የምንኖርበት አለም ብዙ ነገሮች የተለመደ ቅርጻቸውን የሚቀይሩበት ወይም የቀየሩበት አለም ነው።ቅርጻቸውን ከቀየሩ ነገሮች መሀከል አንዱ ደግሞ ጦርነት ነው። ዘመናዊው ጦርነት ከጥንቱ በብዙ ነገር ይለያል። በዋነኝነት ከሚለይባቸው ነገሮች መሀከል አንዱ ደግሞ የጦርነቱ አላማ ጠላትን መደምሰስ ሳይሆን የጠላትን የማድረግ አቅም ማሳጣት ላይ ማተኮሩ ነው። ይህ የሆነው በዋነኝነት ለጠላት በማሰብ ሳይሆን ጠላትን ሙሉ ለሙሉ ለማውደም የሚደረገው ጥረት ኢኮኖሚያዊ ጣጣው ብዙ ስለሆነ ነው።
በያዝነው ክፍለ ዘመን በአለም ታሪክ ከየትኛውም ጊዜ በተለየ ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ የቀነሰበት ነው። ይህም ጦርነት ከሚፈልገው ከፍ ያለ ኢኮኖሚ አንጻር እንደሆነም ብዙዎች ይስማማሉ፤ ተጨባጭ እውነታውም የሚያመላክተው ይህንኑ ነው። ይህ ማለት ግን የተለመደው ጦርነት ውድ በመሆኑ ቀንሷል ማለት ጦርነት ቀርቷል ማለት አይደለም።
በተቃራኒው ጦርነት ኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ ኪሳራቸው አነስተኛ በሆኑ ስልቶች እየተቀየረ ከመጣ ውሎ አድሯል። በአነስተኛ ወጪ ጦርነትን በድል ለመወጣት ከተፈበረኩት ስልቶች መሀከል አንዱ እና አሁን በከፍተኛ ደረጃ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የስነ ልቡና ጦርነት ነው።
የስነ ልቡና ጦርነት ምንድን ነው? በግርድፉ ሲተረጎም እንደሚከተለው ነው “የስነ ልቡና ጦርነት ማለት በጦርነት ወቅት፤ የጦርነት ስጋት ባለበት ወቅት ወይም ቀጠናዊ የጂኦፖለቲካ ውጥረት በሰፈነበት ወቅት ከተግባራዊ ጦርነት ውጭ በታቀደ መልኩ ፕሮፓጋንዳን፤ ማስፈራሪያን እና ሌሎች ቴክኒኮችን በመጠቀም ጠላትን በማደናገር፤ ሞራል እንዲያጣ በማድረግ፤ በማበሳጨት፤ ተስፋ በማስቆረጥ —ወዘተ ማለት ነው። በአስተሳሰቡ እና በባህሪው ላይ ተጽእኖ መፍጠር ነው”
ይህ ስልት ከዚህ ቀደምም የሚታወቅ ቢሆንም እንኳ በአብዛኛው ጥቅም ላይ የዋለው ግን ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መግባት በኋላ ነው። በተለይም ሁለተኛው የአለም ጦርነት ለስነ ልቡና ጦርነት በይፋ ጥቅም ላይ መዋሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። ከዚያ በኋላ ተከትሎ የመጣው ቀዝቃዛው ጦርነት ደግሞ ይህን ሁኔታ ከፍ ባለ ደረጃ እንዲያድግ አድርጎታል። ምእራቡም ምስራቁም አንዳቸው ሌላቸውን በፕሮፓጋንዳ በመውቀር ብዙ ውጤት አግኝተውበታል።
ወደኛ ስንመጣ ይህ ሁኔታ ብዙም የማይታወቅ የነበረ ሲሆን ያለፉት 2 አመታት ግን የስነ ልቡና ጦርነት ምን እንደሚያስከትል በግልጽ የታየበት ነው። በተለይም በአሻባሪው ሕወሓት ላይ የተካሄደው ህግ የማስከበር ዘመቻ እና ያን ተከትሎ የተከሰተው ጦርነት እንዲሁም የምእራባውያኑ አቋም የስነ ልቡና ጦርነቱ በይፋ እንደተከፈተብን አመላካች ሆኗል።
በስነ ልቡና ጦርነቱም ነው አሻሪው ሕወሓት ከተንቤን በረሀ ደብረ ብርሀን የደረሰችው። አሁንም ቢሆን የስነ ልቡናውን ጦርነቱ አፋፍሞ ቀጥሏል።የተጠናከረ የፕሮፓጋንዳ ጦርነት፤ የማያቋርጡ ህዝብን ተስፋ እንዲቆርጥ የሚያደርጉ ወሬዎች፤ ህዝብ ከህዝብ ህዝብ ከመንግስት ህዝብ ከመሪዎቹ እንዲቆራረጥ የሚያደርጉ ተከታታይ የተዛቡ መረጃዎችን በስፋት እየለቀቀ ነው።
