መንግሥት መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን እውን ለማድረግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል ብሎ ትኩረት ከሰጣቸው ተግባራት መካከል የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት አንዱ ነው። ፓርኮቹ በሚገነቡባቸው አካባቢዎች ለሚኖረው የሕብረተሰብ ክፍል ሥራ በመፍጠርና ከአካባቢው ጋር ተስማሚ የሆነ የሥራ ከባቢ እውን በማድረግ ለሀገራዊ የምጣኔ ሀብት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ተመራጭ ከሚያደር- ጓቸው ነገሮች መካከል በርካታ አገልግሎቶችን አንድ ሥፍራ ላይ ሰብሰብ አድርገው የሚያቀርቡ መሆናቸው፣ ተገቢ መሰረተ ልማት የሚገነባላቸው እንዲሁም ከሌሎች አምራቾች ጋርም የሚያገናኙ መሆናቸው ይጠቀሳሉ። ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያም ብዙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም እንዲሁም በቂ የሆነ የሰውና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን፣ ማሽኖችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባትን፣ የብድር አቅርቦትን፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን እና የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን እንደማበረታቻ በማቅረብ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲከፍቱ ጥረቶች ተደርገዋል።
በእርግጥም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የማምረቻ መናኸሪያ እንድትሆን የሚደረገውን ጥረት ለማቀላጠፍ እንዲሁም የሥራ አጥነት ችግርን ለመቅረፍ ላቅ ያለ ሚና ይጫወታል ተብሎ የተጣለበት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ውጤቶች ተገኝተውበታል። በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድሎችን በመፍጠር ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ አበርክተዋል።
የግብርና ውጤቶችን እሴት በመጨመር በብዛትና በጥራት ተወዳዳሪ የማድረግ አቅም እንዳላቸው የታመነባቸው የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግርን ያሳካሉ ከተባሉ የኢንዱስትሪ ፓርክ ዘርፎች መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ የአግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለአርሶ አደሮች የግብይት ሰንሰለቱን ቀላል በማድረግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የገበያ ትስስር ይፈጥራሉ። ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን ከአርሶ አደሮች እንዲቀበሉ በማድረግ አርሶ አደሮች የልፋታቸውን ያህል እንዲጠቀሙ አወንታዊ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።
በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን፣ አዳሚ ቱሉ ወረዳ የሚገኘው የ‹‹ቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ›› በሀገሪቱ ከተገነቡ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች (Integrated Agro-Industry Parks) መካከል አንዱ ነው። ፓርኩ በሚያዝያ ወር 2013 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ የተመረቀ ሲሆን የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የወተት፣ የማር፣ የስጋና የእንቁላል ምርቶችን የሚያቀነባብሩ አምራቾች የሚሰማሩበት የኢንዱስትሪ ፓርክ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በፓርኩ ምርቃት ወቅት ‹‹ግብርናችንን በአግሮ ኢንዱስትሪዎች ልማት የበለጠ እናዘምነዋለን። ዛሬ የተመረቀው የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ለግብርናው ዘርፍ፣ ለአርሶ አደሮቻችን እና ለሸማቾች የኢትዮጵያን የብልጽግና ራዕይን የሚያሳይ ነው›› ብለው ነበር።
የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ በ271 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ ሲሆን አጠቃላይ ግንባታው 86 በመቶ ደርሷል። እስካሁን ለግንባታው ሰባት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ አጠቃላይ የግንባታው በጀት ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚሆንና በ2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
