ባለፈው ሰሞን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት እኔን እና ሌሎች ጥቂት ሰዎችን የጸጥታ ተቋማትን እንድንጎበኝ ጋብዞን ነበር። ተጋባዦቹ ከሁሉም የሙያ ዘርፎች የተጋበዝን ነን ማለት እንችላለን። ከኪነ ጥበብ ሰዎች ፋንቱ ማንዶዬ እና ደበሽ ተመስገን ፤ ከፖለቲከኞች አንዱአለም ቤኬቶ ፤ ከአክቲቪስቶች ስዩም ተሾመ፤ ከጋዜጠኞች ጌጡ ተመስገን ፤ ከምሁራን ኢንጂነር ጌታሁን ሄራሞ እና ዶ/ር ወዳጄነህ መሀረነ ፤ ከቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ሰለሞን ካሳ (ቴክቶክ ዊዝ ሰለሞን) ወዘተ.. መጥቀስ እንችላለን። በጥቅሉ ባለሙያዎች በየአይነቱ የተሰባሰቡበት ጉብኝት ነበር።
ጉብኝቱ የተጀመረው ከኢፌዴሪ አየር ሃይል ነበር። ቦታውም ቢሾፍቱ ነው። ማልደን ስንደርስ የተቀበሉን ዋና አዛዡ ጄነራል ይልማ መርዳሳ እና ምክትሎቻቸው ናቸው። ጊቢው መቼም ተውቧል የሚለው ቃል አይገልጸውም። ከአጥሩ ጀምሮ ሁሉም ነገር በውብ ሁኔታ የተሰራ ነው። የበለጠው አግራሞት ግን ገና ከፊታችን እየጠበቀን ነበር። አየር ሃይሉ ጊቢ ከማስዋብም ባለፈ ብዙ ስራ ሰርቷል። ከዚህ ቀደም አየር ሃይልን የሚያውቅ ሰው የቢሾፍቱው ጊቢ ሰፊ ባድማ ነበር።
አሁን ግን ጊቢው ሙሉ አረንጓዴ ነው። ምቹ የአስፋልት መንገድ ተሰርቶለታል። ህንጻዎቹ በፍጹም ጥራት ታድሰዋል። ቴክኖሎጂ ጊቢው ውስጥ ዘልቋል። ሁለት ነገሮች ግን የበለጠ አድናቆት የሚገባቸው ናቸው። አንደኛው ነገር አየር ሃይሉ ጊቢውን ከማስዋብ ባለፈ በወታደራዊውም ዘርፍ ብዙ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ነው። የኢንጂነሪንግ ክፍሉ በተለይ አስደናቂ ስራዎችን እየሰራ ነው። በትምህርት ዘርፍም ብዙ እየተሰራ ነው።
አንድ አየር ሃይል ሊኖረው የሚገባውን ቁመና እየያዘ ነው። ሁለተኛው አስደናቂ ነገር ደግሞ የአየር ሃይሉ መሪዎች ከፖለቲከኛ ይልቅ ወታደራዊ ለዛ የሚጎላባቸው መሆናቸው ነው። በሁሉም ላይ ጥሩ መንፈስ እና የራስ መተማመን ይታያል። ምድሩም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሰማይም የኛ ነው ሲሉ በኩራት ነው። ከዚህ ቀደም አየር ሃይሉ ብቻ ሳይሆን ጠቅላላ ሠራዊቱ ከሕዝባዊነት ይልቅ ፓርቲያዊ ለዛ ነበር። አሁን ያ ጠረን ጠፍቷል።
ከአየር ሃይል ቀጥሎ የተጓዝነው አዲስ አበባ ወደሚገኘው የመከላከያ ዋና ጽ/ቤት ነበር። እዚህ ደግሞ ሌላ አስደናቂ ነገር አየን። ከ13 ዓአመታት መጓተት በኋላ በጣም ግዙፍ ህንጻ ተገንብቷል። ህንጻው ግዙፍ ብቻ ሳይሆን በጣም ዘመናዊ ነው። በመቶዎች የሚቆጠሩ ቢሮዎች ፤ ብዙ ማእድ ቤቶች ፤ እንግዳ መቀበያዎች ፤ የስብሰባ አዳራሾች አሉት። ሁሉም ጽዱ ናቸው። በዚያኑ ልክ ግን በጣም ዘመናዊ ናቸው።
