‹‹አቤት ዝናቡ ሀምሌን መስሎ የለ እንዴ?። ዘንድሮ ደግሞ ለየት ያለ ነው ፤ ገና ከአመጣጡ ያስፈራል። ኧረ ! ጎርፉ የህጻናትን ህይወት እየቀጠፈ ነው፤ አደጋው በዝቷል… ›› ይላሉ በምንጓዝበት ታክሲ ውስጥ ከጎኔ የተቀመጡት አዛውንት። ጉዳዩ የእኔም ስጋት ጭምር በመሆኑ የጨዋታው አካል ላለመሆን አልፈለኩም። ‹‹እውነት ነው›› ስል ሀሳባቸውን ጭንቅላቴን ነቅነቅ አድርጌ አረጋገጥኩላቸው ። ደግሞም እኮ ዝናቡ ከዳር እስከ ዳር ጠንከር ብሏል።ያው እንግዲህ ያየነው የአዲስ አበባን አይደል፤ ጨዋታችንም እዛው አካባቢ ነው። ከወደየክልሉ ከአየር ትንበያ መስሪያ ቤቱ ውጪ ማረጋገጫ የለንም።
‹‹ሞቴን በሀምሌ ጨለማ አያድርገው›› ይሉ ነበር አያቴ። የሀምሌን ወር በጣም አድርገው ይፈሩታል። ቀልባቸው ሀምሌን አይወደውም፤ ቢሆንም እንኳን ከክረምቱ ነሀሴ ይሻላቸዋል። ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ቀለባቸውን፣ ጉዳያቸውን ሁሉ አጠናቀው በሀምሌ በር ዘግተው ይቀመጡ ነበር። ቀኑ ብራ የሆነ ሰዓት ሮጥ ብለው የቤተክርስቲያን ደጅ ይረግጡ ይሆናል እንጂ በጭራሽ ወሩን ለስራ አይመኙትም። ሞታቸውም በሀምሌ ዶፍ እንዳይሆን የሚማጸኑትም ቀባሪ እንዳይመረር ፣ በድናቸው ጎርፍ በሞላው ጉድጓድ ውስጥ እንዳይወድቅም አይደል!።
እንኳንስ በህይወት እያሉ በአይናቸው እያዩ በዝናብ ምንም ማድረግ አይፈልጉም። ክፉውን እንዲያርቀው ነው ጸሎታቸው። እናም ሰውንም ሲመርቁ ሁሉም ነገር በበጋ በፀሀይ እንዲሆን በመመኘት ነው። ‹‹ የሀምሌ ዝናብ ቡጢውን ያሳርፍብናል፤ ወንዝ የማያሻግር ክፉ ወር ነው። እንኳን ሰው የመስቀል ወፍ እንኳን የክረምት ቀለቧን በበጋ ሰብስባ በጎጆዋ ትከትታለች›› ይሉ ነበር። ዘመድ አዝማድ የሚጠየቀው ወንዝ ተሻግሮ የሚኬደው ከመስቀል ወዲያ መሆኑን ደጋግመው የነገሩኝን አስታውሳለሁ።
ዛሬ ዛሬ ‹‹ሰው ከቤቱ ተፈናቀለ፤ ተራበ ፣ እዚህም እዚያም ሰዎች በአሸባሪዎች ተገደሉ፤ በአሰቃቂ ሁኔታ ታረዱ…››የሚለውን ቢሰሙማ ሰማይ የተደፋባቸው ያህል ጭንቀታቸውን ያሳዩ ነበር። ምክንያቱም ለመኖራቸው ሳይሆን ለሞታቸው ይማጸኑ ነበርና ነው። ምን በሀምሌ ጨለማ ብቻ ከዛ የከፋ አለ ቢባሉም ይህን ከምሰማና ከማይ ሞቴን ይሉ እንደነበር እገምታለሁ። ትንሽ አሰቃቂ የሆነ ነገር እንኳን ሲሰሙ ‹‹ኧረ ! የሰይጣን ጆሮ አይስማው›› ነው የጨዋታ ሁሉ ማሳረጊያቸው ።