በኦነግ ሸኔ እና በብጤዎቹ የሚደረገው ግድያ ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተጣምሮ የስነ፣ ልቦናው ጦርነት ዋነኝ አቅም አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። በዚህም ህዝብ ሀገሪቱ እየፈረሰች እንደሆነ እና መንግስትም ሆን ብሎ ህዝብን እየጎዳ እንደሆነ እንዲያስብ እየተደረገ ነው። ለዚህ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያው ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
በመንግስት በኩል ለዚህ ግንባር የሚመክት እሳቤ በቅጡ የተፈጠረ አለመሆኑ ደግሞ የቡድኑን እኩይ ተግባር አቅም እንዲያገን እየረዳው ነው።ሀገራዊ የኮሚኒኬሽን ስራው የተለመደው፤ በተበጣጠሰ እና ትርጉም አልባ በሆነ መልኩ ነው እየተሰራ ያለው።
አሁንም ፌስቡክ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር እየቆራረጠ መፖስት ብቸኛ ስራው የሆነ የኮሚኒኬሽን መዋቅር ያለ ይመስላል። ሀገራዊ ሚዲያው በተናበበ እና በተቀናጀ መልኩ የገባንበትን ተግዳሮት በሚመጥን መልኩ መልስ ለመስጠት ዝግጁ አይመስልም።አሁን ላይ ይህን የስነ ልቡና ጦርነት መልሰን መመከት እና መልሰን ማጥቃት ሲገባን በተቃራኒው ችግሩ መኖሩንም እንደ ሀገር የተረዳን አይመስልም።
ልብ ማድረግ የሚገባው የተደራጀ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የሚካሄደው በዋናነት መንግስት ላይ ይሁን እንጂ ዋነኝ ተልእኮው / ኢላማ ያደረገው ኢትዮጵያ እና ህዝቧ ናቸው።ህዝቡ በብዙ ተስፋ የጀመረውን ለውጥ ማሰናከል ነው።
ስለ ልቡና ግለሰባዊ እና ማህበራዊ ነው።ጥቃቱ የሚያጠነጥነው ግለሰብ ዜጎች ብሎም ማህበረሰብ ላይ ነው።ኢላማው ሰው እና ሀገር ናቸው።ከሀምሌ 1 በኋላ ኑሮ ሰማይ ይነካል፤ ኦነግ ሸኔ አዲስ አበባ በር ላይ ደርሷል፤ መንግስት ለኦነግ ድጋፍ እየሰጠ ስለሆነ ጥቃቱ አይቆምም፤ ንጹሀን እንደ ዶሮ እየታረዱ ነው፤ እነ እገሌ ሀገራት ከኢትዮጵያ መውጣት ለሚፈልግ ፓስፖርት እየሰጡ ነው፤ ወዘተ…የሚሉ ወሬዎች አላማቸው መረጃ መስጠት አይደለም።
አላማቸው ስነ ልቡናን መስለብ ነው።ግባቸው ህዝብን ተስፋ ቆርጦ እንዳይታገላቸው እጅ ማሰጠት ነው።ይህን በሚዲያዎቻቸው ይሰሩታል፤ በሶሻል ሚዲያ ወኪሎቻቸው ያራቡታል፤ የተማረው እና ስልጡኑ የሚባለው፤ መሀል ከተማ ላይ ያለውን በዚህ መልኩ ትጥቅ ካስጣሉ የገጠሩ ህዝብን ደግሞ ስፖንሰር በሚያደርጓቸው እና በሚያስታጥቋቸው ሀይሎች ሰላም ከነሱ ከዚህ በኋላ መንግስትን ለመጣልም ሆነ ሀገሪቱን ለማፍረስ የሚያግዳቸው አንዳች ሀይል አይኖርም።
ለዚሕ ለቡድኑ እኩይ ተልእኮ አሁን መንቃት አለብን። የስነ ልቡና ጦርነት እንደተከፈተብን ማመን እና በዚያ ልክ መደራጀት አስፈላጊ ነው።ለመከላከያው፤ ለፌዴራል ፖሊሱ፤ ለልዩ ሀይሉ፤ ለደህንነቱ፤ ለሳይበር መከላከያ ክንፉ የሚደረገው ድጋፍ ሁሉ የስነ ልቡና ጦርነትን ለሚፋለመው አካል ተደርጎ የመመከት ስራ መስራት ያስፈልጋል።
አልያም መከላከያው ተስፋ የቆረጠ ህዝብን ከኋላው አድርጎ ሊዋጋ እና ሊያሸንፍ አይችልም። ፌዴራል ፖሊሱ ሀገራዊ ስሜቱ በሞተ ህዝብ መሀል ህግን ሊያስከብር አይችልም። ሌላውም እንደዛው።እና ማጠቃለያው መንግስት አሁን የጀመረውን የጸረ ስነ ልቡና ጦርነት ቡድን ግንባታ ማፋጠን አለበት።
(አቤል ገ/ኪዳን)
አዲስ ዘመን ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም