል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጠን ወጣት መሐመድ ሙሳ አይበለውና ቢንያምም ሆነ የትዳር አጋሩ እሌኒ አንዳች ነገር ቢያገኛቸው ማህበሩን እየደገፈ ያለ ሁሉ በድጋፉ ላይቀጥል ይችላል የሚል ስጋት አለው፡፡ በመሆኑም ማህበሩ ከወዲሁ ራሱን በራሱ ማስተዳደር የሚያስችል ቋሚ እና ዘላቂ ገቢ ሊኖረው እንደሚገባ ያምናል፡፡ በመሆኑም የበጎ ምግባሩን ሥራ በዘላቂነት የሚያስቀጥል ፕሮጀክቶች በፍጥነት እንዲያልቁ መላው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ያስተላልፋል።
ጡረተኛ ወታደር ደበሌ ባልቻ በፊናቸው ማህበሩ ዘላቂና ስኬታማ ሆኖ እንዲቀጥል ኅብረተሰቡን ጨምሮ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት በቋሚነት የሚደግፉበት ሁኔታ በሕግ አውጪው፤ አስተርጓሚውና አስፈፃሚው አካል ትኩረት ተችሮት በፍጥነት ቢሠራ የሚል ሃሳባቸውንም ያጋራሉ፡፡ ለአገልግሎት ባስገነባቸው ህንጻዎች ፊት ለፊት ባሉ አንዳንድ ክፍሎች የንግድ አገልግሎት ቢሰጥም ህልውናውን ዘላቂና ቋሚ ለማድረግ የሚያስችል ገቢ ማግኘት እንደሚችልም ሃሳባቸውን ያካፈሉን አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡
መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢንያም ማህበሩ ቋሚና ዘላቂ ገቢ ኖሮት ህልውናው እንዲቀጥል ለማድረግ በንግድ ከመሰማራቱ ውጭ ሁሉንም ሃሳብ ይቀበላል፡፡
‹‹ማህበራችን ለትርፍ የተቋቋመ አይደለም፡፡ በንግድ ተሰማርቶ ትርፍ ማግኘት ዓላማችንም፣ ሙያችንም፣ ፍላጎታችንም አይደለም፡፡ በፍፁም በንግድ የመሰማራት ሃሳብ የለንም›› ይላል፡፡ ግን ደግሞ ነገ እሱና ባለቤቱ ቢያልፉ የማህበሩ ተገልጋዮች ዕጣ ፈንታ ከወዲሁ በብርቱ ያሳስበዋል፡፡ በመሆኑም ዐሻራቸውን ለማሳረፍ ከወዲሁ ቋሚና ዘላቂ ገቢ ለማመንጨት የሚያስችሉ አዳዲስ አሠራሮችን እየዘረጉ መሆናቸውንም ያነሳል፡፡ በውጭም ሆነ በሀገር ውስጥ የተዘረጉ አሠራሮች ሁሉም በወንድማማችነትና እህትማማችነት ስሜት ማህበሩን እየደገፉ በረከት ማግኘት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ እንደሚፈለግም ይገልፃል፡፡
እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢንያም ሃሳብ ማህበሩ ላለፉት አስር ዓመታት ኢትዮ ቴሌኮም የሰጠውን በቀን አንድ ብር ድጋፍ ዕድል ተጠቅሞ ፍቃደኛ ከሆኑ ግለሰቦች በወር 26 ብር ሲሰበስብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ውጭ ማህበሩ እስካሁን ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ቋሚ ገቢ አልነበረውም፡፡ የየእለት ወጪዎቹን ይሸፍን የነበረው በተበታተነ መልኩ በሚገኝ ድጋፍ ነበር፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢንያም እንደሚለው አሁን ላይ ይሄንኑ ገቢ ወጥና ቋሚ ከማድረግ ጀምሮ ለኅብረተሰቡ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት ዘላቂ ለማድረግ የካቲት 1/2017 ዓ.ም የጀመረውን የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ጨምሮ የተለያዩ አሠራሮችን ዘርግቶ እየተጋ ይገኛል፡፡
