ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የችግር መፍቻ ቁልፎች

ሁለቱም ለረጅም ዓመታት በጉርብትና አብረው የኖሩ የመቱ ከተማ ነዋሪዎች ናቸው። አቶ አብዱልጀሉል ቡካር ከወር በፊት ከአቶ ከድር አባጋሮ አንዲት የፈረንጅ ላም በ210 ሺ ብር ይገዛሉ። ሻጭ ላሚቱን የሸጡላቸው ነፍሰ ጡር ናት ብለው ቢሆንም ገዥ ለባለሙያ ሲያሳይዋት ነፍሰ ጡር አልነበረችም። ገዥ “ለምን ታታልለኛለህ”፤ ሻጭ “ነፍሰ ጡር ናት ብዬ አልሸጥኩልህም” የሚል ክርክር ይነሳና በመካከላቸው ግጭት ይፈጠራል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ መገለጫ ከሆኑ አሠራሮች መካከል ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ለዚህ ዓይነተኛ መፍትሔ ናቸውና ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ባሕላዊ ፍርድ ቤት ይሄዳሉ። እነዚህ ፍርድ ቤቶች መሠረታቸውን ድንቅ ተሞክሮው ከሀገር አልፎ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ የባሕልና ትምህርት ድርጅት እውቅና ያገኘው የገዳ ሥርዓት አካል ናቸው። በመሆኑም አሁን ላይ የክልሉ መንግሥትም እውቅና ሰጥቷቸው በአዋጅ ቁጥር 240/2013 ለመቋቋም በቅተዋል። ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ሥራ ከጀመሩ ከሦስት ዓመት ወዲህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሆኑ መዛግብት ውሳኔ በመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን ሂደትና ይሄንኑ ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በብርቱ እያገዙ ይገኛሉ።

በእነዚህ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ቀርቦ ጥፋቱን የሚያስተባብል ወይም የሚክድ ማንም የኦሮሞ ተወላጅ የለም። ኦሮሞ በባሕሪው አይዋሽም፤ ድንገት ዋሽቶ ቢገኝ ደግሞ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የተሰየሙትን አምስት የአባ ገዳ ዳኞች እና አንዲቷን ሀደ ሲንቄ ቀና ብሎ ለማየት እንኳን አይደፍርም። ጉልበቱ ይከዳውና ብርክ ይይዘዋል፤ ይርበደበዳል። ወደነዚህ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛው ፍርድ ቤት እውነቱን ሸምጥጦ እና በሐሰት አስወስኖ ቢመጣም በፍፁም መካድ አይችልም። እውነቱን ተናግሮ በሐሰት የወሰደውን ንብረት ለባለቤቱ ይመልሳል ይላሉ አቶ አብዱልጀሉል ቡካር።

በባሕላዊ ፍርድ ቤቱ በታየው ጉዳይ ላሟን የሸጡላቸው አቶ ከድር አባጋሮ በፍርድ ቤቱ እውነቱን አምነው 210ሺ ብራቸውን እንደመለሱላቸውና ላሟንም መልሰው መውሰዳቸውንም ነግረውናል።

አባገዳ ተስፋዬ ደቻሶ ኩምሳ እንደሚሉት፤ በባሕላዊ ፍርድ ቤት በክህደት የሰው ንብረት ዘርፎ የሚቀር ሰው የለም። ማኅበረሰቡ ፍርድ ቤቱ ከአያት ቅድመ አያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ባሕልንና ዕምነትን መሠረት አድርጎ የሚሠራበት በመሆኑ በእጅጉ ያከብረዋል። በፍርድ ቤቱ ተሰይመው ለሚዳኙት አባገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎችም ከፍተኛ ክብር ይሰጣል። በመሆኑም መደበኛ ፍርድ ቤት እስከ ሰበር በመድረስ በብር እና በተለያየ መንገድ በሐሰት አስወስኖ የመጣ ቢሆንም እንኳን ባሕላዊ ፍርድ ቤት ሲቀርብ አይክድም። እሳቸው እስከሚያውቁት ድረስ ለመካድ የሞከሩ የሉም። ቢኖሩ እንኳን ወዲያው ነው የሚቀሰፉት። ክደው ገና ከፍርድ ቤቱ ከመውጣታቸው የመኪና አደጋ ወይም ሌላ ችግር ያጋጥማቸዋል። እንዲሁም የሞቱ ሰዎች መግጠማቸው የፍርድ ቤቱን ዳኝነት ሂደት እንደእግዚአብሄር ብይን እንዲቆጥረው አድርጎታል። በዚያ ላይ የፍርድ ሂደቱ መሐላ እና እርግማን አለው። የሚቀስፈው ይሄው ነው ተብሎም ይታመናል። በመሆኑ ተገልጋዩ ይሄንኑ ፍራቻ እውነቱን እንዲናገር አስገድዶታል። በአዳማ ባሕላዊ ፍርድ ቤት እየሠሩ ያሉት አባ ገዳ ተስፋዬ በሥራቸው የገጠማቸውንም ለማሳያነት ያቀርባሉ፡፡

አባገዳው እንደሚሉት ከ15 ቀን በፊት ሁለት ተከራካሪዎች ወደ ፍርድ ቤቱ መጥተው ነበር። አንዱ የሌላውን መሬት ወስዶበት ተካክደው ነው የመጡት። ወሳጁ በ1994 ዓ.ም መሬቱን በሐሰት ቀምቶ ወስዶ እስከ ፌዴራል ሰበር ደርሶ ውሳኔም አግኝቶበታል። እነሱ ጋር መጥቶ መካድ ባለመቻሉ በሳምንቱ 12 ሚሊዮን ይሸጣል ተብሎ የተገመተውን መሬት ለባለቤቱ የመለሰበት ሁኔታ አለ። አሁን በመካከላቸው እርቅ ወርዷል። ወደ ድሮ መልካም ግንኙነታቸው ተመልሰዋል። በፍርድ ቤቱ እስከ ደም መቃባት ደርሰው በጎማ የታረቁና ቀድሞ ወደ ነበረው መልካም ግንኙነታቸው ተመልሰው በሰላም እየኖሩ ያሉ ቁጥራቸው በርካታ ነው። ፍርድ ቤቱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አሉት። ከመደበኛው ፍርድ ቤት ጋር ሲነፃፀር ለተገልጋዩ ማኅበረሰብ የሚያስገኘው ፋይዳ በብዙ መልኩ ይለያል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከራካሪዎቹ በሚኖሩበት አቅራቢያ ያለና ክርክሩም በዚሁ አካባቢ የሚካሄድ በመሆኑ የትራንስፖርትና ሌሎች ወጪዎች የሚያስወጣ አለመሆኑ አንዱ ነው። እንግልቱንም ቢሆን በተለያየ መንገድ ያስቀራል። መተማመንን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ጠበቃና ሰነድ የማያስፈልገው መሆኑም ከሚያስገኘው ጥቅም ይጠቀሳል፡፡

አባ ገዳው እንደሚሉት አሁን ላይ በዚህና በሌሎች ፍርድ ቤቱ በሚያስገኘው ጥቅም ተገልጋዩ እየተበራከተ መጥቷል። ፍርድ ቤቶቹን እየገነባ ያለውም ጥቅማቸውን የተረዳው ይሄው ተገልጋይ ነው። በመሆኑም እሳቸውና አምስት ባልደረቦቻቸው በሳምንት ሁለት ጊዜ እየገቡ ኅብረተሰቡን በመዳኘት በባሕላዊ ፍርድ ቤቱ እየሠሩ ይገኛሉ። ከሰው ብዛት ስድስት ሰዓት መውጣት ሲገባቸው እስከ ዘጠኝ ሰዓትና በላይ የሚቆዩበትም ሁኔታ አለ። ሆኖም በበጎ ፈቃድ በነፃ ነው እንጂ የሚሠሩት ደመወዝ የላቸውም፡፡