የታክሲው ላይ ጨዋታ የሁላችንንም አንደበት አፍታታው አይደል? እኔም አያቴን ከነምክራቸው፣ ፍርሀትና ስጋታቸው ሁሉ በምልሰት አስታወስኳቸው። ምነው በዚህ ዘመን ቢኖሩ ነበር ስል ተመኘሁ። የክረምቱን ማየል እንዲያዩ ሳይሆን በክረምቱ ከቤት ንብረቱ የተፈናቀለውን፣ በየቦታው የሚሞተውን ህጻን አዋቂ፤ ሴት ወንድ ፤አዛውንት ፣ የሀይማኖት አባት ሁሉ ሲሞት፣ ሲቃጠል፣ ሲታረድ ፤ ቤተክርስቲያን መስጊዱ ሲቃጠል ሲያዩና ሲሰሙ ምን ይሉ እንደነበር ለመስማት ነው። ብቻ የእሳቸው ጸሎት ‹‹ክፉ አታሳየኝ›› ነበርና የአሸባሪውን ሸኔ፣ የሴረኛውን ሕወሓት ግፍ የሌላውንም ክፉ ክፉውን ሳያዩ በጊዜ አሸለቡ።
እናት አንጀቷ እያረረ በልጆቿ ስቃይ ስትተክን፤ የቤተሰብ አስከሬን በእሳት ጋይቶ አመድ ሲሆን፤ ከልጅነት እስከ እውቀት ያፈሩት ንብረት ወደ ፍርስራሽነት ተቀይሮ ትዝታ ሲሆን ይህን ሁሉ ጉድና መከራ ቢሰሙ ከሟቾቹ ቀድመው ጉድጓድ ያስምሱ ነበር። ያውስ ሟቾች የሚቀብራቸው ካገኙ ማለቴ ነው!። የክፋቱ ጥግ እንኳን ለእሳቸው እኛም ለሰማነው ጉድ! አሰኝቶናል አይደል!?። ምነው ጆሮ ወሬ ጠገብኩ ብሎ ቢያስቀርልን ኖሮ።
የክረምቱ ነገር ስንቱን አስታወሰን፤ የድሮ ክረምትም እንዲሁ ቀደም ብሎ እየገባ በጋው ሁሉ ዝናብ ይሆን ነበር አሉ። ያኔ ታዲያ ሁሉ ነገር ጥጋብ ነበር። ከብቱ ሳር እንደልቡ ይግጣል። ውሃውም ሞልቷል። በበልጉ እህል ይመረታል… በዛው ልክ ኑሮው ጥጋብ ነው ምን ጠፍቶ ሁሉ ሞልቶ። ዘንድሮ ግን ጊዜው ተቀየረ እንዴ ሀምሌ በሰኔ ላይ ቀድሞ የገባ ይመስላል።
የሰኔው ዝናብ እጅግ ከበድ ብሏል። በጸሀይ ተቃጠልን፣ ነደድን፣ ሙቀቱ መተንፋስ እስኪያቅተን ብለን ዣንጥላ መጎተት ጀምረን ነበር። ሌሊት ሳይቀር ‹‹ ልብስ ቀንሱ›› የጨዋታ ማድመቂያ አልነበር። ምን ይሄ ብቻ የቧንቧ ውሃ በሳምንት፣ በአስራ አምስት ቀን፤ አንዳንዶች እንዳሉት እስከወር ድረስ ውሀ የውሀ ሽታ የሆነበትም ምክንያት አንዱ ድርቁ እኮ ነው።
እነቦረናን ሶማሌ ክልልም የነበረውን ድርቅ አንረሳም ስንቱ የቦረና በሬ በውሃ እጦት፣ በመኖ አለመኖር በድርቁ ረግፏል፤ አርብቶ አደሩ የቀሩት ከብቶቹ ከእጁ ሳያልቁ እየተንገዳገዱ የሚራመዱ እንስሳቱን ይዞ ተሰዷል። ያ ሁሉ አለፈ ተመስገን ነው። አሁን ከዳር እዳር ዝናብ መጥቷል። መሬቱ መረስረስ ቀጥሏል። አብሮት ግን ስጋቱ አይሏል። ጎርፍ አደጋ ሆኖ ፊት ለፊት ተደቅኗል። ይሄ ጥንቃቄ ይፈልጋል አይደል?።
አዎ! ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አውቀን ሁሉንም ነገር በጥንቃቄ መያዝ አለብን። እውነት ነው፤ የሚያስማማ ሀሳብ በራሳችን እራሳችን ተነጋግረን ተስማምተን ችግሩን ልንፈታ እንችላለን። ቦይ ሰርተን ጎርፉ እንዲሄድ እናደርጋለን… ሌላም ሌላም። ይሄ የሚቻል አይደል? ይቻላል እንጂ ለምን አይቻልም።