የዝግጅት ክፍላችን እስካነጋገረው እስከ የካቲት 11/2017 ዓ.ም ድረስ በገቢ ማሰባሰቢያው መርሐ ግብር ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ነግሮናል። በተጨማሪ ወራቤ ላይ እየተከፈተ ያለውን አንድ ማዕከል ጨምሮ በሀገሪቱ 45 ከተሞች ላይ የሚገኙ ከ8ሺህ በላይ ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያንን፣ አቅመ ደካሞች፣ የአእምሮ ህሙማንን፣ አካል ጉዳተኞችን እንዲሁም በጎዳና የወደቁና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በማንሳት ዘላቂ አገልግሎት ለመስጠት ሁሉም ዜጎች የማህበሩ አባል የሚሆኑበት የቴሌ ብር የክፍያ ሥርዓት መጀመሩ ተጠቃሽ ነው፡፡
በውጭ ሀገር ያሉ ዜጎች ወገናቸውን የሚደግፉበት ድረ ገፅ፣ በተለይም Zol Cash up GoFund Me የተሰኘ 02409382992፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር 7979 ሌላው የገቢ ማሰባሰቢያ መንገድ ነው፡፡ እንዲሁም በዚሁ ሂሳብ ቁጥር ቴሌ ብር ገቢ የሚሰበሰብበት አዳዲስ አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ከፔሮል ተቆርጦ ገቢ የሚሆን ደመወዝም እንደ አማራጭ ተይዟል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ ቢንያም እንደሚናገረው አሁን ላይ ኅብረተሰቡ የስልክ የአየር ሰዓት በፓኬጅ ወደመጠቀም በመግባቱ በግለሰብ ደረጃ በኢትዮ ቴሌኮም አማካኝነት ያገኘው ገቢ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ በዚህ ምክንያትም አዳዲስ አሠራር መዘርጋት ማስፈለጉንም ያነሳል፡፡ የማህበሩ የምግብና መጠጥ ዕለታዊ ወጪ አሁን ላይ ከ2 ነጥብ 5ሚሊዮን ብር በላይ እያደገ መምጣቱም አዳዲስ አሠራር ለመዘርጋት ማስገደዱን ያወሳሉ፡፡ በተጨማሪ በቀጣይ በሌሎች 250 ቦታዎች አገልግሎቱን ለመጀመር መታቀዱ አሠራሩን ለመዘርጋት ምክንያት መሆኑን ያስረዳል፡፡
የማህበሩ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ቢንያም 5 ቢሊዮን ብሩ በዋናነት በዋናው ግቢ በተንጣለለ ሥፍራ ላይ የሰፈረውን ሆስፒታልና የተጋልጋይ መኖሪያ ቤት ሥራ ለማጠናቀቅ፤ ከተረፈም በክልል ከተሞች የተጀመሩ ሥራዎችን ለማከናወን የሚውል ስለመሆኑም ይናገራል። መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጨምሮ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ቀደም ሲያደርግ እንደቆየው፤ ማህበሩ ዘላቂ አገልግሎት የሚሰጥበትን ተግባር አጠናክሮ እንዲደግፍ ጥሪም ያቀርባል፡፡
ድጋፍ የግዴታ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ተቋማት የቢሮ ዕቃ፤ ግለሰቦችም እንዲሁ አዳዲስ የቤት ዕቃ፤ አልጋ፤ ፍራሽ፤ ሲቀይሩ ነባሮቹን ወደ ማህበሩ ቢልኩ መልካም መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ በማህበሩ የማይፈለግ ቁሳቁስ እንደሌለም ይናገራል፡፡
‹‹ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው›› የሚለው የማህበሩ መሥራች ቢንያም በተለይ ከገንዘብ ይልቅ በበጎ ፈቃድ የሚያገለግል ሰው ባለሙያም እንደሚያስፈልግ ይናገራል፡፡ የመገናኛ ብዙሃን ይህንን መረጃ ለማኅበረሰቡ የማድረስ የዘወትር ድርሻቸውን እንዲወጡም ጠይቋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም