የዘንድሮ ክረምት ገና ከመግቢያው ጠንከር ያለ ነው። የሚያወርደውን ዶፍ በአዲስ አበባ ከሚገኙ የቀበሌ ቤቶች አብዛኞቹ ሊቋቋሙት አልቻሉም። ቀበሌ ዕድሳት ስለማያደርግላቸውና ነዋሪዎቻቸውም ለማደስ የሚያስችል አቅም ስለሌላቸው አብዛኞቹ በዝናቡ እየፈረሱ ይገኛሉ። በወረዳ አራት መሳለሚያ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ በአንድ ግቢ ውስጥ ከሚገኙ ሰባት የቀበሌ ቤቶች የሶስቱ ዕጣ ፈንታ ይሄ ሆኖ መቆየቱን በቤት ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ይናገራሉ ።
ዕድሜያቸውን በውል ባያውቁትም ጃንሆይ ፋሽሽትን ድል አድርገው ወደ አገራቸው በተመለሱ ሦስተኛ ዓመት ላይ ነው ግንጪ በሚባለው አካባቢ የተወለዱት፤ እናት እልፍነሽ በአሉ ግቢ ውስጥ በሚገኘው የቀበሌ ቤት መኖር ከጀመሩ 35 ዓመታትን አስቆጥረዋል። ወደዚህ ቤት የገቡት መርካቶ አውቶቡስ ተራ አካባቢ ወንዝ ዳር የነበረውን ቤታቸውን ለውጠው ነው ። ሲገቡ ቤቱ በጥሩ ይዞታ ላይ እንደነበረ ያስታውሳሉ ። ከጊዜ ብዛት በማርጀቱ እየፈረሰ መጣ።
በተለይ ጣሪያው ብዙ ቦታዎች በመበሳቱ ባለፉት አራት ክረምቶች ቁም ስቅላቸውን ሲያሳያቸው ነው የኖረው። በቤት ውስጥ ያለውን ዕቃ፤ ከጎረቤት በተበደሩት በትላልቅ የልብስ መዘፍዘፊያ በሙሉ በመደቀን ቆመው የሚያድሩበት ጊዜ ብዙ ነው ። እንዳያድሱት አቅም የላቸውም። ባለቤታቸው በዕድሜ ምክንያት ይሰሩበት የነበረውን የግል ጫማ ቤት ሥራ አቁመው ቤት ከዋሉ ብዙ ጊዜያቸው ነው።
ከዚህ በፊት ከወዲያ ወዲህ ተሯሩጣ ምትደጉማቸው አንዲት ሴት ልጅ ብትኖራቸውም ገና በወጣትነቷ ታማ የአልጋ ቁራኛ ከሆነች 30 ዓመቷ ነው። በመሆኑም ጎረቤቶቻቸው ችግራቸውን ለመንግስት አስረድተው በየወሩ በሚሰጣቸው 700 ብር ነው የሚተዳደሩት። ኑሮ ውድ በመሆኑና ብሩ የቤቱን ክራይ ከፍሎ ለቀለብ ስለማይበቃቸው አንዴ ምሳ ሌላ ጊዜ እራት እያሉ ጎረቤቶቻቸው በሚያበሏቸው ይደጉሙታል። ቤታቸውንም ቢሆን በየክረምቱ ሲጠግኑላቸው ነው የቆዩት። ሆኖም ዘንድሮ ዝናቡ ኃይለኛ በመሆኑ እንደፊቱ ሊቋቋመው ባለመቻሉ ሙሉ በሙሉ በዶፉ ፈርሶባቸዋል።
አሁን ላይ ከዚህ በፊት የአካባቢውን አረጋውያንና ኑሯቸው ዝቅተኛ የሆነ የአካባቢውን ነዋሪዎች ቀለብ በመስፈርም ሆነ በገንዘብ ይደጉሙ የነበሩ የአካባቢው ተወላጅ ሙሉ በሙሉ አፍርሰውና አንድ ክፍል የዕቃ ቤት ሁሉ ጨምረው በብሎኬት እየሰሩላቸው እንደሚገኙም ወይዘሮ እልፍነሽ ነግረውናል። እስኪያልቅ ከቅዝቃዜ ጋር ተያይዞ የሚነሳ ኃይለኛ አስም ስላለባቸው ሁሌ የምትደግፋቸው ጎረቤታቸው መኝታ ቤቷን ለቃላቸው ከነባለቤታቸው እሷ ጋር ነው ያሉት።
በዚሁ ግቢ ከሚገኙት በዝናቡ ምክንያት ከፈረሱ ሦስት የቀበሌ ቤቶች ሁለተኛው የአራሷ የወይዘሮ አይሻ አወል ነው። አይሻ እንደነገረችን አቅፋ እያጠባች ያለችውን የሁለት ወር እርጥብ ልጅ ጨምሮ ስድስት ልጆች አሏት። ቤቱ በላይዋ ላይ በመውደቁ ልጇን የወለደችው ጎረቤት ተጋግዞ አውጥቷት እዛው ላይ ሸራ ወጥሮላት ነው። የወደቀው በተደጋጋሚ ለቀበሌ አመልክታ ባለመታደሱ ነበር። በግሏ እንዳታድሰው ድንችና ሽንኩርት ቸርችራ ነበር የምታድረው፤ አሁን ላይ ደግሞ እሱንም መስራት የማትገችልበት የጀርባ ህመም ከፍተኛ የአጥንት ስብራት ስላጋጠማት ስራውን ትታለች።