በእርግጥ የዝናብ መክበድ ሊያጋጥም ይችላል። የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ምን ልናደግ እንችላለን በእኛ አቅም አስቀድሞ የአደጋ ስጋት የሆኑትን ስፍራዎች መለየት፣ በምን መልኩ ችግሩን መቋቋም እንደምንችል መነጋገርና መስራት ይገባናል። ሌላውን ደግሞ የሚመለከተው ትኩረት እንዲሰጠው ጉዳዩን ማሳሰብ አይደል?።
ከጎኔ የተቀመጠችው ወይዘሮ አልፎ አልፎ ከእሷ ደግሞም ከእኔ የሚወጡትን የመወያያ ጉዳዮች ለብቻዋ ራሷን ካጫወተች በኋላ መሰለኝ እንዲህ ስትል በመሃላችን የነበረውን ዝምታ ሰበረች። ‹‹ይሄ የተፈጥሮ አደጋ ሁላችንንም አሳሰበን መሰለኝ፤ እኔን ያሳሰበኝ ግን ከዚህ በላይ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ናቸው አለች›› የቱ? ስል ጥያቄ አንስቼ ወሬውን አራዘምኩ ። ምንም ሳትፈራ ፊቷን ጨምደድ ፈካ እያደረገች አሁን እኮ ሁሉም ነገር እንደልብ ይወራል፤ መፍትሄ ባይኖርም ችግሩ ይገለጻል። ማን ማንን ይፈራል? ማንን ያከብራል? ምክንያቱም የመናገር ዲሞክራሲ አለና ነዋ!። እሷም መብቷን ተጠቅማ ነው መሰል ቀጠለች።
‹‹ሰኔን ጠብቀው የክረምቱን መግባት አስበው ህዝብን የሚያፈናቅሉ፤ ዜጎችን የሚጨፈጭፉ፤ ቤትና ንብረት የሚያቃጥሉ የውስጥና የውጪ ሀይሎች ሴራ ነው የሚያሳስበኝ። አይገርምሽም! ከለውጡ ጀምሮ ብዙ አስፈሪና ጭካኔ የተሞላቸው አሰቃቂ ክስተቶች በሀገራችን ታይተዋል። ድሮ ‹ሰኔና ሰኞ› ሲባል እሰማ ነበር። ሰኔና ሰኞ ሲገጣጠሙ መልካም ነገር አይገጥምም የሚል አባባል ።
አሁን አሁን ግን ሰኔና ሰኞ ሲገጥም ሳይሆን ሰኔ…ሰኔ ሲመጣ ጀምሮ መሳቀቅ እጀምራለሁ፤ ክረምቱ ምን ይዞብን ይመጣ ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ዘንድሮ ደግሞ እልቂቱ የትኛው ቦታ ላይ ይሆን በማንነቱ የተፈረደበት? የየትኛው እምነት ተከታዮች ይሆኑ የሚጨፈጨፉት እያልኩ ማውጣት ማውረድ፣ ጆሮ ጥሎ ማድመጥ ስራዬ ሆኗል›› አለች። ቀና ብላ አምላኳን እባክህ እየን፣ ተመልከተን፤ በቃ በለን! የምትል በሚመስል ተማጽኖ።
ወይዘሮዋ ረጅም ትንፋሽ፣ ተስፋ የቆረጠ ድምጸት ካወጣች በኋላ መለስ ብላ ያለፈውን እያስታወሰች መናገሯን ቀጠለች። ‹‹ትዝ ይልሻል?››አለች ‹‹ ሰኔ 16 ቀን ህዝቡ ባገኘው ለውጥ ተደስቶ ለጠቅላይ ሚንስትሩ እውቅና እና ምስጋና ለማቅረብ መስቀል አደባባይ የተገኘ እለት›› ራሴን ነቀነቅኩ። የደስታውም የችግሩም አካል ነበርኳ። ‹‹ደስታው እኮ በሀዘን፣ በድንጋጤ፣ በጭንቀት እንዲደመደም ነው የተደረገው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ላይ የተደረገው የመግደል