ማኅበረሰቡ ወደ ባሕላዊ ፍርድ ቤቱ የሚመጣው ያስታርቁኛል፣ ንብረቴን ያስመልሱልኛል ብሎና ግልጽ ሆኖ ነው። ይሄን እምነቱን ማሳካት ከደመወዝ በላይ በመሆኑ በበኩላቸው ደስተኛ ናቸው አባገዳ ተስፋዬ። በዚህ መልኩ እንደ አዳማ ያሉ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ስኬታማ በመሆናቸው በክልሉ በሌሎችም አካባቢዎች ካሉ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ጋር ተወዳድረው አንደኛ በመውጣታቸው ተሸላሚ ስለመሆናቸውም ይናገራሉ።

አዳማ ላይ ያለውና እነ አባ ገዳ ተስፋዬ የሚሠሩበት ብቻ ሳይሆን እንደ ክልል ኦሮሚያ ላይ በባሕላዊው መንገድ እየተሠራባቸውና ዳኝነት እየተሰጠባቸው ያሉት ፍርድ ቤቶች በክልሉ የፍትሕ ተደራሽነትን በማስፋፋቱ ረገድ የድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡

ሀደ ሲንቄ ወርቅነሽ ጎፋ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ ተገልጋዮቻቸው እየተበራከቱ በመምጣታቸው ፍርድ ቤቶች መስፋፋት አለባቸው ይላሉ። እንደእርሳቸው በአሁኑ ወቅት ፋይዳቸው የጎላ መሆኑም በማኅበረሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ተይዞባቸዋል። ተገልጋዩ የሚመጣው በልበ ሙሉነት ተማምኖባቸው ነው። ንብረቴን ያስመልሱልኛል፤ ከባላንጣዬ አስማምተው በሰላም እንድኖር ያደርጉልኛል፤ ትክክለኛ ፍትሕ አገኛለሁ ብሎ በሙሉ እምነት ነው።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና በባሕላዊ ፍርድ ቤቱ መፍትሔ ማግኘታቸውን የተናገሩት እንዲህ ሲሉ ነው። “የሌላ ብሔር ተወላጅ ብሆንም ያበደርኩትን ገንዘብ ተክጄ ትክክለኛ ፍትሕ አግኝቻለሁ” የሚሉት አስተያየት ሰጪ ኦሮሚኛ ቋንቋ ባይችሉም አስተርጓሚ ቀርቦላቸው በራሳቸው ቋንቋ መዳኘታቸውን ይናገራሉ። ፍርድ ቤቶቹን በማደራጀትም ሆነ በሌሎች መንግሥት እገዛ ሊያደርግላቸው ይገባል የሚል ሀሳብ እንዳላቸውም ነግረውናል። በየቋንቋው የሚዳኙ በመሆኑም በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በመላው ሀገሪቱ ቢስፋፉ መልካም ነው የሚል ሀሳብ አላቸው። በተለይ ቀላል የሚባሉ ጉዳዮችን እነሱ የሚያዩበት የአሠራር ሥርዓት ቢዘረጋ በፍርድ ቤት የሚታየውን መጨናነቅ ይቀንሰዋል ባይ ናቸው፡፡

አቶ ፈይራ ኃይሉ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተርና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ (ተወካይ) ናቸው። ኃላፊው አሁን ላይ ፍርድ ቤቶቹ በብዙ ነገር ተመራጮች እየሆኑ መምጣታቸውን ይናገራሉ። ማኅበረሰቡ በሰላም እርስ በእርስ ተከባብሮ፤ ተሳስቦና ማኅበራዊና ባሕላዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲኖር ከማስቻል አንፃር እያበረከቱት ካለው ፋይዳ አንፃር መስፋት ያለባቸው መሆኑን ማመናቸውንም አልሸሸጉም።