ምንም እንኳ የፓርኩ አጠቃላይ የግንባታ አፈፃፀም 86 በመቶ ቢሆንም ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚችልበት አቅም ላይ ደርሷል። ፓርኩ ባለሀብቶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ ባከናወናቸው ተግባራት አንዳንድ አምራች ኩባንያዎችም ወደ ፓርኩ ገብተው በግብርና ምርቶች ማቀነባበር ሥራ ላይ ለመሰማራት የሚያስችሏቸውን የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እያከናወኑ ይገኛሉ። ማር በማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማራ አንድ አምራች ድርጅት ደግሞ የሙከራ ምርት መጀመሩ ተገልጿል።
በኦሮሚያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊና የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አማካሪ አቶ መሐመድ ሐሰን አምራቾች ወደ ፓርኩ ገብተው ሥራ እንዲጀምሩ ለማስቻል ሲከናወኑ የቆዩ ተግባራት እንዳሉ ይናገራሉ። እንደእርሳቸው ገለፃ፣ የፓርኩ አጠቃላይ የግንባታ አፈፃፀም 86 በመቶ ቢሆንም አሁናዊ የግንባታ ደረጃውና የመሰረተ ልማት አቅርቦት አቅሙ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው ሥራ እንዲጀምሩ የሚያስችለው ነው። በመሆኑም ባለሀብቶችን ሥራ ለማስጀመር የሚያስችሉ የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የቆሻሻ ማጣሪያና ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። የቆሻሻ ውሃ ማጣሪያው ከ56 በመቶ በላይ ተጠናቋል።
የኃይል አቅርቦትን በተመለከተ ‹‹የኃይል አቅርቦት ሥራ የሚከናወነው በፌዴራል መንግሥት ነው። በዚህም መሰረት የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ተጀምሯል። እስከዚው ድረስ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ መጥተው በመብራት እጥረት እንዳይቸገሩ በማሰብ በኮርፖሬሽኑ ገንዘብ 10 ሜጋ ዋት ኃይል እንዲቀርብ አድርገናል›› ብለዋል። ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ መጥተው ሥራ ለመጀመር የሚያስቸግራቸው ነገር እንደሌለና ከመጡ መስተናገድ እንደሚችሉም አቶ መሐመድ ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን የጥራት መሰረተ ልማት ዳይሬክተርና የጥራትና የምግብ ደህንነት ግብረኃይል ቡድን መሪ አቶ ጌታቸው ፈይሳ በበኩላቸው፣ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው ሥራ እንዲጀምሩ የሚያስችሉ ዋና ዋና የመሰረተ ልማት ሥራዎች መከናወናቸውን ይገልፃሉ። የመብራት፣ የመኖሪያ ቤት፣ የውሃ መስመር፣ የህክምና፣ የፖሊስ ጣቢያ፣ የሥልጠናና የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ተዘጋጅተዋል። ፓርኩ በማር፣ በስጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዘይትና በጥራጥሬ ማቀነባበር የሚሰማሩ ባለሀብቶች ይገቡበታል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚቋቋሙባቸው ዓላማዎች መካከል አንዱ ብዙ የሥራ እድሎችን በመፍጠር ዜጎችን የሥራ ባለቤትና አምራች ማድረግ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ረገድ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ በግንባታው ሂደት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥሯል። በቀጣይም በተለያዩ የፓርኩ የሥራ ደረጃዎች ብዙ የሥራ እድሎች እንደሚፈጠሩ ይጠበቃል።
አቶ መሐመድ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ- ኢንዱስትሪ ፓርክ ስለፈጠራቸውና ወደፊትም ስለሚያስገኛቸው የሥራ እድሎችና ሌሎች ጥቅሞች ሲያስረዱ ‹‹ፓርኩ በተገነባበት አካባቢ የሚገኘው የሕብረተሰብ ክፍል በተለያዩ መንገዶችና ደረጃዎች ተጠቃሚ ይሆናል። በፓርኩ ግንባታ ወቅት በተፈጠሩ የሥራ እድሎች በርካታ ሰዎች ተጠቃሚ ሆነዋል። ለፓርኩ ግብዓት የሚያቀርቡ ስድስት የገጠር ሽግግር ማዕከላት ተቋቁመዋል፤ በግንባታው ወቅት ጥሬ እቃዎችንና የግንባታ ግብዓቶችን የሚያቀርቡ ማሕበራት እንዲሁም አገልግሎት የሚሰጡ (የምግብ ዝግጅት፣ የመስተንግዶ …) አካላትም አሉ። እነዚህ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሥራ እድል ተጠቃሚ ሆነዋል። በሌላ በኩል በልማት ተነሺ ከሆኑ የአካባቢው የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ወጣቶችንም ከባለሀብቶች ጋር በማገናኘት የሥራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል። በአጠቃላይ በፓርኩ የግንባታ ሂደት ለ13 ሺ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል መፍጠር ተችሏል።
ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው ሼዶችን በመገንባት ሂደት የሚፈጠሩ የሥራ እድሎችም አሉ። ወደ ፓርኩ የገቡ ባለሀብቶች ግንባታቸውን ጨርሰው ወደማምረት ሲሸጋገሩ ተጨማሪ የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ። አርሶ አደሩ ለባለሀብቶች ግብዓት ሲያቀርብ በግብርና ቦታ ላይ በሚከናወኑ ሥራዎች (መዝራት፣ መንከባከብ፣ ምርት መሰብሰብ …) ለአካባቢው ሕብረተሰብ የሚፈጠሩ የሥራ እድሎችም ፓርኩ ያስገኛቸውና ወደፊትም የሚያስገኛቸው ጥቅሞች ናቸው›› በማለት ያስረዳሉ።
የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክ የግብርና ውጤቶችን በማቀነባበር ላይ አተኩሮ የሚሰራ እንደሆነ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ለፓርኩ ምርቶች የግብርና ግብዓቶችን የሚያቀርቡ በግብርና ሥራ ላይ የተሰማሩ የአካባቢው ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ፓርኩ በማር፣ በስጋ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በዘይትና በጥራጥሬ ማቀነባበር የሚሰማሩ ባለሀብቶች የሚገቡበት በመሆኑ አርሶ አደሮች ለአምራቾቹ ግብዓት በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ ጌታቸው ተናግረዋል። ‹‹ፓርኩ ለአካባቢው ማሕበረሰብ ብዙ የሥራ እድሎችን ፈጥሯል። የአካባቢው ሕብረተሰብ ለፓርኩ የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማው ተከታታይ ሥልጠናዎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች ተሰጥተዋል›› ብለዋል።
በቀጣይ ጊዜያት ከ80 እስከ 120 አምራቾች ወደ ፓርኩ ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፣ የልማት አጋሮችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የኢንዱስትሪ ፓርኩን ወደ ሥራ ለማስገባት ለሚደረገው ጥረት ዘርፈ ብዙ እገዛዎችን እንዳደረጉና በዚህ ረገድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢንዱትሪ ልማት ተቋም (UNIDO) እና አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተጠቃሽ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ባለሀብቶች ወደ ፓርኩ ገብተው ለመሰማራት ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ የተናገሩት አቶ መሐመድ ሐሰን፣ እስካሁን ድረስ ከስድስት ኩባንያዎች ጋር የመግባቢያ ስምምነቶች እንደተፈረሙም ገልጸዋል። አምራቾቹም በስጋ ማቀነባበሪያ፣ በአቮካዶ ዘይት፣ በማር ምርትና በምግብ ዘይት ማምረት ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ያላቸው ናቸው። ሸካ ሞርዲ የተባለ የማር ማቀነባበሪያ ድርጅት ደግሞ የሙከራ ምርት ጀምሯል። ይሁን እንጂ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ባለሀብቶችን ለመቀበል ዝግጁ ቢሆንም ባለሀብቶቹ ከፋይናንስ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሟቸው ቢሮክራሲያዊ መሰናክሎች በፍጥነት ሥራ እንዳይጀምሩ ጫና እንደፈጠረባቸውም አቶ መሐመድ ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮች ለሀገራዊ የኢንቨስትመንት እድገት ትልቅ አስተዋፅኦ የማበርከት ግብ አላቸው። በዚህ ረገድ የቡልቡላ የተቀናጀ አግሮ-ኢንዱስትሪ ፓርክም ለሀገራዊ ኢንቨስትመንት ዘርፈ ብዙ ሚና እንደሚኖረው አቶ መሐመድ ይናገራሉ። እርሳቸው እንደሚሉት፣ ኢንዱስትሪ ፓርኩ አምራቾችን በመሳብ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ያደርጋል። ፓርኩ ብዙ የሥራ እድል በመፍጠር ከሚኖረው ሚና በተጨማሪ ግብርናውን በማዘመንና ምርቱን በማሳደግ ምርት ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአቅርቦትና የውጭ ምንዛሬ ችግሮችን ለማቃለል ያግዛል። የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖርም ያደርጋል። ለአርሶ አደሩ የገበያ ትስስሩን ቀላል በማድረግ ተጠቃሚነቱ እንዲያድግ ያስችላል።
የአገሪቱን የምጣኔ ሀብት መዋቅር ከእርሻ መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ለማሸጋገር የሚያግዙ በርካታ መልካም አጋጣሚዎችና እድሎች አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህን መልካም አጋጣሚዎች በመጠቀም የኢኮኖሚውን መዋቅራዊ ሽግግር ለማሳካት የተከናወኑ ተግባራት ሀገሪቱ ካላት አቅምና ፍላጎት ጋር የሚጣጣሙ አይደሉም። ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ ያላትን አቅም በመጠቀምና ከዚሁ ዘርፍ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግር ለማሳካት አምራች ዘርፉ አሁን ካለው አፈፃፀም በብዙ እጥፍ እንዲጨምርና እንዲሻሻል ማድረግ ያስፈልጋል።
የአምራች ዘርፉ እድገት ሊሻሻል የሚችለው ከኢንቨስትመንት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ነው። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ደግሞ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ ለኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ናቸው። ስለሆነም መዋቅራዊ የምጣኔ ሀብት ሽግግሩን ለማሳካት የኢንዱትሪ ፓርኮችን አፈፃፀም ማሻሻል ይገባል። ይህም ባለሀብቶች ወደ ፓርኮቹ ገብተው ለማምረት የሚያስችሏቸውን የመሰረተ ልማት ግብዓቶች፣ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የፋይናንስ አቅርቦት ማሟላትን እንደሚያካትት ሊታወቅ ይገባል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሰኔ 23/2014