አሁን የምትተዳደረው ባሏ ግለሰብ ጋር ጥበቃ እየሰራ በሚያገኘው 800 ብር ነው። ብሩ ገና ሳይመጣ በ15 ቀኑ በሱቅ ዱቤ ነው የሚያልቀው። ደግነቱ አምስቱ ልጆቿ ትምህርት ቤት ስለሚመገቡ ቁርስና ምሳ አታስብም። የኮረና ጊዜግን በጣም ተቸግራ ነበር። እሷ በቤት ውስጥ የሚላስ የሚቀመስ ጠፍቶ ሦስት ቀን ጦሟን ማደሯን ታስታውሳለች። በዚህ ችግሯ ደርሰው ቤቷን በብሎኬት እየገነቡላት የሚገኙትንና በጎነትን ከ102 ዓመቱ የዕድሜ ባለፀጋ አባታቸው ሀጂ መሐመድ ብርሃን የወረሱትን አቶ አላሚን መሐመድን ደጋግማ ታመሰግናለች። ግለሰቡ በደረሳቸው መረጃ መሰረት ሰዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ከነልጃቸው መጥተው አይተው የነበሩበትንም ታነሳለች። ደሆችን በመርዳትና ከግቢው ጀርባ ያለውን ትልቁን የቢላል መስጂድ በመገንባት በአካባቢው የልማት ሥራዎችን ሲያከናውኑ የኖሩ ቅኖች መሆናቸውን ትጠቅሳለች።
ሦተኛው የተደረመሰው የቀበሌ ቤት የሶስት ወላጅ አልባ ልጆች ቤት ነው። የቤቱ ትልቅ የምትባለው ወጣት እንደምትለው አባታቸው ከሞተ 16 ዓመት ፤ እናታቸው ከሞተች ደግሞ 10 ዓመት ሆኗታል። እናቷ ስትሞት የ10 ዓመት ልጅ ነበረች። እሷን ጨምሮ ወንድሞቿን ያሳደጓቸው ጎረቤቶች ናቸው ። ዓመት በዓልን የሚያከብሩት የግቢው ሰው ከየኪሱ ገንዘብ አዋጥቶ ከቅርጫ ጀምሮ ለበዓሉ የሚያስፈልጋቸውን አድርጎላቸው ነው። በተለይ የቤዛ አለማየሁ እናት ከልጆቿ እኩል እያበላች እያጠጣች ነው እዚህ ያደረሰቻቸው። እሷ ትምህርቷን እስከ ስምንተኛ ክፍል
ወንድሞቿም የተወሰነ ደረጃ እንዲማሩም አድርጋለች። አሁን ላይ እርሷ የጋራዥ ሰራተኞችን ልብስ እያመጣችና አንዳንድ ሥራዎች እየሰራች ወንድሞቿን ብታስተዳድርም የፈረሰውን ቤት ለመሥራት ግን አቅም አልነበራትም። ቤቱ ከመፍረሱም በላይ ከሥር የመፀዳጃ ፍሳሽ ስለሚገባበት ለመኖር ተቸግረው ነበር ።
አሁን ላይ አባታቸውና እሳቸው ደሆችን በመርዳት በጣም የታወቁ ነጋዴ በብሎኬት እየገነቡላቸው በመገኘታቸው ተደስታለች።
አቶ አላሚን መሐመድ ግንባታውን በ150 ሺህ ብር መጀመራቸውን ይናገራሉ። ተወልደው ያደጉት እዛው አካባቢ ነው ።ሰዎቹንም ነዋሪዎች በመሆናቸው ያውቋቸዋል። ኑሯቸው ለቤት ዕድሳት ቀርቶ የእለት ጉርሳቸው አይሸፍንም። ያሉበትን ያዩት ከቀናት በፊት ከ102 ዓመቱ አባታቸው ጋር ጎብኝተዋቸው ነው። ወላጅ አባታቸው ሀጂ መሐመድ ብርሃን ለጉምሩክ፤ለኦሜድላና ለተለያዩ ክለቦች ተጫዋች የነበሩ ናቸው። የንግድ ምክርቤትን ከመሰረቱት አንዱ ናቸው። የቢላል መስጂድንም መስርተውና አሰርተዋል።የፈረሱ የደሃ ቤቶችን በመገንባትና ችግርተኞችን ሁሉ ሰብስበው በመርዳት በርካታ የልማት ሥራዎች በመሥራትም ይታወቃሉ። በቅርቡ ሦስቱ የቀበሌ ቤቶች ሙሉ በሙሉ በመፍረሳቸው ነዋሪዎቻቸው በእጅጉ መቸገራቸውን ተመልክተዋል።
በወረዳ 4 የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የአካባቢው ነዋሪ አቶ ንጉስ አድነው እንደሚሉት እሳቸውም ሆኑ አባታቸው ቅን ልቦች አሏቸው።በብርቱ ደሆችን ያስባሉ።በተለይ አባታቸው እንደ አገር በስፖርቱና በንግዱ ዘርፍ ካበረከቱት አስተዋጽኦ ባሻገር በበጎ ሥራቸው በአካባቢው ይታወቃሉ። ልጃቸውም በጎነትን ከአባታቸው ወርሰዋል። ያሉበትን አይተው እጅግ አዝነው ቤታቸውን አስገንብተውላቸዋል። ሰው ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው በሚል ቢሂል በአካባቢው የፈረሱ የደሃ ቤቶችን ከመገንባት ጀምሮ ፤ቀለብ በመስፈርና ማዕድ በማጋራት እንዲሁም በሚያንቀሳቅሱት ንግድ ለአካባቢው ወጣት የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2014