ሙከራ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ብለሽ አስበሽዋል ሀገር ይተራመስ ነበር፤ የጎበዝ አለቃ ሁሉ ከየቦታው ሊፈጠር ይችል ነበር፤ ብቻ ፈጣሪ ሁሉንም ነገር ኩም አደረገው። ያኔ የተጀመረው የሰኔ ትርምስ ዛሬም ድረስ ዘልቋል›› ስትል ስጋት በሰፈንበት ድምፅ አጉረመረመች። ቀጠለች፤ ‹‹ዓመት ዓመት ቆጥሮ በየክረምቱ ህዝብና ሀገርን ማሸበር ነው። በሰኔ 16 በዓመቱ ሰኔ 15 ቀን ደግሞ የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም፣ የአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች የመሳሰሉ የሀገር ባለውለተኛዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። ይሄ አስደንጋጭም አሳዛኝም ክስተት ነበር።
በዛው ግን ግድያው አልቆመም አሁን ድረስ የውስጥ አሸባሪዎች ከኢትዮጵያ ጠል የውጪ ሀይሎች ጋር ሆነው ሀገር የማተራመስ ህዝብ የማስጨነቅና የማሰቃየት ስራቸውን ቀጥለዋል። ሰማይና ምድሩን በደም እያራጩ አሰቃቂ ሞትን ሁሉ አሳይተዋል።›› እያለች በምልሰት የየዓመቱን የሰኔን ወር አሰቃቂ ጊዜያት ሁሉ አስቃኘችኝ።
ጋዜጠኛ ትሆን እንዴ? ዜናውን ከነጊዜው ታስታውሰኝ ቀጠለች ። ግን እኮ አሁን ሁሉ ነገር በእጅ በደጅ አይደል፤ የሚደበቅና የሚረሳ ነገር የለም። ጎግል ጎልጉሎ መረጃውን ሁሉ እጃችን ላይ ያደርሰዋል። እና ሁሉም ጋዜጠኛ ባይሆን ይገረማል። ምን ጋዜጠኛ ብቻ ፖለቲከኛም ሆኗል እንጂ። ወዲያው በአንድ ወቅት ከመገናኛ ብዙሀን የሰማሁት ትዝ አለኝ። ‹‹ሁሉም ፖለቲከኛ ሆኗል። ሁሉም አራት ኪሎ ገብቷል። ስለዚህ ‹ሰዎች› መገኘት ባለባቸው በቤተክርስቲያንና በመስጊድ ጸሎተኛ ጠፍቷል፤ በየቤተ መጽሀፍቱ አንባቢ ርቋል፤ ሁሉም ከሙያው ተፈናቅሏል›› የሚል ነበር።
‹‹እንዳው በሞቴ አሁን በኢትዮጵያ የሚሰማው እልቂት ሁሉ ታሪክ ይቅር የሚለው ይመስልሻል?›› ሀሳቧን በጥያቄ አስደግፋ አቀረበችልኝ እንደ ድግስ ቡፌ ምርጫውን ለእኔ ትታ። መልስ አልሰጠሁም ግን ማን ጠብቆኝ ‹‹እኔ በበኩሌ›› ብላ የበኩሏን ስሜት እንዲህ ስትል አጋራችኝ። ‹‹ሌላ የሰማዕታት ሀውልት እንድናቆም የሚያደርግ ነው። ከነበረው ከጠላነው፣ ከአወገዝነው ስርዓት፣ ነበር ካልነው ጭፍጨፋ አልተማርንም። እንዳውም ባይብስ ብቻ ይሄን ሁሉ ያስታወሰን ክረምቱ ነው›› ብላ ዞር ዞር ብላ አካባቢዋን በአይኗ ቃኘች።