የተቋሙ ቅጽር ጊቢ ውስጥ ተሳስታ የምትገባ ወፍ እንኳን የሚለይ የደህንነት ሥርዓት ተዘርግቷል። የበለጠ አስደናቂው ነገር ግን ዘመቻ የሚመራበት ቴክኖሎጂ ነው። ፍጹም ዘመናዊ ሥርዓት ተዘርግቷል። ጦሩ በአሸባሪው ሕወሓት ወረራ ከገጠመው አደጋ አሁን ሙሉ ለሙሉ አገግሟል። በሰው ሃይልም በትጥቅም ተደራጅቷል። የቴክኖሎጂ ድጋፍ አግኝቷል። ልክ እንደ አየር ሃይሉ ሁሉ የምድር ጦሩም ከፖለቲካ እንደተነጠለ መሪዎቹ በሙሉ እምነት ይናገራሉ።
የሁለተኛው ቀን ጉብኝታችን የተጀመረው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ነው። ቦሌ የሚገኘው ህንጻ ፍጹም ውብ ነው። በቅርቡ ነው የተመረቀው። ህንጻው ውብ ቢሆንም ከባድ ውጊያ የሚካሄድበት ቦታ ነው። ውጊያው የሳይበር ነው። በባንኮቻችን ፤ በግድቦቻችን ፤ በጸጥታ ተቋማቶቻችን እና ሌሎች ላይ በየሰከንዱ የሚደረገውን ጥቃት የሚመክተው እና መልሶ የሚያጠቃው የብሩህ አእምሮ ኢትዮጵያውያን ስብስብ ያለው እዚህ ነው። ውጊያው 24 ሰአት ነው። ኢንሳም 24 ሰአት ይሰራል።
ከሁሉ በላይ አስደሳቹ ነገር ኢንሳ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂዎችን እንዴት አድርገው ኢትዮጵያዊ እንደሚያደርጉት ማየቱ ነው። ብዙ ድንቅ ጭንቅላት ያላቸው ልጆች ብዙ የፈጠራ ስራዎችን አሳዩን። ድህነት ባይዘን ኖሮ እና እነዚህ ወጣቶች ላይ ተጨማሪ በጀት መመደብ ቢቻል ብዙ ታሪክ እንደሚሰሩ እርግጠኛ ሆንን።
የኢንሳ ቆይታን ስንጨርስ እዚያው ጊቢ ውስጥ የሚገኘውን አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲቲዩት ጎበኘን። ይህ ደግሞ ፈረንጆቹ ጨዋታ ቀያሪ (game changer) የሚባሉ የቴክኖሎጂ ስራዎች እየተሰሩበት ያለ ተቋም ነው። የኢንስቲትዩቱ ወጣት ምሁራን በተለይ ቴክኖሎጂ ለጤና አገልግሎታችን መሻሻል የሚፈጥረው እድል እጅግ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ አሳይተውናል።
ዶክተር ብርቅ በሆነባት ሀገር የሚያስፈልገንን ዶክተር ማፍራት እስክንችል ድረስ ያለን አማራጭ አንዲህ አይነት ቴክኖሎጂን ማላማድ ነውና ተቋሙ እየሰራ ያለው ስራ በጣም የሚደነቅ ነው። ከጤናው ዘርፍ ባለፈ በቋንቋ፤ በሳይበር ደህነንት እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ እየተሰራ ያለው አስደሳች ነው።
ቀጣዩ የጎበኘነው ተቋም ለወትሮው እንኳን ለጉብኝት በበሩ ሲያልፉ እንኳ አተኩሮ ለማየት የሚያስፈራውን የብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ቢሮ ነው። አሁን ግን ተጋብዘን ገባንበት ፤ ይባስ ብሎም ምሳ ተጋበዝንበት። ዋና ዳይሬክተሩ ተመስገን ጥሩነት እና ምክትሎቻቸው በር ድረስ መጥተው ነበር የተቀበሉን። ከዚያም ለወትሮው ድብቅ የነበረው ያ አስፈሪ ተቋም አሁን በብርሃን ምን እንደሚመስል አስረዱን።