ባሕላዊ ፍርድ ቤቶቹ ከዘመናዊ ፍርድ ቤቶች የሚለዩበትን አስመልክተው እንደሚናገሩት፤ እነርሱ ጋር የሰነድ ማስረጃ አያስፈልግም። ከአያት ቅድመ አያት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እምነት ብቻ ነው የሚጠየቀው። እምነቱ ደግሞ እውነት መናገር ነው። በፍርድ ሂደቱ እምነቱን የሚያፀና ታላቅ መሐላም አለ። የፍርድ ቤቶቹ ዳኞች የሥራ መሣሪያ ይሄው ነው። ባሕሉንና የአኗኗር ዘይቤውን ማዕከል በማድረግ የሚከናወን ሥርዓት በመሆኑ ለመዋሸት አይመችም። ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ ቀርቦ ገለፃ ከተደረገለት በኋላ ወደ መሐላ ይገባል። ያጠፋው ይቅርታ በመጠየቅ አጥፍቻለሁ ብሎ ያምናል። የተጎዳውም ምንም አይደለም ይቅር ብዬሃለሁ ብሎ ሁለቱም መተማመን ላይ ይደርሳሉ። ዳኞች አስቀድመው ይሄን ካደረጉ በኋላ በሁለቱም ለቀረበው ጉዳይ እልባት ወደሚገኝበት ይዞራሉ። ፀብ ከሆነ ከፍቅር በቀር እንዳይዳረሱ አክለውበት በዚሁ መንገድ ይቋጫል። ንብረት ወይም ገንዘብ ከሆነም ለባለቤቱ እንዲመለስ ውሳኔ ይሰጣል። የውሳኔው ቀነ ገደብ ሲኖረው ከቀነ ገደቡ እልፍ አይባልም፡፡

ኃላፊው እንደሚናገሩት፤ ዘመናዊውና መደበኛ ፍርድ ቤት ግን ፍትሕ ለማግኘት ዋናው ጉዳይ የሰነድ ማስረጃ ነው። አንድ ዜጋ ፍርድ ቤት ቀርቦ ፍትሕ ለማግኘት በርካታ ነገሮች ያስፈልጋሉ። ሕግ ማወቅ አስፈላጊና ዋነኛው ነው። የሕግ ባለሙያ ጠበቆችን መቅጠር ወይ የሕግ ባለሙያ መሆን የሚያስፈልግበት ጊዜም ብዙ ነው። በዘመናዊ ፍርድ ቤቶች የማሸነፍ የመሸነፍ ሁኔታ ሲኖር የሚቀርቡ ጉዳዮችም ይበዛሉ። የሚታዩትም በውሱን የሰው ኃይል በውሱን ዳኞች ከመሆኑ አንፃር የባለጉዳይ መጉላላት ያጋጥማል። በአገልግሎት ጥራት ችግር ሊከሰትም ይችላል። ከቦታ ቦታ መሄድም፤ የትራንስፖርት፤ የመኝታ፤ የምግብና ሌሎች ወጪዎች ይጠይቃል፡፡

በባሕላዊ ፍርድ ቤት ግን ፍርድ ቤቶቹ ኅብረተሰቡ ከሚኖርበት አካባቢ የሚርቅበት ሁኔታ የለም። ክስ ለመመሥረት፤ ለትራንስፖርትና ለሌሎች ተብሎ የሚወጣ ወጪም አይኖርም ።

በመሆኑም በዚህ ብቻ እንኳን ነፍሰ ጡርና የሚያጠቡ እናቶች፤ አቅመ ደካሞች፤ አካል ጉዳተኞች፤ በአጠቃላይ ረጅም ጉዞ መጓዝና ከቤትና አካባቢያቸው ርቀው መሄድ፤ ማደር በማይፈልጉና በማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች ፍርድ ቤቶቹ ተመራጭ ሆነዋል። በአጠቃላይ በክልሉ እየተሠራባቸው የሚገኙ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች የፍትሕ ተቋማትን ከማስፋት አንፃር ከፍተኛ ሥራ እየተሠራ በመሆኑ በመደበኛው ፍርድ ቤት ከመጨናነቅ የተነሳ በአገልግሎት ጥራት ላይ የነበረውን ከፍተኛ ጫና መቀነስ ችለዋል።