ጨዋታውን ያደመጡት አዛውንቷ መርካቶ ደርሰን ከታክሲው ሳንወርድ ያሰቡትን ሀሳብ ጣል ጣል አደረጉ። እውነታቸውን ነው ‹‹የሰው በልቶ…››የሚል የሀበሻ ተረት አለ አይደል? እንዲያ በሉት። ‹‹ኧረ ምኑ ቅጡ ›› ሲሉ የጨዋታ ማሞቂያ አፋቸውን እያሟሹና እያሻሹ ነው የጀመሩት ‹‹ያ ተወዳጅ የኦሮምኛ ዘፋኙ ስሙ ማን ነበር? ›› እያሉ ለማስታወስ የታክሲውን ጣሪያ ጣሪያ ሲያዩ ወይዘሮዋ ፈጠን ብላ ‹‹ሀጫሉ›› ብላ ከተጓዙበት የሀሳብ መንገድ መለሰቻቸው።
‹‹አዎ! ሀጫሉ። እሱም እኮ እንዲሁ በክረምት ነው የገደሉት የሟቾች ደም በዝናብ ይታጠባል፣ በጎርፍ ይወሰዳል፣ አይታይም ብለው ይሆን? እንጃ ብቻ! አሁንም እኮ ሀገር የሚያተራምሱ ደም የሚያፈሱ በማንነቱ የሚጨፈጭፉ አሸባሪዎች በርክተዋል። እዚያ ማዶ እዚህም ማዶ ጩኸቱ በርክቷል። ሟች በዝቶ ቀባሪ ጠፍቷል። ነፍሰጡርን ገዳይ፣ ህጻናት አራጅ ‹ጀግና› ተስፋፍቷል›› የችግር ክምር አስታወሱን። በዚህም አልረኩም መሰለኝ ‹‹ኧረ እንዳው በሞቴ ›› አሉ አንድ ጊዜ ጆሮ ሰጥተን እንድናደምጣቸው በመማጸን።
ከፊት ከኋላ የታክሲው ተሳፋሪዎችም የጨነቃቸውና መልስ ያጡለት ጉዳይ በመነሳቱ ደስ ብሏቸዋል። በሰፊው ቦታም ባይሆን በጠባቧ መድረክ መተንፈስ አስችሏቸዋል። እናም አዛውንቷ ‹‹አሁን ወለጋ ላይ በማንነታቸው የተጨፈጨፉት ንጹሀን ሰዎች አይደሉም። ሸኔ ብሎ የክፉዎች ክፉ የጨካኞች ጨካኝ ይህን ድርጊት ሲፈጽም እሰይ! አበጀህ! ጎሽ የእኔ ጀግና የሚለው የሚያገኝ እየመሰለው ይሆን እንዴ! ከሆነ ተሳስቷል። አሰላፊዎቹ ከህዝብ ልብ እያወጡት፣ አክ እንትፍ! እየተባለ መሆኑን ማን በነገረው። ህዝብን ጨፍጭፎ ለህዝብ ቆሚያለሁ፤ ህዝብን አደህይቶ ለልማት አለሁ።
ሀገርን አውድሞ ሀገሬ ቢል የቁም ቀባሪ ነው። ከአይዞህ ባይ ቢደጎምም የጊዜ ጉዳይ ነው። አያዋጡትም፤ ግብጥም ብትሆን በውስጥ ጉዳይ ሲተራመሱ ህዳሴ ግድቡ ይስተጓጎላል ከሚል ተስፋ ይመስለኛል። ሞኝ በያት አይሆንላትም! ኢትዮጵያውያን ማለት ‹‹የነብርን ጅራት አይዙ ከያዙም አይለቁ›› መሆናቸውን ባትረዳው ነው። ምንም ነገር ቢመጣ የአባይ ጉዳይ በቃ የህልውና ጉዳይ ነው። እንዳይመስላት የሚቆም ነገር የለም›› እያሉ ቀጠሉ።
‹‹የአውሮፓ ህብረት የምትሉት ግብጽ የአባይን ውሀ የመጠቀም ታሪካዊ መብት አላት …ምናም›› ሲል ነበር ሰሞኑን በዜና እንደሰማሁት አሄ ምንም ቢሉ መብቱማ የእኛው ነው 85 በመቶ ለምናመነጨው፤ እሷንስ ቢሆን መች ከለከልን እንዳው እናንተ ይቅርባችሁ ሁሉ ለእኔ ለእኔ ሆኖ እንጂ!›› ጨዋታው ደርቷል መውረጃችን ተቃርቧል። ባልናገርም ሁሉም በስሌት ነው፤ ሰኔ ሰኔ እየተጠበቀ። ብልጥ ይሄኔ ነው ሰኔን ለጦርነት ድግስ ሳይሆን ለእርሻ የሚያውላት እያልኩ እኔም የምናብ ጉዞዬን ገታሁ ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2014