እዚህም ቴክኖሎጂ ዋና ተዋናይ ሆኗል። የዚህን ጉብኝት ልዩ የሚያደርገው ደግሞ ብዙ አፈታሪኮች እውነት እንዳልሆኑ ማየታችን ነው። ለምሳሌ ያህል ደህንነት መስሪያ ቤቱ እንዲሁ በማሕበራዊ ሚዲያ መንግሥትን የሚቃወሙ ሰዎችን ስልክ ሲጠልፍ እና ፌስቡክ ሲበረብር የሚውል ይመስለን ነበር።
እዚያ ግን ያየነው መስሪያ ቤቱ ከዚያ የበለጠ ብዙ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ያሉ የቤት ስራዎች እንዳሉት ነው። ከዚያም ባለፈ ተቋሙ ብዙ ስራው በአደባባይ የሚታይ ባይሆንም እንኳ እንደማንኛውም መስሪያ ቤት እንደሆነ እና አሁን ከለውጡ ወዲህ ደግሞ ሀገሪቱ ላለባት ተግዳሮት በሚመጥን መልኩ አዲስ ጎዳና ላይ እንዳለ ተረድተናል።
ቀጠልን ፤ ጉዞ ወደ ፌዴራል ፖሊስ ዋና ጽ/ቤት። የተቀበሉን ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ጥሩነህ ናቸው። እሳቸውም ተቋማቸው እያካሄደ ስላለው ሪፎርም እና ስላገኘው ለውጥ ሲያወሩ በኩራት እና በስሜት ነው። አሁን ላይ ተቋሙ የመንግሥትን ትኩረት እንዳገኘ ይናገራሉ። ፌደራል ፖሊስ ላይም አስደናቂው ነገር ተቋሙ ከማኑዋል ወደ ዲጂታል እያደረገ ያለው ሽግግር ነው።
በተለይ የሬዲዮ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ ለጎብኚዎች ተቋሙ እያካሄደ ስላለው ለውጥ ያስረዳው ወጣት አባል ላይ ያለው ከፍተኛ ስሜት እና ቅልጥፍና ተቋሙ አሁን ላለበት ወቅታዊ መነቃቃት ጥሩ ማሳያ ነው። ከዚህም ባለፈ በቴክኖሎጂም በሎጀስቲክስም እያሳዩት ያለው እመርታ ይበል የሚያሰኝ ነው።
የነዚህ የጸጥታ ተቋማት ጉብኝታችን አንድ ተስፋ የሰጠን ነገር ቢሆን የተቋም ግንባታ ስራ እየተካሄደ እንደሆነ ነው። ዛሬ ላይ ጠላቶቻችን በሚሸርቡት ሴራ ብዙ ዋጋ እየከፈልን ቢሆንም ይህ የተቋም ግንባታ ሳይቋረጥ ከቀጠለ ግን ነገ ላይ ጠላቶቻችን ሴራ እንዳይሸርቡ ሳይሆን ሴራ እንዳያስቡ አድርገን ማስቆም እንደምንችል እርግጥ ነው።
በሶስተኛው ቀን ጉብኝታችን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈትቤት ዙሪያ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ለመጎብኘት እድል አግኝተናል። እርግጥ እነዚህ ግንባታዎች በዚያ በኩል ላለፈ ሰው በግልጽ የሚታዩ ቢሆኑም እንኳ ፕሮጀክቱን የሚመሩት ሰዎች እያስረዱ ሲሆን ደግሞ ነገሩ የበለጠ ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ይገኛል።
ለምሳሌ ያህል አራቱ ቤተ መጻህፍትን ብንመለከት ፋይዳቸው እና ትርጉማቸው በጣም ከፍ ያለ ሆኖ አግኝተነዋል። የአብርሆት ቤተ መጻህፍት ፤ የሳይንስ ሙዚየም ፤ የእጽዋት ማእከል እና የማእድን ጋለሪ እያንዳንዳቸው ራሳቸውን ችለው መቆም የሚችሉ ጽንሰ ሃሳቦች እና ተቋማት ናቸው። እነዚህ ተቋማት ስለ ነገይቱ ኢትዮጵያ የሚጠቁሙ የተስፋ ምንጮች ናቸው።
እነዚህ ተቋማት አሁን መገንባታቸው አግባብ እንዳልሆነ የሚያምን ሰው አለ። ከእኛም መሀከል አንዳንዶቻችን ከጉብኝቱ በፊት ያን ስሜት እንጋራ እንደነበር የማይካድ ሀቅ ነው። ነገር ግን በተቋማቱ ውስጥ በአካል ስትገኝ ይህ ስሜትህ አግባብ መሆን አለመሆኑን ትጠራጠራለህ። ተቋማቱ በጣም ውብ እና ግዙፍ ሆነው ነው የተሰሩት። ከውበታቸው እና ከግዝፈታቸው በላይ ግን እንዲይዙ የተፈለገው አላማ በጣም ግዙፍ ነው።
እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ለመድሃኒት እና ለሌላም ተግባር የሚውሉ ብዙ እጽዋት አሏት ስንል ከርመናል። ነገር ግን እነዚያን በስም እንጂ በተግባር የማናውቃቸውን እጽዋት የምናገኘው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊቢ ባለው የእጽዋት ሙዚየም ነው። ኢትዮጵያ ማእድን አሏት እንላለን ነገር ግን እስከዛሬ የትኛው ማእድን የቱጋ እንዳለ ቢጠየቅ አይደለም ተራው ዜጋ ሚኒስቴሩን የሚመራው ሰው እንኳን አይመልሰውም።
አሁን ግን እያንዳንዱ ማእድን ምን አይነት እንደሆነ እና የትኛው የኢትዮጵያ ክልል ላይ እንደሚገኝ ፤ በምን ያህል መጠንም እንደሚገኝ ማወቅ የሚያስችል ሙዚየም እና ሥርዓት ተሰርቷል። ከሁሉ የሚያምረው እና አስደናቂው ደግሞ የሳይንስ ሙዚየሙ ነው። ግዝፈቱ አንድ ደንበኛ ስቴድየም ነው የሚያክለው። ግንባታው ወደ መጠናቀቁ ነው።
ዓላማው የኢትዮጵያ ልጆች አብርሆት ቤተ መጻህፍት ያነበቡትን ንድፈ ሃሳብ በተግባር እንዲያሳዩበት ነው። ተስፋው ከአሁኑ ምራቅ ያስውጣል። ማንም ጤነኛ የሆነ ሰው እነዚህን 4 ተቋማት ከጎበኘ በኋላ የሚለው አንድ ነገር ቢሆን ለምን ተሰራ ሳይሆን ለምን በሁሉም ክልሎች አይሰራም የሚል ነው።
የብሄራዊ ቤተ መንግሥት የመኪና ፓርኪንግ ፤ ከፓርኪንጉ ወደ አንድነት ፓርክ የሚያስገባው ዋሻ ፤ የወዳጅነት አደባባይ እና በአቅራቢያው ያሉ ሌሎች ፓርኮች ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ህንጻ ፤ የማዘጋጃ ቤት እድሳት ወዘተ… ዘላቂ ሀብቶች ናቸው። ስለ እያንዳንዳቸው ብዙ ማለት ይቻላል።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ውስጥ ተቋማት ግንባታ ያለ ዓላማ የሚካሄድ ነበር። ጉምቱ የሚባሉት ባለሥልጣናት ሥልጣን ሲለቁ ስራ ፈትተው ነገር ከሚተበትቡ ተብለው የተቋቋሙ ተቋማት ፤ የተፈጠሩ አደረጃጀቶች ብዙ ናቸው። ብዙዎቹ በጊዜ ሂደት ከስመዋል። ብዙዎቹ የመመስረት ዓላማቸው ፖለቲካዊ ስለነበር ፖለቲካው ሲዛባ አብረው ተናግተዋል። እነዚህ ግን ከፖለቲካ የራቁ ናቸው። ማንም በሥልጣን ላይ ይኑር የሳይንስ ፤ የማእድን፤ የእጽዋት ማእከል ያስፈልገዋል።