ከዚህ በፊት በኦሮሚያ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጉዳዮች ቁጥር ሲጨምር ነበር፤ አሁን ከ2012 ጀምሮ የባለጉዳዩ ቁጥር በተወሰነ ደረጃ እየቀነሰ መጥቷል። የኅብረተሰቡም ግንዛቤ እየሰፋ ሄዶ፤ የባሕል ፍርድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ በመግባታቸው ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች ላይ ጫናው ቀንሷል። ዳኞች ጉዳዮችን በጥራት እንዲያዩ አስችሏል። ጥራትን በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመርም የራሳቸው አስተዋፅዖ አድርገዋል። ኅብረተሰቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል።

አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል 7 ሺህ 481 ቀበሌዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ በ 6 ሺህ 913ቱ ቀበሌዎች ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመዋል። በወረዳ ደረጃም 370 የባሕል ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ፍርድ ቤቶቹ በክልሉ አገልግሎቱን መስጠት ከጀመሩ ከሦስት ዓመት ወዲህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ መዛግብት ውሳኔ በመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እያገዙ ይገኛሉ።

ሆኖም በክልሉ ለዘመናት ሲሠራባቸው የቆዩ እንጂ አዲስ አይደሉም። “የገዳ ሥርዓት በውስጡ ከያዛቸው ሥርዓቶችና ጉዳዮች መካከል የማስታረቅ፤ አለመግባባቶችን በእርቅ የመጨረስ፤ የበደለ ሲቀጣ፤ የተበደለ ደግሞ ሲካስ እንደነበር ያሳያል” የሚሉት ኃላፊው ግጭቶች ሲኖሩ በማኅበረሰቡ ውስጥ በባሕላዊ መልኩ፤ የመጨረስ ጉዳዮች እንደነበሩም ይናገራሉ። ሆኖም እነዚህን የማስፈፀም እና ጉልበት እንዲኖረው የማድረግ ሥራ ያልነበረ መሆኑንም ያነሳሉ። ምክንያቱም በአዋጅ ምክንያት በሀገሪቱ ትልቁ ሕገ መንግሥት ለመደበኛ ሕጎች እውቅና ሰጥቶ ስለነበር ነው። ይሄም በማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ባሕላዊና ሃይማኖታዊ የሙግት መስጫ ዘዴዎች ካሉ የሕዝብ ተወካዮች እና የክልል ምክር ቤቶች እውቅና ይሰጣሉ የሚል ነው። በመሆኑም ተቀዛቅዞ የነበረውና በማኅበረሰብ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የነበረው ባሕል እንደገና እውቅናና የሕግ ሽፋን አግኝቶ ወደ ሥራ ተገብቷል። ሕጉ ከዳኞቹ መካከል አንዷ የግድ ሴት መሆን እንዳለባትም ደንግጓል።

ኃላፊው እንደሚያነሱት ኦሮሚያ ሰፊ ክልል ከመሆኑ አንፃር የባሕላዊ ፍርድ ቤቶቹ አስተዋፅዖ የጎላ ነው። ተገልጋዩ ፍትሕ ለማግኘት አዲስ አበባ ወዳሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ሲመላለስ ኖሯል። ከምዕራብ ወለጋ፤ ከቄለም ወለጋ ጊዳን ወይ ከምስራቅ ሐረርጌ ደግሞ ከኬንያ ጫፍ ቦረና የሚመጣበት ሁኔታ ነበር። ለጉዳዮቹ እልባት የሚያገኘው በዚህ ሁኔታ ብዙ እንግልት ደርሶበት የነበረ ሲሆን 6 ሺህ13ቱ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸው ይሄን ጫና መቀነሱ በግምገማ ታይቷል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ልዑክ ተዘዋውሮ ጉብኝት ባደረገባቸው ቦታዎች ያገኛቸው ዜጎችም የዓይን ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ዓርብ የካቲት 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You