የትኛውም መንግሥት የንግድ ባንክን አይነት ግዙፍ ተቋም ቢያገኝ አይጠላም። ሁሉም መሪ ጠንካራ አየር ሃይል ፤ ግዙፍ ምድር ጦር ፤ ከዓለም የሚፎካከር የሳይበር ተዋጊ ፤ እንኳን የተደረገውን ቀርቶ የታሰበውን የሚያውቅ የደህንነት መዋቅር ተሰርቶ ቢጠብቀው ደስተኛ ነው። አሁን እየተሰራ ያለውም ያ ነው። ሁሉም ሰው በብዙ ምክንያት መንግሥት ሊወቅስ ይችላል። እኛ በጎበኘናቸው ተቋማት ግን መንግሥትን ሊያመሰግን ብቻ ነው የሚችለው።
በጉብኝታችን ወቅት በሙሉ ካገኘናቸው ሹማምንት ጋር ጥያቄ የመጠየቅ እድል ስናገኝ ጠይቀናል። ዋነኛ የነበረው ጥያቄ መከላከያው ፤ ፌዴራል ፖሊሱ ፤ ደህንነቱ ፤ ኢንሳው በዚህ ልክ ከተጠናከረ ለምንድን ነው በየቦታው ያለውን የሰው ግድያ ማስቆም ያቃተን የሚል ነበር። ለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መጨረሻ ላይ የሰጡን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ግልጽ ያደረገልን አንድ ሀቅ ቢኖር ግድያውን ለማስቆም ብቸኛው መፍትሄ የተጀመረውን የጸጥታ ተቋማት ግንባታ ማፋጠን እና ማጠናከር ብቸኛው መንገድ እንደሆነ ነው።
የቀይ ባህር እና የአባይ ፖለቲካ ቁጭ ብሎ በማልቀስ፤ መንግሥት በመውቀስ ፤ መሪ በመቀያየር የሚፈታ አይደለም። ብቸኛው መፍትሄ ከፖለቲካ የጸዱ፤ በእውቀት የሚመሩ ፤ በቴክኖሎጂ የዘመኑ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት አቅምን ማሳየት ነው።
የአየር ሃይሉ ጄነራል ይልማ መርዳሳ እንዳሉን ከሆነ፤ አየር ሃይሉን እየገነቡ ያሉት ለመንደር ግርግር ሳይሆን ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ጋር ለማከባበር ለጠላቶቿም ምንም ነገር ከማድረጋቸው በፊት ሁለቴ እንዲያስቡ ለማድረግ ነው።
ደህንነቱ እየተሰራ ያለው ለካፌ ወሬ ለቀማ ሳይሆን ከድንበር ወዲያ የሚሸረብብንን ሴራ አንፍንፎ ለማክሸፍ ነው ፤ ኢንሳ እየተገነባ ያለው የግለሰብ ፌስቡክ ለመበርበር ሳይሆን ለታላቁ ዓለምአቀፍ ጦርነት ነው።
አብርሆት እና የሳይንስ ሙዚየም የሚሰሩት ለማትሪክ ፈተና ሳይሆን ለዓለም አቀፉ ፉክክር ብቁ ሃይል ለማዘጋጀት ነው። እየተሰራ ያለው ለነገ ነው። ይህን እንደ ሕዝብ እኛ ባንረዳ ጠላቶቻችን ግን ከአሁኑ ታውቋቸዋል። ለዚህ ነው አሁን ላይ ወጥረው የያዙን። ጉብኝትቱም ከዛሬው ክስተት በላይ የነገ ተስፋችንን ያየንበት ነውና አስደሳች ነበር ማለት ይቻላል።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2014